“የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት የሚመራበት ሥርዓት በመስተካከሉ የነበሩት ችግሮች ተወግደዋል”

አቶ ሰለሞን ገብሬ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ

ባለፉት ጊዜያት የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ፈተና ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ለፈተናው በዋና ምክንያትነት ሲጠቀስ የነበረው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ቢሆንም ከእሱ ባልተናነሰ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሥርዓቱም ማነቆ እንደነበር የዘርፉ አካላት ይጠቅሳሉ፡፡

ከዚህ አኳያ አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩንና ሰፋፊ የመንግሥትና የግል እርሻ ባለቤቶችን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓት እንዳይቸግራቸው ተቋሙ በአቅርቦቱም ሆነ በዋጋ መረጋጋቱ ላይ ምን እየሰራ ነው ሲል አዲስ ዘመን በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት ከአቶ ሰለሞን ገብሬ ጋር ቆይታ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ በዋናነት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ምንድን ናቸው?

አቶ ሰለሞን፡- የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ የተቋቋመውም የግብርና ሥራውን ለመደገፍ ነው፡፡ ዋና ተልዕኮው ለግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የግብርና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደሩ ማቅረብ ነው፡፡

ይህ ተግባሩ ዘርዘር ተደርጎ ሲታይ ኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘር በማባዛት ለተለያዩ ስነ ምህዳር የሚውሉ ዘሮችን ያዘጋጃል፡፡ ከምርምር ተቋማት መነሻ ዘር ተቀብሎ በሶስት ደረጃ አባዝቶ ለአርሶ አደር ያደርሳል። ይህ ፕሪቤዚክ፣ ቤዚክና ሰርቲፋይድ ዘር በሚል አምርቶ በሀገሪቱ ላሉት የተለያየ ስነ ምህዳር ያቀርባል። እነዚህ ምርጥ ዘሮች በሽታን የመከላከል፣ ምርታማነት የመጨመር ብቃት ያላቸውና የተሻሻሉ ዝርያዎች ናቸው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ናቸው ከሚባሉት ውስጥ የአፈር ማዳበሪያ በጠጣርና በፈሳሽ ያቀርባል፡፡ ለሰብል እንክብካቤ የሚውሉ የተለያዩ አግሮኬሚካልስ ጸረ በሽታ፣ ጸረ አረም እንዲሁም ጸረ ተባይ በዚህ ልክ ከውጭ አስመጥቶ ያቀርባል። ሶስተኛው ደግሞ የእርሻ ሜካናይዜሽን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የእርሻ ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሲባል ከማረስ ጀምሮ ጎተራ እስከማስገባት ድረስ እንደ ኮምባይነር ያሉ መሳሪያዎች አይነት አገልግሎት ነው። ማረስ ሲባልም ለአርሶ አደሩ በኪራይ የሚውል ሲሆን፣ ያርሳል፤ ይከሰክሳል፤ በሜካናይዜሽን ይዘራል፡፡ ከዚያ በኋላ እህሉ ሲደርስ አሁንም በኪራይ ከአጨዳው እስከ ጎተራ እስኪገባ አገልግሎቱ ለአርሶ አደሩ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

ከኪራይ አገልግሎቱ ውጪ ደግሞ ግዥዎችን ያከናውናል፡፡ የእርሻ መሳሪያዎችን፣ ትራክተሮችን፣ ኮምባይነሮችን፣ ማረሻዎችን፣ መከስከሻዎችን እና መሰል መሳሪያዎችን ከውጭ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ ለአርሶ አደሩ ያቀርባል፡፡

የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት አንጻር የእጣን ምርቶችን ከበረሃ አካባቢዎች አስለቅሞ በማምጣትና በማዘጋጀት ወደውጭ የመላክ ተግባር ያከናውናል። ከዚያ ውጭ ደግሞ የመለዋወጫዎች፣ ፓምፖችና የመሳሰሉትን ለአነስተኛ አርሶ አደሮች አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በኪራይ ለውስጥ አገልግሎት ይሰጣል።

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ የግብርና ግብዓት ከሚባሉት ውስጥ ዋናው የአፈር ማዳበሪያ ነውና በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የተፈጠረው እጥረት መንስዔው ምን ነበር? ዘንድሮስ በምን መልኩ ለማስተካከል ተሰርቷል?

አቶ ሰለሞን፡- ኮርፖሬሽኑ በሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ አቅራቢ ብቸኛ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ አካሄዱም የአርሶ አደሩን የማዳበሪያ ፍላጎት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልል ተጠናክሮ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ፍላጎት ይመጣል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር በዚያ ልክ በጀት ከገንዘብ ሚኒስቴርም ከብሔራዊ ባንክም አስይዞ በዛ መሰረት ግዢው ይከናወናል፡፡

ባለፈው ዓመት የተወሰነ ችግር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ይኸው ከዚህ በፊት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ላይ ሲውል የነበረ የግዥ ሥርዓት ነው፡፡ ያ ደግሞ አካሄዱ ውስብስ የሆነ ነው፡፡ ጨረታ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ግልጽ ጨረታ መውጣት አለበት፤ አንዴ ውለታ ከታሰረ በኋላ ዋጋ እንኳ ቢቀንስ መቀነስ አይቻልም፡፡ የነበረው የግዥ ሥርዓት ግትር/አሳሪ ነበር፡፡ በመሆኑም ችግር ነበረበት፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን እሱን ችግር ለማስተካከል ጥረት በመደረጉ ሊያሰራ የሚችል የግዥ ሥርዓት መሆን ችሏል፡፡

ስለሆነም የዓለም ገበያ እየታየ ጨረታ መውጣት ካለበት ጨረታ ይወጣል፡፡ በውስን ጨረታ መሄድ ካለበትም በውስን ጨረታ እንዲከናወን ይደረጋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድም ይህን በአግባቡ መምራት እንዲያስችል ሙሉ በሙሉ በአዲስ ተቀይሯል።

ይህንን ኮርፖሬሽኑን እንዲመሩ በቦርድ የተመደቡት የግብርና ሚኒስትር፣ የሎጂስቲክና ትራንስፖርት ሚኒስትር፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ኃላፊ ናቸው፡፡ ይህ የሆነው የባለፈው ዓመት ችግር እንዳይከሰት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተሳለጠ ሁኔታ ሥራዎች በመሠራት ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለአርሶ አደሩ በሰዓቱ እንዲቀርብለት ለማድረግ በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት በመሰራት ላይ ነው፡፡ ይህም ለውጥ አምጥቷል፡፡

ከዚህ ቀደም የአፈር ማዳበሪያው ጨረታ ወጥቶለት ውጤት መጥቶ መርከቦቹ የሚደርሱት ታኅሣሥ ላይ ነው፡፡ አሁን ግን መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የማዳበሪያ አሰራር ሥርዓትም በመሻሻሉ ከዚህ በፊት ተደርጎ በማይታወቅ ጥቅምት 18 ግዥው አልቆ ጂቡቲ ደርሷል፡፡ ይህ ለውጥ በተቀየረው የአሰራር ሥርዓት የመጣ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ለበልግ እና ለመስኖ የአፈር ማዳበሪያ ግዢው ተፈጽሞ ወደአርሶ አደሩ በፍጥነት መድረስ ችሏል፡፡ ድሮ ቢሆን በዚህ ሰዓት አንድም መርከብ ወደ ጂቡቲ ወደብ አይደርስም ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ችግር ተፈትቷል፡፡ ምክንያቱም ውሳኔ ሰጪዎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው፡፡ ግዥው ግልጸኝነት የተሞላው ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ገበያ በሰፊው ይታያል፡፡

የዓለም አቀፍ ገበያ ከፍ ባለበት ጊዜ አንዴ ውል አስሮ የሚቀጥል አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ገበያውን የሚያጠኑ አጥኚዎችን አልቀጠርንም፡፡ አሁን ግን ዓለም አቀፍ ገበያውን የሚያጠኑ አጥኚዎች ተቀጥረዋል። የእነዚህ አጥኚዎች መረጃ ተይዞ ቦርዱ ያለው የግዥ ቴክኒካል ኮሚቴው ታክሎበት የሚሰራ በመሆኑ ችግሩ ሊፈታ ችሏል፡፡

ባለፈው ዓመት ችግሮች ነበሩ፡፡ ችግሩም በአሳሪ የግዥ ሥርዓት የተነሳ ነው፡፡ የኤልሲ ችግርም በስፋት የሚንጸባረቅ ነበር፡፡ በወቅቱ ንግድ ባንክ ቢጠየቅም የምንዛሬ ችግር እንዳለ አመልክቷል፡። አቅራቢዎቹ ደግሞ ከነበረው ሀገራዊ ሁኔታ አንጻር እያዩ ኤልሲው ይሁንታን ያገኘ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ ያ ማለት ዋስትና ያለው ኤልሲ ማለት ነው፡፡ ያንን ደግሞ ዋስትና ያለውን በቀጥታ ለመክፈት ከነበረው ሁኔታ አንጻር ባንኮች ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ አቅራቢዎቹ ኤልሲ የተረጋገጠ ካልሆነ ሽያጩን ማከናወን አይችልም የሚል ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በመሃል ወደሁለት ወር አካባቢ በመዘግየቱ ኤልሲ መክፈት አልተቻለም፡፡ እሱ ደግሞ የፈጠረው ክፍተት ከእቅድ ውጪ መሄድን ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ይህንን እጥረት በመጠቀም አርሶ አደሩ ዘንድ የተለያየ ተገቢ ያልሆነ መረጃ መናፈስ ጀመረ፡፡

ነጋዴዎች እጥረት ባለበት አካባቢ ስለሚመጡ ወደዚያ የማምራት ሁኔታዎች መጡ፡፡ በአማራ ክልልም ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የመሳሰሉ ነገሮች ተደራርበው ባለፈው ዓመት ችግር እንዲፈጥር አድርገው ነበር፡፡ በአሁኑ ውቅት ግን መንግሥት ያንን ችግር በማየት ችግሩ እንዳይደገም በማድረጉ አሁን በተሳለጠና በተሳካ ሁኔታ ግዥዎች ተከናውነው በሰዓቱ ለበልግና ለመስኖ ለአርሶ አደሩ በበቂ ሁኔታ እና በጊዜ እየደረሰ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ችግር ሲፍጥር የነበረው የማዳበሪያ ግዥ ሥርዓቱ ችግር ስላለበት ነው ተብሏል፤ ችግሩ ከዚህ በኋላ የማያዳግም ችግር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?

አቶ ሰለሞን፡– አዎ! የግዥው መመሪያ የተዘጋጀው በግብርና ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር ነው። መመሪያውን መንግሥት ከላይ ክትትል በማድረግ ማነቆው መፈታት አለበት በሚል ከሀገሪቱ አጠቃላይ የግዥ ሥርዓት የተሻሻለ እና የተለየ፣ እንደየሁኔታው ተለዋዋጭ የሆነ የማዳበሪያ እጥረት ሊያጋጥም በማይችል መልኩ ይፈታል ተብሎ ታስቦ የተዘጋጀና ራሱን የቻለ መመሪያ አለ፡፡ መመሪያው በገንዘብ ሚኒስቴር ጸድቆ ለፍትህ ሚኒስቴር ተልኳል። ስለዚህ የተሰራው ሥራ የማያዳግም ነው ማለት ይቻላል፡፡

የክልሎችን፣ የገንዘብ ሚኒስቴርን፣ በማዳበሪያ ግዥ ላይ ያሉ ሁሉ ተዋናይ ኃላፊነታቸውን፣ መብታቸውን፣ ግዴታቸውን የጠቀሰ ነው፡፡ ጸድቆ በሥራ ላይ ስለዋለ በገንዘብ ደረጃ ብዙ ለውጥ አምጥቷል፡፡

ለአብነት ያህል በባለፈው ዓመት የነበረው አሰራር አንድ ጊዜ በዚህ ወቅት ጨረታ አውጥተን ጥቅምትና ኅዳር አካባቢ የነበረን ዋጋ ወስነን እንይዛለን፡፡ የአፈር ማዳበሪያው ኅዳር ላይ ሊቀንስ ይችላል፡፡ በተለይ ዩሪያ የሚባለው ዋጋው በጣም ተለዋዋጭ ነው፤ አንዴ ክፍ፤ አንዴ ደግሞ ዝቅ ይላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ እንደ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ብራዚል ያሉ ሀገራት በሚያወጡበት ሰዓት እኛ እንዳጋጣሚ ሆኖ እዛ ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ በዚያን ሰዓት የሰጡንን ከፍተኛ ዋጋ ይዘን እንቀመጣለን፡፡

የቀደመው ግዥ አሰራር አንዴ ውለታ ከተገባ በመንግሥት ግዥ ባለስልጣን ተነጋግሮ ለማስቀነስ ፈቃድ ተጠይቆ ነው፡፡ እንደዚያ አይነት አሰራር ደግሞ የሚያመጣው ሙስናንም ጭምር ነው፡፡ አንዴ ውል ከተገባ ቢጨምርም መቀነስ አይቻልም፡፡ ቢቀንስም ደግሞ እንደዚያው ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመን ፈተና አቅራቢዎቹ መሸሻቸው ነው። ሲጨምር “ማቅረብ አንችልም” በሚል ኮንትራቱ የሚፈርስበት እድልም አለ፡፡ እኛ ደግሞ በመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር መመሪያ ስለምንመራ እናስቀንስ ሲባል አይፈቀድም፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን በመመሪያው የምንፈልገው መጠን ዓለም አቀፍ ገበያውን እያየን በተለየ ሁኔታ በቦርዱ ውስጥ ያለው የአመራሩ ስብጥርም የዓለም አቀፍ ገበያው እውቀቱ ያላቸው እንደመሆናቸው በዛ ልክ ተረድተው “በዚህ ጊዜ ጨረታው ይውጣ፤ ይህንን አሁን እንግዛ፤ በቀጣይ ደግሞ እንዲህ እናድርግ፤” የሚሉ በመሆናቸው መርሀ ግብር ወጥቶለት እየተሰራ ነው፡፡ ስለሆነም አካሄዱ መልካም የሚባል ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለ2016/17 የምርት ዘመን እንዳለፈው ጊዜ የአፈር ማዳበሪያ ችግር እንደማይኖር ተጠቅሷል፤ በዚህ ዓመት በእቅድ ደረጃ የተያዘው ምን ያህል ነው?

አቶ ሰለሞን፡– በዚህ ዓመት እንደ እቀድ የተያዘው የአፈር ማዳበሪያ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ኤንፒኤስ ወደ 332 ሺ ቶን፣ ኤንፒኤስ ቢ ወደ አንድ ሚሊዮን ቶን፣ ሲሆን፣ ዩሪያም ተጠቃሽ ነው። መንግሥት በፈቀደው የውጭ ምንዛሬ የሚገዛ ነው፡፡

ነገር ግን የተፈቀደለት እቅድ የያዝነው አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ቶን ነው፡፡ ይህ መርሀ ግብር ወጥቶለታል። አሁን ያሉት የቦርድ አመራር በእውቀትም ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያም የተለዩ ናቸው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር መቼ? ምን? መገዛት አለበት የሚለውን አቅርቧል፡፡ ለመኸር ይህን ያህል፣ ለመስኖና ለበልግም ይህን ያህል ተብሎ ተቀምጧል። በዛ መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የባለፈው አይነት ችግር እንዳይፈጠር የባንኩ ፕሬዚዳንት አብረውን ናቸው፡፡ የምንዛሬ ችግር ከተባለ እንኳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥው የቦርድ አባል በመሆናቸው የሚሰራው በመናበብ ነው፡፡ ከጸጥታም ሆነ ከሌላ ችግር አንጻር እንኳ ችግር እንዳያጋጥም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁ በቦርዱ የተካተቱ ናቸው፡፡ የትራንስፖርት ችግር አለ ቢባል እንኳ ሚኒስትሩ የዚሁ የቦርድ አባል ናቸው። ከዚህ አኳያ ችግሩ የማያዳግም እንዲሆን ተብሎ መንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

ስለዚህ ለበልግና ለመስኖ በቂ ግብዓት ለአርሶ አደሩ እየደረሰ ነው፤ ምናልባት አማራ ክልል ባጋጠመው የጸጥታ ችግር በተወሰነ መልኩ ችግር ብለን የምንለው ተሽከርካሪዎች በአጀብ እየሄዱ መሆኑን እና አሽከርካሪዎች ደግሞ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ስጋት ብጤ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ከዛ ውጪ በአሁኑ ወቅት በታቀደው መጠን እየተሰራበት ነው፡፡

የኤንፒኤስ ዝርያ የሚባሉት 60 በመቶ የአፈር ማዳበሪያ ድርሻ የሚይዙት ውለታው ተፈርሞ ግዥው ተከናውኗል፡፡ አሁን በወጣለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ኤልሲዎች እየተከፈቱ መርከብ ይዞት ይመጣል፡፡ ከዚያም ወደየአርሶ አደሩ ይደርሳል፡፡ ዩሪያን ስንወስድ አቅራቢዎቹም የተበጣጠሱ ናቸው፡፡ ዋጋ ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በጣም ተለዋዋጭ ነው፡፡ ዛሬ ርካሽ ነው ሲባል ነገ የሚወደድበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ ዩሪያን በብዛት የሚጠቀሙ አገሮች አሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ ሕንድ፣ ቻይና እና ብራዚል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ቻይና ለራሷ ሲያንሳት ወደውጭ የምትልከውን ማዳበሪያ ትጠቀማለች፡፡ በዚያን ወቅት በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ እጥረት ይፈጠራል። በሌላ መልኩ ሕንድ ገበያ ላይ ስትወጣ ከፍተኛ ግዥ ትፈጽማለች፡፡ በዚያን ጊዜ አቅራቢዎች የሚሄዱት ወደ ሕንድ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ዋጋው ከፍ ይላል፡፡

ስለዚህ አሁን በመንግሥት የአሰራር ለውጥ በመደረጉ እንደገበያው ሁኔታ ተለዋዋጭ ሆነን መግዛት እንድንችል አድርጎናል፡፡ ዋጋው ውድ ከሆነ አንገዛም፡፡ ርካሽ ከሆነ ደግሞ እንገዛና ይዘነው እንቆያለን፡፡ ስለዚህ ከገበያው ባህሪ ጋር እንድንሰራ አድርጎናል፡፡ የበፊቱ የግዥ ሥርዓት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ግትር በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ አንዴ ከተዋዋልን ተዋዋልን ማለት ነው፤ መቀየር አያቻልም። እንቀንስ ለማለም ጭንቅ ነው።

እንዲያውም የአሁኑ የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስትር ወደ ሚኒስትርነት ከመጡ በኋላ እንደምንም ብለው ያስቀነሱበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ለውጥ መምጣት ስለቻለ ጥሩ ሒደት ላይ ነው ያለው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ለበልግና መስኖ የሚያስፈልግ የአፈር ማዳበሪያ ወደአርሶ አደሩ በምን መልኩ እየተሰራጨ ነው?

አቶ ሰለሞን፡– ለበልግም ለመስኖም የተያዘው መጠን ሙሉ በሙሉ ግዢው ተከናውኗል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አማራ አካባቢ ካለው የጸጥታ ችግር ባሻገር 80 እና 90 በመቶ ወደ አርሶ አደሩ ሄዷል፡፡ ጂቡቲ ላይ ያለው የማጓጓዝ ሥራ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ይህም ከመጣ በኋላ የበልግም የመስኖም ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖችና አርሶ አደሮች እንዲደርስ ተደርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከመኸሩስ ጋር በተያያዘ ከወዲሁ ምን እየታሰበ ነው?

አቶ ሰለሞን፡- የመኸሩ ገና ነው፤ አስቀድሜ እንዳልኩት 60 በመቶ የሚይዘው ኤንፒስ ግዥው ተከናውኗል፡፡ ይህ ማለት ለሶስቱም የምርት ወቅቶች ማለትም ለበልግ፣ ለመስኖ እና ለመኸር ውለታው ተገብቶ ግዢው ተፈጽሟል፡፡ ችግሩ ታድያ ምንድን ነው? ከተባለ በአሁኑ ወቅት አምጥተነው ማከማቻ ማቆየት አንችልም። ከአቅራቢው ጋር ውለታ ተፈራመናል። አስቀድሜ እንደጠቀስኩት ለመስኖም ለበልግም መጥቷል፡፡ ይህንንም ለአርሶ አደሩ አድርሰናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለበልግና ለመስኖ እንጂ ለመኸር ጊዜው ገና ስለሆነ ይህ እንዳለቀ ሄዶ ማምጣት ብቻ ነው፡፡ የመጣውን ደግሞ በሰዓቱ እናደርሳለን፡፡

ውለታ ያልፈጸምነው የዩሪያን ነው፤ የቀረው የመኸር ነው፡፡ የመኸሩን ያልፈጸምንበት ምክንያት ደግሞ እንደድሮ ግትር የሆነ አተያይ ስለሌለን ነው፡፡ አስቀድመን ገበያውን እናጠናለን፡፡ ገበያ ላይ ዛሬ ውድ ሊሆን ይችላል፡፡ ውድ ከሆነ ደግሞ እኛ አንገዛውም። እንጠብቅና ርካሽ የሚሆንበትን ጊዜ አይተን ወቅቱ ከመድረሱ በፊት ግዥውን ፈጽመን እንደርሳለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- አንዱ ተልዕኳችሁ የግብርና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩና ለከፊል አርብቶ አደሩ ማቅረብ እንደመሆኑ በማቅረቡ በኩል የደላላን ጣልቃ ገብነት የምትከላከሉት እንዴት ነው?

አቶ ሰለሞን፡– የግብርና ስራዎች ግዥ የሚከናወነው በግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ነው፡፡ የተወሰነ ከአጠቃላይ ግዥው ደግሞ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ እና ከዛ በታች በሆነ መንገድ የማሰራጨት ስራም ይሰራል፡፡ ይህ ማለት 95 በመቶው ወደ ክልሎች ቀጥታ የሚሄደው ከጂቡቲ ነው፡፡ በመጀመሪያም ቢሆን ፍላጎቱ የሚነሳው ከክልሎች ነው፡፡ ይህም ከቀበሌ ጀምሮ ነው፡፡ እሱ ፍላጎት ተጠናቅሮ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ግዥው እንዲፈጸም ወደእኛ ዘንድ ይመጣል፡፡

እኛ ግዥውን እንዳከናወንን የባህር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክ አገልግሎት መርከብ ተከራይቶም ሆነ የራሱ መርከብም ካለው ከመጫኛ ወደብ ይዞት ይመጣል፡፡ ከዚያም ጂቡቲ ያራግፋልና መኪና አዘጋጅቶ ወደዩኒየኖች ያደርሳል፡፡ ይህ ማለት 95 በመቶ እና ከዚያም በላይ ማለት ነው፡፡

እንደጠቀስኩት አምስት በመቶ እና ከዚያ በታች የሆነችውን እኛ መጋዘን ይገባል፡፡ ያኛው 95 በመቶው ያልኩሽ ቀጥታ ለአርሶ አደሩ የሚሰጥ ነው። የግል ኢንቨስተሮች፣ ሰፋፊ ባለእርሻዎችና የምርጥ ዘር አባዥ ድርጅቶች የሚገዙት ከእኛ ነው፡፡ ይህንንም ቢሆን የምንሸጠው እኛ አይደለንም፡፡ ኢንቨስተሩ ቀጥታ ለግብርና ሚኒስቴር፣ ክልል ላይ ያለ ኢንቨስተር ከሆነ ደግሞ ክልሉ መረጃውን ገልጾ ለግብርና ሚኒስቴር ይልካል፡፡ ግብርና ሚኒስቴሩ ሳይፈቅድ እኛ አንዲት ፍሬ መሸጥ አንችልም፡፡ ለግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን “እከሌ የሚባል የእርሻ ባለቤት ወይም እከሌ የሚባል የምርጥ ዘር ድርጅት ይህን ያህል ሔክታር መሬት በዚህ ክልል ስር ስላለውና ክልሉም ስለደገፈው ከእናንተ ይህን ያህል የአፈር ማዳበሪያ እንዲገዛ ተፈቅዷልና ሽጡለት” ይላል፡፡ እኛ በዛ መልኩ ሽያጩን እናከናውናለን። በዚህ መልኩ ክልል አረጋግጦ ለግብርና ሚኒስቴር ልኮ ግብርና ሚኒስቴር ደግሞ ይሸጥለት ሲል በትእዛዙ መሰረት ሽያጮችን እናከናውናለን፡፡

በዚህ መሃል ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ማዳበሪያ ወዳልተፈለገ ቦታ ሊሄድ አይችልም ወይ? ከተባለ አይታወቅም ሊሄድ ይችላል፡፡ የእኛ ኃላፊነት ግን ሽያጭ ማከናወን ነው፡፡ ነገር ግን ክልሉ ያስፈቀደለትን እና የደገፈውን ድርጅት እዛ ድረስ መምጣቱን መከታተል ይፈልጋል፡፡

ክልሉ ለግብርና ሚኒስቴር የሚልከው ሰነድ “ለእከሌ ድርጅት ማዳበሪያ ይሰጥልኝ፤ እደግፋለሁ፤ እኔ ዘንድ ኢንቨስተር ነው” ብሎ ነው፡፡ ግብርና ሚኒስቴርም ወደእኛ ዘንድ ይልከዋል፡፡ ግልባጭ ላይ የሚደረገው ማዳበሪያው ክልል መድረሱንና ለተፈለገው መዋሉን ክትትል ያድርግ ይላሉ፡፡ ስለዚህ የእኛ ሚና እዚህ መስጠት እንጂ ክልል ላይ ሔዶ መከታተል አይደለም። በዚህ አጋጣሚ ግን ሕገ ወጦችን በምናይበትና በምናገኝበት ጊዜ የበኩላችንን ለመከላከል ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ እንደ ሀገሪቱ ስንመለከት አንድ ሚሊዮን 940 ሺ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ተገዝቷል፡፡ የዚህ 90 በመቶ ቀጥታ የሚሄደው ክልሎች ዘንድ ነው።

እኛ በቅርቡ ያደረግነው ነገር ቢኖር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ፈጥረን መረዳቱ እንዲኖር ነው። በተለይ ችግር ሲኖር መከላከል እንዲቻልና የአሰራር ሥርዓት መለወጡን እንዲሁም ማዳበሪያው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚመጣ መሆኑን ግንዛቤ እንዲኖር ነው። መንግሥት የአሰራር ለውጥ ስላመጣ እነርሱም በዚያው ልክ እንዲረዱ ባለድርሻ አካላትን አወያይተናል።

በእርግጥ በማዳበሪያ ዙሪያ እጥረት ሲኖር ሕገ ወጦችም አብረው ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር ተያይዞ አሸከርካሪዎች ጭምር ክትትል ይደረግባቸዋል። በተለይ ከጂቡቲ ጭነው ሲወጡ አራት ቦታ ክትትል የሚደረግባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ አጉድሎ የመጣ ትራንስፖርት ሰጪ በወንጀል እንዲጠየቅ ይደረጋል። የሚከፍለው ደግሞ እኛ በገዛንበትና ለአርሶ አደሩ በሚደርሰው ዋጋ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ትራንስፖርት ሰጪ ድርጅት ቀደም ሲል ሲያደርግ የሚስተዋለው ማዳበሪያውን ገበያ ላይ ወስዶ በውድ ዋጋ ይሸጠውና “ጎደለብኝ ልክፈል” ይል ነበር። እሱ ግን አሁን አይሰራም፡፡ ድሮ ጉድለት ሲኖር ራሱ የጉድለት ማስከፈያ ሥርዓት አለ፤ የመበላሸት፣ የመገልበጥና በተለያየ ምክንየያት የሚመጡ ጉድለቶችን ያን ያህል ሕገ ወጥ የሆነ ስላልነበር በዛ መልኩ ይሰራ ነበር፡፡ አሁን ግን የሚያስጠይቀው በወንጀል ነው። ከፍሎ ብቻ መገላገል የሚባል ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ማኅበሩን እስከማገድና ተጠያቂ እስከማድረግ የሚያደርስ ሲሆን፣ ይህ ሹፌሩንም የሚጨምር ነው። በአሁኑ ወቅት ግን በተለይ በዚህ ዓመት አቅርቦቱም አስተማማኝ ሲሆን፣ ስራውም የተሳለጠ ነው ማለት ይቻላል፡፡

እስካሁን ባለው አካሔድ የታየው ነገር ቢኖር ስኬታማነቱ ነው፡፡ በተለይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ስርዓት ከግትር ባህሪው ተላቅቆ እንደየግዥ ባህሪው ሊለዋወጥ ስለሚችል ችግሩ ተወግዷል፡፡ ትንሽ ችግር ያለው ዩሪያ ላይ ነው፡፡ የበልግና የመስኖው እንዳልኩት ሙሉ በሙሉ የቀረበ ሲሆን የቀረን ጥቂት የበልግ ነው፤ እሱም በትክክለኛው ሰዓት የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ትንሽ በቀይ ባህር አካባቢ እንደ ስጋት ከሰሞኑን የታዩ ነገሮች አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ ምናልባት እንደስጋት ልናይ የምንችለው እሱን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ ከምርምር ተቋማት መነሻ ዘር ተቀብሎ እንደሚያባዛና ለተለያዩ ስነ ምህዳር እንዲውሉ ማድረግ ላይ ይሰራል፤ ከዚህ አኳያ የተከናወኑ ተግባራት እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ሰለሞን፡- ኮርፖሬሽኑ ሲመሰረት የተለያዩ አምስት ድርጅት ተዋህደው ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ምርጥ ዘር ድርጅት፣ የእርሻ መካናይዜሽን አገልግሎት፣ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኮርፖሬሽኑ የተቋቋመው ከ2008 ዓ.ም ነው። ከዛ በፊት ግን ለሀገሪቱ ብቻውን ምርጥ ዘር አቅራቢ የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑም የምርጥ ዘር ክፍተቶችን እየሸፈነ ከመሆኑም በተጨማሪ በራሱ ደግሞ አዳዲስ የሚላቸውን እያስመጣ እና እያባዛ ነው፡፡ የአቅሙን ያህል እያደረገ ነው፡፡

በመካናይዜሽኑም በኩል ያለው ከመካናይዜሽን አገልግሎት ጋር ከመዋሃዳችን በፊት ልክ እንደ ምርጥ ዘሩ መካናይዜሽንም ለብቻው በራሱ ይሰራ የነበረ ነው፡፡ የመካናይዜሽን አገልግሎት ቀደም ሲል ማረስ፣ መከስከስና ምርት እስከመሰብሰብ ድረስ ያለውን ይሰራ ነበር፡፡ ወደ እኛ በሚመጣበት ጊዜ አቅሙ ያን ያህል ከፍተኛ አልነበረም፡፡ ወደ እኛ የመጣው ተዳክሞ ነው።

ከዛ በኋላ ግን አዳዲስ ትራክተሮችን፣ ኮምባይነሮችን ተቀጽላ ማሽነሪዎችን አገልግሎት በመስጠትም ተደራሽም በመሆን ላይ ነው፡፡ የገበያ ክፍተት አለባቸው ወደሚባሉ ክልሎች ዘንድ እየሄደ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ይሁንና ውስንነት መኖሩ የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኮርፖሬሽኑ በተሰጠው ካፒታል መጠን ባሉት ትራክተሮችና ኮምባይነሮች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ነው፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የእርሻ መሳሪያ የሚሆኑ መለዋወጫዎችን እየገዛን እናቀርባለን፡፡ ይሁንና አሁን ላይ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ አለ፡፡ ቢሆንም የአማራ ክልል የውጭ ምንዛሬ አግኝቶ ስለነበር ከ80 ትራክተሮች በላይ ገዝተን አስረክበናቸዋል። እኛም በራሳችን የምናመጣቸውን ለሚፈልጉ ክልሎች እንዲሁም ለባለሀብቶች የእርሻ መሳሪያውን ብቻ ሳይሆን አብሮ ተቀጽላ መሳሪያዎችን እያመጣን እንሸጣለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰግናለን።

አቶ ሰለሞን፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

በአስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You