‹‹የሥጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም›› እንደሚባለው ነው መሰለኝ የኩረጃ ነገር አይጠየቅም፤ አይመረመርም። የፈተና ኩረጃ የሰነፍ ተማሪ ምልክት ነው። የባህል ኩረጃ ደግሞ የሰነፍ ሕዝብ ምልክት መሆኑ ነው። ሰነፍ ተማሪ ሲኮርጅ ለመኮረጅ ቀላል የሆኑ ነገሮችን ነው የሚኮርጅ። ምርጫ፣ እውነት ሐሰት፣ አዛምድ እና ባዶ ቦታ ሙላ የመሳሰሉትን፤ በቀላሉ አይቶ የሚጻፉትን ማለት ነው። ቀመራዊ አሠራር ወይም ሌላ ሰፊ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸውን አይኮርጅም። አንደኛው ምክንያት ሲኮርጅ ፈታኙ መምህር ይደርስበታል። ሁለተኛው ምክንያት ግን ቢፈቀድለት ራሱ አይችልም። ያንን ውስብስብ ቀመራዊ አሠራር አይችለውም። ተለዋዋጭን በተለዋዋጭ ተክቶ፣ ቅንፍ የሚከፈትበትን ከፍቶ የሚዘጋበትን ዘግቶ፣ የሚጣፋውን አጣፍቶ ቀመሩን በትክክል ሊያስቀምጠው አይችልም። ማድረግ የሚችለው የምርጫና የእውነት ሐሰት መልሶችን ብቻ መኮረጅ ነው።
የፈረንጅ ባህል የመኮረጅ ልማዳችንም እንደዚሁ ሰነፍ ተማሪ ነው። የምንኮርጀው ቀላል ቀላሉን ነው። ለምሳሌ የተራቆተ አለባበስ ስንኮርጅ የልብስ አሠራሩን ግን አንኮርጅም። ምክንያቱም ከእንብርት በላይ የሆነ ልብስ መልበስ በጣም ቀላል ነው፤ ምንም እውቀትና ጥበብ አይጠይቅም። ያንን ልብስ መሥራት ግን እውቀትና ብቃት ይጠይቃል። የፈረንጆችን ይቅርና የራሳችንን የልብስ አሠራር እንኳን አንችልም። እናቶቻችን የዛፍ ፍሬ (ጥጥ) ለቅመው ልብስ እስከሚሆን ድረስ የሚሄዱትን የአሠራር ቅደም ተከተል እንኳን አናውቀውም። ልብስ ከጥጥ እንደሚሠራ እንጂ እንዴት እንደሚሠራ አናውቅም። ይሄን እናቶቻችን የሚያደርጉትን ነገር ያልቻልን ግን የፈረንጅ አለባበስ እንኮርጃለን።
በነገራችን ላይ ኩረጃ ጥበብም ነው። የሰው ልጅ ሲወለድ ከየትኛውም ሙያ ጋር አይወለድም። በማህበራዊ ሕይወቱ ውስጥ ነው የሙያና የተሰጥኦ ባለቤት የሚሆነው። አንዳንድ ሙያዎች ልዩ ተሰጥኦ ቢፈልጉም አብዛኛው ግን በልምድ የሚመጣ ነው። በልምድ ውስጥ ማለት እንግዲህ አንዱ ሌላውን እያየ ማለት ነው። ይሄ ማለት በቀጥታ ኩረጃ ማለት ነው። ልዩነቱ የኩረጃው አይነት ነው። ጎበዝ ማለት ቀጥታ መገልበጥ ሳይሆን ካየው ነገር ተነስቶ ለራሱ በሚስማማ መንገድ መሥራት ማለት ነው። ችግሩ እኛ የምንኮርጀው የሰነፍ ኩረጃ ነው። ይሄ ደግሞ ሁሌም ጥገኛ ያደርጋል።
የባህል ኩረጃና የባህል ወረራ ከሚነሳባቸው ነገሮች አንዱ አሁን ያለንበት የገና ሰሞን ነው። በየሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የገና በዓል ማስታወቂያዎች ተጀምረዋል። በየዓመቱ በዚህ ሰሞን በየሆቴሎች በር ላይ የምናየው አንድ የተከናነበ አርቲፊሻል ሽማግሌ ነው። ይህ ሽማግሌ የፈረንጆች የገና አባት ነው። እውነት እኛ ለዚህ የሚበቁ የጥንት አባቶች የሉንም? የገና ዛፍ ተብሎ በውድ ዋጋ የሚሸጥ አርቲፊሻል ዛፍ በትልልቅ የገበያ ቦታዎች ይታያል። እውነት እኛ ሀገራዊ የገና መጫወቻ አልነበረንም? ከተሞች ውስጥ ግን ይሄ ባህላዊ ገና አይታይም።
ይህ የሶስት ማዕዘን ቅርፅ ያለው የፈረንጆች አረንጓዴ ዛፍ፤ በጥንት ጊዜ ጀርመናውያን ያመልኩበት እንደነበረ እና፤ ቅዱስ ቢኒፋሴ የተባሉ ቄስ ነገሩን ለማስቀረት በሥላሴ ተምሳሌነት ይጠቀሙበት እንደነበረ፤ መረጃዎች ያሳያሉ። በኋላም በተለያዩ ጌጣጌጦች እያሸበረቀ መጣ። እኛ ኢትዮጵያውያን ይሄን ኮርጀን ስንገለብጥ ግን ምን እንደሆነ እንኳን ሳናውቅ ነው። ባህላዊም ይሁን ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን የራሳችን የሆኑ ነገሮችን በመጣል ነው። ፈረንጆች የገና አባት የሚሉት ‹‹ሳንታ ክላውስ›› ምናባዊ ይሁን እውነተኛ አከራካሪ በሆነበት፤ በሀገራችን የታወቁ ሰዎችን ግን የእርሱን ያህል ክብር አያገኙም።
ይህ ማለት ግን በሁሉም ቦታዎች ነው ማለት አይደለም። ከሁለት ይሁን ሦስት ዓመት በፊት ያየሁት ነበር። አንድ የምግብ ቤት በር ላይ (ጉርድ ሾላ አካባቢ) በትልቁ የተጻፈ የተዘጋጀ ሸራ ላይ፤ እንደ መሰንቆ፣ ክራር፣ ከበሮ፣ በገና የመሳሰሉ የባህል የሙዚቃ መሣሪያዎች ተደርድረዋል። ከመሃል ላይ ደግሞ ባህላዊ ገና በትልቁ ይታያል። እንዲህ አይነት በባህሉ የሚኮራ ሰውም አለ ማለት ነው። ልብ በሉ! ቤቱ የሙዚቃ መሣሪያ ወይም ገና የሚሸጥበት ሳይሆን ምግብ ቤት ነው። ያንን ቤት ያየ ፈረንጅ ሁሉ ኢትዮጵያን አወቀ ማለት ነው። የገና አባት ቢሆን ግን ምንም የተለየ ስሜት አይፈጥርበትም።
በነገራችን ላይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለውጥ እየመጣ ይመስላል። አስታውሳለሁ 2005፣ 2006 እና 2007 ዓ.ም አካባቢ በየመገናኛ ብዙኃኑ ይቀርብ የነበረ ወቀሳ ‹‹የራሳችን ነገር ተረሳ›› የሚል ነበር። የፈረንጅ አምላኪዎች መሆናችን በየጋዜጦችና መጽሔቶች ወቀሳ በዝቶበት ነበር። ምናልባት ያ የመጣው ለውጥ ይሁን በሌላ ምክንያት ባይታወቅም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ባህላዊውን የገና ጨዋታን ማሳየት ጀምረዋል። ማስታወቂያዎች በባህላዊ የገና ጨዋታ መታጀብ ጀምረዋል። ቢያንስ በመገናኛ ብዙኃን ደረጃ ይህን ያህል ለውጥ መታየቱ ይበል ያሰኛል።
በዚያው ልክ ግን ለባህል ወረራው ምክንያቶችም መገናኛ ብዙኃን ናቸው። መገናኛ ብዙኃኑ ጎንደር ላይ ያለ፣ አክሱም ላይ ያለ ወይም ቦረና ላይ ያለ የገና በዓል አከባበርን ከሚያቀርብ ይልቅ ፈረንሳይ ወይም ጃፓን ወይም ዱባይ ውስጥ ያለውን እየደጋገመ ስለሚያሳይ ተፅዕኖ መፍጠሩ የግድ ነው። መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ኃይል አላቸው። ለብዙ ዘመናት የኖረውን ባህል ነው አሥር እና አሥራ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የባህል ወረራውን ያፋጠኑት። የሚሠሩትም ገንዘብ ያለበት ቦታ ላይ ስለሆነ ነው ስለሀገራዊ ገጽታው የማይጨነቁት። ገበያው በሞቀበት አካባቢ ከማስታወቂያ ሥራዎች ጀምሮ ይረባረቡበታል።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ማህበረሰቡ ላይም ችግር የለም ማለት አይደለም። የፈረንጅ ባህል መከተል መሰልጠን የሚመስለው ሰው ብዙ ነው። ከፈረንጆች፤ የፈጠራ ሥራዎቻቸውን፣ የንባብ ባህላቸውን፣ ሰዓት የማክበር ልምዳቸውን… አንኮርጅም። የምንኮርጀው በቀላሉ መተግበር የምንችለውን ነገር ነው። ልጆችም የሚያድጉት ይህን እያዩ ነው። ከጥጥ ልብስ መሥራት እንደሚቻል ለልጇ የምታሳይ እናት የለችም። ስለገና አባት ልጁን የሚያስተምር አባት ስለኢትዮጵያዊው የገና ጨዋታ ግን አይነግረውም። አርቲፊሻል ሽጉጥ ለልጁ የሚገዛ አባት ስለሞፈርና ቀንበር ግን አይነግረውም። ልጁ ሲያድግ ገበሬ ይሆናል ባይባል እንኳን የአባቶቹን ጥበብ ማወቅ ነበረበት።
የኩረጃ ነገር እንደዚህ ነው፤ ከሁለቱም ያሳጣል። የራስን እንዳያውቁ ያደርጋል የሰዎችንም በትክክል እንዳይተገብሩ ያደርጋል። የፈረንጆች የሸቀጥ ማረገፊያ ስንሆን የራሳችንን ግን ማንም ፈረንጅ እንዳይገዛው እያደረግን ነው። እንኳን ፈረንጅ ራሳችንም ንቀነዋል። የቱንም ያህል ጥንካሬ ይኑረው ከኢትዮጵያዊ ዕቃ ይልቅ የፈረንጅ ዕቃ የሥልጣኔ ምልክት ይመስለናል። የቱንም ያህል ጤናማ የምግብ ይዘት ይኑረው ከኢትዮጵያዊ ባህላዊ ምግብ ይልቅ በፈረጅ አዘገጃጀት የተዘጋጀው የሥልጣኔ ምልክት ይመስለናል።
የውጭውን ማወቅ ዘመኑ የሚያስገድደው ዓለማቀፋዊነት ነው፤ ዳሩ ግን የራስን እየረሱና እያጣጣሉ መሆን የለበትም!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም