እንደምን ሰነበታችሁ… ዛሬ የማካፍ ላችሁ ኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክ ያላት ብቻ ሳትሆን የረጅም ዘመናት ታሪኳ በልዕልና የታጀበ እንደነበር የሚያሳየውን የታላቁን ንጉሰ ነገሥት የአፄ ካሌብን ታሪክ ነው። ይህን ታሪክ እንዳካፍላችሁ ያነሳሳኝ ሰሞኑን (ግንቦት 20 ቀን) የአፄ ካሌብ እረፍት መታሰቢያ በመሆኑ ነው፡፡ የመረጃው ምንጮች ልዩ ልዩ የታሪክ ጽሑፎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ክርስትና ከተሰበከ ወዲህ ከነገሱ የአክሱም ነገሥታት መካከል ከንጉሥ ኢዛና ቀጥሎ ከፍ ያለ ስም ያላቸውና ከፍተኛ ተግባርም ያከናወኑ ናቸው። በአፄ ካሌብ ዘመነ-መንግስት ኢትዮጵያ ከከፍተኛ ብልፅግና እና የስልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰች ቢሆንም፤ የሰላም ጊዜ ግን አልነበራትም። አገሪቱ በውስጥም ሆነ በውጭ የተለያዩ ጦርነቶች ነበሩባት። ስለአፄ ካሌብ ዘመነ ስልጣኔና ጦርነት ብዙ ማስረጃዎች በድንጋይ ላይ ከተቀረፁ ፅሁፎች ተገኝተዋል።
የአፄ ካሌብን ታሪክ አስመልክቶ በተወሳ ቁጥር በብዙ ፀሐፊዎች የሚጠቀሰው ንጉሱ ወደ ደቡብ አረቢያ (የአሁኑ የመን) ያደረጉት ታሪካዊ ዘመቻ ነው። አፄ ካሌብ ወደ ደቡብ አረቢያ ያደረጉት ዘመቻ ዓላማ ሀይማኖታዊ፤ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ፍላጎት እንደነበረው ታውቋል። እንደታሪክ ማስረጃዎች ከሆነ አፄ ካሌብ ወደ ደቡብ አረቢያ የዘመቱበት ዋነኛ ምክንያት ፊንሐስ የተባለው ንጉሥ በደቡብ አረቢያ አካባቢ በነበሩ ክርስቲያኖች ላይ የፈፀመውን ግድያ ለመበቀል ነው፡፡ ይሁን እንጂ፤ ከአጼ ካሌብ በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ ነገሥታትም ወደ ደቡብ አረቢያ እየዘመቱ የአካባቢውን ሕዝቦች ያስገብሩ እንደነበር በታሪክ መዛግብት ላይ መስፈሩ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይህ ደግሞ የነገሥታቱ ዘመቻ ሃይማኖታዊ ይዘት ብቻ እንዳልነበረው ማሳያ ተደርጐ ይጠቀሳል፡፡
ከአፄ ካሌብ በፊት የነበሩት የአክሱም ነገስታት የጦር አበጋዞቻቸውንና እንዲያም ሲል አልጋ ወራሾቻቸውን እየላኩ በደቡብ አረብ ውጊያ አድርገዋል። ነገር ግን፤ ንጉሡ ራሱ የጦርነቱ መሪ በመሆን ከኢትዮጵያ ውጭ ውጊያ ያካሄደ ንጉስ አፄ ካሌብ የመጀመሪያው እንደነበሩ የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ። አፄ ካሌብ ጦርነቱን አውጀውና ሰራዊታቸውንም ይዘው ባህር ተሻግረው ለዘመቻ ከመሄዳቸው በፊት የሕዝቡን ድጋፍ ጠይቀዋል።
በዚያን ዘመን ሕዝቡ የሃይማኖት መሪዎችን አጥብቆ ያዳምጥ ስለነበር “የአክሱም ህዝበ ክርስቲያን ርቀው እንዳይሄዱ” የሚለውን ትዕዛዝ በማንሳት ወደ ደቡብ አረቢያ ሄደው ለሚያደርጉት ጦርነት ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የነበሩትን አቡነ ጴንጤልዮንን ጠየቁ። አቡነ ጴንጠልዮንም ሙሉ ድጋፋቸውን ከመስጠታቸውም በላይ ጦርነቱን በአሸናፊነት አጠናቅቀው በክብር ወደመናገሻ ከተማቸው አክሱም እንደሚመለሱ ያላቸውን መልካም ምኞት ገለፁላቸው። አፄ ካሌብ ይህን መሰል ማበረታቻ ከጳጳሱና በእሳቸው በኩል ከሕዝቡ ካገኙ በኋላ ሰራዊታቸውን የሚያጓጓዙባቸውን ብዙ መርከቦች አዶሊስ አጠገብ በሚገኘውና ገበዛን በሚባለው የመርከብ መስሪያ ቦታ ማሰራት ቀጠሉ።
በአፄ ካሌብ ዘመን የኢትዮጵያን መርከቦች አሠራር አስመልክተው የባዛንታይን የታሪክ ፀሐፊዎች መጠነኛ ሃሣብ አስፍረው አልፈዋል። እንደነርሱ አገላለፅ ከሆነ፤ በዚያን ዘመን የኢትዮጵያ መርከቦች የሚገጣጠሙት በሚስማር ሳይሆን በገመድ ነበር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በዚያን ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ ብረት ባለመመረቱ ነበር ብለው ጽፈዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን የመርከቦቹ መጠን በሮማ ግዛት አፄ እና በአካባቢው ከሚሰሩት መርከቦች ያነሰ አልነበረም፡፡
አፄ ካሌብ ወደ ደቡብ አረቢያ የዘመተውን ሠራዊት በባህር ላይ ያጓጓዙባቸው መርከቦች ብዛት 230 ያህል እንደነበሩ የጽሑፍ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በነዚህ መርከቦች የተጓጓዘውን የአፄ ካሌብ የሠራዊት ብዛት በተመለከተ አንዳንዶቹ የጽሑፍ ማስረጃዎች 32 ሺህ ነው ሲሉ፤ ሌሎቹ ቁጥሩን ወደ 70 ሺህ ከፍ ያደርጉታል፡፡ አፄ ካሌብ ሠራዊታቸውን አጓጉዘው ደቡብ አረቢያ በደረሱ ጊዜ የደቡብ አረቢያ መሪ የአክሱም ንጉሥ ጦር በመገስገስ ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ነበርና መርከቦቹ በወደቡ ላይ ጭነታቸውን እንዳያራግፉ ረጅምና የማይበጠስ ሰንሰለት አጋደመበት። ይህንንም የሚጠባበቁ ወታደሮች ዘብ አቆመበት፡ ፡ በዚህም ምክንያት የአፄ ካሌብ መርከቦች ደቡብ አረቢያ ሲደርሱ መልህቅ ጥለው ጦሩን ወደየብሱ ለማራገፍ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ከላይ የፀሐዩ ሙቀት፤ ከታች ደግሞ ቅዝቃዜው ሲያጠቃው የሠራዊቱ መንፈስ እንዳይዳከም ያሰቡት ንጉሡ ከወደቡ ራቅ ብለው በመጓዝ አመቺ በሆነ ቦታ እየቆሙ የተወሰነውን ወታደር አራገፉና ወደቡን ይጠብቁ የነበሩትን ወታደሮች ከበስተጀርባቸው ሄደው አጠቋቸው፡፡ ሰንሰለቱም ተበጠሰና ለብዙ ቀናት ባህር ላይ ይጉላላ የነበረው ጦር ወርዶ የደቡብ አረቢያውን ጦር በብርቱ ተዋግቶ ድል አደረገ፡፡ አፄ ካሌብ በመጨረሻ በአሁኑ የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ደርሰው ሰላምን ካፀኑ በኋላ በቂ የጦር ኃይል ትተው በድል አድራጊነት ወደመናገሻ ከተማቸው ወደ አክሱም ተመለሱ።
ከዘመቻቸው ከተመለሱ በኋላም “ይህን ሁሉ ላደረገልኝ አምላክ ምን ላድርግለት” ብለው በማሰብ ዙፋናቸውንና መንግሥታቸውን ለልጃቸው ለአፄ ገብረ መስቀል ትተው፤ መንነው አቡነ ጴንጠልዮን ገዳም ገብተው ለ12 ዓመታት ያህል ቆይተው ግንቦት 20 ቀን 525 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ አፄ ካሌብ ባሕር ተሻጋሪም መናኝም ንጉሥ ነበሩ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
አዎን! ኢትዮጵያ ባሕር ተሻግረው የሚዋጉና የሚያሸንፉ ገናና ነገሥታት የነበሯት አገር ናት፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
አንተነህ ቸሬ