የግብጽ አካሄድ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ጠጅ የመጥመቅ ዓይነት ነው!

 የመላው ኢትዮጵያውያንን የዘመናት የቁጭት እንጉርጉሮ የሻረ፤ የዘመናት መሻትና ምኞታቸውን እውን ያደረገ፤ የዘመናት ተስፋና ቁዘማ የተፈራረቀበት መብሰክሰካቸውን በእንችላለን ድርጊት አስመልክቶ በፌሽታ በአንድ አውድ ለደስታ ብስራት ያሰባሰበ፤ በጥቅሉም ‘ዳግማዊ ዓድዋ’ የሚል ተቀጽላ ተሰጥቶት የኢትዮጵያውያንን የማድረግ አቅም ለዓለም ገልጦ ሌላ የብሔራዊ ትርክት ዓውድን የፈጠረ ነው፤ የዓባይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ፡፡

የዓባይ ግድብ፣ የኢትዮጵያውያንን ሕልምን ወደ ተጨባጭ እውነት የመቀየር አቅምን ያሳየ፤ ኢትዮጵያውያን የጋራ ፕሮጀክታቸው ሆኖ የጋራ ትርክትን የፈጠሩበት አውድ ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፤ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ለራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ሲሉ ሌሎችን የመጉዳት አንዳችም ፍላጎት የሌላቸው፤ ነገር ግን ለጋራ ጥቅምና ብልጽግና (በራስ መልማት እና መበልጸግ ውስጥ ሌሎች አብረው እንዲለሙና እንዲበለጽጉ በማድረግ ውስጥ የሚገለጽ) አካሄድን የሚከተሉ መሆናቸውን ዓለም እንዲገነዘብ ያደረጉበት የአስተዋይነታቸው ማንጸሪያ ፕሮጀክት ነው፡፡

ዓባይ ግድብ፣ ለኢትዮጵያ ከድህነትና ኋላቀርነት መላቀቂያ ነው፤ ለኢትዮጵያውያንም ከጨለመው መንገዳቸው ወጥተው ብርሃንን መመልከቻቸው፤ በብርሃናማው መንገዳቸውም ሕልውናቸውን ማረጋገጫቸው እንጂ፡፡ ዓባይ ግድብ፣ ለኢትዮጵያ የቅንጦት አይደለም፤ ይልቁንም ለመልማት፣ ዜጎቿን ለመመገብ፣ ዜጎቿን ለማስተማር፣ ዜጎቿን አክሞ ለማዳን፣ ዜጎቿን ከቴክኖሎጂም፣ ከኢንዱስትሪም፣… የማስተዋወቅና የማቆራኘት ከፍ ያለ የብልጽግናዋ መሻት መፈጸሚያ እውነት ነው፡፡

ይሄ የሕልውናዋ፣ የዜጎቿም ሰው የመሆን ልዕልና መከሰቻ ፕሮጀክት ታዲያ፤ ኢትዮጵያ ገና ከጅምሩ አንድ ብላ ስትተገብረው፤ “የውሃው አመንጪ እኔ፣ የምገነባውም በራሴ መሬት፣ ሀብትና ጉልበት ነው” ብላ በሯን ዘግታ የተገበረችው አልነበረም፡፡ ይልቁንም ምንም እንኳን የውሃው አመንጪ ብትሆንም፤ ምንም እንኳን በራሷ ሀብትና ጉልበት እንዲሁም በሯሷ ግዛት የምትገነባው ቢሆንም፤ ውሃው ድንበር ተሻጋሪ ነውና ሌሎች የውሃው ተጋሪ ሀገራትና ሕዝቦችን ስለ ሁኔታው ለማስረዳት ጥራለች፡፡

እስከዛሬም ለውይይትና ድርድር በሯን ክፍት አድርጋ የዘለቀችው ኢትዮጵያ፤ በተለይ በግብጽና በሱዳን በኩል ሲነሱ የነበሩ “የግድቡ ይጎዳናል” ስጋት ለማቃለል፣ ተደጋጋሚ ምክክር አድርጋለች፡፡ ገለልተኛ ዓለምአቀፍ የባለሙያዎች የጥናት ቡድን ተቋቁሞም ስለ ተጽዕኖው እንዲያጠናና ሪፖርት እንዲያቀርብ በማድረግ፤ ግድቡ የኢትዮጵያ የልማት ዋስትና፤ ለተፋሰሱ ሀገራትም አብሮ የማደግና የመበልጸግ አቅም መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ ቀድሞውኑ ግብጽ አብሮ የመልማት ሳይሆን ለብቻ የመበልጸግና ሌሎችን የበዪ ተመልካች የማድረግ እሳቤዋን ለማጽናት በብዙ ጥራለች፡፡ ይሄንኑም በድርድሩ ሂደት በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን፤ አንድ ጊዜ የቅኝ ግዛት ውሎችን በመጥቀስ፤ ሌላ ጊዜ የግድቡን ጎጂነት በመተረክ፤ ሲያሻትም የውሃ አያያዝና አለቃቀቅ ላይ ሚና ይኑረኝ (ግድቡን የማስተዳደር ሥራ ውስጥ እጄን ካላስገባው እንደማለት ነው) እስከማለት የዘለቀ ድርድሩን የማደናቀፍ ተግባርን ስትፈጽም ቆይታለች፡፡

ይሄ ደግሞ ለግብጻውያን ጥቅምና ፍላጎት የመቆም፤ ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ልማትና ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ የመገዛት ፍላጎት እንደሌላት በግልጽ ያረጋገጠ ሆኗል፡፡ ይሄው አቋምና ፍላጎቷ ታዲያ ዛሬ ግድቡ በሦስት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት በጀመረበት፤ አጠቃላይ ግንባታውም 93 በመቶ በተሻገረበት፤ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ፈጽሞ ሊጎዳ እንደማይችል፤ ይልቁንም በብዙ የሚጠቅማቸውና ከጥፋት የሚታደጋቸው ስለመሆኑ በተከታታይ በተደረጉ የግድቡ የውሃ ሙሌት ተግባራት ማረጋገጥ በተቻለበት ወቅትም፣ ወደኋላ ተመልሳ የቅኝ ግዛት ውሎችን ለመደራደሪያ ሃሳብነት ይዛ ቀርባለች፡፡

እነዚህጋ ግብጽ ያልተረዳችው፣ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውል የማይገዛት ነጻ ሀገር መሆኗን ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትናንት በራሷ አቅም ወራሪዎችን መክታ የቅኝ ገዢዎች በትር በባህልና ኢኮኖሚዋ ላይ ያላረፈ፤ ዛሬም ድረስ የሚንጣት የባህልም ሆነ የሥነልቡና ስንጥራት የሌለባት ነጻ ሀገር ናት፡፡ የዚህ ማሳያው ደግሞ የዓባይ ግድብ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዓባይ ግድብ ዳግማዊ ዓድዋ እየተባለ በኢትዮጵያውያን የመቻልና የጋራ ትርክት አውድ ሆኖ የሚገለጸው፡፡ ታዲያ ግብጽ እንዴት በዳግማዊ ዓድዋ (ዓባይ ግድብ) ጉዳይ የቅኝ ግዛት ውሎችን ይዛ ከኢትዮጵያ ጎን ተቀምጣ ልትደራደር ትችላለች?

ይሄንን እውነታ ጠንቅቃ የምትገነዘበው ግብጽ፣ ኢትዮጵያ ፈጽሞ የማትወከልባቸውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎችን አንጠልጥላ ወደ ድርድር ለምን መቅረብ ፈለገች፤ የሚለው ዐቢይ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ የዚህ መልሱ ታዲያ፣ ግብጽ በዓባይ ግድብ ዙሪያ በፍትሃዊ አቋም ተነጋግራና ተደራድራ ለውጥ እንደማታመጣ ስለምታውቅ ሂደቱን ለማደናቀፍ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ግድቡ ግብጽ እንደምትለው ግድቡ የሚጎዳት ሳይሆን፤ በተቃራኒው የተፋሰሱን ሀገራት ሕብረትና አብሮ የመልማትና የመጠቀም መንገድ የሚያጸና ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ሲታይ የግብጽ መንገድ ድርድሩን የማደናቀፍ፤ የግብጽን ሕዝብ የውስጥ ጥያቄ መስመር ማስቀየር እና የውጭ ጠላትነት ስዕልና ስጋት የመፍጠር፤ በዓባይ ጉዳይ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የተዛባ ዕይታ እንዲኖረውና በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር የመፈለግ ከፍ ያለ ምኞት፤ በጥቅሉ የጋራ ብልጽግናን አጥብቆ የመጥላት ውጤት ነው፡፡ እናም ዛሬ ላይ ከመርህ ያፈነገጠ የቅኝ ግዛት ዘመን ውሎች ላይ የተንጠለጠለው የግብጽ መንገድ፣ ውጤቱ በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ ከመጥመቅ አይነት እሳቤ ተለይቶ የሚታይ አይሆንም!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You