
አዲስ አበባ፡- ንባብን የማረሚያ ቤቶች ባህል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት አገልግሎት ገለጸ፡፡
አገልግሎቱ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር በቃሊቲ ማረሚያ ቤት “በመጻሕፍት እንታረም” በሚል መሪ ሃሳብ ትናንት የንባብ ቀን አውደ ውይይት ወቅት አካሂዷል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖ አምላክ መዝገቡ እንደገለጹት፤ የንባብ ጽንሰ ሃሳብ ወደ ማረሚያ ቤት መግባቱ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ንባብ የአእምሮ ማበልጸጊያ እንደመሆኑ በንባብ የተለወጠ አእምሮ ብዙ ነገሮች የመለወጥ አቅም አለው፡፡
በመሆኑም ንባብን የማረሚያ ቤቶች ባህል ለማድረግና የማረሚያ ቤቶችን ቤተመጻህፍት ለማደራጀት በኮሚሽኑ እየተሠራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
በዚህ ረገድ ከዚህ ቀደምም ከማረሚያ ቤቶች ጋር በርካታ ሥራዎች በትብብር ሲሠራ እንደነበር ያወሱት ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይም የቤተመጻህፍት አገልግሎቱ ከኮሚሽኑ ጋር የሚሠራው ሥራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የተሃድሶ ልማት ምክትል ኮሚሽነር ደስታ አስመላሽ በበኩላቸው፣ እውቀት ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፈውና አስተሳሰብ የሚቀየረው በንባብ ነው ብለዋል፡፡
የማረሚያ ቤቶችን ቤተመጻህፍት የማጠናከር ሥራ ለታራሚዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ ማረሚያ ቤቶች ለታራሚዎች የሚሰጡትን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ጥራትና ስፋት ለመጨመር እየሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በራሱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የሌሎችን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦችን ደጋፍ የሚሻ መሆኑን ጠቅሰው፤ የትብብር ሥራዎችን በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ጋር እየሠራ ያለው የትብብር ስራም የዚሁ አካል ነው ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ እንዳሉት፣ የሕግ ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከሌላው ማኅበረሰብ በተሻለ የንባብ ጊዜ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህም ከብቸኝነት ስሜት ወጥተው ጊዜያቸውን ከመጻሕፍት ጋር እንዲያሳልፉ፣ እውቀት እንዲሸምቱ ብሎም ከማረሚያ ቤት ውጪ ስላለው ሁኔታ እንዲረዱ በማድረግ ረገድ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡
ዓለም አቀፍ የታራሚ ስምምነቶች ላይም ታራሚዎች የማንበብ መብታቸውን ሊከበር እንደሚገባና የንባብ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ የተደነገገ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ረገድ ኮሚሽኑም ይህንን በመተግበር የታራሚዎችን አገልግሎት ለማስፋት በቀጣይም የትብብር ሥራዎችን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት 170 ሺህ ብር የሚያወጣ የመጻሕፍት ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፤ በአውደ ውይይቱ የተለያዩ ደራሲያን፣ ከያኒያን እና የተለያዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ተሳትፈዋል፡፡
ዮርዳኖስ ፍቅሩ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም