የቁም እንስሳት ሀብትን ከሕገወጦች የመታደጉ ሥራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም!

በእንስሳት ሀብቷ ከዓለም ግንባር ቀደሞቹ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ ከዚህ ሀብት የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች ስለአለመሆኗ ሁሌም ይገለጻል፡፡ ለዚህ ደግሞ በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ቢችሉም፣ አንዱ መሠረታዊ ችግር ኮንትሮባንድ ነው፡፡

ሀገሪቱ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሰፋፊ ጥረቶችን እያደረገች መሆኗ ይታወቃል፤ በብዙ ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ሸቀጦችን በቁጥጥር ስር እያዋለች ትገኛለች፡፡ ችግሩን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴው መሰረታዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ ንግድ በሀገሪቱ የቁም እንስሳትና ሌሎች የግብርና ምርቶች ንግድ ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽእኖ አስመልክቶ ያካሄደውና ሰሞኑን ይፋ የተደረገው ጥናትም ይህ ችግር ሀገሪቱን ከቁም እንስሳት ሀብቷ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን እያደረጋት ስለመሆኑ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡

ጥናቱ በየሩብ ዓመቱ ከ106 ሺ በላይ የቁም እንስሳት በሕገወጥ ንግድ ከሀገር እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል፡ ፡ ይህ አሀዝ ለማሳያነት ጥናት በተደረገበት በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ እየተደረጉ ያሉት የቁም እንስሳትና ሌሎች የግብርና ምርቶች ውጤቶች በሕጋዊ መንገድ ከሚወጣው ተመሳሳይ ሀብት እንደሚበልጥም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡

ጥናቱ በምሥራቁ የሀገሪቱ ድንበር በሕገወጥ መንገድ እንዲወጡ የሚደረጉትን የቁም እንስሳት ብቻ የተመለከተ ነው፡፡ የሰሜን፣ የደቡብና ምእራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በጥናቱ ቢካተቱ ደግሞ የጉዳቱ መጠን ከዚህም በእጅጉ ሊልቅ እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ይህ የሩብ ዓመት አሀዝ በዓመት ሲሰላ ከ420 ሺ በላይ የቁም እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ከሀገሪቱ እንዲወጡ ይደረጋል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ለዚህ ሕገወጥ ተግባር ገፊ የተባሉ ምክንያቶችም ተጠቁመዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የተቀባይ ሀገሮችን ፍላጎት የሚያሟላ የተስተካከለ የኳረንታይን ሥርዓት አለመኖርና ያሉትም ቢሆኑ አቅማቸው የደከመና አገልግሎት የሚሰጡ አለመሆናቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ጥናቱ መፍትሔ ያለውንም ጠቁሟል፡፡

ለአንድ ችግር መፍትሔ ለማግኘት ችግሩ በሚገባ መለየቱና የመፍትሔ ሃሳብ መመላከቱ ችግሩን መፍታት እንደመጀመር ሊቆጠር ይችላልና ጥናቱ ችግሩን ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱና መፍትሔ ማመላከቱን ችግሩን ለመፍታት የተወሰደ አንድ ርምጃ አድርጎ መመልከት ይቻላል፡፡

ይህን ጥናት መሠረት አድርጎ ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥ ቀጣዩ ትልቅ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ ችግሩን የመፍታቱ ሥራ እዚህ ላይ እንዳይቆም አጥብቆ መሥራት ግን ያስፈልጋል፡፡ ሀገሪቱ እጅግ ትልቅ ሀብት እንድታጣ እየተደረገች ትገኛለች፡፡

ገፊ ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን በየዓመቱ ይህን ያህል የቁም እንስሳት ሀብት በሕገወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጣ መደረጉ በሀገር ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡ የሀገሪቱ ቄራዎች / ለሀገር ውስጥም ለውጭ ገበያም ሥጋ የሚያቀርቡት ቄራዎች/ የሚፈልጉትን ያህል ከብት ማግኘት እንዳይችሉ ወይም የከብት ገበያ ውድነት እንዲከሰት ሊያደርግ አይችልም ተብሎም አይታሰብም፡፡

የሀገሪቱን የቁም እንስሳት ከዚህ ሕገወጥ ንግድ ለመታደግ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ኳረንታይኖች እየገነቡ ስለመሆናቸው ከዓመታት በፊት ሲገለጽ ነበር፡፡ አሁን ይህ ጥናት ያወጣው መረጃ ግን የተቀባይ ሀገራትን ፍላጎት የሚያሟላ የተስተካከለ የኳረንታይን ሥርዓት በሀገሪቱ አለመኖሩን አጋልጧል፤ ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ቀደም ሲል የነበረው ችግር አሁንም መቀጠሉን ነው፡፡

መንግሥት የኮንትሮባንድ ንግድን በኢትዮጵያ ጉምሩክ ከሚሽንና በሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በኩል ለመቆጣጠር እየሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፈው ዓመት ወርቅና ሌሎች ሕገወጥ ንግዶችን ለመቆጣጠር የሚሠራ ግብረ ኃይል ከተለያዩ ተቋማት በማውጣጣት አቋቁሞ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም በተለይ በወርቅ ሕገወጥ ግብይትና ማምረት ተግባር የተሰማሩ አካላትን በቁጥጥር ማዋል የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህን ተከትሎም ለብሔራዊ ባንክ በሚገባው የወርቅ መጠን ላይ ለውጥ ማምጣት መቻሉን ከወርቅ አልሚ አካባቢዎች የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህን ዓይነቱ ርምጃ የቁም እንስሳት በሕገወጥ መንገድ ከሀገር በሚያስወጡ አካላት ላይም መደገም ይኖርበታል፡፡ በእርግጥ ይህ ጊዜያዊ መፍትሔ ይችላል፡፡ በዚህ ብቻ የተወሰነውን የሀገሪቱን የቁም እንስሳት ሕገወጥ ንግድ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ሕገወጦች ይህን ያህል የሀገር ሀብት ከሀገር እያወጡ መቀጠል እንዳይኖርባቸው ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ከእስከ አሁኑም በላይ ሀብት ሀገር ታጣለች፡፡

ችግሩ ግዙፍ እና ሀገሪቱን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እያሳጣ ያለ እንደመሆኑ ዘላቂ መፍትሔን ይፈልጋል፡፡ ዘላቂው መፍትሔ ግን በግብይቱ ሥርዓቱ ላይ አለ የተባለውን ችግር ቀርቦ መፍታት፣ ደረጃውን የጠበቀ ኳረንታይን እንዲኖር ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባሮች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ካረንታይኖች ለይስሙላ የሚገነቡ መሆን የለባቸውም፡፡ የቁም እንስሳት ተቀባይ ሀገሮችን ፍላጎት መሠረት ተደርገው መገንባት ይኖርባቸዋል፡፡

በዚህ ሀብት ላይ እየፈጸመ ያለ ሕገወጥ ንግድ ሀገርን ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እያሳጣ ስለመሆኑ ይህ ጥናት በሚገባ አመላክቷል፡፡ ይህን ችግር ለመቀነስ የሚወጣ የትኛውም መጠን ያለው ሀብት ችግሩን በማስቀረት ሊተካ የሚችል፣ ከዚያም አልፎ ለሌላ ሀገራዊ ልማት የሚውል ሀብት ማስገኘት የሚችል እንደመሆኑ ይህ ችግር ሆኖ የማይጠቀስበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡

የቁም እንስሳት ሀብትን ከሕገወጦች የመታደጉ ሥራ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም! በመሆኑም የኳረንታይን መሠረተ ልማቶች በተገቢዎቹ ስፍራዎች ላይ መገንባትና በሕገወጦች በቀላሉ ሊረበሽ የማይችል የግብይት ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል!

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You