የጉርብትናችን ነገር …

ከዓመታት በፊት ነው አሉ:: አንዲት በአካባቢው የታወቁ ወይዘሮ ከሰፈሩ ሴቶች ጋር ዕድር ይገባሉ:: ሴትየዋ ‹‹አፈር አይንካኝ የሚሏቸው አይነት ሀብታምና ቅንጡ ናቸው:: እንዲያም ሆኖ ከእሳቸው በኑሮ ዝቅ ከሚሉ ነዋሪዎች ጋር ዕድርተኛ ከሆኑ ቆይተዋል::

ወይዘሮዋ በሰፈሩ ለቅሶ ባጋጠመ ጊዜ እንደ ማንኛውም ዕድርተኛ እንጀራና ወጡን ከማምጣት አያጓድሉም:: ወርሀዊ ክፍያም ቀርቶባቸው አያውቅም:: በየጊዜው ግዴታቸውን በአግባቡ ይወጣሉ:: እሳቸው ይህን ሲያድርጉ ግን ከሰፈርተኛው ጋር በአካል ተገናኝተው አይደለም ::

በለቅሶ ጊዜ እንደማንኛውም አባል ከድንኳን፣ ከፍራሹ ተቀምጠው ሀዘንተኞችን አያጽናኑም:: የሚፈለግባቸውን ሁሉ በሠራተኞቻቸው ትከሻ አሸክመው ስፍራው ያደርሳሉ:: ከቤታቸው ተቀምጠውም የራሳቸውን ሕይወት ይመራሉ ::

ይህ ልማዳቸው ታዲያ በዕድርተኞች ዘንድ አላስወደዳቸውም:: ከዛሬ ነገ ይሻሻሉ ይሆናል የሚሉ ሰፈርተኞች እየነደዳቸውም ቢሆን ጊዜ ወስድው ጠበቋቸው:: እሳቸው ግን የዕድር አባልነታቸውን እንጂ የጉርብትናውን ጉዳይ የፈለጉት አይመስልም::

ሀዘን ባጋጠመ ቁጥር እንደለመዱት እንጀራና ወጣቸውን እያስላኩ፣ መዋጯቸውን እየከፈሉ ዓመታትን ዘለቁ:: ዕድርተኞቹ በሁኔታቸው ቢበሽቁም በትዝብት አብረዋቸው ተጓዙ ::

ከቀናት በአንዱ ግን በወይዘሮዋ ቤት ድንገቴ ሞት ገባ:: ሟቹ የቤቱ አባወራ ነበሩ:: ሞታቸውን ተከትሎ በመንደሩ ጩኸት በተሰማ ጊዜ ቀድመው የደረሱት የቅርብ ጎረቤቶች ሆኑ:: ቆይቶ ግን ዘመድ አዝማድ ቀስ በቀስ ግቢውን ሞላው:: ከቀብር መልስ እንደወጉ ጎረቤቶችና ዕድርተኛው ማስተናገድ ነበረባቸው:: ይህ ነባር ልማድ ግን በወይዘሮዋ ግቢ ፈጽሞ አልተሞከረም::

ዕለቱን ወዳጅ ዘመድ ራሱን ሲያስተናግድ፣ እንግዶችን ሲሸኝ ቆየ:: መሸትሸት ሲል አብዛኛው ግቢውን ለቀቀ::

 አሁንም አንድም ጎረቤት ብቅ አላለም:: ማግስቱን ግን እያንዳንዱ ዕድርተኛ በትሪው እንጀራውን፣ በሰሀኑ ወጡን ሞልቶ ወይዘሮዋ ግቢ ደረሰ:: ሁሉም የእጁን እያሳየ ፣ ከማጀቱ ዘልቆ ያመጣውን ሁሉ ደረደረው::

ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም የዕድሩ አባል ከድንኳን፣ ከፍራሹ አልተቀመጠም:: ለሴትዬዋ ክብር ሲል የተጨነቀ፣ ሰላም ውለው ስለማደራቸውም የጠየቀ አልተገኘም:: ለቀናት ብቻቸውን ሲቀመጡ ሀዘናቸውን ለግላቸው ትቶ ከስፍራው የተገለለ ነዋሪ በረከተ::

ይህን ተከትሎ በመጣው የበረከተ እንጀራና ወጥ የሚስተናገድ ጎረቤት ዝር አለማለቱ ታወቀ:: በርካቶቹ የሩቅ እንግዶች ስለምን ብለው መገረማቸው አልቀረም ::

ይህ ግርምታ ግን የእነሱ ብቻ ነበር:: ወይዘሮዋ የጉዳዩን ምስጢር አሳምረው ያውቁታልና ውስጣቸው ክፉኛ ተረበሸ:: አዎ! እስከዛሬ ጎረቤቶቻቸው የሚያውቁት እሳቸውን ሳይሆን የሚያመጡትን እንጀራና ወጥ ብቻ ነበር :: እናም ስለብድራቸው ወጥና እንጀራቸው ተቆጥሮ ተከፍሏቸዋል::

ሀዘንን ማጽናናት፣ ለቅሶን በአካል ሄዶ መድረሰ የማያውቁት ሴት በሆነው ሁሉ ስለምን ብለው ማንንም አልወቀሱም:: ይህ የሆነው በራሳቸው ያልተገባ ልማድ ነውና ራሳቸውን ደጋግመው ወቀሱ :: ስለ ሰው ባልከፈሉት ዋጋ የተከፈላቸውን ተረድተውም መላውን ጎረቤት ይቅርታ ጠየቁ::

ይህ ተረት የሚመስል እውነት ጥቂት ቆየት ቢልም በትክክል የተፈጸመ ታሪክ ነው:: ይህን ሀቅ መለስ ብለን እንመርምረው ካልን ደግሞ ማኅበረሰባችን ስለአብሮነት የሚሰጠውን ግምት ጥርት አድርጎ ያሳየናል::

ተደጋግሞ እንደሚነገረው የኢትዮጵያዊነት አንዱ መገለጫ የማኅበራዊ ሕይወታችን ገጽ ነው:: የማኅበራዊነት ልብና ሳንባው ደግሞ ጉርብትና ይሉት ጥንታዊ አብሮነት ነው::

የዛሬን አያድርገውና በጉርብትና ዓለም ብዙ ድንቅ የሚባሉ እውነታዎች ነበሩ:: ዘመኑን ወደኋላ ጥቂት ሳብ አድርገን ባስታወስን ጊዜ ይህ አይደገሜ ሀቅ ‹‹ትዝታ ›› ሆኖ እናየዋለን:: የዛኔ እንጀራውን ከቤት ፣ ወጡን ከጎረቤት ወስዶ መብላት ብርቅ አልነበረም :: የአንዱ ቤት ልጅ ሲያጠፋ የሌላው ቤት ወላጅ ዱላ ይዞ መግረፍ መቆጣቱ አያስገርምም ::

በዕድር ማኅበሩ፣ በዕቁብ የሚገናኘው ነዋሪ በችግር ደስታው መሰባሰቡን ያውቅበታል:: እናቶች ልጆችን ለማሳደግ፣ ቤተሰብን ለመምራት የተለየ ምስጢር የላቸውም:: በመሀላቸው ጠብና ቅያሜ ቢኖር ውሎ አያድርም:: ችግሩ በሽምግልና ወግ ፣ የሚፈታበት ጥበብ ለየት ይላል::

ለቅሶ ቢያጋጥም የሀዘን፣ የመርዶው ልማድ ይለያል። ከድንኳን ተቀምጦ ውሎ ከፍራሽ ማደር ተለምዷዊ ግዴታ ነበር:: ሀዘንተኛን ከለቅሶው ለመመለስ፣ የእያንዳንዱ ጨዋታ በጥበብ የተዋዛ ለባህልና ወግ የተገዛ ነው::

ዛሬ ላይ ያለፈውን ዘመን እያስታወስን ‹‹በነበር›› ስናወጋው እውነት ላይመስል ይችላል:: በእኔ ዕምነት ግን ይህ ያለፈ ታሪክ በትውስታ እንዲነሳ የሆነው በጎነታችንን ይዘን ባለመጓዛችን ነው:: አሁን በቆምንበት ዘመን ‹‹ጉርብትና›› ይሉት መልካም ነገር ከራቀን ሰነባብቷል:: የጥንቱ የአብሮነትና የመተሳሰብ ቀለም እየተፋቀ ማኅበራዊነታችን ተፋዟል::

ባይገርማችሁ በአንዳንድ ሰፈሮች ዓመታትን በጉርብትና ‹‹አሳልፈናል›› የሚሉቱ ስማቸውን እንኳን አይተዋወቁም :: ከመንገድ በተገናኙ ጊዜ ለእግዜር ሰላምታ ሳይበቁ ተገፋፍተው ያልፋሉ:: በአንዳቸው ቤት ሀዘን ይሉት ደስታ ቢገባ የመድረስ፣ የመጠራራት ልምዱ የላቸውም:: ሁሌም ቢሆን ልጆቻቸው አብረው አይጫወቱም፣ እነሱም በአካል ተገናኝተው አያወጉም::

አሁን ላይ በአብዛኞቹ ዘንድ ይህ ዓይነቱ ልማድ ከበጎነት ተወስዶ ዘመናዊ እንደመሆን ይቆጠር ይዟል:: ግቢን በግንብ አጥሮ፣ በብረት በር መዝጋት የሀብት ምልክት ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ባይኖረውም ጉርብትና ይሉት ጉዳይ ከነአንካቴው ተረስቷል ለማለት ያስደፍራል ::

የዘመናችን አጋጣሚ ሆነና ዛሬ ላይ የጋራ መኖሪያዎችን መጠቀም ከጀመርን ቆይተናል:: የእነዚህ ቤቶች ስያሜ የ‹‹ጋራ›› ቢባልም አብዛኞቹ ግብራቸው ከስያሜያቸው ይለያል :: ቤቶቹን ለመኖሪያነት የሚመርጡ በርካቶች ማኅበራዊነትን ርቀው ከጉርብትና ዓለም የራቁ ናቸውና::

ጥቂት የማይባሉት ከጎናቸው ግድግዳ የሚጋራቸውን ሰው ማወቅ ቀርቶ ማየትን አይሹም:: ሲወጡ ሲገቡ በር ዘግተው፣ ዓመታትን ሲኖሩም ከሌሎች ተዘጋግተው ነው:: ይህ እንደ ሕግ የወረደ አጉል ልማድ አሁን ላይ የማንነታችንን እሴት እየሸረሸረው ይገኛል:: የአብሮነት መገለጫ የሆነውን የጉርብትና ስርም መንግሎ እየነቀለው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል::

ቀደም ሲል በወሬ እንደምንሰማው በውጭ ሀገራት ያሉ በርካታ ነዋሪዎች የጉርብትና ልማድን አያውቁትም:: ለዓመታት ለብቻቸው የመኖር ሕይወትን አዳብረዋል:: በእነሱ ኑሮ የአብሮነት ዓለም ትርጉም ኖሮት አያውቅም:: እጅግ ሰፊ በሚባል ቤትና ግቢ ለብቻቸው ገብተው ይኖራሉ::

ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች አብዛኞቹ መኖር መሞታቸው አይታወቅምና የት ናችሁ የሚል አስታዋሽ የላቸውም:: እነሱም ቢሆኑ ‹‹ዘመድ ሳይጠይቀኝ፣ ችግሬን ሳይካፈለኝ›› ብለው አያስቡም:: ከዚህ ተለምዷዊ ሕይወታቸው አንድ ቀን ከዓይን በራቁ ጊዜም ያለመታወሳቸው ጉዳይ ይቀጥላል ::

የእነሱን በር ቀርቦ የሚያንኳኳ ፣ሰላም ውሎ ማደራቸውን የሚጠይቅ ጎረቤት የለምና መሞት መኖራቸው አይታወቅም:: ምንአልባትም ሕይወታቸው አልፎ ቢሆን ይህ እውነት ሳይታወቅ ቀናት፣ ወራት አልያም ዓመታት ሊቆጠሩ ይችላል::

ይህ የሰለጠኑት ሀገራት እውነታ ቀስ በቀስ ወደእኛ ሀገር መግባት ይዟል:: ዛሬ ላይ ጉርብትና ይሉትን የሚጠሉ፣ አብሮነትን የሚንቁ፣ ማኅበራዊ ሕይወትን አንጓለው የጣሉ ብቸኞች በዝተዋል:: በር ዘግቶ መቀመጥ፣ አንገት ደፍቶ መውጣት መግባት፣ ስልጣኔ የሚመስላቸው በርካቶች ከማንነታቸው እሴት እየወረዱ ባልተገባ መንገድ እየተራመዱ ነው::

እኔ ግን ወደ ቀደመው ልምዳችን እንመለስ፣ አብሮነታችንን እናድስ፣ የጉርብትና ወግ ይበጃል ፤ የአብሮነትን ቀ ለም ያ ደምቃል እላለ ሁ::

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You