የጋራ አደጋ የሆነውን ወንጀል በጋራመከላከል ይገባል

 የሰው ልጅ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎችም እንቅስቃሴና መስተጋብሮቹ ሰላማዊ ሆነው በሰላም እንዲከናወኑለት ይሻል፡፡ ይሁን እንጂ ሁልጊዜ እንዳሰበውና እንደተመኘው ወጥቶ ላይመለስ፤ ሰርቶም ውጤታማ ላይሆን ይችላል፡፡ ይሄ የሰው ልጅ ወጥቶና ሰርቶ በመግባት ሂደት ውስጥ በዚህ መልኩ የሚገጥሙት እክሎች ደግሞ ከወንጀል ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

ወንጀል በተለያየ መልክና ደረጃ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን፤ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ሊፈጸም የሚችል ነው። ከግል ቂምና ያልተገባ መሻት ጀምሮ፤ ከተራ ሌብነት ከፍ እስካለው የሰው ልጆችን ሕይወት እስከመንጠቅ የሚደርሱ በብዙ ገጻቸው የሚዘረዘሩ የወንጀል ተግባርና ዓይነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ወንጀሎች ጊዜንና ሁኔታን ማዕከል አድርገው ሊቀንሱ አልያም ሊበራከቱ የሚችሉበት እድልም ስለመኖሩ በርካታ ማሳያዎችም አሉ፡፡

ለወንጀል መበራከት እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው የሰላም መደፍረስና ግጭት ነው፤ በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ ከተራ ሌብነት ጀምሮ፣ ዘረፋ፣ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ እንዲሁም የጅምላ ፍርድን የመሳሰሉ የወንጀል ተግባራት ሲፈጸሙ ይስተዋላል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም በተለይ በበዓላት ሰሞን እና ሕዝባዊ ሁነቶች በሚኖሩባቸው አጋጣሚዎች እነዚህ ወንጀሎች ይበራከታሉ፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም አሁን ላይ በአንድ በኩል ሰላምና አለመረጋጋቱ፡፡ በሌላ በኩል የበዓላትና ሕዝባዊ በዓላት ድባቡ እየተቃረበ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት የመከሰቻ ምቹ ሁኔታዎች በአንድ የሚገጣጠሙ ናቸው። በዚህም የወንጀል ተግባራት ሊበራከቱ እንደሚችል ይገመታል፡፡ የሰላም መደፍረሱ ለወንጀለኞችና ሕገወጦች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ ከመሆኑ ባሻገር፤ በዓላትና ሕዝባዊ ሁነቶች ሲደመሩበት ወንጀለኞች ሕዝብን መስለው ለመንቀሳቀስም፤ ግርግሩንም ለወንጀሉ ማሳለጫ ለመጠቀምም ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡

የሰሞኑ የጉምሩክ ኮሚሽንም ሆነ የፖሊስ ኮሚሽን መረጃዎች በዚህ ረገድ የሚጠቁሙት ሃቅ አለ፡፡ ለምሳሌ፣ በተለያየ ጊዜ የሚወጡ የፖሊስ መረጃዎች እንዳመለክቱት፣ በኮትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ዝውውሩ ሂደት ከውጭ የሚገቡም፣ ወደ ውጭ የሚወጡም እቃዎች አሉ፤ ከነዚህ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ መድኃኒት፣ የጦር መሳሪያዎች፣ ተተኳሾች፣ ምግብ ነክ እቃዎች፣ አልባሳት፣ ኮስሞቲክስ፣ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ይሄን መሰል ሕገወጥ የወንጀል እንቅስቃሴ ደግሞ በማህበረሰቡ ጤና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ብሎም ሰላምና ደህንነት ላይ ከፍ ያለ አደጋን የሚፈጥር ነው፤ ይሄንን ተግባር ለመከላከልም ፖሊስ ከአጋር ተቋማት ጋር እንዲሁም በኅብረተሰቡ ትብብር ታግዞ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ከሰሞኑም የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች በጋራ በሰሩት የኦፕሬሽን ሥራ ከአንድ ሺህ የሚልቁ ተጠርጣሪዎችን ከነሕገወጥ ቁሳቁሶቻቸው በቁጥጥር ስር ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ፖሊስ ኮሚሽኖቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ መሠረት፤ የኅብረተሰቡን ሰላምና ደህንነት በማወክ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ከአንድ ሺ በላይ የሆኑት እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት፤ ለሕገወጥና ወንጀል ተግባራቸው የሚጠቀሙባቸው አራት ሽጉጦች፣ 68 የሽጉጥ ጥይት፣ አምስት ልዩ ልዩ መኪኖች፣ 64 የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች፣ 1461 ልዩ ልዩ የተሽከርካሪ ዕቃዎች፣ ሶስት ባጃጅ፣ አንድ ጀነሬተር፣ 290 ሞተር ሳይክሎች፣ ስምንት ፔዳል ብስክሌቶች አብረው ተይዘዋል።፡

ከእነዚህ በተጨማሪም 31 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ 1578 ልዩ ልዩ የሞባይል ስልኮች፣ 52 ታብሌት፣ 71 ላፕቶፕ፣ 12 ኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ስታብላይዘር፣ 58 ልዩ ልዩ የዲሽ ዕቃዎች፣ 48 ቴሌቪዥን፣ 44 ሲምካርድ፣ 10 የመንገድ ፍሳሽ ማስወገጃ የብረት ክዳን፣ ሁለት በግራይንደር፣ ከ5ኪሎ ግራም በላይ ካናቢስ አደንዛዥ ዕፅ፣ 1292 የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች እና 153 ልዩ ልዩ አልባሳት እንዲሁም በግለሰብ ቤት ተከማችቶ የነበረ ለግብይት የሚያገለግሉ 90 ከረጢት የኢትዮጵያ ሳንቲሞች በተመሳሳይ በኢግዚቢትነት ተይዘዋል፡፡

በተመሳሳይ በኦፕሬሽኑ 37 ቁማር ቤቶች እና 3241 የቤቲንግ ቤቶች የታሸጉ ሲሆን፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በቤት ውስጥ ጥይቶችን የሚያመርት አንድ ተጠርጣሪም ከ4052 የክላሽ ጥይት፣ 1297 ባዶ የክላሽ እርሳስና 1319 የክላሽ ቀለሀ ከሚያመርትበት ማሽኖች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

እነዚህ እና መሰል የወንጀል ድርጊቶች ታዲያ፣ ከግለሰብ እስከ ሀገር የሚያደርሱት ቀውስ ቀላል አይደለም። ሰዎች በልቶ የማደር፤ ሰርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት፤ ወልዶ የመሳም፤ ሌላው ቀርቶ ወጥቶ የመግባት ሕልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች አደጋቸው የአንድ ወገን ሳይሆን የሁሉም እንደመሆኑ፤ ወንጀሉን የመከላከል ሂደትም ለአንድ ወገን የሚተው ሳይሆን የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You