‹‹የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ድጋፎች ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ የማቅረቡ ጥረት ከጅምሩ ውጤታማ ሆኗል››አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እየተስተዋሉ ባሉ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ፣ እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶችና መንግሥት ባስቀመጣቸው መፍትሄዎች ዙሪያ ትናንት ከጋዜጠኞች ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፦

ጥያቄ፦ ክቡር ሚኒስትር ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር በቅድሚያ እያመሰገንኩ ለመነሻ እንዲሆነን አሁን በኢንዱስትሪው መስክ የደረስንበት ደረጃ ሲታይ በአጠቃላይ ምን ይመስላል?

አቶ መላኩ አለበል፦ የኢትዮጵያ ኢንዱስትራላይዜሽን ባለፉት ዓመታት በጣም ብዙ ጥረት ሲደረግበት የቆየ መስክ ነው። በተለይ ደግሞ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ተቀርፆ በመጪዎቹ አስር ዓመታት በሴክተሩ ምን እናሳካለን የሚለው ከተለየበት ጊዜ አንስቶ ሰፋ ያሉ ዘርፉን ሊቀይሩና ሀገራዊ ተወዳዳሪነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው።

እንደሚታወቀው፤ ኢንዱስትራላይዜሸን ከግሎባላ ይዜሽን ጋር በአጅጉ የተሳሰረ፣ በዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ውስጥ በአዎንታዊም፣ በአሉታዊም ተፅዕኖው የሚያርፍበት፤ በዓለም ያለው የቴክኖሎጂ ዕድገት ሁልጊዜ የራሱን የሆነ ሚና የሚጫወትበት ቀዳሚ ዘርፍ ቢኖር ኢንዱስትራላይዜሽን ወይም የኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው።

ይሄንን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ሀገር የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ /ሆም ግሮውን ኢኮኖሚክ ሪፎርም/ አጀንዳ ከተለየበት ጊዜ ጀምሮ እና እሱን ተከትሎ የወጣውን የ 10 ዓመት የልማት ግብ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፉ እናሳካለን ብለን ያሰብነውን የልማት ግብ ለማሳካት ያሉት ተግዳሮቶች ምንድናቸው? እንደ ሀገርስ ያሉት እድሎች ምንድናቸው? የሚለውን በመለየት ዘርፉ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።

በዚህ ሥራ ውስጥ የመጀመሪያውና ዋነኛው እንደ ሀገር የወደፊት አቅጣጫችንን የሚያመላክተው የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ነው። ከዚህ በፊት የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ነበረን። ይሄ የኢንዱስትሪ ስትራቴጂ ከሞላ ጎደል የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

ስትራቴጂው አሁን ካለው ዓለማዊና ሀገራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ባለመሆኑ፤ የዓለም አቀፍ፣ የአህጉር እና የኢትዮጵያን ሁኔታ ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።

ቀደም ሲል የነበረው ስትራቴጂ ከ20 ዓመት በላይ አገልግሏል። የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በእጅጉ ተለዋዋጭ ነው፤ በተለይ ከኮቪድ በኋላ ያለውን የዓለም ሁኔታ ብናየው በጣም በርካታ ነገሮች ቀደም ሲል ከነበራቸው እሳቤ እና አተገባበር በጣም በተለየ መንገድ ነው እየሄዱ ያሉት።

ቴክኖሎጂውም በእጅጉ እያደገ ነው፤ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ፣ የባዮ ቴክኖሎጂ በፍጥነት ሁኔታዎችን እየቀየሩ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል፤ በመሆኑም ይሄንና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ፖሊሲ ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር።

ይሄ ፖሊሲ በቅርቡ ፀድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። ፖሊሲው አልቆ ከመፅደቁ በፊት ከፖሊሲው ጎን ለጎን መሠራት ያለባቸውን በጣም በርካታ ሥራዎች ስናከናውን ቆይተናል። ይህም የሀገር ውስጥ ባለሀብትን በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሬና የውጭ ባለሀብቶችን በማምጣት፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ በመሳሰሉት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይታሰባል።

ፖሊሲዎች ብቻቸውን የሚቆሙ አይደሉም። የመንግሥትን ቁርጠኝነት ለፖሊሲውና ለልማት እቅዶቹ ያለውን ቁርጠኝነት ማረጋገጥ የሚቻለው መንግሥት በዘርፉ በሚመድበው ካፒታል እና በሚሠራቸው የመሠረተ ልማት ሥራዎች ነው። መሠረተ ልማቶች ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በጣም መሠረታዊ ተደርገው ይወሰዳሉ።

የትኛውም ዓይነት የሀብት ምንጭና የትኛውም ሰፊ ገበያ ቢኖረን፣ ይሄንን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችል መሠረተ ልማት ካልተገነባ የዘርፉ እድገት ሊሳለጥ አይችልም። ከዚህ አኳያ እንደ አንድ ትልቅ ተኩረት ተሰጥቶ የተሠራው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማልማቱ ሥራ ነው። ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን በተለይ ታዳጊ ሀገራት ያለባቸውን የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር በጥራትም፣ በአቅርቦትም በማሻሻል ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ናቸው። ያለ መሠረተ ልማቶቹ የተሳለጠ ዘመናዊ አገልግሎት ሊኖር አይችልም፤ ይህን ዘመናዊ አገልግሎት በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ ለማድረግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

በዚህ በኩል መንግሥት ሰፊ የሆነ ፓርኮችን የማልማት ሥራ ይሠራል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርኮችን የማልማቱን ሥራ የግሉም ሴክተር ሊገባበት የሚገባው በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የግል ባለሀብቶችን ከሀገር ውስጥም ከውጭም እንዲገቡበት ለማድረግ የሕግ ማሻሻያዎችና ለዚያ የሚሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራ ተሠርቷል።

እንደሀገር ትልቁ ኢኮኖሚያችን የሚመሠረተው ግብርና ላይ ስለሆነ ግብርናውን በዘላቂነት ለማዘመን ፓርኮችን የመሥራት ፣ የመገንባት እና ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ወደ ዓለም ገበያ እንዲቀርቡ የማድረግ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ነበረበት። በዚህም በተለይ በሙከራ ደረጃ የተጀመሩት የቡልቡላ፣ ቡሬ እና የይርጋለም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ባለፉት አራት ዓመታት ተጠናቀው ወደሥራ እንዲገቡ እና የሀገር ውስጥም የውጭም ባለሀብቶች ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡበት ለማድረግ ጥረት ተደርጓል።

ቀደም ሲል ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ለውጭ ባለሀብቶች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ዝንባሌ ነበረ። አሁን ባለው እሳቤ ይሄ ተቀይሮ ቢያንስ ቢያንስ 50 በመቶ የሚሆኑት ኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች መያዝ አለባቸው የሚል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው። በዚህም አሁን በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ሼድና መሬት ከወሰዱ 127 ባለሀብቶች 61ዱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል። የተቀሩት 66ቱ የውጭ ባለሀብቶች ናቸው።

ይህ መሆኑ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ፣ በዓለም ገበያ ውስጥ ለመግባት እና የሀገር ውስጥ ጠንካራ ባለሀብት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፤ ስለዚህ መሠረተ ልማትን የማሟላት ብቻ ሳይሆን በዚህ በተፈጠረ አስቻይ ሁኔታ ሌሎች የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲገቡ ለማድረግ የተደረገው ጥረት እንደ አንድ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ፖሊሲዎቹንና መሠረተ ልማት ማቅረቡን አይተን ከዚያ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ ያለው ለኢንዱስትሪዎቹ አስፈላጊው የተቋማት ቅንጅት መፍጠር ነው። እስካሁን ድረስ ባለው ሁኔታ ለኢንዱስትሪዎቻችን ያሉ ፖሊሲዎች የየራሳቸው ጥንካሬ ቢኖራቸውም፣ እንደ ድክመት የሚታየው ተቋማት ተቀናጅተው ያለመፈጸም፣ ያለመናበብና የግል ዘርፉን በተደራጀ ሁኔታ ያለመደገፍ ችግር ነው።

ይሄ ችግር ከተለየ በኋላ በተለይ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ 35 ተቋማት ያሉበት ወደ ስድስት ክላስተሮች ተፈጥረዋል፤ እነዚህ ስድስት ክላስተሮችና በስራቸው ያሉ 35 ተቋማት የየራሳቸውን እቅድ አዘጋጅተው፣ በጀት ይዘው፣ የሰው ኃይል አሰማርተው ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የተደረገው ጥረት ከጅምሩ ውጤት ማምጣት ጀምሯል ።

ይሄ የመንግሥትን ቁርጠኝነትና ለሴክተሩ ድጋፍ ያለውን ዘላቂና ሩቅ እይታ የሚያመላክት ነው። ይህንንም እንደ አንድ ጥሩ መነሻ እድርገን እንወስዳለን። ሌላው ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደ አንድ ትልቅ ሥራ ተደርጎ የሚወሰደው የፋይናንስ አቅርቦት ነው ። ለዘርፉ ፋይናንስ እጅግ በጣም ያስፈልጋል።

ከዚህ በፊት አንዱ ትልቁ ችግር ዋነኛው ተበዳሪ መንግሥት የሆነበት ሁኔታ ነው። አሁን የግል ዘርፉ ነው ከፍተኛ ብድር እንዲወስድ ተደርጓል። የመንግሥት የብድር መጠን ከአጠቃላይ ከሚቀርበው ብድር ውስጥ ወደ 14 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፤ ቀደም ሲል 70 በመቶ የሚሆነውን ብድር መንግሥት ነበር የሚወስደው። አሁን የመንግሥት ብድር መጠን ወደ 14 በመቶ ዝቅ ብሏል፤ ቀሪው 86 በመቶ የግል ዘርፉ የሚበደረው ነው።

ከዚህ የብድር አቅርቦት መጠን ውስጥ ደግሞ አምራች ዘርፍ የምንላቸው እንደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና እንደ ግብርና ያሉት የተሻለ ድርሻ እንዲያገኙ የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው።

በ2015 ብቻ ወደ 60 ቢሊዮን ብር የሚደርስ ብድር ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎቹ እንዲቀርብ ተደርጓል። በዚህ በያዘነው በጀት ዓመት አራት ወራት ውስጥ 15 ቢሊዮን ብር ብድር ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ቀርቧል።

ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ብቻ ባለፈው ዓመት /አመቱን ሙሉ/ ለሊዝ ፋይናንስና መሥሪያ ኮፒታል ወደ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ቀርቦላቸዋል። በዚህ አምስት ለእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ወራት አራት ቢሊዮን ብር ለሊዝ ፋይናንስና ለመሥሪያ ኮፒታል እንዲቀርብላቸው ተደርጓል።

ይህም ብቻ ሳይሆን በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁለተኛ ሪፎርም በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት እንሠራለን ካለነው ውስጥ የአምራች ዘርፎቹ ከነበራቸው የ12 በመቶ የፋይናንስ ድርሻ ወደ 24 በመቶ እንዲያድግ ተወስኗል ማለት ነው። ይሄ ከፍተኛ ነው። በሚቀጥሉት ጊዜያት ለእነዚህ ዘርፎች የሚቀርበው የፋይናንስ መጠን እያደገ ይሄዳል። በዚህ ውስጥ የሥራ እድል እየተፈጠረ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እየሳብን የምንሄድባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉ።

ኢንዱስትሪዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፉ ምክንያት ከሚሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ግብዓት ነው። የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል ስለሚያስፈልግ በኢንዱስትሪዎቹ መካከል እንዲሁም ከአርሶ አደሮች ጋር ትስስር እንዲኖር ለማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል።

ለምሳሌ ቅድም በገለጽኳቸው የተቀናጁ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ሥራ ከገቡ ስምንት ባለሀብቶች ጋር 246 የሚደርሱ አርሶ አደሮች፣ 60 መሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት እና 6 ዩኒየኖች ግብዓት በማቅረብ ውስጥ እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። ይሄ በመሆኑ ምክንያት የኢንዱስትሪዎችን የግብዓት አቅርቦት በዘላቂነት ለመፍታት አቅም እየፈጠረ ነው።

አንዱን አነሳን እንጂ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው፣ በቆዳ ኢንዱስትሪው እና በሌሎችም ኢንዱስትሪዎች  ላይ የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው። እነዚህን ሥራዎች ከፖሊሲዎች እና ቅድም ካነሳኋቸው መሠረተ ልማቶች ባሻገር ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ መምራት ስለሚያስፈልግ ከፖሊሲው ትይዩ ፖሊሲውን የሚደግፉ፣ የሚያጠናክሩና የፖሊሲውን ተፈጻሚነት የሚያረጋግጡ ሌሎች ስትራቴጂዎች እንዲዘጋጁ ተደርጓል። ለምሳሌ የተኪ ምርት ስትራቴጂ አንዱ ነው።

የቆዳ ሀብታችን በጣም ከፍተኛ ነው። በሀገሪቱ እስከ 165 ሚሊዮን የሚደርሱ የቀንድ ከብቶች አሉ። በየዓመቱ ወደ 41 ሚሊዮን የሚሆን ቆዳ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን እየተጠቀምንበት ያለው መጠን በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ ይህንን የሚያሻሽሉ ሥራዎች መሥራት ስላለባቸው ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው እንዲሠራ እየተደረገ ነው።

በግል ዘርፍና በመንግሥት በኩል የማስፈጸም አቅም ክፍተት ስላለ የአቅም ግንባታ ስትራቴጂ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አስፈላጊ ስለሆነ ይሄ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እየተሠራ ነው።

በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ የኢንዱስትሪ ባሕል ገና አልገነባንም። ሥራ ላይ ያሉት ሠራተኞች ባለሀብቶች፣ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የኢንዱስትሪን ባህሪ በተገቢው መንገድ አውቀው ሲደግፉ ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው፤ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ቀጣይ እንቅስቃሴ እንዲያግዝ ለማድረግ በሚያስችል አግባብ ተቀርጾ ሥራ እየሠራ ነው። እያንዳንዱን ችግር ነቅሶ በማውጣት ለመፍታት የሚያስችሉ ወደ 18 የሚደርሱ ስትራቴጂዎችም ተዘጋጅተው ወደ ሥራ እየተገባ ነው።

ይሄ በመሆኑ ምክንያት ምንድነው የተገኘው ውጤት የሚለው በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ይመስለኛል። አንደኛ ዓለምአቀፋዊ ሁኔታውን ስናየው አሁን በዓለም ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመዋቸዋል። በተለይ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የአቅርቦት ሰንሰለት የሚባለው የግንኙነት ሰንሰለት በተለያየ መንገድ ተጎድቷል። ከኮቪድ በኋላም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ ግጭቶችና የፖለቲካ ሹክቻዎች የፈጠሩት ጫና አለ። ስለዚህ እኛ የቀየስናቸው ስልቶች እነዚህን ጫናዎች ለመቀነስና ለመቋቋም አስተዋጽኦ አበርክተውልናል።

እነዚህን ሥራዎች ሠርተን ባንደግፋቸው ኖሮ ኢንዱስትሪዎቹ ከጨዋታ የመውጣት እድላቸው በጣም ሰፊ ይሆን ነበር። ውስጣዊም ውጪያዊም ጫናዎችን ለመቋቋም የሠራናቸው ሥራዎች ራሳቸውን የቻሉ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብሎ መውሰድ ይቻላል። አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በ2015 ብቻ ወደ 993 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ ወደማምረት እንዲገቡ ማድረግ አስችሏል። ይህ ከዚህ በፊት ከነበረው ቁጥር አኳያ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የአነስተኛዎችንም፣ የከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችንም ቁጥር ወስደን ስናይ ወደማምረት የገቡት ኢንዱስትሪዎች ቁጥር በጣም ትልቅ ነው።

የሳብናቸው አነስተኛ እና መካከለኛ የሳብነውን ኢንቨስትመንት ብናየው በ2015 ብቻ ወደ 5 ሺ 47 የሚደርሱ አዳዲስ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ለመሳብ አስችሎናል። ከፍተኛው ወደ 744 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎችን መሳብ አስችሎናል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ 136 የሚደርሱ የውጭ ባለሀብቶች እንዲመጡ ማድረግ አስችሏል። በ2016 ዓ.ም ወደ 84 የሚደርሱ አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲመጡ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ነው። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ፍሰቱ የበለጠ እየጨመረ እንዲሔድ ለማድረግ አስችሏል። በዘርፉ መሰማራት የሚያስገኘውንም ውጤት በመረዳት በማስገንዘብ ረገድ እሱ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የሥራ እድል በመፍጠር በኩልም ባለፈው ዓመት ወደ 256 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አስችሏል። በዚህም ባለፉት አራት ወራት ወደ 48 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል። በመጪዎቹ ወራትም ይህ አኀዝ ከፍ እንደሚል ተስፋ እናደርጋለን።

ገቢ ምርትን በመተካት ረገድ ባለፈው ዓመት ወደ ሁለት ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገቢ ምርትን መተካት ችለናል። ቀደም ሲል ይህ ሲታይ 70 በመቶ የሚሆነው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውጤት ከውጭ ነበር የሚመጣው። ስለዚህ ይህንን መቀየር አለብን ብለን በሠራነው ሥራ አፈጻጸሙ ተስፋ ሰጪ ነው።

የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ድርሻቸው 30 በመቶ ነበር። አሁን ወደ 38 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል። ይህ በቀጣይም የበለጠ እየተሻሻለና እያደገ የሚሄድ ነው።

ኢንዱስትሪዎቻችን በጣም ከፍተኛ የሆነ የማምረት አቅም አጠቃቀም ችግር ነበረባቸው። የማምረት አቅም አጠቃቀማቸው በ2013 ዓ.ም ላይ ወደ 46 በመቶ ወርዶ ነበር ፤ ይህ ማለት የማምረት አቅም አጠቃቀማቸው በጣም ወርዷል ማለት ነው።

በዚያው ልክም ምርታቸው ቀንሷል፤ የሚፈጥሩት የሥራ እድልም ቀንሷል፤ ችግሩ የዘርፉንም ሳቢነት በዚያው ልክ ዝቅ አድርጎታል። ይህ የማምረት አቅም አሁን ወደ 56 በመቶ ከፍ ብሏል። ከሴክተር ሴክተር ያሉ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ግን የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 56 በመቶ ከፍ ብሏል።

በመጪዎቹ ሰባት ስምንት ዓመታት ወይም በልማት ግቡ /በልማት እቅዱ/ በመጪው አስር ዓመት ውስጥ በተያዘው ውስጥ ይህንን ወደ 85 በመቶ ማሳደግ አለብን ብለን እየሠራን እንገኛለን። ስለዚህ እነዚህን ስኬቶች ወስደን ስናይ በዘርፉ አሁን ያለው አጠቃላይ ሁኔታ በጣም አበረታች ነው።

ዜጎች የሀገራቸውን ምርት የመጠቀም ባህላቸውም እየተሻሻለ መጥቷል። በቅርቡ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉበት ባዛርና ኤግዚቢሽን በስካይ ላይት ሆቴል ተካሂዶ ነበር። መድረኩ ወደ 85 የሚደርሱ ኢንተርፕራይዞች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ የተዘጋጀ ነው።

ይህም ከ36 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የጎበኙት፤ በብዙ ሚሊየኖች ብር የሚቆጠር ግብይት የተከናወነበት እና ኢንዱስትሪዎች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር መፍጠር የቻሉበትን መሆን ችሏል። እንደ መንግሥትም አሁን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት፣ ሕግ እና አሠራር በማስቀመጥ እያከናወናቸው ያሉ ተግባሮች አሉ። በዚህም ለሀገር ውስጥ ምርት ማደግ አውንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህም የዘርፉን ዘላቂ ዕድገት የበለጠ በማሻሻልና ስኬታማ በማድረግ በኩል ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል የሚል ሃሳብ አለኝ።

ጥያቄ ፡- ከላይ እንደጠቀሱት የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 46 በመቶ ወርዶ ነበር። ለእዚህ ገፊ ምክንያቶች ከሆኑት መካከል የፋይናንስና የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎች ስለመሆናቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ይጠቅሳሉ። እነዚህን ችግሮች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምን ያህል ያውቃቸዋል?

ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሰሞኑን አንድ ሁለት ትልልቅ የሚባሉ ኩባንያዎች ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሠራተኞቻቸውን እስከመበተን የሚያደርስ ርምጃ ስለመውሰዳቸው እየተገለጸ ነው። የፋይናንስ አቅርቦት ጥያቄ ያላቸውን ባለሀብቶች ችግሮች ከመፍታት አንፃር ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ምን ያህል ተቀራርቦ ይሠራል? ዞሮ ዞሮ ወደ ምርት ሥራ እንዲመለሱ የማድረግ ሃላፊነትም ስላለበት በዚህ በኩል ምን እየተሠራ ነው?

አቶ መላኩ አለበል፡- የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን እንደ ሀገር ስንጀምር መነሻ ያደረግነው ኢንዱስትሪዎቻችን በምን ሁኔታ ላይ ናቸው የሚለውን ለመለየት ጥልቅ ጥናት ለማካሄድ ሞክረናል። ያንን መረጃም ይፋ አድርገናል፤ ጥናቱን ስናደርግ በዳሰሳችን 446 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች ናቸው ሥራ አቁመው የተገኙት። እነዚህን ኢንዱስትሪዎች ማምረት አቁመው፣ ሠራተኞቻቸውን በትነው ነው ያገኘናቸው። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ ወደ 10 ሺህ የሚጠጋ ሠራተኛም ጭምር የነበራቸው ናቸው። ለምሳሌ እንደ እነ አይካ አዲስ እና ሳይገንዲማ፣ እንደ እነጆርጁሹ የመሳሰሉት በጣም ትልልቅ ፋብሪካዎች ናቸው ሥራ አቁመው የነበሩት።

እናም የእያንዳንዱ ኢንዱስትሪ ችግር ይለያያል፤ የአንዳንዱ ችግር የግብዓት ሲሆን፤ የአንዳንዱ ደግሞ የፋይናንስ ይሆናል። የአንዳንዱ የገበያ ሲሆን፣ የሌላኛው ደግሞ የሰው ኃይል ይሆናል፤ የአንዳንዱ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ይሆናል። ስለዚህ መነሻችን እነኚህን ችግሮች ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀራርበን መፍታት አለብን የሚል ነበር። ባለፉት ዓመታት /ወደ ሁለት ዓመት አካባቢ/ በተደረገ ርብርብ ወደ 376 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል።

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ሲደረግ፤ የግብዓት ችግር ያለባቸውን ትስስር በመፍጠር፤ ከባንክ ጋር ችግር ያለባቸውን ከሚመለከታቸው ባንኮች ጋር በመነጋገር፤ የኃይል አቅርቦት ችግር ያለባቸውን የኃይል አቅርቦት ችግሮቻቸውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃ ለየት ያለ ንቅናቄ በማድረግ ለመፍታት ጥረት ተደርጎ ችግሮቹ ተፈትተዋል።

ነገር ግን የኢንዱስትሪ ችግር በጣም ቀጣይነት ያለው ነው። በዚህ ወር ግብዓት ያገኘ ኢንዱስትሪ በሚቀጥለውም ያንን ግብዓት ካላገኘ ዛሬ ሥራ ላይ ያየነውን ኢንዱስትሪ በሚቀጥለው ሥራ ላይ ላናገኘው እንችላለን። ዛሬ በተገቢው መንገድ ኃይል አግኝቶ ሥራ እየሠራ ያለ ኢንዱስትሪ፣ ያንን ኃይል በሚቀጥለው ጊዜ ካላገኘ ያ ሥራ ሊቋረጥ ይችላል።

ይሄ እንዳይቆራረጥ ለማደረግ የተጀመረውን ውጤት ማምጣት የቻለውን አፈፃፀም የበለጠ ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ቅድም ያነሷኋቸው ክላስተሮች በፌዴራል እንዲሁም በክልል ደረጃ ልዩ ክትትል እንዲያደርጉ በእቅድ ይዘው የትኞቹ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ራሳቸውም ባለቤት ሆነው እንዲያግዙ ነው እያደረግን ያለነው።

እንግዲህ ችግሮቹ በባህሪያቸው በአንድ ሴክተር ብቻ የሚፈቱ አይደሉም። የፋይናንስም ችግር ከፋይናንስ ተቋማት ጋር ካልሆነ አይፈታም። የኤሌክትሪክም ችግር ከኤሌክትሪክ ተቋማት ጋር ካልተቀናጀን በስተቀር ልንፈታው አንችልም። ይህንን በማድረግ እነዚህ የፈጠርናቸው ክላስተሮች ቴክኒክ ኮሚቴ አላቸው፤ የክላስተር ኮሚቴ አላቸው፤ የባለ ድርሻ አካላት ኮሚቴ አላቸው። እስከ ክልል ድረስ የሚደርስ አደረጃጀት ስለሆነ በየአንዳንዱ ክልል ውስጥ የትኛው ኢንዱስትሪ ምን ችግር አለበት የሚለውን ከመለየት ጀምሮ ችግሮቹን ለመፍታት የራሱ መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ አቅድ ተዘጋጅቶ አንድ በአንድ ለመፍታት ነው ጥረት እየተደረገ ያለው።

ይሄ በመሆኑ የግብዓት ችግርን በተለያየ መንገድ ለማቃለል ተችሏል። እውነት ለመናገር ባለፉት ሁለት ሶሰት ዓመታት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ ያደረገውን ያህል ጥረት ከዚህ በፊት አድርጓል የሚል እምነት የለኝም። ዋናው ራሳቸው የሥራ ባለቤት ሁነው አብዛኞቹ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱሰትሪው ልዩ መስኮት ከፍተው ሠርተዋል፤ ለምሳሌ ልማት ባንክ፣ ንግድ ባንክ ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሁም ጉሙሩክ ልዩ መስኮት አላቸው።

ይሄንን የሚያደርጉበት ዋና ምክንያት ምንድነው? ኢንዱስትሪዎቹ ከዚህ በላይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚለውን በእምነት በመያዝ በመስራታቸው ነው፤ ኢንዱስትሪዎቹን እኛ ብቻ ሳይሆን የምናውቃቸው እነዚህ ሴክተሮችም አውቀዋቸው ችግሮቹን ለይተው ለመደገፍና ለመፍታት ብዙ ጥረት እያደረጉ ነው። ግን በቂ አይደለም።

የውጭ ምንዛሪ ባለፈው ዓመት ለኢንዱስትሪዎቹ ወደ አራት መቶ ሃምሳ ሶስት ሚሊዮን ዶላር ነው የቀረበው። ለመለዋወጫ እቃና ለግብዓት መግዣም ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ወደ 266 ሚሊዮን ዶላር ለኢንዱስትሪዎቹ ቀርቦላቸዋል።

ግን ፍላጎቱን ስናየው ከዚህ በላይ ነው። ይሄ ፍላጎት በመኖሩ ምክንያት አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ላይ የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ አቅርቦት አለመኖሩ የሚያሳድረው ተፅእኖ ይኖራል። ነገር ግን ያለው አጠቃላይ የፋይናንስ ምህዳሩ የግብዓት አቅርቦት ምህዳሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየተሻሻለ ነው። ባለፈው ዓመት ግብዓት በአጠቃላይ ሁሉንም አሰባስቦ ለማቅረብ የተቻለው ወደ አስራ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነበር።

ይህ በ2014 ወደ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ይጠጋል ፤ አራት ነጥብ ዘጠኝ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነበር የቀረበው። በዚህ አምስት ወር ውስጥ ብቻ ወደ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ወደ አራት ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ግብዓት ማቅረብ ተችሏል።

ነገር ግን አሁንም ፍላጎቱ ከዚህ በላይ ነው። በጣም ከፍተኛ ፍላጎት አለ። ስለዚህ ይህን ችግር ለመፍታት ኢንዱስትሪዎችን ከኢንዱስትሪ ጋር የማስተሳሰር ሥራ ነው እየተሠራ ያለው። አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ለሃያ አምስት ኢንዱስትሪዎች ይመግባሉ። ከእነሱ ላይ የሚገኘውን ምርት ለሌሎች ኢንዱስትሪዎቸ በመሰጠት የምርት ትስስር ለማድረግም እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ስላሉ ችግሩን ለመፍታት እየተሠራ ነው።

በመሠራቱም የተገኙ ውጤቶች አሉ፤ ነገር ግን አሁንም ከዚህ በላይ በጣም ሰፊ ጥረት ማድረግና የኢንዱስሪዎችን ችግር ቀረብ ብሎ መፍታት ያስፈልገል። ይህ በፌዴራል ብቻ ሳይሆን በክልል ደረጃም ከኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጋር እየተሠራ ያለው ኢንዱስትሪዎችን በልዩ ሁኔታ የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ይሆናል ማለት ነው።

ጥያቄ ፡- በኢትዮጵያ ሰፊ የውጭ ምንዛሬ ከሚያስገኙት መካከል አንደኛው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ወደ ውጭ የሚልከው ምርት ነው። ከዚህ አኳያ ባለፉት አራትና አምስት ወራት በውጭ ምንዛሬ ግኝት ረገድ ካስቀመጣችሁት እቅድ ምን ያህሉ ተሠርቷል? የንግድ ሚዛኑን መዛነፍ ይታያልና ይህን ሚዛን ለመጠበቅ ኤክስፖርት ላይ በስፋት መሥራት ይጠበቃል። ከዚህ አኳያስ ምን ተሠርቷል? በእቅድ ካስቀመጣችሁት ምን ያህል ገቢስ ተገኝቷል?

አቶ መላኩ አለበል፡- የኤክስፖርት አፈፃፀማችን በእቅድ ደረጃ በመጠን እንልካለን ብለን ያሰብነው የምርት መጠን ከመቶ በመቶ በላይ ተልኳል፤ በገቢ ሲታይ ግን በጣም ዝቅተኛ ነው። እቅዱን የሚያሳካ አይደለም። በአምስት ዓመቱ የተገኘው መጠን ወደ አንድ መቶ ሰለሳ አንድ ሚሊዮን ዶላር ነው ።

ይህ በእኛ ግምገማ ዝቅተኛ አፈፃፀም ነው ብለን ነው ያየነው ምክንያቶችን ለመለየት ሞክረናል። አንደኛው ችግር ብለን የለየነው ለምንልከው ምርት ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ በምላሹ እያገኘን አይደለም የሚል ነው። ይህ ከምን ጋር የሚያያዝ ነው? ምርቶች በሚላኩበት ጊዜ ቢያንስ መምጣት ያለባቸውን የውጭ ምንዛሬ መምጣት ለሁሉም ምርቶች አልተወሰነም፤ ከዚህ በፊት የወሰንላቸው ምርቶች አሉ ለምሳሌ እንጀራ ብንወስድ አንድ እንጀራ ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ነው ይዞ መምጣት ያለበት የሚለውን ከወሰንን በኋላ ያለው ውጤትና ከመወሰናችን በፊት የነበረው ውጤት የተለያየ ነው።

ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ወደ ሰለሳ ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው ከእንጀራ ላይ ያገኘነው። እንጀራ ኤክስፖርት አድርገን፤ ይህ ግኝት በዚህ ዓመት መጨረሻ ምናልበት ወደ ስልሳ ሚሊዮን ዶላር ያድጋል ብለን እንገምታለን፤ ምክንያቱም የዋጋ ማሻሻያ በመደረጉ ምክንያት አንድ እንጀራ ማምጣት ያለበት የውጭ ምናዛሬ ያድጋል። ይህ በእያንዳንዱ ምርት ላይ አልተሠራም።

አንዳንድ ምርቶች በባህርያቸው አስቸጋሪ በመሆናቸው ዝቅተኛ ዋጋ ለመወሰን አላስቻሉም፤ ነገር ግን ከዚህ ጋር ተያይዞ የምንልከውን መጠን ያህል ገቢ እያገኘን ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም ዝቅተኛ ዋጋ ማስመዝገብ /under invoicing/ አለ። በተላከው ምርት ልክ ዶላሩን መልሶ አለመምጣት ችግሮች አሉ ። ይህንን በአሠራር መመለስ ይኖርብናል።

ስለዚህ እሱ አካባቢ ላይ አንዳንድ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ። ሁለተኛው የእኛ እሴት ጭመራ መጠን ተጨማሪ ሥራ ይጠይቃል። የምንልከው ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እሴት ስንጨምርበት የሚያስገኘው የዶላር መጠንና የእሴት ጭማሪያችን ዝቅተኛ በሚሆንበት ጊዜ የሚያስገኘው መጠን በዛው ልክ ዝቅ ይላል። ከዚህ ጋር ተያይዞ መስተካከል ያለባቸው አሉ።

ይሄ ሆኖም ወደ 131 ሚሊዮን ዶላር አግኝተናል፤ ነገር ግን በሚቀጥሉት ወራት ይህን በሚገባ የሚያሻሽል ሥራ ይሠራል። ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት፣ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከስር ከስር የመፍታትና ወጪን የሚቀንሱ ጉዳዮችን በመሥራት በኩል የሚሠሩ ሥራዎች ይኖራሉ።

በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ‹‹አጎዋ›› ምርቶች ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ ገበያ የሚገቡበት / ያሳደረው ተፅእኖ አለ። የአጎዋን ገበያ ታሳቢ አድርገው የመጡ ኢንዱስትሪዎች ነበሩ፤ የአጎዋ ጉዳይ ይሻሻላል የሚል ግምት ነበረን። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች እስካሁን ድረስ እንደምንም እየተፍጨረጨሩ ሥራ ላይ ለመቆየት ጥረት አድርገዋል። የአጎዋን አድል በሰጠችው ሀገር በኩል ያለው ሁኔታ እስከመጨረሻው ባለመታወቁ ምክንያት በወጪ ንግዱ ላይ ያሳደረው ተፅእኖ አለ። በቀጣይ ይህን የማሻሻልና ባለሀብቶችን በዘላቂነት የመደገፍ ሥራ መሠራት አለበት። ስለዚህ ከወጪ ንግድ እቅድ አኳያ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ በመሆኑ ይህ መሻሻል አለበት የሚል ግምገማ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ተደርጓል።

ጥያቄ፡- በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ነገር ግን ከውጭ እየገቡ ያሉ በርካታና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስወጡ ያሉ ምርቶች አሉ። እነዚህን ምርቶች ለመተካት ተኪ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረት እንዳላባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል። ተኪ ምርቶች ላይ ምን አይነት ሥራዎች ናቸው እየተሠሩ ያሉት?

አቶ መላኩ አለበል፡- በተኪ ምርቶች ላይ በፖሊሲ አቅጣጫችን ውስጥ ልዩ ትኩረት የሰጠነው ጉዳይ አለ። የቀድሞው ፖሊሲ በወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ነበር፤ የአሁኑ ደግሞ የገቢ ምርት መተካት ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል። ተኪ ምርት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት ያለበት እንዲሆን ተደርጓል። ስለዚህ ምንድን ነው ያደርግነው፤ ስትራቴጂ መዘጋጀት አለበት ፤ ፍላጎታችንን በፖሊሲ ስናንፀባርቅ እንዴት ይፈፀማል? የሚለው ደግሞ በስትራቴጂ መመለስ አለበት። ይህን በተመለከተ ያዘጋጀነው ስትራቴጂ በጣም ጠለቅ ያለ ነው። የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በደንብ አይቷል።

በገቢ ምርት የተሳካላቸው ሀገራት አሉ። በገቢ ምርት ኢኮኖሚያቸውን የጎዱ ስላሉ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ይህን የገቢ ምርት ስትራቴጂ እንዴት ውጤታማ ልናደርግ እንችላለን? የነማንን ተሞክሮ መውሰድ አለብን? የሚለውን ለመመለስ ጥልቀት ያለው ጥናት ተሠርቷል። አንደኛው ሥራም ይኸው ነው።

ሁለተኛው በእኛ ሀገር ውስጥ ምን አይነት ግብዓት አለ? የትኞቹ ኢንዱስትሪዎች በፍጥነት ገቢ ምርትን መተካት ይችላሉ? ገበያውና ፍላጎቱስ ምንድን ነው የሚመስለው? ችግሮቻቸውስ ምንድን ናቸው? በምን ያህል ጊዜስ መቶ በመቶ ከውጭ የሚመጣውን ምርት ሊተኩ ይችላሉ? የሚለውን መመለስ የሚችል ጥልቀት ያለው ጥናት ተካሂዶ ስትራቴጂ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።

ይህ ስትራቴጂ ከተዘጋጀ በኋላ በስትራቴጂ ዝግጅት ውስጥ ባለሀብቶችም አብረው እንዲሳተፉ ለማድረግ ተሞክሯል። እነርሱም ግብዓት ሰጥተውበታል። ከዛም በኋላ ወደ ክልሎችም መውረድ ስለነበረበት የክልል አመራሮችና ባለሙያዎች በስትራቴጂው ላይ ውይይት እንዲያደርጉበትና ሥልጠና እንዲሰጥ ተደርጓል። የስትራቴጂው ማስፈፀሚያ እቅድም ተዘጋጅቶለት ወደትግበራ እየተገባ ነው።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ወደ 96 የሚደርሱ ምርቶች ናቸው የተለዩት። ይህ መቶ በመቶ ፍላጎታችንን የሚያሳካ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሁሉንም መጀመር ሊያስቸግር ስለሚችል አሁን ካለን አጠቃላይ ቁመና አኳያ 96 የሚደርሱ ምርቶችን በፍጥነት መተካት አለብን በሚሉ ስትራቴጂዎች ተለይተው የትኞቹ ኢንዱስትሪዎች ላይ ምን እንሠራለን? የሚለው ተለይቶ በዛ መሠረት ወደተግባር ተገብቷል።

በመንግሥትም በኩል የተሰጠ አቅጣጫ ይህንን የሚያጠናክር አለ። ይህ አቅጣጫ ምንድነው? የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመንግሥት ተቋማት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥተው ግዢ መፈፀም አለባቸው የሚል ነው። እነርሱም ገበያውን በመጠቀማቸው የሀገር ውስጥም የውጭ ተወዳዳሪነታቸው የበለጠ እያደገ የሚሄድበት ሁኔታ ይኖራል።

ስለዚህ የገቢ ምርት ከመተካት አኳያ እንደሀገር የተጀመረውን ስትራቴጂ ለመጪዎቹ ሶስት አራት ዓመታት የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት ማምጣት ይችላል የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ውስጥ በግል ዘርፉ በኩል መሠራት ያለባቸው ነገሮች አሉ። እንዳንድ ጊዜ መንግሥት እንዲህ አይነት እድል ሲሰጥ እድሎችን በተሳሳተ መንገድ፣ ለኢኮኖሚ በማይጠቅም መንገድ፣ ዘርፉን በማያሳድግ መንገድ ለመጠቀም የመፈለግ አዝማሚያዎች ይኖራሉ። እርሱን ለማስተካከል ውድድርን እንዲያጠናክር በማድረግ በእነርሱ በኩል ከግል ሴክተሩ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል ግን የሀገር ውስጥ ምርት ያው ገና ነው። ለሀገር ውስጥ ምርት ያለን አመለካከት ያው እስከ ሆነ ድረስ ለውጥ ያለ አይመስለንም፤ ስሙና ስያሜው አይገለፅም እንጂ አብዛኛው ገበያ ላይ ያለው ምርት የኢትዮጵያ ምርት ነው። ከፍተኛ የሀገር ውስጥ ምርት በጥሩ ዋጋ፤ በጥሩ ጥራት ለሀገር ውስጥ ገበያ እየቀረበ ነው። ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ እያነቃነቅን ነው ብለን እናስባለን።

ይሄ የኢትዮጵያ ምርት ነው፤ ይህ የኢትዮጵያ ነው ብለን በማሳወቅ የግንዛቤ ክፍተቶችን እንሞላለን ብዬ አስባለሁ። ወደ ፊት ገበያውን፣ የፋይናንስ አቅርቦቱን፤ የማበረታቻ ሥርዓቱንና የመሳሰሉትን በሚያጠናክር መልኩ እየሠራን፤ እያሻሻልን እንሄዳለን።

ጥያቄ – በኢንዱስትሪው መስክ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ያከናወናችሁትን በ100 ቀናት ሪፖርታችሁ ላይ ተመልክቻለሁ፤ በዚህም መሠረት 122 ባለሀብቶችን ለመሳብ አቅዳችሁ 94 (የእቅዱን 86 በመቶ) መድረሳችሁ በሪፖርቱ ላይ ሠፍሯል። ባቀዳችሁት ልክ እንዳትሄዱ ያደረጋችሁ ምክንያቱ ምንድን ነው?

አቶ መላኩ አለበል፡- በውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (ኤፍዲኢ) ያለው ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከኮቪድ ጀምሮ እንደ ወረደ ነው ያለው፤ ገና አልተነሳም። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ፣ ከዛ ቀጥሎ መካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለው ችግር ተፈጠረ፤ በዓለም ላይ የተፈጠረው የፋይናንስ ኮስት ሌላው ችግር ሲሆን፣ ይህም የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትና ኢንቨስት ለማድረግ ችግር ፈጥሯል።

በእነዚህ ምክንያቶች በዓለም ላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ከፍተኛ የሆነ መደናገር አለ። ይሄ ለእኛ ብቻ ሳይሆን እንደ አህጉርም፤ እንደ ዓለምም ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳደረ በመሆኑ እኛም ጋ ያው ነው።

ሌላው ከዚህ ከሪፓትሪዬሽን ጋር የተያያዘው ጉዳይ ነው። የውጭ ባለሀብት ወደ እዚህ መጥቶ ኢንቨስት ለማድረግ ሲነሳ መጀመሪያ የሚያነሳው ጥያቄ “እዛ ያለኝን ዶላር እንዴት ነው እዚህ የማወጣው?” የሚል ነው። እነዚህን ጥያቄዎች በማስተናገድ በኩል የሚኬድበት መንገድ የሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ አለው።

ይሁን እንጂ በ2025 እና 2016 ዓ.ም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት ነው እየታየ ያለው፤ ከፍተኛ ጥያቄ ነው እየቀረበ ያለው። በተለይ ደግሞ የስፔሻል ኢኮኖሚ ዞን፣ የድሬዳዋው በሕግ መውጣቱና ወደ ተግባር እየተሸጋገረ መሆኑ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ አስቻይና ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ነው። እናም፣ ሁኔታው በፍጥነት እየተቀየረ ይሄዳል።

በአንፃራዊነት በዓለም ላይ ርካሽ የሚባለውን የኤሌክትሪክ ዋጋ የምናቀርበው እኛ ነን፤ ይህንን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ታሳቢ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ የመምጣት ፍላጎታቸው በጣም ከፍተኛ ሆኗል። ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ምቹ ሁኔታ ላይ ስላሉ እነሱም እንደ አንድ መሳቢያ ሊያገለግሉ ይችላሉ። የኢትዮጵያ ገበያም ቀላል አይደለም፤ በጣም ከፍተኛ ገበያ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ 120 ሚሊዮን ነው፤ ይህንን ገበያ ለመጠቀም ይፈልጋሉ። አሁን የብሪክስ አባል በመሆናችን የቻይናና ህንድ ባለሀብቶች ወደ ሀገራችን መጥተው ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት ስለሚጨምር ይህ ቁጥር በመጪዎቹ ወራት በከፍተኛ ደረጃ ይሻሻላል። ከእቅድ በላይ ሁሉ ሊሄድ ይችላል።

ጥያቄ – ከአጎዋ ጋር በተያያዘ ሚኒስቴሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ እንዲቆዩ ሲሰራ ቆይቷል፤ እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ባለሀብቶች ምርቶችን ወደ ውጭ ከመላክ ጋር በተያያዘ ጥርጣሬና ፍርሃት ነበራቸው። ባለሀብቶቹ እንዲቆዩ ከማበረታታት አኳያ የተሠራውን ቢገልጹልን?

አቶ መላኩ አለበል፡– ብዙ ሥራዎች ናቸው የተሠሩት፣ አንደኛው እነዚህ የውጭ ባለሀብቶች የሀገር ውስጥ ገበያን እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ነው፤ ከአንድ እስከ ሃምሳ በመቶ የሚሆነውን ምርታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ አስገብተው እንዲሸጡ በልዩ ሁኔታ ተፈቅዶላቸዋል። አንዳንዶቹ ምርቶች በልዩ ሁኔታ እስከ መቶ በመቶ ድረስ ለምሳሌ ሀገር ውስጥ ላሉ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉትን እስከ መቶ በመቶ ድረስ እንዲሸጡ ተፈቅዶላቸዋል፤ አንዱ ይሄ ነው።

የመከላከያና አጠቃላይ የፀጥታ መዋቅራችን ዩኒፎርሞች ከዚህ በፊት በውጭ ነበር ሲዘጋጁ የነበረው። ይሄን በሀገር ውስጥ መተካት አለብን ብለን ስንሠራ ከፍተኛ የሆነ ገቢ አግኝተዋል ፤ በዚህ ውስጥ ተጠቅመዋል። እነሱም የተሻለ ቴክኖሎጂ ስላላቸው በዚህ ገበያ ውስጥ ትስስር እንዲፈጠርላቸው አድርገናል። ጫማዎችን እንዲያቀርቡ ተደርጓል። የፀጥታ መዋቅር ዩኒፎርምችን የደንብ ልብሶችን እንዲያመጡ አድርገናቸዋል ይሄ ለነሱ ትልቅ ገበያ ፈጥሮላቸዋል።

አንዳንድ ከዚህ በፊት በዶላር ሲከፍሏቸው የነበሩ ክፍያዎችን በብር እንዲሆን አድርገንላቸዋል። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እነሱ በዚህ ገበያ ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እሱ ብቻ ሳይሆን ያለንን የንግድና ዲፕሎማቲክ ግንኙነት በመጠቀም አንዳንድ ሀገራት ከዚህ በፊት ያልሰጡንን ዕድል ከታሪፍ ነጻ ምርቶቻችንን እንድናስገባ እንዲፈቀድልን አድርገን ያንን ገበያ እንደ አንድ ድርጅት ተጠቃሚ ለማድረግ ሞክረናል። ለምሳሌ ከዚህ በፊት ከዩኬ እንግሊዝ ገበያ ውስጥ ከቀረጥ ነጻ የምናስገባበት ሁኔታ አልነበረም፤ ነገር ግን ይሄ እንዲፈቀድልን አድርገናል። ያ ገበያም ቀላል ገበያ ስላልሆነ እነሱም እንዲጠቀሙ ለማድረግ ተሞክሯል።

ቻይናም እንዲሁ ሰፋ ያለ የገበያ እድል ሰጥታናለች፤ በዚህም አንዳንድ ምርቶችን ወደ እነሱ ገበያ አስገብተን እንድንሸጥ የሰጡን እድል ስለነበረ በእነዚያም እድሎች እንዲጠቀሙ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። ስለዚህ በአንድ በኩል ገበያ የማፈላለግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ ገበያ ላይ ሊቆዩ የሚችሉበትንና ሠራተኞቻቸውን ሳይቀንሱ በሥራ ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች አሉ። ይህም እስከ አሁን ድረስ ባለው ሁኔታ የነሱን ቆይታና ምርታማነት አሻሽሏል።

ጥያቄ፡- ሥራ አቁመው ከነበሩ 446 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች መካከል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ 376 ቱን ወደ ሥራ መመለስ ተችሏል፣ የንቅናቄው ሥራ የፈጠረውን መነሳሳት ለማስቀጠል ንቅናቄው ከዘመቻ ሥራ በማውጣት በዘላቂነት ሥርዓት ተዘርግቶለት እንዲሠራ ከማድረግ አንጻር ምን ዓይነት ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው?

አቶ መላኩ፡- ይሄ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የዘመቻ ሥራ አይደለም። ከዚህ በፊትም ለማንሳት እንደሞከርነው በዓለም ላይ በኢንዱስትራላይዜሽን የተሳካላቸው የሚባሉት ሀገራት በተለይ ደግሞ እንዱስትራላይዜሽን ሲጀምር አብረው ያልጀመሩ፣ በኋላ ላይ የጀመሩ ፣ ኢንዱስትራላይዜሽንን የተቀላቀሉ የምንላቸው ሀገራት የተሳካላቸው፣ ኢንዱስትሪ እግር እንዲተክል ማድረግ የቻለ ሥራ የሠሩ ሀገራት ናቸው።

የነዚህን ሀገራት ተሞክሮ ዝርዝር በጥናት ለይተን ምን ያህል ጊዜ ወሰደባቸው ፣ እንዴት ተሳካላቸው ምን አደረጉ የሚለውን ወስደን ነው የገባንበት ። እንግዲህ ዘመቻ የሚባለው ብዙውን ጊዜ አንድ ዓመት ማክሲመም ሁለት ዓመት የሚቆይ ሥራ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ቢያንስ ቢያንስ የአስር ዓመት ቆይታ እንዲኖረው ተደርጎ የተዘጋጀ በፕሮጀክት ኦፊስ ደረጃ የሚመራ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የኢንዱስትሪ ኮሚቴ አለው፣ ክላስተሮች ያሉት፣ ክላስተሮቹ በሥርዓት የሚመሩ፣ እያንዳንዱን ሚኒስቴር መሥርያ ቤት በኃላፊነት የሚከታተለው፣ መደበኛ ሥራዎቻውን በዘላቂነት ለማስፈጸም የሚያስችል እቅድ ያለው፣ ኢትዮጵያ ታምርትን ለማስፈጸም የተዘጋጀውን የአስር ዓመት የሶስት ዓመት ዕቅድ እና በእያንዳንዱ ተቋም ምን እንደሚፈጸም የተቀመጠውን ስናይ ያ ሥራ የዘመቻ ሥራ እንዳልሆነ የሚያመላክት ነው። ስለዚህ ተቋማዊነ ዘላቂ እንዲሆን በሚያደርግ መንገድ ነው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እየተካሄደ ያለው።

ንቅናቄው ለምድንነው ያስፈለገው?፤ ከላይ እንዳነሳሁት አንዱ ትልቁ ችግር በተቋማት መካከል ያለው የባለቤትነትና የቅንጅት ችግር ነው፤ ይሄ አንድ ሴክተር ብቻውን የትኛውንም አይነት እንቅስቃሴ ቢያደርግ ሊያሳካው የማይችል ትልቅ ግብ ስለሆነ ነው። ስለዚህ ይህንን ችግር ለመፍታት ምንድነው ማድረግ ያለብን? ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ፕላት ፎርም /ምቹ ሁኔታ/ መኖር አለበት። ያንን ፕላት ፎርም ካልፈጠርን በስተቀር ሄዶ ሄዶ በግብዓት ምክንያት የሚቆም ከሆነ፣ ሂዶ ሂዶ በፋይናንስ ምክንያት የሚቆም ከሆነ፣ ሂዶ ሂዶ በገበያ ችግር የሚቆም ከሆነ ሥራው ዋጋ የለውም። በእዚህ ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ አለባቸው።

የኢትዮጵያ የችግር /የድህነት/ መውጫ አንደኛው ኢንዱስትሪያላይዜሽን ነው። ኢንዱስትሪያላይዜሽን በጣም ወገብ የሚያጎብጥ ከባድ ሥራ ነው። ይሄንን ሥራ ግን ሁላችንም ተቀናጅተን በባለቤትነት መሥራት አለብን ወደሚል መተማመን ካልተመጣ በስተቀር ሥራው ቀላል አይደለም። በጣም! በጣም! ብዙ ነገሮች አሉበት። ዓለም አቀፍ ውድድሩ በጣም ከባድ ነው። አንዳንድ ጊዜ እኛ የምንጠቀምባቸው ቴክኖሎጂዎች በሌሎች ሀገሮች ላይ ከ20 ዓመት በፊት የቀሩ፤ ከ10 ዓመት በፊት የቀሩ ቴክኖሎጂዎች ሁነው እናገኛቸዋለን።

በቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ፣ በሰው ኃይል እና በግብዓት ተወዳዳሪ መሆን አለብን፤ በሎጂስቲክ ተወዳዳሪ መሆን አለብን፤ የፋይናንስ ወጪያችን /ኮስታችን/ በጣም ተመጣጣኝ መሆን መቻል አለበት። በጣም አዳጊ የሆነ የምርምርና ልማት ሥራ መሠራት አለበት። በየጊዜው አዳዲስ ምርቶችን እያመረትን ወደ ገበያ ማስገባት አለብን።

ይህን ሁሉ ሥራ ሁሉም ተቋማት ተቀናጅተው ነው የሚሠሩት። ይህ ካልሆነ በስተቀር፤ ሥራው በተናጠል የሚሆን አይደለም። ምክንያቱም የአንዱ መሳሳት፣ የአንዱ መጉደል በሌሎች ምርታማነት፣ እና ውጤታማነት አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል። ስለዚህ አንዱ “ኢትዮጵያ ታምርት” እንዲፈታው የፈለግነው በተቋማት መካከል ያለውን ስር የሰደደ የቅንጅት ችግር ዘላቂነት ባለው መንገድ በአሠራር መፍታት ነው።

ይሄንን ግን የሚያገናኝ፣ የሚያንቀሳቅስ ያስፈልጋል። የት ደረሳችሁ የሚል ያስፈልጋል። ምን አቀዳችሁ? ምን ሠራችሁ? ምን ችግር አጋጠማችሁ? ወዴት ነው የምትሄዱት? ብሎ የሚጠይቅ ያስፈልጋል። ይሄንን ለማድረግ ንቅናቄው በከፍተኛ ደረጃ /at higher level/ እንዲመራ ለማድረግ የተሞከረው።

ስለዚህ የመጀመሪያው ነገር ንቅናቄው የአጭር ጊዜ አይደለም፤ ዘመቻ አይደለም፤ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው። አመለካከት ከመቀየር የሚጀምር ነው። የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ የማሳደግ፣ አመለካከታቸውን የመቀየር፣ በዛ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያደርግ ነው። ይህን በማድረጋችን ተጠቅመናል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ10 ሺህ 774 ሄክታር መሬት በላይ ለኢንዱስትሪዎቹ ለማቅረብ ተችሏል። ይህ በተናጠል አይሳካም ነበር፤ ክልሎቹ አምነውበት ተቀናጅተው ባይሰሩ ኖሮ። ወደ 773 የሚደርሱ ሼዶች ባለፉት ሁለት ዓመታት፤ ሁለት ከተማ አስተዳደርና በአራት ክልሎች ተገንብተው ለኢንዱስትሪዎቹ እንዲተላለፉ ማድረግ ተችሏል። ጥቅም ሳይሰጥ የቆየ ከ600 ሄክታር መሬት በላይ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል።

ፋይናንስ ላይ ምን ብናደርግ ነው ኢንዱስትሪው ሊያድግ የሚችለው? ፖሊሲያችንን ምን ብናደርግ ነው ኢንዱስትሪው ሊያድግ የሚችለው? ስትራቴጂዎቻችን ምን ቢሆኑ ነው ኢንዱስትሪው ሊያድግ የሚችለው? የሚለውን የውስጥና ጥልቀት ያለው እይታ ማግኘት የተቻለው ይሄ ንቅናቄ በፈጠረው ግንዛቤ ነው።

ስለዚህ ግንዛቤው መንግሥትና የግል ሴክተሩ የበለጠ እንዲቀራረቡና ችግሩንም አውቀው እንዲፈቱት ለማድረግ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይሄ አሁን የምንሠራው ሥራ ባለቤት አለው። አንደኛው ባለቤቱ ራሱ ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ ነው። ግን ደግሞ ሌሎች ባለቤቶችም አሉ። እነዚህ ባለቤቶችም ሥራቸውን በተገቢው መንገድ አውቀው እንዲሠሩ የመከታተል፣ የመደገፍ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ቀደም ሲል የአንደኛውና ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በሚል በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመሥራት ታቅደው የነበሩ ትልልቅ እቅዶች ነበሩ። እነዚህ እቅዶች አልተሳኩም።

ይህ በአስር ዓመት በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው እንደርስበታለን በሚል ያስቀመጥነው እቅድ በጣም ትልቅ ነው። ትልቅ ግብ ነው የጣልነው። ይህን ግን በተለመደው መንገድ በመሄድ ልናሳካው አንችልም። አዳዲስ እይታዎችና አሠራሮች ያስፈልጋሉ።

ሌሎች ሀገሮች ኢንዱስትራላይዜሽንን ከኋላ ተነስተው እንዴት አሳኩት ስንል የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ ጠንካራ ፖሊሲ እንዲሁም ፖሊሲን በተሟላ መንገድ መተግበር፣ ማድረግ ነው። የግል ሴክተሩ ደግሞ ዋነኛ የሴክተሩ ባለቤት እንዲሆን ማስቻልና ዘላቂነት ያለው ክትትልና ድጋፍ ማድረግ መቻል ነው።

ስለዚህ ወደ 40 ወርዶ የነበረውን የማምረት አቅም አጠቃቀም ወደ 85 በመቶ እናድረሰናል ስንል ይህ የብዙ ነገር ድምር ውጤት ነው። አሁን ያለውን ዝቅተኛ ኤክስፖርት ወደ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በአስር አመት ውስጥ እናድርስ ስንል በየአመቱ ሲፈጠር የነበረውና 172 ሺህ የነበረውን የሥራ እድል በዓመት ከ850 ሺህ በላይ አድርሰን በአስር ዓመቱ መጨረሻ አምስት ሚሊዮን እንድረስ ስንል 70 በመቶ ከውጭ የሚመጣውን ወይም ደግሞ 30 በመቶ የነበረውን የእኛ ድርሻ ወደ 65 በመቶ እናሳድግ ስንል የሚጠይቀው በጣም ብዙ አለ።

ይህን ለማስፈፀም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነበር። አሁን ላይ ተቋማዊና ዘላቂ ለማድረግ ኮሚቴ አለ። ይህ ኮሜቴ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ፣ ከስሩ ሚኒስትሮችና የክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድሮች ያሉበት ነው። በዓመት ሁለት ጊዜ እየተገናኘ ሥራውን ይገመግማል። ከስሩ ስድስት ክላስተሮች አሉ። እነዚህ ክላስተሮችም መሠረተ ልማትን፣ ኢንቨርስትመንት ፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ፣ ባለሀብት መሳብን ፣ ከአቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ይገመግማሉ። የየራሳቸው አቅድ አላቸው። ክላስተሮቹ በየሩብ ዓመቱ ነው የሚገናኙት። ከክላስተሮቹ ስር ደግሞ ቴክኒክ ኮሚቴዎች አሉ። በየወሩ ይገናኛሉ።

ይህን የሚያስተባብር ደግሞ የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ቢሮ አለ። ይህ ቢሮ እስከ እቅዱ ማጠቃለያ ድረስ አብሮ የሚቀጥል ነው የሚሆነው። ስለዚህ ተቋማዊ ሆኖ እንዲሠራ እየተደረገ ነው። ይህ ውጤት አስገኝቷል።

ይሁንና ሴክተሩ ከቆየበት ችግር አኳያ በአንድ እና ሁለት ዓመት የሚያልቅ ስላልሆነ በዘላቂነት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ እነዚህን ችግሮችን ፈትቶ ዘርፉ በኢኮኖሚ ውስጥ ሊያበረክት የሚገባውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ያስችላል። በዚህ መልኩ ቢታይ ጥሩ ነው የሚል አስተያየት አለኝ።

ጥያቄ፡- ይህ ዘርፍ ከአምስቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች መካከል አንደኛው ነው። ብዙ ሥራ የሚፈልግ መሆኑም ይታወቃል። አሁንም ድረስ ብዙ ጥያቄዎች ያላቸው ኢንዱስትሪዎች አሉ። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚያቀርቧቸውን ጥያቄዎች ከመመለስና ችግራቸውን ከመፍታት አንፃር በአስር ዓመቱ የመሪ የልማት እቅዱም ሆነ በአመትና በሩብ ዓመት ከሚቀመጡ እቅዶች አንፃር ምን ያህል ተግታችሁ እየሠራችሁ ነው?

አቶ መላኩ፡- ከኢንዱስትሪዎች ጋ በሁለት ደረጃ ከፍለን ብንመለከት ጥሩ ነው። አንደኛው በፌዴራል ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል ከባለሀብቶች ጋር የምንሠራው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ኢንዱስትሪዎቹ በሚሠሩበት ክልልና ከተማ አስተዳደር የሚሠራ ነው። አንዱ ጥሩ መሠረት ጥለናል የምንለው በየደረጃው ያለው የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ለመደገፍ የተቋቋሙት ተቋማት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግሉ ዘርፍ ጋር ተቀራርበው የሚሠሯቸው ሥራዎች ናቸው።

አንደኛው ራሱን የቻለ አደረጃጀት አለው፤ በማህበራትና ዘርፍ ማህበራት አማካኝነት የሚደረጉ ግንኙነቶች አሉ። ሁለተኛው ደግሞ በቀጥታ የመንግሥት አስፈፃሚዎች ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ በመሆን ችግሮቻቸውን በመለየት የሚሠራው ሥራ ነው። ይሄ ሥራ በጅምሩ ጥሩ ነው። ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ብንሄድ የትኛው ኢንዱስትሪ ምን ችግር አለበት፤ ማነው የሚፈታው፤ እንዴት ነው የሚፈታው የሚለው በዝርዝር አለ። እያንዳንዱ ክልል በዚህ መሠረት ነው የሚሠራው። ይሄ በሁለቱም መካከል ያለና ይበልጥ ተሰሚ ነው ፤ እየተጠናከረ ይሄዳል።

በሌላ በኩል ሁለተኛው በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል የሚሠራው ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማህበራቱ ጋር የመገናኘት እንደዚሁም ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸውን ኤክስፖርትና የገቢ ምርትን በመተካት ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ስላሉ እነሱን በቀጥታ በማግኘትና በምንፈጥራቸው ፕላት ፎርሞች ሃሳቦቻቸውን እንዲያነሱና መፈታት ያለባቸውን ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ ነው እየተሠራ ያለው። ይሄ አሁን በጀመርናቸው ስትራቴጂዎች ወደ ተግባር እያስገባነው ባለው ፖሊሲ የበለጠ እየተጠናከረ የሚሄድ ነው። ግን እስካሁን ድረስ ያየናቸው ሥራዎች በጣም ውጤት እያመጡ ስለሆነ ይሄንኑ የበለጠ ማጠናከር ያስፈልጋል።

ጥያቄ፡- በጦርነትና በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች ኢንዱስትሪዎች መልሰው እንዲያገግሙ ምን አይነት ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው?

አቶ መላኩ፡- መልካም በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ኢንዱስትሪዎች በሁለት ከፍለን ብናያቸው ጥሩ ነው። የመጀመርያው በአፋርና በአማራ ክልል አካባቢ ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎችን ናቸው። እነዚህን ኢንዱስትሪዎች በቅድሚያ ምን አልባት ከፀጥታ መዋቅሩ ቀጥሎ ወደ ቦታው ደርሶ ኢንዱስትሪዎች ያለባቸውን ችግር ለይቶ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ያደረገ ተቋም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው።

ስለዚህ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች አነሰም በዛም በሙሉ አቅማቸው እንዳያመርቱ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ጨምሮ እስከ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች ድረስ ያሉት ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ጥረት ተደርጓል። ይሄ በቅርብ ጊዜ አማራ ክልል ላይ ያሉትንና አሁን ሥራ ያቆሙትን የሚጨምር አይደለም። እሱ ገና መነሻ ጥናት ስላልተሠራ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ አናውቅም።

ነገር ግን በ2013፤2014 እና 2015 ዓ.ም በነበረው ግጭት ችግር የደረሰባቸውን በተመለከተ በጣም በጣት የሚቆጠሩ ወደ ሥራ ያልተመለሱ ካልሆኑ መስተቀር አብዛኛዎቹ በተለያየ የድጋፍ ማዕቀፍ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ ተሞክሯል፤ የውጭ ምንዛሬ የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ከፋይናንስ ተቋሞቻቸው ጋር የነበሩት ችግሮች እንዲፈቱ የስፔር ፓርት (የመለዋዋጫ እቃ) ግብዓት እንዲያገኙ፤ ከደንበኞች ጋር ተያይዞ ችግር የነበረባቸውንም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ችግሮች እየተፈቱ ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል። አሁንም ግን ተጨማሪ ድጋፍ የሚጠይቁ ኢንዱስትሪዎች አሉ።

ሁለተኛው ከዚሁ ጋር የሚያያዘው በትግራይ ክልል ያሉትም በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ ችግሮችን የመለየት ሥራ ተሠርቷል። ከዚህ ውስጥ ቶሎ ወደ ማምረት መግባት የሚችሉት ወደ ማምረት እንዲገቡ እየተደረገ ነው።

ትልልቅ የሚባሉና በኢንዱስትሪ ፓርኮችም ያሉ ወደ ሥራ እየተመለሱ ነው። በቀጣዮቹ ሶስት አራት ወራትም አሁን የጀመሯቸውን ሥራዎች እያጠናከሩ፤ ተጨማሪ ሠራተኞችንም እየቀጠሩ እንደሚሄዱ ከባለሀብቶች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል።

በዚህ ሥራ ላይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን በኩል ክትትል እያደረግን ነው። አሁንም ግን የፋይናንስ በተለይም የውጭ ምንዛሪ ችግር ያለባቸው አሉ፤ እነሱም እንደ ሀገር በጋራ በተቋቋመ ኮሚቴና በተለይም ከመልሶ ግንባታ መርሃግበሩ ጋር ተያይዞ መታየት ያለባቸው ነገሮች እየታዩ የጋራ መፍትሔ የሚፈለግላቸው ይሆናል።

ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ በጣም ተስፋ ሰጪ ሊባል ሚችል ነገር ነው ያለው። በምናዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ወይም ሁነቶች መጥተው ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ፤ የገበያ ትሥሥር እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ በውጪ ያሉትም ጭምር እየተደገፉ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተለይም የኢንጂነሪንግ ፓርት መሣሪያ በማምረት በኩል አሁን በትግራይ ክልል ላይ ያሉ ኢንተርፕራይዞች ጥሩ አቅም ስላላቸው ከመሃል ገበያ ጋር እንዲተሳሰሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህም በቀጣይ እየተጠናከረ እንዲሄድ ይደረጋል።

ዋናው ነገር ለኢንዱስትሪ ሁልጊዜም ሰላም ያስፈልጋል። ዛሬም ነገም ከነገወዲያም በየትኛውም አካባቢ ሰላም እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። የተመረተ ምርት ገዢ ካላገኘ ፣ ጥሬ እቃ ካልተገኘ፣ ፋይናንስና ጉልበት በነጻነት ካልተንቀሳቀሰ ኢንዱስትሪዎች ለብቻቸው ሊያድጉ የሚችሉበት እድል አይኖርም፤ እናም በሁሉም አካባቢዎች ሰላም እጅግ በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ ነው።

ይህ ከሆነ እንደ ሀገር አሁን ያለው የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ተስፋ የሚሰጥና በተለይም የጀማመርናቸው ነገሮች የበለጠ እየተከናወኑ ሲሄዱ በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚቻልበት ሁኔታ ይኖራል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ።

ጥያቄ፡- አዲሱ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ምን ተስፋ ይዞ መጥቷል?

አቶ መላኩ፡– አዲሱ ፖሊሲ ብዙ ነገሮችን ይዟል። ትልቅ ተስፋ አለው። አንደኛው ተስፋው የሀገር ውስጥ አምራቾች ልዩ ትኩረት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው። ሁለተኛው ኢንዱስትሪ ከዚህ በፊት በጣም በተበተነ ባልተጠና መንገድ ሲሄድበት የነበረውን በክላስተር የማልማትና በጣም ሪሶርስን በሚቆጥብ መንገድ በጣም ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በሚያደርግ መንገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። ሶስተኛ ተወዳሪነትን እና እንደሀገር ያለንን የመወዳደሪያ አቅሞች ለይቶ በነሱ ላይ የሚሠራ ስለሆነ በተለይ የመወዳደር አቅማችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ቀደም ሲል ያልታየ ለኤክስፖርት ብቻ ሲደረግ የነበረውን ድጋፍ አሁን ገቢ ምርትን በመተካት በኩል መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች በፖሊሲ ያመላከተ ስለሆነ ገቢ ምርትን በመተካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ ይሄ ባጠቃላይ በሴክተሩ ውስጥ አዲስ እድል የሚፈጥር ነው። ተጨማሪ የሥራ እድል ለመፍጠር ተጨማሪ ገበያ በመፍጠር አዳዲስ ባለሀብቶችን ከሀገር ውስጥም ለማሳደግ ፤ ከውጭ የሚመጡትን በማስገባት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ።

እና አዲሱን ፖሊሲ በዝርዝር ከሚዲያ ሰዎቻችን ጋር በቀጣይ የምንነጋገርበትና ግንዛቤ የምንፈጥርበት ነው የሚሆነው። ነገር ግን እንደማእቀፍ አዲሱ የኢንዱስትሪ በስሩ እና በውስጥ ብዙ ነገሮችን የያዘና ፤ ከፋይናንስ ለምሳሌ ፋይናንስ ማኑፋክቸሪንግ እንዱስትሪው ለራሱ ራሱን የቻለ ባንክ ሊኖረው ይገባል የሚለውን መፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል።

ምቹ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ መኖር አለበት። ሥነ ምህዳሩ ጥሩ ከሆነ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ደግሞ የተመቸ ሁኔታ ይኖረዋል። የሚል ሪኮመንድ የሚያደርግ ስለሆነ እና በግብይት ትስስር በኩል ያሉ ችግሮች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው አቅጣጫ የሚጠቁም ስለሆነ ይሄ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ በዚህ መንገድ ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉ በዘርፉ በቀጣይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። በኢኮኖሚ ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ሊያበረክት ይገባል ተብሎ የሚታሰበው የሰው ሃይል ለመፍጠር ፤ የጂዲፒ ድርሻውን በማሳደግ ትልቅ ሚና ይጫወታል የሚል አስተያየት ነው ያለኝ።

ጥያቄ፡- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አቶ መላኩ አለበል በዘርፉ ላይ ባሉ ጉዳዮች ላይ ላደረግነው ቃለመጠይቅ ላደረጉልን ትብብር ከልብ እናመሰግናለን።

አቶ መላኩ፡- እኔም እጅግ በጣም አመሰግናለሁ::

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You