ግብርናው የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ፤ ዘርፉን በሁለንተናዊ መልኩ በማሳደግ ሀገራዊ ጠቀሜታውን ለማጎልበት በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። የታሰበውን ያህል ባይሆንም የተወሰኑ ለውጦችን እያደረገ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ሀገሪቱ እንደ ሀገር ካላት ለግብርናው ዘርፍ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ፣ ለም መሬት፣ የውሃ ሀብትና ሰፊ አምራች የሰው ኃይል አኳያ ፤ እስካሁን ሀገራዊ የምግብ አቅርቦት ፍላጎቶችን ማሟላት በማይችል ሁኔታ ውስጥ ሲዳክር ቆይቷል። ሌላው ቀርቶ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችን ሕይወት መቀየር የሚያስችል አቅም መፍጠር አቅቶት ኖሯል።
ዘርፉ እንደ ሀገር ትርፍ ምርት ማምረት የሚያስችል አቅም መጎልበት ካለመቻሉም የተነሳ ፤ በጥቂትም ይሁን በብዙ የተፈጥሮ አደጋዎች በጋጠሙ ማግስት ሀገር እንደሀገር ለልመና እጆቿን እንድትዘረጋ ተገዳለች ፤ ይህም በዜጎች ብሄራዊ ክብር ላይ ከፍያለ አሉታዊ ተጽእኖ ሲፈጥር ፣ አንገት ሲያስደፋ ቆይቷል።
ይህንን ዘመናት የተሻገረ ሀገራዊ ችግር ለዘለቄታው ለመፍታት ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት ለዘርፉ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤጥ ተስፋ ሰጪ ከመሆን ባለፈ በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ እያመጣ ነው።
እንደ ሀገር ያሉ አቅሞችን ዓይንን ከፍቶ ከማየት የሚነሳው የመንግሥት ዘርፉን የማልማት ስትራቴጂ ፤ እነዚህን አቅሞች በተገቢው መልኩ አውቆ በተቀናጀ መልኩ ማልማት ላይ የተመሠረተ ነው ፤ ዘርፉን በማዘመን ውጤታማ የሚሆንበትን አስቻይ ሁንኔታ መፍጠርንም ታሳቢ ያደረገ ነው።
ለዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶችን ፤ በተለይም በስንዴ ልማት እየተመዘገበ ያለው ውጤታማነት ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ፤ በተሞክሮ ደረጃ ተጠቃሽ እየሆነ የሚገኝ ነው። ሀገርንም ከችግር በመታደግ ሂደት የነበረው ፣ አሁንም ያለው አበርክቶ ከፍ ያለ ነው።
ይህ የመንግሥት ከፍተኛ ቁርጠኝነት በስፋት የሚስተዋልበት የግብርናው ዘርፍ ፣ በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ዘርፉን በማዘመን ምርታማነትን ለዘለቄታም ማሳደግ የሚያስችል መሠረት የሚጥል እየሆነ ነው።
የግብርና ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው ፤ ባለፉት አምስት ወራት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የሚያስችሉ ከ 919 ሺህ በላይ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ከተደረጉ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች መካከል አራት ሺህ 117 ትራክትሮች ከነተቀጽላ መሣሪያዎቻቸው ፣ 137 ሺህ 295 የመስኖ ፓምፖች ፣ 632 የሰብል አጭዶ መውቂያዎች እና 116 የእንስሳት መኖ ማዘጋጃ መሣሪያዎች ይገኙበታል፡፡
የአፈር መሸርሸርና ጨዋማነት እንዳይከሰት የሚረዱ ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎች፤ 203 ሺህ 127 የነፍስ ወከፍና የትራክተር ተቀጣይ የመርጫ ቴክኖሎጂዎች፤ 547 ሺህ 291 ዘመናዊ የእህል ማከማቻ ቴክኖሎጂዎች ፣ 27 ሺህ 14 እንስሳት እርባታ ቴክኖሎጂዎች እና መሣሪያዎች ወደ ሀገር ውስጥ ከቀረጥ ነጻ ገብተዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ባለፈም የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች አጠቃቀም ዙሪያ ሥልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ ሥልጠና እየሰጡ ነው፡፡ ሥልጠናዎቹ በፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት የሚሰጡበትን አግባብም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየመከረ ነው፡፡
ይህ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ /በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው የግብርናውን ዘርፍ የማዘመን ሥራ ፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት እየተሞከረ ብዙም ውጤታማ ያልሆነውን ዘርፍን ለዘለቄታው በማዘመን ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ጅማሪ እንደሆነ ይታመናል።
በተለይም እንደሀገር በምግብ እህል ራሳችንን በመቻል ከጠባቂነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ በመደገፍ ፣ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ትልቅ አቅም መገንባት የሚያስችል ነው። በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎቻችንን የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግም ያለው አስተዋጽኦ የማይተካ ነው ።
ከዚህም ባለፈ በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ዜጎቻችንን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና እውቀት የማስታጠቁ እውነታ ፣ በአጠቃላይ ዘርፉን ለማዘመን የተጀመረውን ጥረት በተሻለ መልኩ ውጤታማ በማድረግ ዘርፉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አበርክቶ በማሳደግ ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ ተጨባጭ ማድረግ ያስችላል።
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም