“15 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሰብዓዊ ርዳታ እየተከፋፈለ ነው ”ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰቱ ፈተናዎችና መፈናቀሎች እየበረከቱ መምጣታቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኗል:: ከዚህ የተነሳ ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ከቀዬአቸው የሚፋናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሲቸገሩ ይስተዋላሉ::

መንግሥትም ለችግራቸው የሚሆን ጊዜያዊ መፍትሔ ለመስጠት የተቻለውን ሲያደርግ ይታያል:: መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጓዳኝ ደግሞ ሕዝቡ እርስ በእርስ ሲረዳዳ ማየትም የተለመደ ጉዳይ ነው:: የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 70 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማስተባበርና በማቀናጀት በሀገሪቱ የሚከሰቱ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋን መከላከል፣ መቀነስ፣ ዝግጁነት፣ ምላሽ መስጠት፣ መልሶ ማቋቋምና ግንባታ ለመተግበር የተመሠረተ ነውና ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ያከናወናቸው ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ከኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል:: መልካም ንባብ::

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያከናወናቸው አንኳር ተግባራት ምንድን ናቸው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያቀዳቸው እቅዶች ከ2016 እስከ 2018 የመካከለኛ ዘመን እቅድ ሲሆን፣ በአመዛኙ በ2016 በጀት ዓመት ለሚከናወኑ ቁልፍና አብይ ተግባራት የዝግጅት ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰድ ነው::

የመጀመሪያው ተቋማዊ ለውጥንና አቅም ግንባታን በሚመለከት ሲሆን፣ ከ10 ዓመታት በላይ የቆየውን የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲን የመከለስ ሥራ ነው:: ዘመኑ የሚጠይቀውን ያልተማከለ፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ በቂና ብቃት ባለው የሰው ኃይል የሚታገዝ ሚዛኑን የጠበቀ የአደጋ ስጋት አመራር እውን ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅርቧል::

ፖሊሲውን ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችል ሥራም ተሠርቷል:: በተለይም ሠብዓዊ ድጋፍን በመንግሥት መሪነት በሀገር-በቀል አቅም ምላሽ የሚሰጥበትን እና ለቅጽበታዊ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍና የእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች አገልግሎት ለማቋቋም የሚያስችል ደንብ ተዘጋጅቷል:: ይህ ደንብም ለፍትሕ ሚኒስቴር ቀርቧል:: በተቋሙ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩልም የመጀመሪያ ግብረ-መልስ በመቅረቡ የማሟላት ሥራ እየተሠራ ይገኛል::

በሌላ በኩል የተቋማችንን መዋቅራዊ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት እንዲጠና በማድረግና በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከጸደቀ በኋላ የሰው ኃይል ድልድል በማድረግ ላይ እንገኛለን::

ሌላው በተቋማዊ ለውጥና አቅም ግንባታ ዙሪያ የተከናወነው በመልቲ ሃዛርድ – ኢምፓክት ቤዝድ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ (Multi – Hazard, Impact based Early Warning Early Action Road Map) ፍኖተ ካርታ ላይ በመመስረት ሰፋፊ ዓለም-አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጥና ሀብትን የማፈላለግ ሥራ ተሠርቷል:: በሚቀጥሉት ወራት ወደ ተጨባጭ ተግባራት ለመሸጋገር የሚያስችል ምቹ ሁኔታም ተፈጥሯል::

በዚሁ ሩብ ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአራት ቦታዎች ተበታትኖ የነበረውንና በዓመት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ለኪራይ የሚከፈለውን ወጪ በማዳን በአንድ ቢሮ የማሰባሰብ ሥራ ተሠርቷል:: ይህም በምልልስ ይጠፋ የነበረውን ጊዜና ሀብት ከማዳኑም በላይ ቀልጣፋና ውጤታማ የአመራር ሥርዓትን ለመተግበር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል::

ይህንን ምቹ የመሥሪያ ቦታ የተሳለጠ ለማድረግ ባለ ስምንት ወለል ሕንፃ በኮሚሽኑ ቅጥር ጊቢ እያስገነባን ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቃል ተብሎ ይጠበቃል::

ከተቋማዊ ለውጥና አቅም ግንባታ አኳያ ሌላው በሩብ ዓመቱ በትኩረት የተሠራው ጉዳይ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት ላልተገባ ዓላማ እንዳይውል በአመለካከት ዙሪያ ከተሰሩ ስራዎች በተጨማሪ የሠብዓዊ ድጋፍ ተጠቃሚዎች የልየታ፣ የምዝገባ እና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚያገኙትን የመወሰን አሠራርን መከለስና ከክልሎችና ከአጋር አካላት ጋር መግባባትን መፍጠር ነበር::

በዚሁም የሠብዓዊ ድጋፍ ተረጂ የልየታ ሥራ ተገቢ ካልሆኑ ጣልቃ ገብነት እንዲጠበቅ ተደርጓል:: የሰብዓዊ ድጋፍ ሀብትን ላልተገባ ዓላማ የሚያውሉ በመዋቅርና ከመዋቅር ውጭ ያሉ አካላት ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲወሰድም ሆኗል:: የዛሬ ተረጂ ቋሚ ተጧሪ እንዳይሆንና የበኩሉን የምርት ድርሻ እንዲያበረክት ድጋፍ ማድረግ፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ቁሳቁስ በገበያ፣ በሱቆችና በእህል ወፍጮ-ቤቶች ከተገኘ የሚያስጠይቅ መሆኑ በአሠራሩ ላይ እንዲካተትም ተደርጓል::

አዲስ ዘመን፡- የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎችስ ምን ይመስላሉ?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- የአደጋ ስጋትን ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎች ዘንድ ሲመጣ ደግሞ የሀገራችን የአደጋ ስጋት አመራር በአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት የሚመራ ነው:: ሰብሳቢው የተከበሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው:: ይህ ምክር ቤት መደበኛና ወቅታዊ ስብሰባዎችን በሩብ ዓመት ሁለት ጊዜ ያካሄደ ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሾችንና ዘላቂ መፍትሔዎችን በማስተባበር ጉልህ ሚና ተጫውቷል::

የአደጋ ስጋትን ከመቀነስ አኳያ ዋናው መሠረት የወረዳ አደጋ ስጋት ፕሮፋይል ሲሆን፣ በሩብ ዓመቱ የተከናወኑትን ጨምሮ 522 ወረዳዎችን መሸፈን ተችሏል:: የአደጋ ስጋቶች አደጋ ፈጥረው ጉዳት እንዳያደርሱ የመከላከል ሥራ የሚፈጸመው የአደጋ ስጋት ፕሮፋይልን መሠረት በማድረግ የመከላከል ሥራ ሲሠራ ነው:: ይህም ከቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች ጋር ተዳምሮ ሴክተሮች የአደጋ ስጋት ቅነሳን በእቅዶቻቸው በማካተት (mainstreaming) እንዲተገብሩ መሠረት የሚጥል ነው::

በሌላ በኩል የወረዳ አደጋ ስጋት ፕሮፋይል መሠረት ያደረጉ ማሳያ ፕሮጀክቶች በአጋር ተቋማት ድጋፍ የተከናወኑ ሲሆን፣ እነዚህም የእንስሳት ርባታ፤ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የመስኖ እርሻና መሰል ተግባራትን የሚያካትት ነው::

በዚሁም በአፋር፣ በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በሲዳማና በአማራ ክልሎች በአውሮፓ ህብረት፤ በስፓንሽ ድጋፍና በዩ.ኤን.ዲ.ፒ (በUNDP) የተደገፉ ፕሮጀክቶች የዚህ ሩብ አመትን አፈፃፀም ጨምሮ ከ300 ሺ በላይ ዜጎቻችን ተጠቃሚ አድርገዋል::

የአደጋዎች ምላሽና ማገገምን በተመለከተ እቅድ በተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎቻችንን የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ የሚፈልጉትን በመለየት ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስን የሚመለከት ነው:: ከዚህ አኳያ ከ2015 ዓ.ም ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ታህሳስ አጋማሽ 2016 ዓ.ም ድረስ የአጋር ድርጅቶች ድጋፍ በመቋረጡ መንግሥት በራሱ አቅም የአጋር ድርጅቶች ድርሻንም ጭምር በማካተት ምላሽ ሰጥቷል::

የድርቅ አደጋን በሚመለከት በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች፣ በትግራይ ሶስት ዞኖች እና በአፋር ክልል ሶስት ዞኖች እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም የተለያዩ ኪስ ቦታዎችን ጨምሮ ሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ወገኖች ጉዳት ደርሶባቸዋል::

በሌላ በኩል የጎርፍ አደጋ በሶማሌ ክልል በተለይም ሸበሌ፣ አፍዴርና ሊበን ዞኖች፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም ደቡብ ኦሞ ዞን እና ዳሰነች ወረዳ፤ በኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌና ምሥራቅ ባሌ፤ በአማራ ምዕራብ ጎጃም እና ማዕከላዊ ጎንደር፤ በጋምቤላ አኞሐ፣ ኑዌር፣ ኢታንግ ልዩ ወረዳና ጋምቤላ ከተማ፤ በአፋርና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን (1,500,000) በላይ ዜጎች በተለያየ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል:: ከእነዚህ ውስጥ ከ630 ሺ (630,000) ሕዝብ በላይ ተፈናቅሏል::

በዚህ ጐርፍ ምክንያት 125 ሺ (125,000) ሄክታር የእርሻ መሬት እና 123 ሺ (123,000) የግጦሽ መሬት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል:: እስከ 21 ሺ 500 የሚጠጋ የእንስሳት ሞትን አስከትሏል:: ጐርፉ የወንዝ ፈለጐችን በመጣስ ያደረሰው ጉዳት መንገዶች፣ አገልግሎት መስጫ የትምህርት፣ የጤና እና የውሃ ተቋማት ወድመዋል:: የበሽታ ወረርሽኞችም ያገረሹበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር::

የጐርፍን ሁኔታ ለመታደግ በየክልሉ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን እና በውሃ በተከበቡ ደሴቶች ከመከላከያ እና ከባሕር ኃይል በተገኙ ድጋፎች ሕይወት-አድን የሄሊኮፕተርና የጀልባ ኦፕሬሽን በማድረግ ስንቅን የማቀበልና ከአደጋው የመታደግ ሥራዎች ከክልሎች ጋር በመሆን ተከናውኗል:: በተጨማሪም ሰፋፊ የክትባት መርሃ ግብሮችን በማካሄድ ወረርሽኞችን የመቆጣጠር፤ የመጠለያና የውሃ ማከሚያ መድኃኒቶችን በማቅረብ የጉዳት መጠንን የመቀነስ ሰፊ ርብርብ ተደርጓል::

በመንግሥት በኩል እየተደረገ ከሚገኘው ርብርብ በተጨማሪ ለጐርፍ አደጋ ምላሽ የሚሆን ስምንት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በUN-OCHA Central Emergency Response Fund (CERF) በኩል የተገኘ ሲሆን፣ በአጋር ድርጅቶችም በኩል ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል:: በተመሳሳይ በድርቅ ለተጎዱ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች 10 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተመደበ ሲሆን፣ ወረርሽኞችንም ለመመከት የሚያስችል አምስት ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ በአጋር አካላት በኩል እየተፈጸመ ይገኛል::

በሦስት ዙሮች የተከናወኑ ምግብ፣ ምግብ-ነክ ያልሆኑ የገንዘብ ስርጭቶች የተከናወኑና በመሰራጨት ሂደት ላይ የሚገኙም አሉ:: እነዚህም በድርቅና በጐርፍ ለተጐዱ ወገኖች ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተከናወነ ተግባር ተጠቃሽ ነው:: በአንደኛ ዙር በሐምሌ እና ነሐሴ ወር የተከናወነው ተግባር 249 ሺ ኩንታል እና አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በድምሩ ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለሰባት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ተረጂዎች ነው::

በሁለተኛው ዙር መስከረምና ጥቅምት የተከናወነው ደግሞ 613 ሺ ኩንታል ለሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ተረጂዎች በአራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ነው:: በሶስተኛው ዙር በመንግሥት 487 ሺ ኩንታልና በአጋር አካላት 376 ሺ ኩንታል እንዲሁም 560 ሚሊዮን ብር በድምሩ ለስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተረጂ በመንግሥት አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብርና በአጋር አካላት አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን በድምሩ ስምንት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የሚያወጣ ድጋፍ በኅዳርና ታህሳስ ወር እንዲደርስ እየተደረገ ይገኛል::

በነዚህ ሦስት ዙሮች በኮሚሽኑ አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ አርባ ዘጠኝ ሺ (1,349,000) ኩንታል በ11 ቢሊዮን ብር ወጪ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው:: ይህም የመንግሥት ምላሽ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው::

በሦስቱም ዙር በመንግሥትና በአጋር አካላት የተላከውን ጨምሮ አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ ሃያ አምስት ሺ (1,725,000) ኩንታል እየተሠራጨ ይገኛል:: ይህ በብር ሲገመት በአንድ ላይ የአጋር አካላትን ጨምሮ 15 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለተጎጂው ማህበረሰብ እየተዳረሰ ይገኛል::

አዲስ ዘመን፡- በዙሩ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና የተቀመጠ መፍትሔ ምንድን ነው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡– በዚህ ሩብ ዓመት ካጋጠሙን ዋና ዋና ተግዳሮቶች አንዱ የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተላቸው ድርቅና ጐርፍ ባለፈው ዓመት ከነበረበት የድርቅ አደጋ ሲያገግሙና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ደግሞ የግጭት ጫናዎች ለማቅለል በሚሠራበት ወቅት መሆኑ ነው:: ሌላው እስከዛሬ መሻገር ያልተቻለው በአደጋ ስጋት አመራር ሚዛናዊ የሆነ የአደጋ ስጋት ቅነሳ፣ ምላሽና የማገገም ሥራዎች በተገቢው እይታ በመከናወን ዙሪያ የሚታየው የአጋሮችም ይሁን በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት መዋቅር ትኩረት ማሻሻልን የሚሻ መሆኑ ነው:: የአደጋ ስጋቶችን በመከላከል ላይ ያተኮረ ርብርብ ከዜጋው ጀምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል:: ይህንን የአደጋ ስጋት አመራር ሚዛኑን የጠበቀ የሠብዓዊ ድጋፍ ፍላጐት ሰነድ ላይ በማካተት ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ የተቻለውን ምላሽ እንዲሰጥ በትኩረት ተሠርቷል::

በሌላ በኩል የተረጂነት አስተሳሰብ፤ የተረጂ ቁጥር ማናርና ለአይበገሬነት የሚሆኑ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ይልቅ ቋሚ ተጧሪ የመሆንና የሠብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴን በአቋራጭ ባለሀብትነትና ለዘመድ-አዝማድ መጠቀሚያ ለማድረግ የሚሞከሩ ዝንባሌዎች አሉ:: ተገማች ያልሆኑ የአጋር አካላት የሀብት አቀራረብ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ በፈረንጆች 2023 እንዲቀርብ የተደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጐት መጠን ሶስት ነጥብ 99 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፤ ይህም በመቶኛ ሲሰላ የቀረበው 33 ብቻ ነበር:: በዚሁም አብዛኛውን ሠብዓዊ ድጋፍ መንግሥትና ሕዝብ በራስ አቅም እየተወጣ መሆኑን የሚያመላክት ነው::

በሩብ ዓመቱ ሌላው ያጋጠመው ተግዳሮት በካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም መጓተት ነበር:: ከነዚህ ከምግብ ማከማቻ መጋዘኖች ግንባታ የተያያዙ ከወሰን ማስከበርና ከዋጋ መናር ችግሮች ሲሆን፣ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ይገኛል::

የአጋር አካላት የሠብዓዊ ድጋፍ ማቋረጥና ከፍተኛ ሀብት መንግሥት እንዲመድብ መደረጉም የሠብዓዊ ድጋፍ በራስ አቅም ለመሸፈን ሰፋፊ የምክክር ሥራ እየተሠሩ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው::

አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሚያስፈልግ የምርት መጠን በበቂ ሁኔታ አላት?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡– በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶችን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም:: በመሆኑም ከማህበረሰብ ጀምሮ በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በግል በጐ አድራጊዎች ጭምር አቅም ማሰባሰብ የሚጠይቅ ነው:: በመሆኑ የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍን በሚመለከት ምላሽ እየተሰጠ ይገኛል::

በሀገራችን በሰፊው እየተተገበረ የሚገኘው የስንዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት እንቅስቃሴዎች የኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘይቤ ጨምሮ በቂ ምርት እየተመረተ መሆኑ ይታወቃል:: ይሁንና የግብይት ሰንሰለት ቀልጣፋ አለመሆንና የደላላ መረብ የሚፈጥረው መሰናክል የግዥ ዋጋ እንዲያሻቅብ በማድረጉ በተለያዩ በሀገር-ውስጥና በራስ-አቅም አማራጮች ፍላጐታችንን ለመሸፈን እየተረባረብን እንገኛለን::

የሚያስፈልገንን የሠብዓዊ ድጋፍ ፍላጐት በራስ አቅም ለማሟላት የተረጂነት አስተሳሰብ መግራትና ተረጂዎች እንዳይበራከቱ በትጋት መሥራት አንዱ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ ምርት በማምረት የመጠባበቂያና የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላት እየተሠራ ይገኛል::

ይህ እንዳለ ሆኖ መንግሥት በአሁኑ ወቅት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሹ ወገኖችን አቅምና ሁኔታዎች እስከፈቀዱ ድረስ ለመደገፍና አደጋዎች ወደ ባሰ ጉዳት እንዳይሸጋገሩ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ እንወዳለን::

አዲስ ዘመን፡- አጋር አካላት የሠብዓዊ ርዳታ ላለመስጠት መፈለጋቸው ይታወቃል:: ለዚህ ዋናው ምክንያት ምንድነው? በአሁኑ ወቅት ያለው የአጋር አካላት ድጋፍስ የሚገለጸው እንዴት ነው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡– በአሁኑ ወቅት የሚታየው የዓለም-አቀፍ የፖለቲካ አውሎ-ነፋስ ያልተረጋጋና በየጊዜው የሚቀያየር ግለትና ትኩረት የተጫጫነው ነው:: በመሆኑም የሠብዓዊ ርዳታ ከፖለቲካ ፍላጐት ጋር መያያዝ የማይገባው ቢሆንም ነባራዊ ሁኔታው ግን ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡

በዚሁም ምክንያት በለጋሽነታቸው የሚታወቁ አካላት የሠብዓዊ ድጋፍ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስና ተገማች አለመሆን በስፋት ተስተውሏል:: በተለይም የሠብዓዊ ድጋፍ ፍላጐትን በአደጋ ስጋት አይበገሬነት ለማቅለል የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ ማሻሻልን የሚጠይቅ ነው::

በሀገራችን የሚገኙ ለጋሾች የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ከ2015 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ እስከ መጀመሪያዎች የታህሳስ 2016 ዓ.ም ሳምንታት የገቱበት መነሻ ምክንያት ሠብዓዊ ድጋፍ ላልተገባ ዓላማ ውሏል በሚል ነበር:: ሠብዓዊ ድጋፍን ላልተገባ ዓላማ ማዋል በመንግሥታችንም የተወገዘና የሚያስጠይቅ መሆኑ ቢታወቅም ይህንኑ የተጠያቂነት አካሄድና አዲስ አሠራር በመዘርጋት ሂደት ላይ ልዩነቶች ተፈጥረው ነበር:: በአሁኑ ወቅት በጋራ አሠራር ወደ ሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በ20 በመቶ አቅም የተመለሰበት ሁኔታ በጐ ነው፤ በራስ አቅም አመዛኙን ሠብዓዊ ድጋፍ መንግሥትና ሕዝብ እየተሸከመው መሆኑን መገንዘብ ይቻላል:: ይህም በየትኛው የሠብዓዊ ድጋፍ ሁኔታ (Scenario) ሳይቀለበስ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል::

በዚሁ አጋጣሚ ሠብዓዊ ድጋፍን በሚመለከት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች በአጽንኦት መያዝ አለባቸው:: የመጀመሪያው ጉዳይ “ተረጂነት” ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች የሚገባበት እንጂ “መደበኛ ሁኔታ“ አለመሆኑን በመገንዘብ በተቻለ ፍጥነት የተለያዩ የልማት አማራጮችን በመጠቀም ከርዳታ መላቀቅን ይጠይቃል:: ለአደጋ ስጋት የማይበገር ሕዝብና ሀገር የመገንባት ራዕያችንን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም::

ሁለተኛው ጉዳይ የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦቶች ዓላማቸው የተጐዱ የህብረተሰብ ክፍሎቻችንን ለመታደግ በመሆኑ የአቋራጭ ባለሀብትነት ፍላጐቶች፣ የዝምድና እና የትውውቅ መጠቀሚያ ማድረግና የሚገባውን መንፈግና የማይገባውን ማካተት የተወገዘና በሕግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው:: በዚህ ላይ ሁሉም የፍትህ፣ የፀጥታና የደህነነት መዋቅሮቻችን ርብርብ ይጠይቃል::

ሶስተኛው ጉዳይ በየአካባቢው ማህበረሰብ ይሁንታና በተረጂ ልየታው ጥቅም ላይ በዋሉ ሳይንሳዊ መስፈርቶች የሚለዩ ጊዜያዊ ተረጂዎች አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃታቸው እስከፈቀደ ድረስ በወል ልማት ሥራዎች እንዲሳተፉና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ማድረግ ይገባል:: ይህም የነፃ-ስጦታ አመለካከትን በመቅረፍ በኩል ድርሻ የሚኖረው ሲሆን፣ በወል መሬት ላይ ምርትን መፍጠር ከቻሉ የራሳቸውን የሠብዓዊ ድጋፍ ፍላጐት በራስ አቅም የሚሸፍኑበትን ዕድል የሚያሰፋ ይሆናል::

አዲስ ዘመን፡- በተያዘው በጀት ዓመት አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል የሚባሉ ዜጎች ቁጥር ምን ያህል ነው?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የፈጠሩትን የሠብዓዊ ድጋፍ ፍላጐት በዓመት ሁለት ጊዜ በበልግና በመኸር በሚደረግ ሀገር-አቀፍ ዳሰሳ ጥናት የሚለይበት አሠራር ተዘርግቷል:: በተጨማሪም የተፈናቃዮችን ሁኔታ የሚከታተልና በየአካባቢው በቅድመ-ማስጠንቀቂያ መረጃዎች የሚደገፍ አሠራርም በዓመቱና በወቅቱ የሚኖረውን የተረጂ መጠን ለመወሰን ጥቅም ላይ ይውላል::

በዚህ አሠራር መሠረት በ2015 በጀት ዓመት በመኸር ጥናት መሠረት የነበረው የተረጂ ቁጥር 20 ነጥብ አንድ ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ 2015 በጀት ዓመት የበልግ ጥናት ወደ 15 ነጥብ አራት ሚሊዮን ወርዷል:: በሀገራችን የተካሄደውን 2016 የምርት ዘመን የመኸር ዳሰሳ ጥናት መሠረት በማድረግ በፈረንጆቹ 2024 የሚኖረው የተረጂ ቁጥር 10 ነጥብ አራት ሚሊዮን ሲሆን፣ በመጀመሪያዎቹ ወራት/ወቅት (ጥር፣ የካቲት እና መጋቢት) የሚኖረው የተረጂ ቁጥር ስድስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ይሆናል::

ስለዚህ ከፊታችን በሚገኙ ወራት ሠብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ስድስት ነጥብ አራት ሚሊየን በመሆን ከዚሁ ውስጥ በኮሚሽን 30 በመቶ እና በክልሎች 70 በመቶ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሹትን በአካባቢው ማኅበረሰብና በልየታ – መስፈርቱ መሠረት ድጋፍ ይደረጋል::

እነዚህን ዜጎቻችን ከሠብዓዊ ድጋፍ ጐን ለጐን በተፈጥሮም ይሁን በሰው-ሠራሽ ችግሮች የተጋረጠባቸውን ጉዳት ለመቅረፍ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ እና መዋቅራዊ ድጋፍ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል:: የመንግሥትንና የአጋር አካላትን ድጋፍም በተገቢው፣ በተመረጠና ሥነ- ምግባርን በተላበሰ ሁኔታ በመጠቀም “ለወገን ደራሽ ወገን’’ መሆናችንን የማረጋገጥ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል::

አዲስ ዘመን፡- ከለጋሽ አካላት ጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያስችል ጥናት መዘጋጀቱ ተገልጿል:: ይህ ማለት ድጋፋን በራስ አቅም ለማስኬድ መቻል ነውና በምን አኳኋን ተግባራዊ ለማድረግ ይቻላል? ከአጋር አካላት ውጭ በመንግሥት እንቅስቃሴ ብቻ ርዳታን ማድረስ ይቻል ይሆን?

ኮሚሽነር ሽፈራው፡- ሠብዓዊ ድጋፍን በመንግሥትና በአጋር አካላት ትብብር መከናወን ዓለም-አቀፍ የሠብዓዊ ድጋፍ መርሆዎችን የሚከተል በመሆኑ እንደ ጉድለት ላይወሰድ ይችላል:: የሠብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት በአመዛኙ በአጋር አካላት በሚሆንበት ሁኔታ ግን ፈተናዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በግልጽ እያሳዩ መጥተዋል::

ከነዚህም መካከል ዕርዳታው የተጠቃሚውን የአኗኗር ዘይቤ ታሳቢ ያላደረገ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በግዥ ትርፍ አምራች ከሆኑት አካባቢዎች አቅርቦቱን ወደ እጥረት ላለባቸው ከማድረስ ይልቅ ከውጭ ሀገር በውድ ዋጋ የሚቀርበው ዕርዳታ የልገሳ ሽፋኑን እየቀነሰው ይገኛል::

በሀገራችን ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች፣ ክረምት-ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች፣ ከአጥጋቢ በላይ ዝናብ የሚያገኙ ትርፍ አምራች አካባቢዎች፣ የመስኖ ልማት መሠረተ-ልማት ያላቸው ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት እና በምርት ተግባር ሊሰማራ የሚችል ወጣት ሕዝብ እያለን ሠብዓዊ ድጋፍን በአመዛኙ በሀገር-በቀል አቅም የማንሸፍንበት በቂ ምክንያት አይኖርም::

በዚሁም በፌዴራልና በክልል ደረጃ የሚያስፈልገንን የመጠባበቂያና የአስቸኳይ ጊዜ የዕለት ደራሽ ርዳታን ከገበያ መሸመት ሳያስፈልግ ተጨማሪ ምርት በማምረት መሸፈን እንደሚቻል ከተደረጉ ዳሰሳ ጥናቶችና ትንተናዎች መረዳት ችለናል:: በተለይም በግብርና የኮሜርሻል ክላስተር አርሶ አደሮች፤ በባለሀብቶችና በበጋ ስንዴ የተገኙ ልምዶች ሠብዓዊ ድጋፍን በአመዛኙ በራስ አቅም በየደረጃው ማሟላት እንደሚቻል ማረጋገጫ ናቸው:: በዚህ ሂደት ሁሉም ባለድርሻዎች ሚናቸውን ከዓለምንም መቆጠብ እንዲያበረክቱ፣ የሀገራችንና የሕዝባችን ክብር ለማስጠበቅ እንዲረባረቡና በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደተገለጸው “እውነተኛ ነፃነትን ለመጐናጸፍ እናምርት” መርሆ በአርበኝነት ለማሳካት እየሠራን እንገኛለን::

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ::

ኮሚሽነር ሽፈራው፡– እኔም አመሰግናለሁ::

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You