መልካም ድባብ የፈጠረው የዩኒቨርሲቲዎች አቀባበል

 ከአንዳንድ ጉዳዮች አኳያ ካየነው ሳምንቱም ሆነ ወሩ፤ ወይም እያንዳንዱ ወቅት፣ አንዱ ከአንዱ ጋር እኩል አይደለም። ወይም፣ አቻነት አይስተዋልበትም። በመሆኑም በዓመቱ ውስጥ ያሉት 52 ሳምንታት መንትያ ናቸው ማለት አይቻልም። ይበላለጣሉ፣ ይለያያሉም። ልዩነታቸው ደግሞ እንደ ነጮቹ በቀን ብዛትና ማነስ ሳይሆን በሚያስተናግዷቸው ሀገራዊ ሁነቶች ነው።

ያለፉት ሳምንታት፣ በተለይም ያለፈው ሳምንት በከፍተኛ ትምህርት (ዩኒቨርሲቲዎች) አካባቢ ደምቆና አሸብርቆ ነው ያለፈው። ምናልባትም ቀደም ባሉት ጊዜያት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመረቀ ሰው ጉዳዩ ያኔ የሌለና እንግዳ ነገር በሚመስል መልኩ ሳምንቱ በየተቋማቱ ልዩ ነበር። ይህ “መቼ ተጀመረ፣ እንዴት ተጀመረ፣ ለምን ተጀመረ?” የሚሉ ጥያቄዎችን እስካላስነሳ ድረስ የሁነቱ ዕድሜ ቅርብ መሆኑን መግለፅና በሳምንቱ ውስጥ የነበረውን ገፅታ አስመልክቶ የተወሰኑ ሃሳቦችን ማንሳት ይቻላል።

ምንም እንኳን ነባሩና ዘመናትን ያስቆጠረው የትምህርት ቤቶች የመከፈቻ ጊዜ (ወር) መስከረም ቢሆንም እራሳችን ባመጣነው ጣጣ ይህ በመስከረም የመክፈትና በሰኔ የመዝጋቱ ጉዳይ ተግዳሮት እየገጠመው ከመጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡በመሆኑም፣ ዛሬ ዛሬ የትምህርት ቤቶች የመክፈቻም ሆነ መዝጊያ ሰሞን ከ“አንፃራዊ ሰላም” ጋር እየተያያዘ መሆኑና “አንፃራዊ” የተባለው ሰላምም እየራቀ በመምጣቱ የመክፈቻና መዝጊያ ወቅቶች እንደየአካባቢውና እንደ ተቋሙ ወቅታዊ ይዞታ እየተለያየ መጥቷል።

መለያየት ብቻም አይደለም፤ አንዳንድ አካባቢዎች መክፈቱም ሆነ መዝጋቱ ከናካቴው እየተረሳ የመጣ ይመስል የትምህርት ተቋማት ሥራ አቁመው ተማሪዎች በመባከን ላይ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን በአማራ ክልል በሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በማህበራዊ ድረገፆች (በተለይም በቴሌግራም) “ያለ ትምህርት ቁጭ ብለን ወራት አልፈዋል፤ ፍትህ እንሻለን” ከሚለው በላይ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም።

በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ፣ ድሮ በማያወላውል መልኩ “መስከረም” መክፈቻ ሲሆን፣ “ሰኔ” መዝጊያ ነው። ዛሬ ይሄ አለ? የለም። ባለመኖሩ ምክንያትም የትምህርት ተቋማት የመክፈቻና የመዝጊያ (የማስመረቂያም ጭምር) ወቅቶች (ወራት) ዓመቱን ሙሉ ለማለት በሚያስደፍር ደረጃ ሲከናወኑ ይታያል። ለአንዱ የመዝጊያ ወቅት የሆነው ለሌላው የመክፈቻ ይሆንና ግራ እስኪያገባን ድረስ ግር ይለናል።

ይህ የመክፈቻና የመዝጊያ መዘበራረቅ (በክረምቱ መርሀ-ግብር ሳይቀር) በመክፈትና መዝጋት ብቻ የሚቆም እንዳልሆነ ይታወቃል። ወደ ክፍል ውስጥ መማር-ማስተማሩ ሁሉ ይገባና “ክራሽ ፕሮግራም”፣ “ሰፕሊመንታሪ”… የሚሉ፤ ድሮ ብዙም የማይታወቁ የግር ግር መማር-ማስተማር ተግባራት እንዲካሄዱ አድርጓል። ተማሪው ስለ “ሀ” ሳይረዳ “ፐ” ላይ የሚያደርሱት እነዚህ ፕሮግራሞች ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለትምህርት ጥራት ውድቀት የራሳቸውን አስተዋፅኦ አላበረከቱም ማለት ስለማይቻል ወደ ድሮው የመክፈቻና መዝጊያ ሥርዓት ይመለሱና ሁሉም ነገር በተረጋጋ መልኩ ይከናወን ዘንድ የሚመለከተው ሊረባረብ ይገባል፡፡

የባለፈው ሳምንት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድምቀትና አሸብርቆት እንመለስ። ከሀዋሳም እንጀምር። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሳሙኤል ጂሎ እንደሚገልፁት፣ ዩኒቨርሲቲው 4 ሺ የተፈጥሮ ሳይንስ እና 2 ሺ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን በድምሩ 6 ሺ ተማሪዎችን ተቀብሎ ወደ መማር-ማስተማር ተግባሩ ገብቷል።

ሌሎቹስ? አሁን፣ ለ2016 ዓ∙ም የትምህርት ዘመን የማለፊያ (መቁረጫ) ነጥብ በማምጣት በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን 832 አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተቀብሎ የመዘገበውን አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጠቅሰን፤ በሀገሪቱ ከሚገኙ 15 የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው ዲላ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ ምዝገባና ቅበላን አጠናቅቆ ወደ ተግባር መግባቱን አመልክተን፤ አስፈላጊዎቹን የመመገቢያ፣ የማስተማሪያ እና የመኝታ አገልግሎቶች በማሟላት ለዚሁ ዓመት (የትምህርት ዘመን) የተመደቡለትን 364 የተፈጥሮ እና የማህበራዊ ሳይንስ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተቀብሎ የማስተማር ሥራውን መጀመሩን የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ መግለፃቸውን አንስተን ወደ መደወላቡ እንሂድ።

በ2016 ዓ.ም በመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ አዲስ የተመደቡ፤ እንዲሁም፣ በ2015 ዓ.ም የሪሜዲያል ፕሮግራም የተከታተሉና የማለፊያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ምዝገባ ታኅሣሥ 15 እና 16/2016 ዓ.ም መሆኑን ያስታወቀው መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩ ተግባርም ታኅሣሥ 17/2016 ዓ.ም እንደሚጀምር አስታውቋል። ጅግጅጋስ?

“ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ.ም የድህረ-ምረቃ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች (በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን የድህረ-ምረቃ የመግቢያ ፈተና (GAT) ወስደው ያለፉ አመልካቾች) ምዝገባ ከታኅሣሥ 05 እስከ 11/2016 ዓ.ም” ያካሄደና ወደ ሥራ የገባ መሆኑም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው የዚሁ ወር የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ቅበላና ምዝገባ ክንውን አካል ነው። ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንምጣ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2016 የትምህርት ዘመን በመደበኛ መርሐ ግብር የመጀመሪያ ዲግሪ አዲስ የተመደቡ ተማሪዎች የማመልከቻ እና ወደ ዩኒቨርሲቲ ሪፖርት ማድረጊያ ጊዜውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ይፋ በማድረግ ቅበላውን ታኅሣሥ 09፣ 10 እና 11/2016 ዓ.ም በደመቀና ባሸበረቀ ሁኔታ ሲያካሂድ ቆይቷል። የምዝገባው ፕሮግራም በተለያዩ ዝግጅቶች የታጀበ ሲሆን፣ ከሚኒ ሙዚቃ ባንድ ጀምሮ የተለያዩ ድርጅቶችና ስፖንሰር አድራጊዎች ተገኝተው ለፕሮግራሙ ድምቀትን አጋርተዋል።

እንደ ሌሎቹ ተቋማት ሁሉ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅበላ ዝግጅት ታስቦበትና ታቅዶ ስለመሆኑ ከዋናው ካምፓስ መግቢያ በር ጀምሮ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚገልፁ ሲሆን፣ ከፌዴራል ፖሊስ ጀምሮ ያሉት የፀጥታ ኃይላት፣ ተማሪዎቹን መረጃዎቻቸውን እየተመለከቱ የሚያረጋግጡ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች፣ ልዩ መለያን የለበሱና ልጆቹን (ሻንጣቸውን ተቀብሎ እስከ ማገዝ ጭምር) ይዞ ወደ ውስጥ የሚያስገቡና የሚያስተናግዱ የፈቃደኞች (ቮለንቲየርስ) ቡድን አባላት፣ ውስጥ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ባንኮች ጊዜያዊ ቢሮዎች፣ ነፃ ለስላሳ መጠጥ አቅራቢዎች፣ እዚህም እዛም የተሰቀሉና የተለጠፉ የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” መልእክቶች ወዘተ ተጠቃሽ ናቸው።

በዚሁ ምክንያትም የአዲስ ገቢ ተማሪዎች ፊት በደስታ ፈክቶ የሚታይ ሲሆን፣ አንድም የእንግድነትና ባይተዋርነት ስሜት ሲንፀባረቅባቸው አልተስተዋለም። በግቢው ውስጥ ተዘዋውረን እንደተመለከትነውም አዲስ ገቢዎቹ ከነባሮቹ ጋር በእኩል የመንፈስና የስሜት ደረጃ ላይ ሆነው ነው ያገኘናቸው። እዚህም እዛም ባሉት መዝናኛ ክበባት ውስጥ ሻይ/ቡና ሲባባሉ፤ በየጥላዎቹ ስርና ሣር ላይ ጋደም እያሉ ሲጫወቱ ነው ያየናቸው።

በቡድን በቡድን ወደተቀመጡት በማጋደል ከውጭ ወደ ውስጥ ሲገባ በስተ ኬኔዲ ቤተመጻሕፍት በኩል ሶስት ሆነው፣ ጋደም ብለው ከሚጨዋወቱት ጋ ጠጋ አልን። ከሰላምታና የማንነት መረጃ ልውውጥ በኋላም በቀጥታ ወደ ጉዳያችን ገባን።

ባነጋገርኳቸው ቅደም ተከተል ሲቀመጡ፤ ሰጠኝ ደፋሩ፣ ደመረ መንግሥቱ እና ዮሐንስ ሽታ ይባላሉ። ሶስቱም የአንድ አካባቢ ልጆች ናቸው (ሰሜን ሸዋ፣ መራቤቴ)፣ ሶስቱም አንድ ትምህርት ቤት (ፌጥራ) ነው የተማሩት፤ አሁን ደግሞ ሶስቱም አንድ ዩኒቨርሲቲ፣ አንድ ካምፓስ ደርሷቸው ዘና፣ አረፍ ባለ መልኩ፣ ለምለሙ ሳር ላይ ጋደም ብለው የሆድ የሆዳቸውን ይጨዋወታሉ።

ለሶስቱም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ነበር ያቀረብኩላቸው። የመጀመሪያው “ምን ተሰማችሁ?” የሚል ሲሆን፣ የሶስቱም መልስ “ደስታ” የሚል ነበር።

“አቀባበሉን እንዴት አገኛችሁት” ለሚለውም፣ “ያልጠበቅነው ነው። በርግጥ በፊትም ቢሆን ችግር ይገጥመናል ብለን አላሰብንም። ግን ደግሞ በዚህ መልኩ ይቀበሉናል ብለንም አላሰብንም። በመሆኑም፣ አቀባበላቸው ትንሽ ለየት ብሎብናል፤ ያስደስታል።” በማለት ነው የመለሱት።

“ቤተሰቦቻችሁ እንዴት ሆነው ይሆን፣ ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ሌሎች የሚያውቋችሁም ሆኑ ወዳጅ ዘመዶቻችሁ ሊጨነቁ ይችላሉ። ለእነሱ ምን የምትሏቸው ነገር አለ?” ለሚለው ድንበር ተሻጋሪ ጥያቄያችንም “በደህና ደርሰናል። ምግብም ጀምረናል። መኝታ ክፍልም ተሰጥቶናል። ሁሉም ተደርጎልናል። የቀረን ትምህርታችንን በትጋት መከታተል ብቻ ነው። በመሆኑም፣ ምንም የሚያሳስባችሁ ነገር የለም እንላቸዋለን።” የሚለውና ሶስቱም የተስማሙበት፤ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ያስተላለፉት መልእክት ነው።

ምድቡ አምስት ኪሎ (ቴክኖሎጂ ፋክልቲ) የሆነው የአዲስ አበባው የአብፀጋ ደሳለኝም ከእነ ሰጠኝ፣ ደመረ እና ዮሐንስ የተለየ የነገረን ነገር የለም፡፡ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ማለፉ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ ውጤት ላመጡ 1 ሺ ተማሪዎች “በምርጫቸው” በሚል በወሰነው መሠረት እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመመደቡ ደስተኛ መሆኑን አጫውቶናል። ከዚህ ከአብፀጋ ስኬት መረዳት የሚቻለው ከፍተኛ ውጤት ማምጣት ጥቅሙ ማለፍ ብቻ ሳይሆን የልዩ ዕድል ተጠቃሚነትንም ያመጣልና የወደፊት ተፈታኞች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጡት ይገባል እንላለን።

“በየትኛው የትምህርት መስክ፣ ማለትም የትኛውን የጥናት መስክ ነው መከታተል የምትፈልጉት፤ ፍላጎትና ዝንባሌያችሁ የትኛው ዘርፍ ነው?” ለሚለው ጥያቄያችንም ሰጠኝና ደፋሩ ኢኮኖሚክስ ማጥናት እንደሚፈልጉ የነገሩን ሲሆን፤ የዮሐንስ ምርጫ ግን ሕግ ነው፡፡ “አሁን በትምህርት ላይ ላሉት፣ ለታናናሾቻችሁ ምን መልእክት ታስተላልፋላችሁ?” ላልናቸውም፤ መልሳቸው “በርትተው መማር፣ ጥሩ ውጤት በማምጣት ዩኒቨርሲቲ መግባት አለባቸው።” የሚል ነው።

በደቡብ ሱዳን፣ ጁባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በ2023/2024 የትምህርት ዘመን በኢትዮጵያ በሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የነፃ ትምህርት ዕድሉን ላገኙና ተጠቃሚ ለሆኑ 120 ተማሪዎች የሽኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ የነበረ መሆኑ፤ ነፃ የትምህርት ዕድሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል በአቅም ግንባታ እና በሰው ኃይል ልማት ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ፤ እንዲሁም፣ ለተጨማሪ 120 ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ መሰጠቱን በደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ባለሥልጣን አምባሳደር ነቢል ማህዲ አማካኝነት ከኤምባሲው የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

እነዚህ ተማሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት በሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ደመቅና ሸብረቅ ብለው ያለፉት የቅበላ ፕሮግራሞች አካል መሆናቸውን እዚህ ጋ ጠቅሶ ማለፍ ያስፈልጋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተን በነበረበት ወቅት የተመለከትነውም ይህንኑና የነፃ ትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚዎች በቡድን በቡድን ሆነው በጊቢው ውስጥ ሲንሸራሸሩ ነው። ለተጨማሪ 120 ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በሁለተኛ ዲግሪ መሰጠቱን ከኤምባሲው የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡

ይህ እየተነጋገርንበት ያለው ጉዳይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውጭ በሆኑት እና እራሳቸውን ችለው በሚንቀሳቀሱ ተቋማትም እየታየ ያለ ጉዳይ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢ ማሳያዎች ናቸው። ኅዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ላምበረት በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ዝግጅታቸውን አጠናቅቀው ሰልጣኞችን በመቀበል ላይ ናቸው።

መግለጫውን የሰጡት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት ከሆነ “በ2016 ዓ.ም 844 ሺህ 384 የሚሆኑ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ወስደዋል። ከእነዚህ ውስጥ በእኛ ምልከታ 632 ሺህ 587 የሚሆኑት ወደ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ይመጣሉ የሚል ግምት አለን” ያሉ ሲሆን፣ “የሰው ኃይል ለመቀበል የተሻለ ዝግጁነት አላቸው ያልናቸውን የመንግሥትና የግል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማትን ፈትሸናል ያሉት ሚኒስትሯ፣ እስካሁን ባለው ከ28 ሺህ በላይ የሚሆኑ አሰልጣኞች፣ ወደ 1ሺህ 400 ገደማ የተሻለ ብቃት ያላቸው ማሰልጠኛ ኮሌጆች” እንዳሉም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ በዓመት 600 ሺህ ተማሪዎችን ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና የመቀበል አቅም መፈጠሩን ከዚህ በፊት ሚኒስቴሩ ማስታወቁም ይታወሳል።

በጥቅሉ ያለፈው ሳምንት በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ለ2016 ዓ∙ም የትምህርት ዘመን የማለፊያ (መቁረጫ) ነጥብ በማምጣት በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡላቸውን አዲስ ገቢ ተማሪዎች በልዩ ሥነ ሥርዓት የተቀበሉበት፣ አዲስ ገቢ ተማሪዎቹም በልዩ መስተንግዶና አቀባበሉ የተደሰቱበትና በቀናት ውስጥ የነባር ተማሪነትን መንፈስ የተላበሱበት ወቅት ሆኖ አልፏል።

ይህን የአቀባበል ጉዳይ እንደ ማሳያ አድርገን ወስደን እዚህ ጠቀስነው እንጂ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አቀባበል ተደርጎ ሁሉም ገብተዋል ማለታችን አይደለም። ያልገቡ አሉ። የገቡት የተደረገላቸውን አቀባበልና ያገኙትን የመንፈስ እርካታ ያልገቡትም እንደሚያገኙት ይጠበቃል።

 ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You