የታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወትየመመለስ ውሳኔ የሚያስመሰግን ነው

 አንድ ሀገር እንደ ሀገር እንድትጸናም ሆነ ሁለንተናዊ እድገት በማምጣት ለዜጎቿ ተስማሚና ተመራጭ የመኖሪያ ስፍራ ለመሆን ሰላም ወሳኝ ጉዳይ ነው ። ነገና ቀጣይ ቀናትን ቀርቶ መጪዎቹን ደቂቃዎች በተስፋ ለማሰብ የሰላም ጉዳይ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ከልማትና ከልማት ጋር የተያያዙ ብሩህ ነገዎችን አስቦ ለመተግበርም ሰላም አልፋና ኦሜጋ ነው።

ከዚህ የተነሳም ባለንበት ዘመን የሰላም ጉዳይ ከግለሰብ ፣ ከማህበረሰብና ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል። ዓለምም ከቀደሙ የሰላም እጦቶች / ግጭቶችና ጦርነቶች በመማር ፣ ተመሳሳይ የታሪክ ክስተቶች እንዳይደገሙ ከፍ ባሉ ድምጾች ስለ ሰላም እየጮኸ ይገኛል። በዚህም የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ከትናንት ዛሬ የተሻለ የሰላም አየር ሲነፍስ ይስተዋላል።

ይሄንን የሰላም አየር ከማንገስ አኳያ አሁን ላይ ዘመኑን እየዋጀ ያለው ችግሮችን በውይይትና በድርድር የመፍታት እሳቤ ነው፡፡ ይሄም በየትኛውም መልኩ ተከስተው ወደግጭት የሚወስዱ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በዘላቂነት በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዓለም በተሻለ ሰላምና መረጋጋት መንቀሳቀስ እንድትችል መተኪያ የሌለው አቅም እየሆነ ይገኛል። በዚህም ዓለም ብዙ ዋጋ ሊያስከፍሏት ከሚችሉ ችግሮች እራሷን መታደግ ችላለች።

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር የዚህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ አካል መሆኗን በመገንዘብ፤ እኛም ችግሮቻችንን በውይይትና በድርድር መፍታት ሲጠበቅብን፤ ዛሬን ሳይቀር ችግሮቻችንን በይዋጣልን ፤ እንሞካከር በሚል ሀገርና ሕዝብን ከፍ ያለ ያልተገባ ዋጋ በሚያስከፍል ፣ ዘመኑን በማይዋጅ፤ አሮጌ እና ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ብሩህ ነገዎቻችንን ለመሰዋት ተገደናል።

በቀደሙት ዘመናት አባቶቻችን ስልጡን እና ገናና የሆነች ሀገር በመፍጠር ከፍ ያለ ዓለም አቀፍ እውቅና ያልተቸሩትን ያህል ፤ እኛ ልጆቻቸው በልዩነቶቻችን ዙሪያ ቀልብ ገዝተን፣ በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብለን መነጋገር ፣ መወያየትና መስማማት ላይ መድረስ ባለመቻላችን ለዘመናት በግጭትና በጦርነት አዙሪት ውስጥ ለመሄድ ተገደናል ፡፡ በዚህም እየከፈልነው ያለው ያልተገባ ዋጋ ነገዎቻችንን አጨልመውብናል።

ዓይኖቻችንን ከፍተን ትናንቶቻችንን በአግባቡ ማየትና ከነሱ መማር አለመቻላችን ፤ ከሁሉም በላይ ለታሪክ ያለን አረዳድና አረዳዳችን የፈጠረውን የአስተሳሰብ መዛነፍ ለማረም በጎ ህሊና ማጣታችን፤ እንደ ሀገር በየዘመኑ መጥተው የሚሄዱ ትውልዶች ተስፋ ያደረጉትን ሕይወት ኖረው እንዳያልፉ አድርጓቸዋል። ይሄም የታሪክ ባለእዳ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል።

ይህ እውነታ ዛሬም በአዲስ የታሪክ ምእራፍ ውስጥ ሆነን፤ አዲስ የታሪክ ትርክት ለመፍጠር በብዙ መነቃቃት ውስጥ ባለንበት ወቅት ጥላ ሆኖ የለውጥ መንገዳችን ተግዳሮት ሆኖ ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ዛሬም ለታሪክ ካለን አረዳድና አረዳዳችን ከፈጠረው የአስተሳሰብ መዛነፍ የተነሳ፣ ሀገር እንደቀደሙት ዘመናት በግጭት አዙሪት ውስጥ ገብታለች።

እንደ ሀገር በብዙ ሆይታና እልልታ የጀመርነው ለውጥና ለውጡ ይዞት የመጣው ተስፈኝነት፤ ፍሬ አፍርቶ እንደ ሀገር ካለንበት አንገት አስደፊ ድህነትና ኋላ ቀርነት ለመውጣት ይህንን የአስተሳሰብ መዛነፍ ማረም የሚያስችል በጎ ህሊና ያስፈልገናል። የትናንቱን የጥፋት መንገድ ማውገዝ የሚያስችል የቆረጠ ማንነት መፍጠር ይገባናል።

ለግጭት እና ለጦርነት ከተሰጠው ጠመንጃና ኃይል ከሚያመልከው ስብእናችን በብዙ የጥፋተኝነት መንፈስ እና የልብ ስብራት በንሰሀ የተመለሰ ማንነት ያስፈልገናል። ያበላሸናቸውን ፣ በከንቱ ያመለጡንን ብዙ ትናንቶች ዛሬ ላይ ማካካስ የምንችለው ይህን እውነት በአግባቡ ስንረዳና ለዚህ እውነት ያለን ተገዥነት የእውነተኛ ማንነታችን መገለጫ ሲሆን ብቻ ነው።

ከዚህ አንጻር ቀደም ባለው ጊዜ በተለያዩ ምክንያቶች ጠመንጃ አንስተው ልዩነቶቻቸውን በኃይል ለመፍታት ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቡድኖች ጋር አብረው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፣ አሁን ላይ መንግሥት የሰጠውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው ለመመለስ የወሰኑ ዜጎቻችን ፣ ውሳኔያቸው የሚያስመሰግናቸው ነው፡፡ ስለሰላም የመጡበት መንገድም ለእነሱም ፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ሕዝብም ሆነ ለሀገር ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ሆኖም ግን ወደ ሰላም የሚመጡበት መንገድ በውስጣቸው የጥፋተኝነት መንፈስ እና የልብ ስብራት የፈጠረ፣ ጠመንጃ አንግበው ያበላሿቸውን ብዙ ትናንቶች መካስ የሚያስችል መሆን ይጠበቅበታል። ትናንትን ብዙ ዋጋ ያስከፈሉትን ሀገርና ሕዝብን የልብ ስብራት የሚጠግን ፤ ያጨለሙበትን ነገዎች ብሩህ የሚያደርግ ሊሆን ይገባል።

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You