የወንጪ ደንዲ ሐይቅ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ሎጅኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብት ተጠቅማ ከድህነት መውጣት እንደምትችል ማሳያ ነው!

ባለ ብዙ ባሕሎችና ቅርሶች መድብል ከሆነችው ኢትዮጵያ ከጥንታዊም ሆነ ከመካከለኛው ብሎም ከዘመናዊ ታሪኳ የሚቀዱ ዘርፈ ብዙ ሀብቶች አሏት። ከታሪካዊና ባሕላዊ ቅርሶቿም በተጨማሪ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መስሕቦች ባለቤትም ነች። ይህንኑ እውነታ የተረዳው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) 16 ቅርሶቿን በመመዝገብ በአፍሪካ ግንባር ቀደም መሆኗን አረጋግጧል።

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ግንባታዎች በስፋት በማከናወንና እና ለቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር የማይተካ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። እንደ ሀገርም መንግሥት ኢኮኖሚውን ወደ ፊት ያሻግራሉ ብሎ ተስፋ ከጣለባቸው የግብርና፤ ኢንዲስትሪ፤ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ጋር በአንድነት የቱሪዝም ዘርፉን የመሪነት ሚና እንዲኖረው አድርጓል።

ይህንኑ ሀገራዊ ርዕይ መሠረት በማድረግም ሀገራዊ ለውጡ እውን ከሆነበት 2010 ዓ/ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማወቅ፤ በመለየት፤ በማልማትና መመጠቀም ረገድ እምርታዊ ለውጦች ታይተዋል። በአጠቃላይ ወቅቱ ለቱሪዝም ዘርፉ ትንሳኤ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አፍላቂነት እና መሪነት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት የሚያበረታታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገበታ ለሸገር፤ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ በሚል ማዕቀፍ በሀገራችን የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች በዘመናዊ መልክ እንዲለሙ እና ለቀረው ዓለም እንዲተዋወቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደ ሥራ ተገብቷል። መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በአራቱም ማዕዘናት ሀብቶችን በመለየትና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እጅግ በርካታ ሥራዎች ተከውነዋል።

በገበታ ለሸገር የቱሪስት መዳረሻዎች ግንባታ የአንድነት፤ የወዳጅነት እና የእንጦጦ ፓርኮች ለአዲስ አበባ ድምቀት ሆነዋታል። ለወትሮው በቱሪስት መተላለፊያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ የቱሪስቶች መቆያ የመሆን ዕድልም አግኝታለች። በገበታ ለሀገር ፕሮጀክትም የጎርጎራ፤ የኮይሻ እና የወንጪ የቱሪስት መዳረሻዎች ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዕድገት ተጨማሪ ዕድሎችን ፈጥረዋል።

የገበታ ለሀገር አካል የሆነውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመንጪነት መጋቢት ወር 2013 በይፋ ግንባታው የተጀመረው በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ከአዲስ አበባ 127 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በሚገኘው የወንጪ ደንዲ ሐይቅ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ሎጅ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዕድገት አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግና ለአካባቢው ኅብረተሰብም ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ የሚፈጥር ነው።

ፕሮጀክቱ አካባቢውን በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ልዩ የቱሪዝም መስሕብ ከማድረጉም በሻገር የኢኮኖሚያዊ ፋይዳውና የሀገሪቱን ገጽታ ከመለወጥ አንጻር ፋይዳው ትልቅ ነው። ወንጪ ደንዲ የኢኮ- ቱሪዝም ፕሮጀክት በሕዝብ ትብብር የተሠራ በመሆኑ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግና ለ560 ሰዎችም የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው።

የኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክቱ እስከ 39 ኢኮሎጆችና ሌሎች ተጨማሪ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያቀፈ ነው። በፕሮጀክቱ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች፣ ባሕላዊ ሎጅና ሬስቶራንት፣ የአትሌቲክስ መንደር፣ የጎልፍ ክለብ ከመካተታቸውም ባሻገር በስፋት በአደጉት ሀገራት የሚገኙ ግዙፉ የመዝናኛና የውሃ ፓርኮችንም የያዘ ነው።

የወንጪ ደንዲ ሐይቅ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ሎጅ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች በአግባቡ በማወቅ፣ በመጠቀምና በመጠበቅ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ማሳያም ነው። ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ ሀብት ያላት ሀገር በመሆኗ ከመገፋፋትና ከመጣላት ወጥተን ሀብቶቻችንን ማልማት ከቻልን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት መላቀቅ እንድምንችል የወንጪ ደንዲ ሐይቅ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ሎጅ አንዱ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው።

የወንጪ ደንዲ ሐይቅ ዘመናዊ የኢኮ-ቱሪዝም ሎጅ ሁሉ ሌሎች የቱሪዝም ሀብቶቻችንን የብልጽግናችን መሠረት እንዲሆኑ ለማስቻል ለቱሪዝም ዘርፉ እንቅፋት የሆነውን ጦርነትና ግጭት በማስወገድ ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችን እንድትጠቀም ማድረግ ያስፈልጋል።

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You