ትላንትም ይሁን ዛሬ እንደሀገር ያጋጠሙንን ሆኑ አሁን ላይ እያጋጠሙን ያሉ ችግሮችን ተሻግረን ማለፍ ያልቻልነው ችግሮቹን ቁጭ ብለን በሰከነ መንፈስ መነጋገር ባለመቻላችን እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም የመጣንበት የፖለቲካ አመለካከትና አመለካከቱ የወለደው የፖለቲካ ባሕል ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።
በየትኛውም ማኅበረሰብ፤ በተለይ እንደኛ ባለ ብዝኃነት መገለጫው ፤ከዚያም በላይ የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ፤ የሀሳብ ልዩነቶች መፈጠራቸው እንደ ችግር የሚቆጠር ሳይሆን፤ ለለውጥ መነቃቃት እንደ አንድ መልካም ዕድል የሚታይ ነው።
ይህን መልካም እድል መሸከም የሚችል የአስተሳሰብ መሠረት ማዋቀር አለመቻላችን፤ ረጅም ዘመናት ባልተገባ መልኩ በግጭት አዙሪት ውስጥ እንድንዳክር አድርጎናል። በዚህም በየዘመኑ የነበረው ትውልድ ከፍያለ ዋጋ ለመክፈል ተገድዷል። የታሪካችንም አብዛኛው ምዕራፍ የግጭትና የጦርነት ሆኗል።
ከዚህ የተነሳም በአንድ ወቅት ከነበርንበት ትልቅነት /የሥልጣኔ ማማነት/ ቁልቁል ወርደን አሁን የምንገኝበት አንገት የሚያስደፋ ድህነትና ኋላቀርነት ውስጥ እንድንገኝ ሆነናል። ድህነት እና ኋላቀርነት ለሚፈጥረው ለማኝነት/ ጠባቂነት/፤ ለማኝነት ለሚፈጥረው የልብ ስብራት ሰለባ ለመሆን ተገደናል።
የቀደሙት አባቶቻችን እስከዛሬ ዓለምን እያስደመሙ ያሉበትን እውቀትና ክህሎት በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ትንሳዔ እያገኘ ዘመኑን በሚዋጅ የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ አድጎ ሀገርን እንደቀደሙት ዘመናት የትልቅነት ማማ ማድረስ የምንችልበት ሰላምና መረጋጋት አጥተን ዘመናት አስቆጥረናል።
ከራሳችን ጋር መታረቅ አቅቶን ሰላምና መረጋጋት ባጣንባቸው ረጅም ዓመታት፤ ዓለም ከሁሉም በላይ ለሰላሙ ትኩረት ሰጥቶ፤ የሰላሙ ፍሬ/በረከት የሆነውን ዕድገትና ብልጽግና እያጣጣመ ነው፤ ከዕለት ተለት የሕይወት ፈተና ወጥቶ ሕይወትን ድንቅ እያደረገ ይገኛል ።
እኛ እንደ ሀገር ትናንቶቻችንን በአግባቡ አውቀን ከነሱ ለመማር የተከፈተ ልብና አእምሮ በማጣታችን፤ በተመሳሳይ ስህተት አዙሪት ውስጥ እንድንገኝ፤ ተመሳሳይ ያልተጋባ ዋጋ እንድንከፍል እያደረገን ነው። ከዚህም ባለፈ ነገዎቻችን የጽልመት ግርዶሽ እንዲሸፍናቸው ጫና እየፈጠረ ነው ።
አሁን ላይ እውነታዎች እየተቀየሩ፤ ትውልዱ ከትናንት ስህተቶች ተምሮ ዛሬውንም ሆነ ነገዎችን ብሩህ ለማድረግ በሚያስችል መነቃቃት ውስጥ ለመገኘቱ ተስፋ ሰጭ ተግባራት እየታዩ ነው። ለዚህ ደግሞ ችግሮችን በመወያየት ለመፍታት እያሳየ ያለው አሁነኛ መነቃቃት ተጠቃሽ ነው ።
ትውልዱ እያሳየ ያለው ይህ ችግሮችን በውይይት የመፍታት መነቃቃት በአንድም ይሁን በሌላ ትላንቶችን እና ትናንቶች የተገዙበትን እሳቤ ከመረዳት፤ እሳቤው የቱን ያህል ሀገርና ሕዝብን ዋጋ እንዳስከፈለና እያስከፈለ እንዳለ ከመገንዘብ የመነጨ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት አይከብድም ።
በርግጥ አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው፤ አስተውለነው ይሁን ሳናስተውለው ብዙ የኪሳራ ዘመናትን ኖረናል። ለዘመናት ኪሳራ የዳረገን ልዩነቶቻችንን በኃይል እና በሴራ የመፍታት የጥፋት መንገድ፤ አሁን ላይ አንድ ርምጃ ሊያስኬደን አይችልም። ከዚህ ይልቅ እንደ ሀገር በብዙ ውጣ ውረድ የገነባነውን ብሔራዊ ማንነት ሊያፈርስና ሊበትነን የሚችል አሁናዊ የስጋት ምንጭ ነው።
ይህንን አሁናዊ ስጋት አስተማማኝ በሆነ መንገድ መሻገር የምንችለው፤ ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት በትውልዱ ውስጥ ለተፈጠረው መነቃቃት ፤ተገቢውን ዕውቅና ስንሰጥና ፤እንደ ትውልድ ብዙ ትውልዶችን ዋጋ እያስከፈለ ካለው የግጭት አዙሪት መውጣት ስንችል ብቻ ነው ።
በኃይልና በሴራ እርሾ እየተቦካ ሲጋገር የኖረው የሀገራችን የፖለቲካ አስተሳብ /ሥርዓት ትውልዶችን በየዘመኑ ከአስከፈለው ያልተገባ ዋጋ አንጻር ፤ በዚህ ትውልድ እየታየ ያለው አዲስ የፖለቲካ እሳቤ ፤ እሳቤው የወለደው መነቃቃት፤ እንደሀገር ከፊታችን የካሳ ዘመን መቅረቡን አመላካች ነው።
አሁን ላይ በችግሮቻችንን ዙሪያ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለን ለመነጋገር የደረስንበት መግባባት ፤ይህን ተከትሎም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋማችንና ወደሥራ መግባቱ ፤ ትውልዱ ከትናንት ስህተቶች መማር ስለመጀመሩ፤ ችግሮችን በውይይት የመፍታት አዲስ ሀገራዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ስለመምጣቱ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ ሙሉ በሙሉ ህይወት ዘርቶ ለረጅም ዘመናት ያጣናቸውን ባለብዙ ተስፋ ቀናቶች ነገ ላይ በተሻለ መልኩ እጃችን ለማስገባት፤ በዚህም ሀገራችንን እንደሀገር ወደቀደመችበት የዕድገትና የስልጣኔ ማማ ለመመለስ ትውልዱ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የጀመረውን ሀገራዊ እሳቤ የራሱ፤ የብሩህ ዕጣ ፈንታው መሠረት አድርጎ ሊወስደው ይገባል!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም