“ግብፅ የዓባይ ግድብን የውዝግብ ማዕከል የምታደርገው የውሃው ብቸኛ ባለቤት ለመሆን ካላት ፍላጎት ነው”-ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር) የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪ

አዲስ አበባ፡ ግብፅ የዓባይ ግድብን በተደጋጋሚ የውዝግብ ማዕከል ለማድረግ የምታደርገው ጥረት የውሃው ብቸኛ ተጠቃሚ እና ባለቤት እኛ ነን ከሚል ፍላጎት የመነጨ መሆኑን የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር)ተናገሩ።

የውሃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ(ዶ/ር)ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ግብጽ በተደጋጋሚ የዓባይ ግድብን የውዝግብ ማዕከል ለማድረግ የምታደርገው ጥረት ዓባይን ጨምሮ በጠቅላላ በናይል ተፋሰስ ላይ በታሪክም በተፈጥሮም መብታችን ሊነካ አይችልም ከሚል መነሻ የሚመነጭ ነው ።

ግብፆች ከኢትዮጵያ ጋር የመደራደር ፍላጎት ካጡ ቆይተዋል የሚሉት ተመራማሪው የግብፆች ፍላጎት በተለይም የውሃውን ባለቤትነት ኢትዮጵያ እንድትለቅላቸው እንጂ ኢትዮጵያ ባለመብት መሆኗን እና የውሃው አመንጪ ሀገር እንደመሆኗ የራሷ የልማት ፍላጎት እንዳላት ጠፍቷቸው አይደለም ሲሉ ገልጸዋል ።

ግብፆች የሚሉት የውሃ ሙሉ ባለቤትነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ውሃ አመንጪ ሀገራት ተቀባይነት እንደሌለው እንደሚረዱ ተናግረው በ 4ኛው ዙር የተደረገውን ድርድር እንዲሁም ከዛም በፊት በነበሩ ሂደቶች ግብፆች አልተስማማንም የሚሉት እኛ የምንፈልገው ካልሆነ ሌሎችን ቢጠቅምም ባይጠቅምም ድርድሩ ይፈርሳል ከሚል ግምት መሆኑን ተናግረዋል።

የውሃ ተመራማሪው እንደሚሉት ሱዳንና ግብፅ ውሃውን ሙሉ ለሙሉ የመጠቀም ስምምነት ስላላቸው ስምምነቱን ኢትዮጵያም ሌሎች ሀገራትም እንዲያፀድቁ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ በሉዓላዊ ግዛቷ ውስጥ የውሃ ሀብቷን ለዜጎቿ የማልማት መብት ያላት መሆኑን መገንዘብ ይገባል። የዓባይ ግድብ ሥራ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ሌሎች ግድቦችም በዓባይ ምንጮች ላይ መሠራት አለባቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ በውሃ ሀብቶች ላይ የሚሠሩ ልማቶች የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት እስካልጎዱ ድረስ መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረው በዓባይ ግድብ ላይም እነዚህ ሀገራት እንዳይጎዱ እና ለጋራ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን አስታውሰዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ግብፆች መልማት የኢትዮጵያ መብት መሆኑን ተቀብለው ሲመጡ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ድርድር ማካሄድ ይቻላል። ሆኖም ድርድሩ እንዲሳካ የግብፆች ሀሳብ መለወጥን ይጠይቃል። በኢትዮጵያ በኩል ግን ምንጊዜም ለድርድር ክፍት ተደርጓል።

በቀጣይ ውሃን በጋራ የመጠቀምና የመልማት ጉዳይ ላይ ብዙ ሀሳቦች ቀርበው በድርድር ወደ ጋራ ልማት ሊያመራ ይችላል ያሉት ዶክተር ያዕቆብ ይህ ካልሆነ ግን ጊዜ የሚወስድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ግብፅ በሚዲያ የምታደርገው ስም የማጥፋት ዘመቻ ትክክል እንዳልሆነ የተናገሩት የውሃ ተመራማሪው በኢትዮጵያ በኩልም የግል እና የመንግሥትም የሚዲያ ተቋማት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም የልማት ተቋማት የዓባይ ግድብ የኢትዮጵያ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጉዳይ መሆኑን በማስረዳት ረገድ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጨመር እንዳለበት ገልጸዋል።

መዓዛ ማሞ

 አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You