አዲስ አበባ ፡- የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት 150 ሺህ ዲጂታል መታወቂያዎችን ወደ ሀገር ማስገባቱን አስታወቀ:: በሁለት ወር ውስጥ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል::
የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የአይቲ ዳይሬክተር አቶ ቃልኪዳን ገበየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅ እንደገለጹት፤ ዲጂታል መታወቂያው የኤንኤፍሲ (NFC) ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ሲሆን፤ ይህም መታወቂያው ያለ ምንም ንክኪ በሴንሰር እንዲሰራ ያደርገዋል::
ይህ ዲጂታል ካርድ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን የወረቀት መታወቂያ ላይ ያሉትን ችግሮች የሚቀርፍ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም የቀድሞ መታወቂያ በቀላሉ መታተም የሚችል በመሆኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየገጠመ ያለውን የፎርጂድ መታወቂያ መስፋፋት የሚያስቀር ነው ብለዋል::
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ መታወቂያው ዲጂታል ነው ሲባል የአንድን ሰው ሙሉ መረጃ የሚይዝ ነው:: በአውቶቡሶቹ ላይም ካርዱን የሚያረጋግጥ ሶፍት ዌር የሚገጠም መሆኑን ገልጸው፤ የካርድ ማረጋገጫው ወይም “ቫሊዴተሩ” ተገልጋዩ ዲጂታል ካርዱን ይዞ ወደ አውቶቡሱ በሚቀርብበት ወቅት ሙሉ መረጃውን የሚያወጣና የሚተነትን ይሆናል ብለዋል :: ተገልጋዩ የያዘው ካርድ ትክክል ካልሆነም ድምጽ በማውጣት ልክ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል::
ካርዶቹን የሚያነብ ሶፍት ዌር እየለማ ያለው ዘፕሪሚየም ኢትዮጵያ በተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በየጊዜውም ካርዶቹ ላይ ሙከራ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል::
ካርዶቹ ከጥራትም ሆነ ከጥንካሬ አንጻር ቢተጣጠፉ እንኳን የማይሰበሩ በመሆናቸው ተገልጋዮች ካርዶቹን ከአስር ዓመት በላይ እንዲጠቀሙባቸው ታስቦ የተሰራ ነው::
ካርዱ በሀገሪቱ ያለውን የወረቀት ፍጆታ በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በተጨማሪም የቁጥጥር እና አገልግሎት ቀልጣፋነትን የሚጨምሩ ናቸው ብለዋል ::
መታወቂያዎቹ የመንግሥት ሠራተኛው ከትራንስፖርት አገልግሎት በተጨማሪ እንደ ኤቲኤም(ATM) ካርድ ብር በመሙላት ሌሎች አገልግሎቶችን መፈጸም እንዲችል የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል::
በአሁኑ ሰዓት ታትመው ወደ ሀገር የገቡት 150 ሺህ ካርዶች ከሁለት ወር በኋላ በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ይሆናሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በዚህ ዓመትም የሙከራ ሥራውን በማጠናቀቅ በቀጣዩ ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል::
ዳግማዊት አበበ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም