አብዛኞች እንደዋዛ ጥለዋት በሚለይዋት ዓለም በተቃራኒው ጥቂቶች ከራሳቸው ለሌሎች የሚተርፍ አስተዋፅዖ አበርክተው ማለፉ ይሳካላቸዋል። በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፍ ሥራ ሠርተው ስማቸው ሲወሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ፈጣሪው ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ አንዱ ናቸው።
ኢንጂነር ተረፈ ራስ ወርቅ፣ መጋቢት 2 ቀን 1928 ዓ.ም በአንኮበር ውስጥ በምትገኝ አፈርባይኔ በምትባል መንደር ከአባታቸው ከመምህር ራስወርቅ ወልደመስቀልና ከእናታቸው ከወይዘሮ አስካለ ማሪያም ገ/ጊዮርጊስ ተወለዱ።
ኢንጂነር ተረፈ የተወለዱት ውጥንቅጥና ቀውጢ ጊዜ በነበረበት የጣሊያን ወረራ ወቅት ነበር። ረቡዕ መጋቢት 2 ቀን 1928 ዓ.ም። እናታቸው አራስ ቤት ሆነው ሕጻኑን ተረፈን ሲንከባከቡ በድንገት የጠላት ጣሊያን አውሮፕላኖች አንኮበር ላይ የቦምብ ዝናብ ይጥላሉ። በአካባቢው የነበሩት የሳር ክዳን ቤቶች እንደችቦ ይቀጣጠላሉ። ሕዝቡም ነፍሴ አውጭኝ ብሎ ይሯሯጣል፤ ከጥቃቱ በኋላ እሳቱ ይጠፋል።
የተረፈው ሰውም እየፈራ ወደቀዬው ይመለሳል። ነገር ግን የያኔው ሕጻን ተረፈና ወላጅ እናቱ የደረሱበት አልታወቀም ነበር። ሞተዋል ተብሎ ለቅሶ ይጀመራል። አባታቸው መምህር ራስወርቅም ወዲያና ወዲህ ፈልጉ እያሉ ይወራጫሉ። በማግስቱ ረፈድ ሲል ሁሉም እረጭ ሲል ወላጅ እናቱ ሕጻን ተረፈን በጉያቸው አቅፈው ከተደበቁበት ዋሻ ወጥተው ወደመንደራቸው ሲመለሱ በሕይወት በመገኘታቸውን እልልታ ሆነ። መምህር ራስወርቅም ልጄ ተረፈልኝ ብለው እግዚአብሔርን አመስግነው ለልጃቸው ተረፈ ብለው ስም አወጡለት።
ኢንጂነር ተረፈ ፊደል የቆጠሩት አንኮበር ወላጅ አባታቸው ጋር ሆነው ነበር። የጣሊያን ጦር እንደወጣ በ1933 ዓ.ም የኢንጂነር ቤተሰብ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። የያኔው ታዳጊ ተረፈም አንድ ቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ዳዊት ደግመዋል። ከዚያም ለአንድ ዓመት ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ተላኩና የአንደኛ ክፍል ትምህርት አጠናቀው ወደ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተዛወሩ።
ኢንጂነር ተረፈ፣ ተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤትን በጣም ወደዱት ምክንያቱም ቤታቸውና ትምህርት ቤቱን አንድ አጥር ነበር የሚለየው። በዘመኑ በአገሩ ውስጥ ትልቅ ከሚባሉት ትምህርት ቤቶች አንዱ ነበር። ከአንድ ሺህ ተማሪዎች በላይ ነበሩት። የንጉሠ ነገሥቱ ቤተ መንግሥት ቅርብ ስለነበር ጃንሆይ በየጊዜው እነ ኢንጂነር ተረፈን ይጎበኙ ነበር። ይህም ዘወትራዊ ጉብኝት ተማሪዎቹንና መምህራኑን ያስደስታቸውና ያበረታታቸው ነበር።
በወቅቱ ከኢትዮጵያውያን አስተማሪዎች ጋር የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪና መምህራኖቹ ከካናዳ የመጡ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ኢየሱሳውያን የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ነበሩ። ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ታዳጊ ተረፈን የሚያስተምሩት የውጭ አገር ተወላጅ አስተማሪዎች ነበሩ።
በመስከረም ወር 1947 ዓ.ም ኢንጂነር ተረፈ የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ደጅ ረገጡ። ስማቸውን በሳይንስ ክፍል ሲያስመዘግቡ ሰው ሁሉ አብደሃል ወይ ብሎ ታዘባቸው። ምክንያቱም ከተፈሪ መኮንን የሚመጡ ልጆች እንደሌሎቹ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ንጹሕ ኬሚስትሪና ንጹሕን ፊዚክስ በመውሰድ ፈንታ ጠቅላላ ሳይንስ ስለሚማሩ የኮሌጅ ሳይንስ ይከብዳቸዋል ይባል ስለነበረ ነው።
እንደአጋጣሚ ሆኖ ኢንጂነር ኮሌጅ ውስጥ እንደገቡ የመጀመሪያው የኬሚስትሪ ፈተና በጣም ቀላል ስለ ነበረ ውጤቱ ሲለቀቅ ዘጠና ዘጠኝ ከመቶ አገኙ። ይህ ውጤት ግሩም ተባለ። ወሬውም ወደ ቲኤምኤስ ተዛመተ። ኢንጂነር ተረፈም፣ የእችላለሁ መንፈስ ውስጣቸው ስላደረ የትምህርት ዘመናቸውን ያለችግርና በራስ መተማመን ለማለፍ ችለዋል።
ኢንጂነር ተረፈ፣ ኮሌጁ ውስጥ ሳሉ በብዙ ተጓዳኝ ሥራዎች ውስጥ ተካፋይ ነበሩ። የኮሌጁ የሶፍት ቦል ቲም ካፒቴን ነበሩ። እንዲሁም በጥንታዊ ባሕላዊ ማኅበረ ጥናት ላይም ይካፈሉ ነበር።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በ1949 ዓ.ም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቲያትር ንጉሠ ነገሥቱ በሚገኙበት ለሀገራችን የትኛው ትምህርት ይበልጥ ይበጃል? በሚል ርዕስ ኮሌጁ አንድ የአደባባይ ሙግት አዘጋጅቶ ነበር። ሙግቱም ለሀገራችን በጣም የሚጠቅመው ትምህርት ሕግ ወይስ ሕክምና ወይስ መሐንዲስነት ወዘተ የሚል ነበር። ኢንጂነር መሐንዲስነት ነው የሚለውን መስመር ሲይዙ ተስፋዬ ገሠሠ ሕግ ይሻላል ብሎ ተነሳ። ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ደግሞ አስተማሪነት ይበልጣል ብሎ ተከራከረ። ኢንጂነር አንደኛው መከራከሪያቸው ለመሐንዲስ ሥራ የሚያስፈልጉትን የደን ውጤቶች መንከባከብ ያስፈልጋል የሚል ሲሆን የሚገርመው ግርማዊነታቸው ተረፈ ሲናገር ማስታወሻ ይወስዱ እንደነበር ይነገራል።
በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ በሳይንስ ዘርፍ ሙሉ የዲግሪ ፕሮግራም ስላልነበረው ከ 3 ዓመት ትምህርት በኋላ በመንግሥት ወደ ውጭ ሀገር ተማሪዎች ይላኩ ነበር። በዚህም መሠረት፣ ኢንጂነር ተረፈ ከሌሎች ጓደኞቻቸው ጋር ወደ ሬንስለር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት ወደ ትሮይ ኒውዮርክ ስቴት ተላኩ።
በነበረው ልማድ መሠረት ተማሪዎች ወደውጭ ሀገር ሲላኩ ንጉሠ ነገሥቱ ጋር ቀርበው መሰናበትና አባታዊ ምክር ይሰጣቸው ነበር። ተሰናባች ተማሪዎች ንጉሡን የተሰናበቱት በደብረ ዘይት ቤተ መንግሥታቸው ነበር። ጃንሆይም ጥሩ አቀባበል ካደረጉ በኋላ ሀገራችሁን ተመልሳችሁ አገልግሉ ሲሉ አደራ ሰጡ።
በ1950 ዓ.ም ነሐሴ ወር ኢንጂነር አዲስ አበባን ለቅቀው ወደ አሜሪካ ለመሄድ ተነሱ። በመጀመሪያ ኢንጂነርና ጓደኛቸው ማህዲ በኤሌክትሪክ መሐንዲስነት መማሪያ ዋና ክፍል ተመዘገቡ። ትምህርቱም በጣም ከባድ ሆኖ አገኙት። ነገር ግን እጅ ባለመስጠት ጠንክረው በመማር በ1952 ዓ.ም የተሰጣቸውን ክፍል ትምህርት ጨርሰው በኤሌክትሪክ ምሕንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ።
ኢንጂኒየር ተረፈ ከውጭ እንደተመለሱ የመጀመሪያ ሥራቸውን ቴሌ ውስጥ ጀመሩ። ሥራውንም እንደጀመሩ ሁሉንም ክፍሎች በሚገባ እንዲጎበኙ ነበር የተደረገው። ከባሕር ማዶም እንደመጡ በሙያቸው ከፍተኛ ተሰሚነት ነበራቸውና፤ የነበሩትን ክፍሎች ከጎበኙ በኋላ የትራንስሚሽንና የረጂም ርቀት ስርጭት ከሚባል ክፍል በኃላፊነት ተመደቡ። የ25 ዓመት ወጣት ሳሉ ቴሌ ውስጥ ትልቅ የሚባል ኃላፊነት ተሰጣቸው። የእድሜ ማነስ አንድም ተፅዕኖ ሳይፈጥርባቸው ሥራቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይሞክሩ ነበር። በዛን ጊዜ የነበሩት ስዊዲኖች አንድን ሰው የሚመዝኑት በእድሜው ሳይሆን በሥራ ብቃቱና በአመለካከት ብስለቱ ነበር።
እርሳቸው ከውጭ መጥተው ቴሌ በሚሠሩበት ጊዜ የፋክስ ግንኙነት አልነበረም። አብዛኛው መልዕክት ይተላለፍ የነበረው በቴሌግራፍ ነበር። ኢንጂኒየር ተረፈ ለአንድ የሀገር ውስጥ ሚዲያ ሁኔታውን ሲገልጹ “እንዲህ ነበር ያሉት… በጣም የደነቀኝ የዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ ቋንቋ የሚላክ ቴሌግራም ሁሉ በላቲን ፊደል ነበር የሚፃፈው። ለምሳሌ ‘እመጣለሁ’ ለማለት ሲፈለግ emetalehu ተብሎ ነበር የሚጻፈው። ” “እንዴት የራሳችን ፊደል እያለን በላቲን ፊደል ይጻፋል ስል ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ። ለምን በራሳችን ፊደል መጻፍ አልተቻለም? የሚል ጥያቄ ባነሳም አበረታች መልስ አላገኘሁም። ‘ፈጽሞ አይቻልም፤ ብዙ ሰዎች ሞክረው ትተውታል’ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነበር የገጠመኝ። በኋላም ኦሊቬቲ የተባለ ኩባንያ የአማርኛ ቴሌፕሪንተርን ለመሥራት ሞክሮ አልቻለም ሲሉ ሌላ መረጃ አቀበሉኝ። እኔም ‘በኢትዮጵያ ፊደል ቴሌፕሪንተር’ ሊኖር አይችልም የሚባለውን ተስፋቢስ ዜና ልቀበለው አልቻልኩም። ” ይላሉ።
በዚህም መነሻ ኢንጂነር ተረፈ የአማርኛ ቴሌፕሪንተር ለመሥራት ተነሳስተው ምርምሩን ጀመሩ። በወቅቱ ፕሪንተሮቹ ለላቲን ፊደል ነው የተፈጠሩት የሚል ግትር መከራከሪያ ተነስቶ ነበር። እንደሚታወቀው የላቲን ፊደል 26 ነው። የአማርኛ ደግሞ 270 ነው። ታዲያ የመከራከሪያ ሃሳቡ ፕሪንተሩ ለ270 ፊደላት ቦታ የለውም የሚል ነበር።
ኢንጂነሩ፣ ይህን ሃሳብ ጊዜ ሰጥተው ምርምሩን ቀጠሉበት። ኢንጂነር ተረፈ ያደረጉት ዋናው ጥናትም የኢትዮጵያን ፊደሎች እንዴት ቴሌፕሪንተር ውስጥ ማስገባት ይቻላል የሚል ነበር። ኢንጂነሩ ያኔ ለማስተዋል እንደሞከሩት የኢትዮጵያ ፊደሎች ቅርጽና ውበት እጅግ የሚያስደንቅ ነው። በብዛት 270 ቢሆኑም፣ ቅርጻቸው ግን ከ20 አይበልጥም።
ያኔ እርሳቸው ለማቅረብ እንደሞከሩት የላቲን ፊደሎች 26 ይባሉ እንጂ “ካፒታል ሌተር፤ ስሞል ሌተር” ሲባል ወደ አርባ ይጠጋሉ። የእኛ ግን ይላሉ የያኔው ወጣት ተመራማሪ “ቅርጹ ሲታይ በጣም ተመሳሳይ ነው። ለምሳሌ ‘ሀ’ ሲገለበጥ ‘በ’ ይሆናል። በአናቱ ላይ ዘንግ ሲደረግበት ‘ሰ’ ይሆናል። ‘ሰ’ ላይ መስመር ሲደረግበት ‘ሸ’ ይሆናል። ” በማለት ጥናታዊ ምርምሩን አጠናክረው ቀጠሉ።
እነዚህን ቅርጾች በማስተካከል ብቻ ቴሌፕሪንተሩን መሥራት እንደሚቻል ኢንጂነር ተረፈ በምርምር ማረጋገጥ ቻሉ። ከዚህ በኋላ የዚያን ዘመን ቴሌፕሪንተር የፊደላት ድርድር (ኪቦርድ) ቅርጽ ማስተካከል ያዙ። ማሽኑ ላይ የሚቀረጹት ፊደሎች ቁመታቸውና አቀማመጣቸው ወረቀቱ ላይ የቱ ጋር እንደሚቀመጡ በደንብ ካስተካከሉ በኋላ ሲጻፍ ፈጽሞ እንደማያስቸግር በሚገባ አረጋገጡ።
የኪቦርዱን ቅርጽ ካስተካከሉት በኋላ በጊዜው የአዕምሯዊ ንብረት ሕግ የፈጠራ ውጤታቸውን በይፋ አስመዘገቡ። በኋላም፣ ሶፍትዌሩን ሲመንስ ለሚባለው የጀርመን ኩባንያ አስረከቡ። በ1960 ዓ.ም (ቴሌፕሪንተሩ) የአማርኛ ፊደል ይዞ ሀገር ቤት ሲመጣ ልዩ ስሜትና የሥራ ተነሳሽነት ተሰማቸው።
ወዲያው፣ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴሌፕሪንተሩን መረቁ። በምረቃው ዕለት አንዱ ቴሌፕሪንተር አሥመራ ቤተ-መንግሥት ተደረገ። አንደኛው አዲስ አበባ ተቀመጠ። በወቅቱ የኤርትራው ገዢ ራስ አሥራተ ካሣ በአዲሱ መኪና መልዕክት ወደ አዲሰ አበባ ሲልኩ ግርማዊነታቸው መልዕክቱን አይተው የደስታ ስሜታቸውን መደበቅ አልተቻላቸውም ነበር።
የዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን አንድነት በ1865 ዓ.ም የተፈጠረ መቀመጫውን ጄኔቭ ያደረገ ትልቅ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ኢንጂነር በሄዱበት ዘመን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ ክፍል ነበር። ያኔ የኅብረቱ ዋና ጸሐፊ የቱኒዚያው ሚስተር መሐመድ ሚሊ ነበሩ። ኅብረቱ ሰዎችን ሊቀጥር ሲያወዳድር የአፍሪካ ክፍል ክፍት ሲሆንባቸው ለአባል ሀገሮች ሁሉ ክፍት ቦታ መኖሩን አሳወቁ። ኢንጂኒየርም ያኔ ነበር ከተወዳዳሪዎቹ አንዱ ለመሆን የበቁት። የትምህርት ሁኔታውና የሠሩት ሁሉ በሚገባ ታይቶ የኅብረቱ ባልደረባ ሊሆኑ ቻሉ። ከዛም በዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት የአፍሪካ ጉዳይ ክፍል ውስጥ ማገልገል ያዙ። በጄኔቭ አንድ ብለው የጀመሩት የሥራ ዘመን ለ40 ዓመታት ዘልቋል።
በኅብረቱ ውስጥ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ሆነው በሠሩባቸው ዓመታት የአፍሪካን የቴሌኮም ዕድገት ዕውን ለማድረግ የአቅማቸውን ያህል ሞክረዋል። የመጀመሪያው የኅብረቱ ቀዳሚ ተግባር የቴሌኮሙኒኬሽን ማሠልጠኛዎች በየሀገሩ መመሥረት ነበር። በዚህ መሥሪያ ቤት በነበራቸው ቆይታ የበርካታ ሀገራትን የቴሌኮም የዕድገት ደረጃ ለመለየት ችለዋል።
ለሀገራቸው እና ለታሪክ ታላቅ ፍቅር የነበራቸው ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ ከ100 ዓመት አስቀድሞ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በቤተመንግሥትነት ይጠቀሙበት የነበረውን የአንኮበር ቤተ-መንግሥትን፣ አንኮበር ሎጂ ብለው የቀድሞ ታሪኩን በጠበቀ መልኩ አሳድሰው ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ ያኖሩ ናቸው። ይህም የበርካታ ቱሪስቶች መስሕብ መሆን የቻለ ነው።
ኢንጂነር ተረፈ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ለዓለም አቀፉ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት ዳይሬክተርነት ለመወዳደር በእጩነት የቀረቡ ታላቅ ሰው ነበሩ። በተለይ ሀገራችን በቴሌኮም ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ልምድና እውቀታቸውን ሲያካፍሉ፤ ምክር ሲለግሱ የነበሩ ናቸው።
በ1954 ዓ.ም ከወይዘሮ ብርሀኔ አስፋው ጋር በጋብቻ የተጣመሩት ኢንጂነር ተረፈ ራስወርቅ፤ በትዳራቸው 3 ልጆችን እንዲሁም የልጅ ልጆችን አፍርተዋል። ከኢትዮጵያ ባለፈ በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ባለሙያዎች ዘንድ በክብር የሚነሱት እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ በተወለዱ በ86 ዓመታቸው ሚያዝያ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።
ኢንጂነር ተረፈ በሕይወት ዘመናቸው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታታሪነትና በጥልቅ ሀገራዊ ፍቅር በማገልገል ታላቅ አስተዋፅዖ ያበረከቱ ሰው ነበሩ። እኛም እኚህን የሀገር ባለውለታ ነፍስ ይማር እንላለን።
ክብረዓብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም