“የተማረ ሰው ማለት ክህሎት ያለው ማለት ብቻ አይደለም፡፡ ከዓመት ዓመት በስልጠና ውስጥ የኖረ እና ያነበበ ሰው ማለትም አይደ ለም፡፡
ሚዛናዊ የሆነ ፤ መጠየቅ የሚችል ፤ ሁኔታዎችን ማገናዘብ የሚችል . . . ወደ ኋላ ሔዶ ስነፅሑፎችን ያነበበ ፤ ትንሽ ታሪክም ለማወቅ የተጋ . . . ታሪክ ወሳኝ ነው፡፡ የሮማው ትልቁ የህግ አስተማሪ ሴሰሮ ምን ይላል ‹‹ከመወለዳችን በፊት ያለውን ታሪክ ካላወቅን ዕድሜልካችንን ህፃን ሆነን እንቀራለን›› ይላል፡፡” በ2004 ዓ.ም ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ ከአዲስ ጉዳይ መጽሄት ጋር ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰደ
የዛሬው የዓለም አቀፍ ዝግጅታችንም ሰሞኑን የተከበረውን የአፍሪካ ነጻነት ቀን አስመልክቶ ኒው አፍሪካ መጽሄት የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን አመሰራረት፣ ለአፍሪካውያን ነጻነት ያበረከተውን አስተዋፅኦና ያስመዘገባቸውን ስኬቶች እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ አሁንም ያልተቋጩ አጀንዳዎችን መኖራቸውን መለስ ብሎ በመዳሰስ ሊያውቁት የሚገባ ታሪክ ነው በሚል የሰራውን ትንታኔያዊ ጽሁፍ ያስቃኛችኋል፡፡
የጋናው ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንኩሩማህ እና የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መሪ ሚና የተጫወቱበትና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 25 ቀን 1963 በአዲስ አበባ የተፈረመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር የአፍሪካ መሪዎች የዓመታት ጥረት ፍሬ ያፈራበት ቀን ነው፡፡ የዛሬው የዓለም አቀፍ ዝግጅታችንም ሰሞኑን የተከበረውን የአፍሪካ ነጻነት ቀን አስመልክቶ ኒው አፍሪካ መጽሄት የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን አመሰራረት፣ ለአፍሪካውያን ነጻነት ያበረከተውን አስተዋፅኦና ያስመዘገባቸውን ስኬቶች እንዲሁም በኢኮኖሚው ዘርፍ አሁንም ያልተቋጩ አጀንዳዎችን መኖራቸውን መለስ ብሎ የዳሰሰበትን ትንታኔ ያቀርብላችኋል፡፡
የአንድነት ህያው መሰረቶች
የመጀመሪያው የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ኑርማህ በአፍሪካ አንድነት ላይ ፅኑ ዕምነት የነበራቸውና በዚህም በመላው ዓለም የሚኖሩ አፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝ እና ዘረኝነትን በመቃወም በጋራ በአንድነት እንዲቆሙና ለነጻነታቸው እንዲታገሉ በማድረግ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ ህያው አባት ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ንክሩማህን ጨምሮ ሌሎችም ቀደምት ፓን አፍሪካን አቀንቃኞች ነጻዋንና ታሪካዊቷን አገር የትግላቸው ሁሉ መነሻ አድርገው ይገልጻሉ፡፡ በጣሊያን ከተደረገባት የአምስት ዓመታት ወረራ በቀር ለሦስት ሺህ ዓመታት ነጻነቷን አስጠብቃ በክብር የኖረችው ኢትዮጵያ ለዓመታት በአውሮፓውያን ኢምፔሪያሊስቶች ቅኝ አገዛዝ ሥር ሆነው በባርነት ይማቅቁ ለነበሩ ሌሎች አፍሪካውያን በጨለማው ዘመን ውስጥ አሾልከው መጭውን ብሩህ ዘመን የሚያጮልቁባት የነጻነታቸው የአጥቢያ ኮከብ ሆና አገልግላለች፡፡ እንደነ ክዋሜ ንክሩማ ለመሳሰሉ ቀደምት የነጻነት ታጋዮችና የአፍሪካዊ አንድነት ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኞች የህልማቸው መጸነሻ ማኅፀን የዓላማቸው ማቀጣጠያ ቆስቋሽ ኃይል ሆናላቸዋለች፡፡
የነጻነት ትግሉ ተጠናክሮ መቀጠልና የድል ጅማሮ
የነጻነት ትግሉ ተጧጡፎ በ1957 እና በ 1963 ባሉት ዓመታቶች መካከል አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል ከቅኝ ገዥዎች እጅ ነጻ ሲወጣ የመላ አፍሪካ አንድነት ንቅናቄ አካሄድና ስልትም መለወጡ የማይቀር ሆነ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት የመላ አፍሪካ አንድነት ንቅናቄን በማስተዋወቅና በማስፋፋት ረገድ ጉልህ ሚና የነበረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሚቀጥል አልሆነም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አፍሪካን የማዋሃድና አንድ የማድረጉ ሀሳብ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት ብቻ ሳይሆን በመላው የአፍሪካ አህጉር ተንሰራፍቷል፡፡ በሰሜን አፍሪካ አልጀሪያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1962 ነጻነቷን እስክትቀዳጅ ድረስ ከፈረንሳይ ጋር ለምታደርገው የነጻነት ትግልና ጦርነት ድጋፍ ማድረግ ተችሎም ነበር፡፡
በሌላ በኩል በአብዛኛው የአህጉሪቱ ክፍል የተገኘው ነጻነት እንዳለ ሆኖ በፖርቹጋል ቅኝ ግዛቶች፣ በደቡብ ሮዴዥያ (የአሁኗ ዚምባብዌ)፣ በደቡብ አፍሪካ እና በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ (የአሁኗ ናሚቢያ) በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎችና በነጭ ሰፋሪዎች ስር የባርነት ሰለባ ሆነው መቀጠላቸው አህጉሪቱን የበለጠ ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ትግል ዋነኛ የትኩረት ነጥብ እየሆነ መጣ፡ ፡ እንደዚሁም በብሪታኒያና በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስርም ገና ነጻ ያልወጡ ጥቂት አገራት በመኖራቸው በቀጣይ በአጭር ጊዜያት ውስጥ ነጻነታቸውን እንዲያገኙ ማድረግም ትግሉ ትኩረት ያደረገበት ሌላው ጉዳይ ነበር፡፡ በመሆኑም ሌሎችም ቀሪ አፍሪካውያን ወንድሞች ነፃነታቸውን የሚያገኙበትን መንገድ በመፈለግ ረገድ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ነገር ግን አስቀድመው ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራት በምን መልኩ ወደፊት መቀጠል እንዳለባቸውና ነጻነታቸውን የበለጠ ማረጋገጥ አለባቸው በሚለው ጉዳይ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡
በልዩነቶች መካከል የተወለደው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
በዚህም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን በተመለከተ የበለጠ ሥር ነቀል አካሄድን ይከተሉ የነበሩ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት በ1961 በሞሮኮዋ ካዛብላንካ ከተማ ተሰባስበው የካዛብላንካ ቻርተር የሚባለውን ስምምነት አጸደቁ፡፡ ይህ ቡድን በዋነኝነት የክዋሜ ንክሩማዋን ጋና፣ በፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬ የምትመራውን ጊኒንና የገማል አብዱልናስሯን ግብፅ ያቀፈ ነበር፡፡ በሌላ በኩል በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የምዕራባውያን ደጋፊ የነበሩትና የአፍሪካ አንድነትን ጉዳይ በጥንቃቄ የሚመለከቱት ወግ አጥባቂ የአፍሪካ አገራት ከግንቦት 8 እስከ 12 1961 በላይቤሪያ ዋና ከተማ ሞኖሮቪያ ተሰብስበው የሞኖሮቪያ ቡድን መሰረቱ፡፡ በመሆኑም የአፍሪካ አንድነትን በተመለከተ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ልዩነት ተፈጠረ፡፡ የልዩነቱ ዋነኛ መንስኤም የመጀመ ሪያዎቹ የካዛብላንካ ቡድን አገራት ሁሉም አገራት ተዋህደው አንድ የአፍሪካ መንግሥት ሊኖ ይገባል የሚል አቋም የሚያራምዱ ሲሆን በተቃራኒው የሞኖሮቪያ ቡድን አገራት ደግሞ እያንዳንዱ ሉዓላዊ አገር እንዳለ ሆኖ በጋራ ጉዳዮች ላይ ብቻ አብሮ መስራት ይገባል የሚል አቋም ያላቸው በመሆኑ ነበር፡፡
የታንዛኒያውን ጁሊየስ ኔሬሬ የመሳሰሉ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ደግሞ ከሁለቱም ወገን ያልሆነ ገለልተኛ አቋምን ያራምዱ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ኒሬሬ ምንም እንኳን የአፍሪካን አንድነት በሚመለከት ባላቸው ስር ነቀል አቋም ከክዋሜ ንክሩማህ ጋር የሚመሳሰሉ ቢሆንም አንድ የአፍሪካ መንግስት ከመመስረቱ አስቀድሞ ግን በአገራት መካከል ቀጠናዊ አንድነት ሊኖር ይገባል የሚል ዕምነት ነበራቸው፡፡ በመሆኑም አንድ የአፍሪካ መንግስትን ለማቋቋም በነ ንክሩማህ የቀረበው ጥሪ ገና ከመጀመሪያው ውድቅ ተደረገባቸው፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ የንክሩማህ ሃሳብ ከአንዳንድ የካዛብላንካ ቡድን አባል አገራት ሳይቀር ተቃውሞ ገጠመው፡፡ በመጨረሻም ፕሬዚዳንት አህመድ ሴኩቱሬና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረውን ልዩነት ለማጥበብና ወደ አንድ ለማምጣት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት አስታራቂ ሃሳብን የያዘው የአፍሪካውያን አንድነት ድርጅት ምስረታ ዕውን መሆን ችሏል፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትና ለነጻነት ያበረከተው አስተዋፅኦ
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ለአፍሪካ ነጻነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በተለይም የነጭ ሰፋሪዎች በብዛት በነበሩባቸው እንደነ ደቡብ አፍሪካ በማሳሰሉ አገራት የነጻነት ትግሉ እጅግ መራራ የነበረ በመሆኑ ያለ ሌሎች አገራት ድጋፍና ትብብር ነጻ ለመውጣት የሚታሰብ አልነበረም፡፡ እናም ትብብርንና አንድነትን መርሁ ያደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በእንዲህ ዓይነቱ መራር የነጻነት ትግል ጉዞ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፡፡ በተለይም በደቡብ አፍሪካ የነጮች የበላይነትና በጥቁሮች ላይ ከፍተኛ ግፍን ይፈፅም የነበረውን የአፓርታይድ የዘር ሥርዓት በማስወገድና አገሪቱን ከቅኝ ገዥዎች መዳፍ አላቅቆ ነጻነትን በማስገኘቱ ሂደት ድርጅቱ ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚህም ደቡብ አፍሪካ ከረጅም ጊዜ እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በ1994 ነጻነቷን መቀዳጀት ችላለች፡፡ በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ አፍሪካ(በዛሬዋ ዚምባብዌ)፣ በአንጎላ፣ በሞዛምቢክ፣ በጊኒቢሳው፣ በኬፕቨርድና በሳኦቶሚና ፕሪንስፕ የነጭ ሰፋሪዎች የበላይነት ምክንያት በሃገራቱ ለረጅም ዓመታት ገንግኖ የቆየው የቅኝ ግዛት የብረት መዳፍ በአፍሪካውያን የተባበረ ክንድ እንዲሰባበር ድርጅቱ ከፊት ሆኖ አስተባብሯል፡፡
ሆኖም ድርጅቱ እንዲህ እንዲህ እያለ በአሁኑ አፍሪካ ህብረት እስተተተካበት ወቅት ድረስ ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም በኢኮኖሚው ዘርፍ አልተሳካለትም ማለት ይቻላል፡፡ እናም ኢኮኖሚያዊ ትብብርን በመፍጠር ረገድ ያለው ድክመት ዛሬም ድረስ የዘለቀ በመሆኑ የአፍሪካ ህብረትም ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብርን በመፍጠርና ከድህነት ነጻ የሆነች የበለጸገች አፍሪካን ዕውን በማድረግ ዙፋን አውራሹ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአህጉሪቱን ህዝቦች በማስተባበር ቅኝ ግዛትን በማስወገድና ነጻነትን በማቀዳጀት ያስመዘገበውን ስኬት ሊደግም ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
ይበል ካሳ