በሕክምና ሂደት የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና አለማድረግ ነው:: በተለይ ደግሞ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ከኢንፌክሽን የፀዱ ካልሆኑና ለቀዶ ሕክምና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ያላሟሉ ከሆነ ሕመምተኞችን ለኢንፌክሽን ከማጋለጥ በዘለለ ለተወሳሰበ የጤና ችግር ብሎም ለሞት የመዳረግ እድላቸው የሰፋ ነው::
የቀዶ ሕክምና ቦታ ኢንፌክሽኖች ደግሞ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት በሚገኙ ሕመምተኞች ላይ ትልቅ የጤና አደጋ እየፈጠሩ እንደሆነ ይነገራል:: ይህንኑ የጤና አደጋ ለመቅረፍ ‹‹ላይፍ ቦክስ›› የተሰኘና ሕይወትን ደህንነቱ በተጠበቀ የቀዶ ሕክምና ለማትረፍ በሚሠራው ለትርፍ ያልተቋቋመ ዓለም አቀፍ ድርጅት አማካኝነት ‹‹ክሊን ከት ኢኒሺዬቲቭ›› የተባለ ፕሮግራም እ.ኤ.አ ከ2015/16 ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ በላይቤሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ቦሊቪያ፣ ማላዊ፣ ሕንድና ኮትዲቯር ውስጥ ባሉ 35 የጤና ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል::
በዚህ ፕሮግራም 208 ሺ ለሚሆኑ ከባድ የቀዶ ሕክምና ሂደት ለሚያስፈልጋቸው ታማሚዎች ተደራሽ መሆን ተችሏል:: በኢትዮጵያም በተመረጡ አምስት የሙከራ ቦታዎች ‹‹የክሊን ከት ኢኒሺዬቲቭ›› ፕሮግራም ተግባራዊ ሆኖ በቀዶ ሕክምና ቦታዎች በ35 ከመቶ ኢንፌክሽኖችን ለመቀነስና 46 ከመቶ ከኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚመጡ ውስብስብ የጤና ችግሮችን በማስወገድ ረገድ ውጤት ማምጣት ችሏል:: ከሰባት ሆስፒታሎች ከተውጣጡና 3 ሺ ከሚሆኑ የቀዶ ሕክምና ካደረጉ ሕሙማን በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ደግሞ ፕሮግራሙ በቀዶ ሕክምና ወቅት ሊፈጠር የሚችለውን ኢንፌክሽን በ34 ከመቶ እንደሚቀንስና በቀጣይ ማደግና ዘላቂ መሆን እንዳለበት አሳይቷል::
ዶክተር ትሕትና ንጉሴ በላይፍ ቦክስ ፋውንዴሽን የክሊኒካል ዳይሬክተር ሲሆኑ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ደግሞ የሕፃናት ቀዶ ሐኪም ሆነው ያገለግላሉ:: እርሳቸው እንደሚሉት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታማሚዎችን ሕመምና ስቃይ ለማስታገስ ሲባል የተለያዩ ቀዶ ሕክምናዎች ይደረጋሉ:: ይሁንና የቀዶ ሕክምናው ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ መደረግ ያለበትና ማደንዘዣውም በአግባቡ መሰጠት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል:: ላይፍ ቦክስም ይህንኑ መሠረት ባደረገ መልኩ በተለይ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን በመንደፍ፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም በማሳደግና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት በዚህ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ይሠራል:: ሕመምተኞችም ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል::
ድርጅቱ ከሚሠራቸው ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ ‹‹ክሊን ከት ኢኒሺዬቲቭ›› አንዱ ሲሆን በቀዶ ሕክምና ሂደት የሚመጡ ኢንፌክሽኖችንና ይህን ተከትለው የሚከሰቱ የተወሳሰቡ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ የተነደፈ ነው:: ይህ ፕሮግራም በቀዶ ሕክምና ክፍሎች ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ቅደም ተከተሎች ሲጓደሉ የሚፈጠረውን ኢንፌክሽንና ከኢንፌክሽን ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የተወሳሰቡ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ ፕሮግራሙ ተነድፏል:: እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል የሚሠራው ደግሞ በትምህርት፣ ሥልጠናና በሌሎች መንገድ ነው::
ይህ ‹‹ክሊን ከት ኢኒሺዬቲቭ›› የተሰኘው ፕሮግራም በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2015/16 የተጀመረ ሲሆን ፕሮግራሙ ከተጀመረ ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰባት ሀገራትና በነዚህ ሀገራት የሚገኙ ሠላሳ አምስት ሆስፒታሎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ችለዋል:: ከ208 ሺ በላይ ታማሚዎች በፕሮግራሙ ተሳትፈው ተጠቅመዋል:: በተቻለ መጠን በዚህ ፐሮግራም የኢንፌክሽኖችንና ከኢንፌክሽን ጋር በተያያዘ የሚመጡ የተወሳሰቡ የጤና ችግሮችን ለመቀነስ ፕሮግራሙ እገዛ እያደረ ይገኛል::
በኢትዮጵያም ከ22 በላይ የሚሆኑ ሆስፒታሎች የዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን ችለዋል:: በሆስፒታሉ ካሉ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ደህንነቱ ከተጠበቀ የቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ የጋራ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፣ በቀዶ ሕክምና ወቅት እንዲፈጠሩ ከማይፈለጉ ነገሮች ውስጥ አንዱ የቀዶ ሕክምናውን ተከትለው የሚመጡ ተጓዳኝ ችግሮች ናቸው:: እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ የቀዶ ሕክምናዎች ደረጃቸውን በጠበቀና ቅደም ተከተሎችን መሠረት ባደረገ መልኩ መከናወን ይኖርባቸዋል:: ይህ ፕሮግራም የተቀረፀውም በመማማር ይህንን ችግር ለማስቀረት ነው::
በኢትዮጵያ የቀዶ ሕክምና ባለሞያዎች እጥረት እንዳለ ይታወቃል:: ሆኖም እጥረቱን ይበልጥ የሚያባብሰው ደህንነቱ ባልተጠበቀ ቀዶ ሕክምና ምክንያት ሕሙማን ለዳግም ቀዶ ሕክምና ሲመጡ የሚከሰተው የሃብት ብክነትና የባለሙያ እጥረት ይፈጥራል:: ከዚህ አኳያ የሚታየውን የባለሙያ እጥረትና ከቀዶ ህክምና ጋር በተያያዘ የሚታየው የኢንፌክሽን ችግር በተቻለ አቅም ደረጃዎችን በጠበቀና ቅደም ተከተሎችን በተከተለ መልኩ ቀዶ ህክምናዎችን በማካሄድ መቅረፍ ይቻላል::
ምንም እንኳን ከራሱ ከሕመምተኛው የሚመነጩና ከሕክምና ባለሞያዎች አቅም በላይ የሆኑና በቀዶ ሕክምና ወቅት የሚከሰቱ የተወሳሰቡ ችግሮች የሚያጋጥሙ ቢሆንም በሕክምና ግብዓት እጥረትና በጤና ባለሙያዎች በኩል ለቀዶ ሕክምና አስፈላጊ ሂደቶችን ባለመከተል ምክንያት የሚከሰቱ ኢንፌክሽኖችንና ከኢንፌክሽን ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ችግሮችን አስቀድሞ መፍታት ይቻላል:: በተለይ ደህንነቱ የተጠበቀ የቀዶ ሕክምና ቅደም ተከተሎችን መከተል የሚቻል ከሆነና በጤና ባለሙያው በኩል ያለውን አመለካከት መቀየር ከተቻለ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ውስብስብና ተጓዳኝ የጤና ችግሮች 50 ከመቶ መቅረፍ ይቻላል::
ስለዚህ ‹‹የላይፍ ቦክስ›› ሌላኛው ዓላማ በትምህርት ያሉትን የቀዶ ሕክምና ፕሮቶኮሎች በመከተል የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ማስቻል ነው:: ይህንኑ በማድረግ ሊከሰቱ የሚችሉ ኢንፌክሽኖችን 35 በመቶ መቀነስ ተችሏል:: ይህም ፕሮግራሙ ትልቅ ውጤት እንዳመጣ ያሳያል:: ሕክምናና የአንስቴዢያ ፕሮግራም ማስተባበሪያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዐቢይ ዳዊት እንደሚሉት፣ የጤና አገልግሎት ሲታሰብ ቀድሞ የሚነሳውና ዋነኛው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ነው:: የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሲነሳ ደግሞ የደህንነት ጉዳይ አብሮ ይነሳል:: በዚህ ረገድ ‹‹ላይፍ ቦክስ›› የጀመረው ‹‹የክሊን ከት ኢንሺዬቲቭ›› በተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ በቀዶ ሕክምናና አንስቴዢያ ዙሪያ ደህንነትን ከማሻሻል አንፃር ጥሩ ውጤቶችን አምጥቷል:: ጤና ሚኒስቴርም የዚህን ፕሮግራም ትግበራ ሲከታተል ቆይቷል:: ውጤት የተገኘበት ስለመሆኑም አረጋግጧል::
የቀዶ ሕክምና ደህንነት ትልቅ ጉዳይ ነው:: የቀዶ ሕክምና ደህንነትን ከማሻሻል አኳያ ጤና ሚኒስቴር የሚያከናውናቸው በርካታ ሥራዎች አሉ:: ‹‹ላይፍ ቦክስ›› ተግባራዊ ካደረገው ፕሮግራም ደግሞ ትልቅ ውጤት ተገኝቷል፤ ትምህርትም ተወስዶበታል:: ምንም እንኳን ፕሮግራሙ በተወሰኑ ሆስፒታሎች ውስጥ የተተገበረ ቢሆንም በቀጣይ ወደ ሌሎች ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ማስፋት ያስፈልጋል::
ከቀዶ ሕክምና ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሆስፒታሎች አንዳንድ ችግሮች ይኖራሉ:: በተለይ በቀዶ ሕክምና ቦታዎች ላይ የሚፈጠሩ የኢንፌክሽን ችግሮች አሉ:: ይህም ይህን በተመለከተ የመረጃ ክፍተት እንዳለ ያሳያል:: በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ታዲያ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ለማወቅ ተችሏል:: በሌላ በኩል ደግሞ ችግሩን ካለበት ደረጃ እንዴት መቀነስ እንደሚቻል ትምህርት ተወስዷል::
መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያብራሩት፣ የቀዶ ሕክምና ደህንነትና አንስቴዢያን ለማሻሻል ሀገራት እንዲሠሩ እ.ኤ.አ በ2016 የዓለም ጤና ድርጅት ውሳኔ አሳልፏል:: ኢትዮጵያም ለዚህ ውሳኔ ምላሽ ከሰጠች ከሰሃራ በረሃ በታች ከሚገኙ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት:: ኢትዮጵያ ለዚህ ውሳኔ ምላሽ የሰጠችው በመጀመሪያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት ሲሆን ‹‹የቀዶ ሕክምና ደህንነትን ማሻሻያ›› ስትራቴጂ አዘጋጅታለች:: ይህም ስትራቴጂ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በቀዶ ሕክምና ቦታዎች ላይ የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖችንና ኢንፌክሽኖችን ተከትለው የሚመጡ ተጓዳኝ ውስብስብ የጤና ችግሮችን፣ የቀዶ ሕክምና ወረፋዎችንና ሌሎችንም ችግሮችን ለመቅረፍ ትልቅ እገዛ አድርጓል::
የቀዶ ሕክምና ደህንነትን ከማረጋገጥ አንፃርም ስትራቴጂው ጉልህ ሚና ተጫውቷል:: በተለይ ደግሞ የዓለም ጤና ድርጅት የሚጠቁመው ‹‹የሴፍ ሰርጀሪ ቼክ ሊስት›› በሁሉም ሆስፒታሎች ውስጥ እንዲተገበር በመደረጉ በቀዶ ሕክምና ደህንነት በኩል በርካታ ለውጦች መጥተዋል::
በሌላ በኩል ደግሞ ልምድ ያላቸው የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ወደታችኛው የጤና ተቋማት ወርደው ሙያዊ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሥርዓት እንዲፈጠር ተደርጓል:: የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ከመጨመር አኳያም በሁሉም ክልሎች ባሉ ጤና ጣቢያዎች 430 የሚሆኑ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ተገንብተዋል:: እነዚህ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች መሠረታዊ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ያስችላሉ:: በተለይ ደግሞ እናቶችን በቀዶ ሕክምና እንዲወልዱ ከማድረግ አኳያ ድርሻቸው ከፍተኛ ነው:: በወሊድ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድም ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል::
የጤና ጉዳይ የጤና ሚኒስቴር ጉዳይ ብቻ አይደለም:: የሁሉንም ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ይፈልጋል:: የቀዶ ሕክምና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ እንዳይከናወን እንቅፋት ከሚፈጥሩ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የኃይል መቆራረጥ ነው:: ወደ ጤና ተቋማት የሚያደርሱ መንገዶች አለመገንባትም የቀዶ ሕክምና በሰዓቱ እንዳይደረግ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል:: ለቀዶ ሕክምና አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እንደልብ አለመሟላትም እንደዛው:: ስለዚህ የጤና ሚኒስቴርም በተቻለ አቅም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል::
ከዚህ በዘለለ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች እጥረትም የቀዶ ሕክምና ደህንነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ በተዘዋዋሪ ያደርሳል:: በዚህ መነሻነት አንጋፋና ልምድ ያላቸው የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች በአብዛኛው በከተማዎች ብቻ መኖር በገጠር አካባቢ የተሻሉና ደህንነታቸው የጠበቀ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተደራሽነት ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርገዋል:: እንደዛም ሆኖ የክልሉ ጤና ጣቢያዎች ላይ በተከፈቱ የቀዶ ሕክምና ክፍሎች ውስጥ የሚሠሩ የጤና መኮንኖችና ነርሶች እንዲሠለጥኑ ተደርጓል:: በዚህም በመጠኑም ቢሆን ችግሩን ለማቃለል ተሞክሯል::
የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በተፈጥሮው በቂ ሀብት መመደብ የሚፈልግ እንደመሆኑና ከሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ጋር ተዳምሮ በሀገሪቱ የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን በሚፈለገው ደረጃና የጥራት ልክ ለሁሉም ማድረስ አልተቻለም:: ነገር ግን ጤና ሚኒስቴር ችግሩን ለመቀረፍ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሰው ሀብት፣ በሥልጠና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በስፋት እየሠራ ይገኛል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም