ሰላም የሕጻናት መንደር፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅትነት ባሻገር

ኢትዮጵያውያንን አንገት ከሚያስደፉ ጉዳዮች መካከል ድህነት አንዱና ዋነኛው ነው:: ለዚህም በ1977 ዓ.ም ተከስቶ የነበረው ድርቅና እሱን ተከትሎ የተከሰተው ረሃብ በሀገሪቱ ዜጎችና ገጽታ ላይ ጥሎት ያለፈው ትልቅ ጠባሳ ይጠቀሳል::

በወቅቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሕጻናት በረሃብ ለታጠፈ አንጀታቸው እህል ውሃ ፍለጋ ፣ መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት፣ ጥሩ እንዲለብሱና እንዲጫሙ እንዲሁም የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ በሚል ገና በለጋ ዕድሜያቸው ለውጭ ሀገር ዜጎች በማደጎ ተሰጥተዋል፤ በዚህም እናት ምድራቸውን ለቀው ከባህር ማዶ ብዙ ርቀው እንዲጓዙ ተገደዋል:: በዚህ አይነት መንገድ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁና ከወላጆቻቸው ዕቅፍ የወጡ ከትውልድ አገራቸው የተሰደዱ ህጻናት በርካታ ናቸው::

ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከልም ‹‹ዞሮ ዞሮ ከቤት፤ ኖሮ ኖሮ ከመሬት›› እንዲሉ ክፉውን ጊዜ አልፈው ወደ ትውልድ ሀገራቸው በመመለስ በበጎ ሥራ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን ጥቂቶች አይደሉም:: የ ‹‹ሰላም የሕጻናት መንደር›› መሥራቾች ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን መካከል ይጠቀሳሉ::

ድርጅቱ በበጎ ሥራ በተለይም ሕጻናትን በማሳደግና በማስተማር የነገ ተስፋቸውን ጭምር ብሩህ የማድረግ ዓላማን ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው:: ሕጻናቱን ከልጅነት እስከ ዕውቀት በዕቅፉ ውስጥ አድርጎ ያሳድጋል:: መግቦ፣ ተንከባክቦና አስተምሮ ለወግ ማዕረግ ያደርሳል::

ላለፉት 38 ዓመታት በተጓዘባቸው መንገዶች ሁሉ የተለያዩ መሰናክሎች ቢገጥሙትም ከበጎ ሥራው አልቦዘነም:: በርካታ ሕጻናትን ከወደቁበት አንስቶ ሕይወት ዘርቶባቸዋል:: ዕድሉን አግኝተው በድርጅቱ ያደጉ በርካታ ሕጻናትም ዛሬ ትልቅ ሰው ሆነዋል:: ትዳር መስርተው ሕይወታቸውን የሚመሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተፈጥረውበታል:: የቢዝነስ ባለቤት የሆኑና ለብዙዎች የተረፉ የትናንት ሕጻናት የዛሬ ጎልማሶችም ጥቂቶች አይደሉም::

‹‹ለልጆች የተሻለ ሕይወት መፍጠር›› በሚል መርህ በጎ ሥራን ከቢዝነስ ሥራ ጋር አጣምሮ የሚሠራው ሰላም የሕጻናት መንደር የተቋቋመው በቁጭት ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ:: በታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያ የገጠማትን ረሃብ ምክንያት በማድረግ ለማደጎ የተሰጡ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ስድስት ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ወደ ስዊዘርላንድ ያቀናሉ:: እነዚህ ስድስት እህትና ወንድማማቾች በስዊዘርላንዳውያን አሳዳጊዎቻቸው እቅፍ በእንክብካቤ ያድጋሉ:: ጥሩ ተመግበው፣ ጥሩ ለብሰው የተሻለ ትምህርት አግኝተዋል::

አድገው ነፍስ ባወቁ ጊዜ ትናንትናቸውን ሲፈትሹ ከበስተጀርባቸው ያለው ታሪክ በእጅጉ ያስቆጫቸውና ሁኔታው እንደ ኢትዮጵያዊ ገጽታን የሚያበላሽ ሆኖ ያገኙታል:: ‹‹ኢትዮጵያውያን ረሃብተኞች አይደለንም›› በሚል ቁጭትም አንዷ የቤተሰቡ አባል ወይዘሮ ፀሐይ ሮሽሊ ወደ እናት ምድራቸው ተመልሰው ሰላም የሕጻናት መንደር ይመሠርታሉ::

የሰላም የሕጻናት መንደር መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ፀሐይ፣ በስዊዘርላንድ እያሉ ስለ ኢትዮጵያ ያገኙት መረጃ ‹‹ረሃብተኛ›› የሚል ቅጽል ስም ነበር:: በመሆኑም የኢትዮጵያን ገጽታ ያጠለሸውን፣ ኢትዮጵያውያንን ለስደት የዳረገውን ድህነት በሥራ ማሸነፍ ይቻላል በሚል ቁጭት በወቅቱ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው የቻሉትን ለማድረግ ወሰኑ::

በወቅቱ በውሳኔያቸው የተደሰቱት ስዊዘርላንዳውያን አሳዳጊዎቻቸውም የበጎ ሥራቸው አጋር በመሆን አግዘዋቸዋል:: ወይዘሮ ፀሐይ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ቅጽበት ሙሉ አቅማቸውን፣ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ ሠጥተዋል:: ማረፊያቸውንም ድርጅቱ ከሚገኝበት ኮተቤ አካባቢ በማድረግ ችግረኛ ሕጻናትን ሰብስበው አሳድገዋል:: ቀስ በቀስም ትምህርት እንዲማሩ ብሎም ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ የበርካታ ሕጻናትን ነገ ብሩህ ማድረግ እንደቻሉ ታሪካቸው ያስረዳል::

በኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ፍቅርና ቁጭት የተመሠረተው ሰላም የሕጻናት መንደር አንድ ሁለት እያለ ሕጻናቱን ከማሳደግና መንከባከብ በተጓዳኝ በማስተማር ሥራ ላይ ይሰማራል:: በዚህም የድርጅቱ መስራችና ባለቤት ወይዘሮ ጸሐይ፤ ቁጭታቸውን በሥራና ሥራ ብቻ መወጣት ችለዋል:: ሙሉ ለሙሉ መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ በማድረግም በጎ ሥራቸውን ሲከውኑ ሶስት አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል:: ወይዘሮ ጸሐይ ሕጻናትን በማሰባሰብ፣ በመመገብና በማስተማር ሥራ ውስጥ በማሳለፋቸው እጅግ ደስተኛ እንደሆኑም ይነገርላቸዋል::

ድርጅቱ ከርዳታ ሰጪ ድርጅትነቱ በተጨማሪ የቢዝነስ ተቋም የመሆን አጋጣሚን በመፍጠር በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ስለመሆኑ በሰላም የሕጻናት መንደር የማምረቻ ክፍል ማናጀር አቶ ሙስጠፋ ታፊሮ ገልፀዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ በድርጅት ውስጥ ሕጻናት እንደ አንድ ቤተሰብ በእንክብካቤ ያድጋሉ፤ ትምህርታቸውን ይማራሉ፤ በሚፈልጉት ሙያ ሰልጥነው ወደ ሥራ ይሰማራሉ:: የድርጅቱ አንድ አካል በሆነው ቴክኒካል ኮሌጅ ውስጥ በግቢው ካደጉ ልጆች በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ ልጆችም በቴክኒካል ኮሌጁ መማር ይችላሉ::

በኮሌጁ በተለያየ የሙያ ሥልጠና ሰልጥነው ራሳቸውን የቻሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ:: ሰላም የሕጻናት መንደር በሀገሪቱ የታወቀ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋምም ነው:: በአፍሪካ ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት በ10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል::

ልጆችን ሰብስቦ ከመንከባከብ፣ ማሳደግና ከማስተማር ጎን ለጎን ወጣቶች የሚሰማሩበትን የተለያዩ በሮች የከፈተው ሰላም የሕጻናት መንደር ቴክኒካል ኮሌጅ ሲከፈት በድርጅቱ ያደጉ ሕጻናትን በሙያ አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማሰማራት በሚል እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሙስጠፋ፤ በሂደት ግን ከድርጅቱ ውጭ ያሉ ተማሪዎችም መሰልጠን የሚችሉበትን ዕድል በማማቻቸት ቴክኒካል ኮሌጁ በምግብ ሙያ፣ በጋራዥ ሥራ፣ በጋርመንት፣ በብረታብረትና በእንጨት ሥራ ሙያተኞችን ሲያፈራ እንዲሁም የተለያዩ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል ሲሉ ያብራራሉ::

በቴክኒክ ኮሌጅ ዕውቅናን ያተረፈውና ከማሰልጠን ባለፈ አምርቶ ለገበያ ሲያቀርብ የቆየው ሰላም የሕጻናት መንደር፣ የማምረት ሥራውን ገቢ ከማመንጨት ሥራ ለይቶ እንዲሠራ ከመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት በ2004 ዓ.ም ‹‹ፀሐይ ሮሽሊ ኢንዱስትሪያል እና አግሪካልቸራል ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ›› ሆኖ በመቋቋም አንድ የቢዝነስ ተቋም ሆኗል:: ከሕጻናት ማሳደጊያ ተነጥሎ የቢዝነስ ተቋም የሆነው ፀሐይ ሮሽሊ ኢንዱስትሪያል እና አግሪካልቸራል ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ ባሰለጠናቸው ሙያተኞች እጅ የተመረቱ የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ ያቀርባል::

‹‹ድርጅቱ ለትርፍ የተቋቋመ እንደመሆኑ ያተርፋል›› ያሉት አቶ ሙስጠፋ፤ ጸሐይ ሮሽሊ ኢንዱስትሪያል እና አግሪካልቸራል የሕጻናት ማሳደጊያው እህት ኩባንያ እንደሆነ ገልጸው፤ የድርጅቱ ምርትም በገበያ ተወዳድሮ እንደሚሸጥ ተናግረዋል:: የሚያተርፈውን ትርፍም መልሶ ለሕጻናቱ ማሳደጊያ ያውላል:: የድርጅቱ ዋና ዓላማና ግብም ትርፉን ሕጻናት እንዲያድጉበትና ነገ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነ ነው አቶ ሙስጠፋ ያስረዱት::

ገቢ እያመነጨ መልሶ ለሕጻናቱ የሚከፍለው ጸሐይ ሮሽሊ ኢንዱስትሪያል እና አግሪካልቸራል ኮሌጅ፣ አዳዲስ ነገሮች በመፍጠር ላይም እንደሚሠራ አቶ ሙስጠፋ ጠቁመዋል፤ ተቋሙ አርሶ አደሩን ሊጠቅሙ በሚችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ ሲሆን፤ በዋናነት አዳዲስ ነገሮችን በመፍጠር እንዲሁም የሰዎችን ሃሳብና ዕቅድ በመውሰድ ደንበኞች የሚፈልጉትን ሥራ ሠርቶ ያስረክባል:: በተለይም አርሶ አደሩ ላይ ትኩረት በማድረግ እህል የሚወቃበትን፣ የሚያጭድበትን፣ መኖ የሚያዘጋጅበትን፣ ወተት የሚይዝበትንና ሌሎችንም ቁሳቁስ ያመርታል::

ድርጅቱ ብረትና እንጨት በመጠቀም ጀልባን ጨምሮ የተለያዩ የእንጨት ሥራዎችና የብረታ ብረት ሥራዎችን ያመርታል የሚሉት አቶ ሙስጠፋ፤ ከምርቶቹ መካከልም የልጆች መጫወቻዎች፣ ኩር ኩር ጋሪ፣ ገልባጭ፣ ውሃ ማውጫ የእጅ ፓምፖች፣ የንብ ቀፎ፣ ማርን ከሰፈፉ መለያ፣ በንብ ከመነደፍ መከላከያ /ማጨሻ/፣ ሩዝን ከገለባ መለያ፣ እንደ በቆሎና ስንዴ የመሳሰሉ ሰብሎችን የሚፈለፍል ማሽን፣ የእንስሳት መኖ መክተፊያ፣ ኮምፖስት ማዘጋጃ፣ ለግንባታ አገልግሎት የሚውል የሸክላ ጡብ፣ የጣሪያ ክዳን፣ ብሎኬት ማምረቻ ማሽን፣ የወፍጮ ድንጋይ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል:: በርና መስኮቶችን ጨምሮ የምግብ ጠረጴዛና የቤት ውስጥ ቁሳቁሶችንም ያመርታል::

በሀገሪቱ ችግር ፈቺ ሥራዎችን እየሠራ ያለው ኮሌጁ፣ ምርቶቹ በሙሉ ጥራታቸውን የጠበቁና ተፈላጊ እንደሆኑም ነው አቶ ሙስጠፋ የገለጹት:: በተለይም አርሶ አደሩን የሚያግዙና የሚደግፉ ማሽኖችን በመሥራት ቀዳሚ እንደሆነ ገልጸው፤ በቅርቡም አዲስ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን መሥራቱን ጠቅሰዋል:: ይህን የበቆሎ መፈልፈያም በቆሎ በስፋት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሆነና ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ማሽኑን በቆሎ በስፋት በሚመረትበት ጦላይ አካባቢ ወስዶ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል::

ከዚህ በተጨማሪም ጤፍ፣ በቆሎና ስንዴን በአንድ ጊዜ መውቃት የሚችል ማሽን መሥራት መቻሉን ገልጸው፤ በተለይም እንደ በቆሎና ባቄላ የመሳሰሉ ምርቶችን ሸልቅቆ ምርቱን ከገለባ በመለየት ገለባውን መኖ እንደሚያደርግ ይገልፃሉ:: እነዚህን ማሽኖችም ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ ማዳን እየተቻለ መሆኑንም ጠቅሰው፣ የአርሶ አደሩን ድካም ከማቃለል ባለፈም እነዚህን ማሽኖች ከውጭ በማምጣት የሚጠፋውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን እንደሚቻል አቶ ሙስጠፋ አስረድተዋል::

‹‹የተለያዩ ድርጅቶች አዳዲስ ነገር ሲሠሩ ወደ ጸሐይ ሮሽሊ ኢንዱስትሪያል እና አግሪካልቸራል ኮሌጅ በመምጣት እገዛና ድጋፍ ይጠይቃሉ›› የሚሉት አቶ ሙስጠፋ፤ በቅርቡም አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ 25 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመገበውን ቆጮ መፋቅ የሚያስችል ማሽን ሠርቶ ወደ ድርጅቱ ማምጣቱን ተናግረዋል:: ከድርጅቱ ጋር በጋራ ለመሥራት ስምምነት መደረጉንም ጠቅሰው፣ በዚህም ቆጮ በሥርዓት ባለመፋቁ የሚፈጠረውን ችግር መፍታት እንደሚቻል ጠቅሰዋል:: ትልቁን ትኩረት ለግብርና ሥራዎች ሰጥቶ የሚሰራው ይህ ተቋም፣ በአሁኑ ወቅት በተለይም መንግሥት ትኩረት ላደረገባቸው የስንዴና የሩዝ ምርቶች መፈልፈያ ማሽን ማምረት ችሏል ብለዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ የተቋሙ አብዛኛዎቹ ምርቶች ሸማቹ በፈለገው መሠረት በትዕዛዝ የሚሠሩ ናቸው:: እስካሁን ያላቸው የገበያ ሁኔታ ትዕዛዝን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት አምርተው ወደ መሸጥ እየገቡ ነው:: የድርጅቱ ምርቶች መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ በሚል በሁለት ይከፈላሉ፤ መደበኛ የሆኑት ለአርሶ አደሩ አገልግሎት የሚውሉትን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁስ ናቸው:: መደበኛ ያልሆኑት ደግሞ ገበያ የሚፈለግላቸው ሥራዎች ናቸው:: በኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ችግሮችን በመለየትና ለችግሩ መፍትሔ የሚሆኑ ቁሶችም ይመረታሉ::

ለአብነትም አርሶ አደሩ ምን እንደቸገረው በመጠየቅ በሚፈልግበት መንገድ ተሻሽለው የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው:: ከእነዚህ ሁለት አይነት አሠራሮች ውጭ ደግሞ አሁን ላይ ድርጅቱ የፈርኒቸር ምርቶችና የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ለመስራት ተዘጋጅቷል:: ለአብነትም ብሎኬት፣ ብረት፣ የጣሪያ ክዳን፣ ጌጠኛ ቪላዎችን፣ ካፌዎችንና ሬስቶራንቶች ለመለየት የሚያገለግሉ ጡቦችን አምርቶ ወደ ገበያ የማውጣት ዕቅድ ይዞ እየሠራ ይገኛል::

‹‹ምርቶቹ በከፍተኛ ጥራትና በትክክለኛው ጥሬ ዕቃ የሚመረቱ በመሆናቸው ዋጋቸው ሌሎች ከሚያመርቷቸው ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው›› የሚሉት አቶ ሙስጠፋ፤ ይህ በመሆኑም የድርጅቱ ምርቶች የጥራት ጥያቄ ተነስቶባቸው እንደማያውቅና ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ እንደሆነም ተናግረዋል::

ድርጅቱ ለእዚህ ስራውም 160 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ሠራተኞቹም በቋሚነትና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፤ በቀጣይም ሥራዎቹን በማስፋት ተጨማሪ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ እንዳለም አቶ ሙስጠፋ ተናግረዋል::

ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻርም ድርጅቱ በራሱ ማህበራዊ ሃላፊነትን የሚወጣ ቢሆንም፣ በኮሌጁ በኩል የተለያዩ ድጋፎችን ለማህበረሰቡ በማድረግ ይታወቃል:: እህት ኩባንያ የሆነው ጸሐይ ሮሽሊ ኢንዱስትሪያል እና አግሪካልቸራል ኮሌጅ፣ እንደ ቢዝነስ ተቋም ለአካባቢው ማህበረሰብ ግማሽ ኪሎ ሜትር የሚደርስ የአስፋልት መንገድ አስገንብቷል:: አካባቢውን ለማስጠበቅ የደንብ ልብስ አሰፍቶ የጥበቃ ሠራተኞችን በመቅጠር፣ ወጣቶችን አደራጅቶ ማምረቻ ማሽን በመስጠትና ሌሎች ማህበራዊ ኃላፊነቶችን በመወጣት የድርሻውን እየተወጣም ይገኛል::

በቀጣይም ድርጅቱ በዋነኛነት የአርሶ አደሩን ችግር በመረዳት መፍትሔ ለመሆን እንደሚሠራ የጠቀሱት አቶ ሙስጠፋ፤ ለእዚህም በአራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉን ጠቁመዋል:: እሳቸው እንዳሉት፤ ለአጨዳና ቅድመ አጨዳ የሚውሉ እንዲሁም የተለያዩ አርሶ አደሩን የሚያግዙ ማሽነሪዎችን ያመርታል:: በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ብሎኬት፣ ጣሪያዎችንና ብረት በጥራት አምርቶ ያቀርባል:: በውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የወፍጮ ድንጋይ በሀገር ውስጥ ያመርታል:: የቤትና የቢሮ ቃዎችንም እንዲሁ አምርቶ ለገበያ እንደሚያቀርብ አመላክተዋል::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You