የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ትውልዱ በማንነቱ የበለጠ እንዲኮራ የሚያስችል ነው!

 ሀገር የትርክቶችና የትርክት ባለቤት ትውልዶች ቅብብሎሽ ነው። ከዚህም የተነሳ እያንዳንዱ ትውልድ እንደ ትውልድ የተገነባባቸውን ትርክቶች አውቆ እና ከራሱ ጋር አስማምቶ ነገዎቹን እንዲዋጅ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ።

በዚህ ሂደት የተሳካለት ቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ ሆነ ሀገር፣ ራሱን የሚያውቅ፣ በራሱ ማንነት የሚመካ፤ ነገዎቹን ከትናንት መሠረቶቹ ጋር አስታርቆ መሄድ የሚችል፤ በነገዎቹ በብዙ ተስፈኛ የሆነና ስለተስፋው በብርቱ የሚተጋ ትውልድ ማፍራት ችለዋል።

ራሱን በሚገባ አውቆና ተረድቶ የሚንቀሳቀስ ትውልድ፣ ለማኅበረሰብ ሆነ ለሀገር ዕድገት ዋነኝ አቅም ነው። አሁን ላይ ያደጉና የሠለጠኑ ከሚባሉ ሀገራት ዕድገትና ሥልጣኔ በስተጀርባ ያለውም በዚህ መልኩ ራሱን አውቆ የትውልዶችን ቅብብሎሽ በተሻለ መንገድ ማስቀጠል የቻለ ትውልድ ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ አቅም እየሆነ የመጣውን የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ስለ ሀገሩ እና ማንነቱ፣ ስለ ታሪኩና ባሕሉ በተገቢው መልኩ እንዲያውቅ ማድረግ ትልቅ ትኩረት እየተሰጠው መጥቷል፣ የማኅበረሰቡን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ ሆኗል።

ከዚህም ባለፈ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ በሀገሩ ብሩህ ነገዎች ተስፋ በማድረግ፤ ዕጣ ፈንታውን በባዕድ ሀገር ከማድረግ ወጥቶ፤ በሀገሩ ሁለንተናዊ ዕድገት ተስፈኛ በመሆን የሚጠበቅበትን ባለው አቅሙ እንዲያበረክት የተሻለ ዕድል እና መነቃቃት የሚፈጥርለት ነው ።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ ቀደም ባለው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ወደ ሀገሩ በመምጣት በሀገሩ ምን እየተካሄደ እንዳለ በአካል ተገኝቶ እንዲታዘብ ጥሪ ማቅረባቸው ፤ በጥሪው መሠረትም ማኅበረሰብ በስፋት ወደሀገር ቤት በመምጣት ለውጡንና በለውጡ እየተደረጉ ያሉ ሥራዎችን በተጨባጭ መታዘብ ችሏል።

ጥሪው በአንድ በኩል በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን/የዲያስፖራ ማኅበረሰብ በብዙ ናፍቆት ሊያያት የሚወዳትን ሀገሩን እንዲያይና ሀገራዊ ናፍቆቱን እንዲወጣ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በለውጡ ላይ የነበረውን ብዥታ በማጥራት ለሀገሩ ማድረግ የሚችለውንና የሚጠበቅበትን በነፃነትና በበጎ ሕሊና ማድረግ የሚያስችለውን ዕድል ፈጥሮለታል ።

ይህ ክስተት በሀገሪቱ ታሪክ ማኅበረሰብ በሀገሩ ጉዳይ አዎንታዊ በሆነ መልኩ በስፋት እንዲንቀሳቀስ ያደረገ ስለመሆኑ በወቅቱ ብዙ ተብሎለታል፣ ሀገርና ሕዝብን በብዙ መልኩ ተጠቃሚ በማድረግ ሂደትም የነበረው አስተዋፅዖ ተጠቃሽ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በውጪ ለሚኖሩ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ተመሳሳይ ጥሪ፣ ትውልዱ ስለ ሀገሩ እና ማንነቱ፣ ማንነቱ ስለተገነባባቸው ማኅበራዊ፣ ታሪካዊ እና ሥነ ልቦናዊ እሴቶች በሚገባ ተረድቶ በማንነቱ የሚኮራ፤ ለሀገሩ እና ለወገኑ የክብር ምንጭ እንዲሆን ለማስቻል ነው ።

የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በተለይም ሁለተኛው ትውልድ ውልደቱና አስተዳደጉ በባዕድ ሀገር ከመሆኑ አንጻር፣ ስለሀገሩና ከዚያ ስለሚቀዳው ማንነቱ ተገቢውን እውቀት እያገኘ እንዲያድግ የሚኖረው እድል ጠባብ ነው። ይህም በራሱ ማንነት እንዳይኮራ ትልቅ ተግዳሮት ሊሆንበት እንደሚችል ይታመናል።

ይህንን ተግዳሮት አሸንፎ እንዲወጣ የብዙ ትውልዶች የብሔራዊ ጀግንነት፣ የነፃነት እና የረጅም ዘመናት የሀገረመንግሥት እና ከፍ ያለ ሥልጣኔ ባለቤት የታሪክ ትርክት ባለቤት ስለሆነችው ሀገሩ ኢትዮጵያ ተገቢውን መረጃ በመስጠት በማንነቱ እንዲኮራ ማድረግ ያስፈልጋል ።

ትውልዱ ከወላጆቹ ሀገር ጋር ቁርኝት እንዲፈጥር፣ መነሻ ሀገሩን በአግባቡ እንዲረዳ፤ በተለይም በሀገር ውስጥ ከሚገኙ እኩዮቻቸው ጋር ቁርኝት እና የትውልድ ትስስር በመፍጠር እና ትስስሩን በሁሉም መልኩ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልካም አጋጣሚ ሊፈጥር የሚችል ነው!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You