መስማት የተሳናቸው ወገኖች ማንኛውንም ነገር መሥራት እንደሚችሉ ለማሳየት ሥራውን የጀመረው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ነው:: መስማት የተሳናቸው የወጣቶች የውዝዋዜ እና የቴአትር ክበብ የሚል ስያሜ ይዞ የወረዳዎችን ደጃፍ መርገጥ ጀመረ:: ‹‹መሥራት እንችላለን፤ አሠሩን!›› ብሎ ራሱን በሚገባ አስተዋወቀ:: በከተማ ደረጃ ብቻ ተወስኖ የተለያዩ መድረኮች ላይ በመገኘት የውዝዋዜ ሥራዎቹን ማቅረብም ቀጠለ:: በ2013 ዓ.ም ፍቃድ አግኝቶ ሥራውን ማስፋፋት ጀመረ:: እንሆ አሁን ሶስት ዓመት ተሻግሯል- ኢትዮ ሀበሻ መስማት የተሳናቸው ማህበር::
መስማት የተሳናቸው ከማኅበረሰቡ ጋር በቅንጅት የመሥራቱ ነገር አናሳ ሲሆንና በምን እንግባባለን? የሚል ስጋት ሲመጣ ማኅበሩ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት መስማት የተሳናቸው ልጆች ላሏቸውና ለሌሎች ወላጆች ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል::፡
ሲሳይ ተሰማ መስማት የተሳነው ወጣት ነው:: የኢትዮ ሀበሻ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ሥራ አስኪያጅ እና የውዝዋዜ አሰልጣኝም ነው:: ሀይማኖት ተስፋዬ ደግሞ የማኅበሩ ጸሐፊ፣ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ፣ ተወዛዋዥ እንዲሁም ሙዚቃዎችን ወደ ምልክት ቋንቋ እየቀየረች መልዕክቶች ለሌሎች እንዲደርሱ በበጎ ፈቃድ ትሠራለች:: ቤተሰቦቿም መስማት የተሳናቸው ናቸው:: ይህንንኑ አምድ ለማዘጋጀትም በእኛና በሲሳይ መካከል ያሉትን ጥያቄ እና መልሶችን በምልክት ቋንቋ እንዲተረጎም አድርጋለች::
ሲሳይ እንደሚናገረው፣ በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ሰዎች መዝናኛ ያስፈልጋቸዋል:: መዝናኛ ሲባል ደግሞ የቴሌቪዝን ፕሮግራም፣ ፊልም፣ የልጆች ፕሮግራም፣ ሙዚቃዎችና ሌሎችንም ያካትታል:: ታዲያ እነዚህን ተመልክተው እንዳይዝናኑ እና ቁምነገር ያላቸውን መልዕክቶች እንዳያገኙ ብዙዎቹ መዝናኛዎች በምልክት ቋንቋ የታገዙ አይደሉም::
ይህንን የሚሠራ የለምና በኪነ ጥበብ አማካኝነት የሚተላለፉ መልዕክቶች፣ የሙዚቃ መልዕክትና ሌሎችን መረጃዎች መስማት ለተሳነው ማኅበረሰብ እንዲዳረስ ዓላማ ያደረገው ማኅበሩ፤ የውዝዋዜ ሥራዎችን በተለያዩ መድረኮች ላይ ቀርቦ ታዳሚዎችን ከማዝናናት በሻገር መዝናኛዎችን አዘጋጅቶ ማቅረብ እንደሚቻል በተግባር እያሳየ ይገኛል::
በርግጥ መስማት የተሳናቸው መስማት አይችሉምና ሙዚቃውን እንዴት ሰምተውት ይደንሳሉ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል:: መናበብ ካለ ብዙ ነገር ማድረግ ይቻላል:: ሙዚቃዎችን ወደ ምልክት ቋንቋ በመቀየር የማይቻል የሚመስልን ነገር እንዴት መሥራት እንደሚቻል እነሲሳይ በተግባር አሳይተዋል::
ሲሳይ እንደሚገልጸው፣ ለሕፃናት የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የምልክት ቋንቋ ነው:: ብዙኃኑ የሕፃናት የቴሌቪዥን ዝግጅቶችና ፊልሞች በምልክት ቋንቋ የታገዙ አይደሉም:: በምልክት ቋንቋ የሚዘጋጁት ደግሞ ለልጆች የሚሆኑ አይደሉም:: ‹‹በቋንቋቸው ቢሠራላቸው ግን ዓይናቸው ይሰማል ወይም ያዳምጣል:: እጃቸው ደግሞ ይናገራል::›› ስለዚህ በዚህ ላይ በሚገባ ትልቅ ሥራ መሥራት ይገባል:: ማኀበረሰቡ መስማት የተሳናቸው መሥራት አይችሉም የሚል የተሳሳተውን አመለካከት መቅረፍ ይቻላል:: ከውዝዋዜው በተጨማሪ የግንዛቤ ሥራዎችን ማኅበሩ መሥራት ይቀጥላል::
ከዚህ ቀደም ማኅበሩ 24 አባላት የነበሩት ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን አስር ብቻ ቀርተዋል:: ለዚህም ከሩቅ ቦታ ለሚመጡ አባላት የትራንስፖርት የመክፈል አቅም አለመኖርና አንዳንድ ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ለመላክ ፈቃደኛ አለመሆናቸው በምክያትነት ይጠቀሳል:: ማኅበሩ በሀዋሳ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በመንቀሳቀስ ሥራውን ያቀርባል:: መስማት የተሳናቸው ምንም መሥራት እንደሚችሉ ያሳያል:: በእግረ መንገዱ በየክልሉ ብዙ የምልክት ቋንቋ የማይችሉ ሞራላቸውን በመገንዘብ ሥራቸውን አጠናክረው ለመሥራት አቅድ አለው::
ኢትዮ ሀበሻ በተለያዩ መድረኮች ላይ ሙዚቃዎችን በምልክት ቋንቋ በመቀየር መስማት ለተሳናቸው ድራማ እና ቴአትር ይሠራል:: በቀጣይም ከፊልም ሠሪዎች በጋራ ለመሥራት ጅምር ሥራዎች መኖራቸውን ሲሳይ ይጠቁማል:: በተለያየ ቦታ መስማት የተሳናቸው ልጆች መኖራቸውን ከግንዛቤ በማስገባት፤ እንዲሁም መስማት የተሳናቸው ወጣቶች መድረስ የሚፈልጉት ቦታ ላይ እንዲደርሱ ለማስቻል ወላጆች፣ መንግሥት እና ሌሎችም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው ያሳስባል::
መስማት የተሳናቸው የነገ የሀገር ተረካቢ ዜጋ ናቸው የሚለው ሲሳይ፤ ወላጆችም መስማት የተሳነው ልጅ ካላቸው ከመደበቅ ይልቅ አምነው መቀበል እና ለልጄ ምን ላድርግ? የምልክት ቋንቋ ልማር ? የሚሉትንና ሌሎች ማሟላት የሚገባቸውን ነገር በማሰብ ቢሠሩ ችግሮችን የበለጠ ለማቅለል እንደሚረዳ ይናገራል:: በአብዛኛው ቦታዎች ላይ የምልክት ቋንቋ አለመኖር ብዙ ችግሮች እንዲፈጠሩም ይጠቅሳል:: የትራንስፖርት አካባቢዎች ላይ የምልክት ቋንቋ ባለመኖሩ ወዴት እንደሚሄዱ የሚያመላክት ነገር ባለመኖሩ ሲቸገሩ እንደሚታዩም ይገልጻል:: በሕክምናና በሌሎች ተቋማትም ችግሩ ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ የምልክት ቋንቋ የግድ መስፋፋት እንዳለበት ያስረዳል::
ማኅበሩ የኪነጥበብ ሥራዎችን በመሥራት የግንዛቤ ሥራ እየሠራ የሚገኝ ሲሆን ፤ ድጋፎችን ቢያገኝ የበለጠ እንደሚሠራ ያምናል:: መስማት የተሳናቸው እንደሌላው ማኅበረሰብ የሚዝናኑበት ቦታ፣ቴአርትር ቤት፣ሲኒማ እና መሰል የመዝናኛ ቦታዎች ካልተዘጋጁላቸው ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ፣ ወደ ሱስ ሕይወት እንዲገቡ እና ወዳልተፈለጉ ድርጊቶች ሊያመሩ ይችላሉ:: ስለዚህም ወደ መጥፎ ነገር እንዳይሄዱ አመቺ የመዝናኛ አማራጮችን በማሟላት ማበረታታት ይገባል::
ከዚህ ቀደም ‹‹ዓለም አቀፍ መስማት የተሳናቸው ቀን›› በኬንያ ሀገር ተከብሮ ውዝዋዜ እንዲያቀርቡ ለማኅበሩ ግብዣ ቢደረግለትም ስፖንሰር ባለማግኘታቸው ምክንያት ሥራቸውን ማቅረብ አልቻሉም:: ከዚህ በኋላም ቢሆን ሌሎች ግብዣዎች እንደሚኖሩ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ማንኛውም አካል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ማኅበሩ ይጠይቃል::
ማኅበሩ አሁን እየሠራ ያለውን ሥራ ከማስፋፋት በተጨማሪ በቀጣይም መስማት የተሳናቸው የሚዝናኑበት ሲኒማ እና መሰል የመዝናኛ ስፍራዎችን ለመክፈት ውጥን ያለው በመሆኑ፤ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እስካሁን ድረስ ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናውን ያቀርባል:: ሌሎችም ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ይጠይቃል::
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም