መሀል መንገድ ላይ ነኝ፡፡ ዛሬም በርካታ መንገደኞች ይተራመሳሉ፡፡ እንዲህ መሆኑ ለአካባቢው ብርቅ አይደለም። በየቀኑ እየተጋፉ የሚያልፉ፣ እያለፉ የሚለፈልፉ፣ እየለፈለፉ ሰላም የሚነሱ ባለጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹ወዳጆቼ! ›› እነዚህን ሰዎች ‹‹ባለጉዳዮች›› ማለቴ በምክንያት ነው፡፡ ሁሉም በሚባል መልኩ የራሳቸውን ሃሳብ ብቻ የሚዘውሩ ስለሆኑ።
አንዳንዴ ከትርምሱ ጋር የነሱ ጉሸማና ወከባ ይረብሻል፡፡ አብዛኞቹ የራሳቸውን ዓላማ ከግብ ሊያደርሱ አይሆኑት የለም፡፡ ከነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ሲሻቸው ከሰው ጆሮ ተጠግተው፣ አልያም ራቅ ብለው የሚሉትን ይላሉ፡፡ ሁሉም በአንድ ቦታና ሰአት የተለያየ ሀይለ ድምጽ ባወጡ ጊዜ ውስጥን አንዳች የሆነ ስሜት ይጋፋል።
በስፍራው ተጠጋግተው፣ ተደጋግፈው የሚያስተጋቡት ዥንጉርጉር ድምፅ የሚፈጥረውን ረብሻ ማሰብ አይቸግርም፡፡ ሁሌም በየግላቸው ድምጸትና ዜማ አንዱ ከሌላው በልጦ ለመሰማት የሚያደርጉት ፉክክር አስገራሚ ነው፡፡ እኔን የሚደንቀኝ ግን ከደመቀው ትርምስ ነጠል ብለው ጉዳያቸውን የሚያራውጡ ሰዎች ድርጊት ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ዓላማቸውን የሚያሳኩት በተለመደው አይነት የገበያ ግንኙነት አይደለም፡፡ ሁሌም ወደ መንገደኛው ተጠግተውና እግረኛውን አስቁመው በግልጽ የሰውን ጊዜ ይነጥቃሉ፡፡ ሃሳብን ሰርቀው በይሉኝታ ያሸማቅቃሉ፡፡
ሰዎቹ ትኩረት ያገኙ ሲመስላቸው በዋዛ አይላቀቁም፡ ፡ ወዲያው የያዙትን ዕቅድ ይዘረጋሉ። ራዕይና ተልኳቸውን እያስረዱም ግባቸውን ሊያስቃኙ ይጣደፋሉ፡፡ እኔ በየመንገዱ እንዲህ አይነቶቹ አድርቆች ስለሚደጋገሙብኝ ሁሌም ‹‹ልብ ውልቅ›› እላቸዋለሁ፡፡
አሁንም የእግረኞች መንገድ ላይ ነኝ። ካሰብኩት ለመድረስ ብጣደፍም ገና ከመንገዱ ጫፍ አልተጠጋሁም። ከጎን፣ ከኋላዬ የሚገፋፉኝ በርክተዋል፡፡ በድንገት አንድ ሰው ከፊት ለፊቴ ብቅ ሲል ዓይን ለዓይን ግጥም አልን። ከሚጨንቀው ትርምስ ለመውጣት እያሰብኩ ነበርና እንዳያስቆመኝ ፈራሁ፡፡ ስጋቴ ትክክል ነበር፡፡ ሰውዬው በተለየ ሰላምታ እየተሽቆጠቆጠ ሊያናግረኝ እንደሚሻ ነገረኝ፡፡
እውነት ለመናገር አለባበሱ የአምባሳደር ያህል ነው። በሙሉ ልብሱ ላይ ሸብ ያደረገው ባለቀለም ከረባቱ ድንቅ አድርጎ አስውቦታል፡፡ ጊዜ እንደሰጠሁት ሲረዳ በእጁ የያዘውን ፋይል መሳይ አጀንዳ እየገለጠ ንግግሩን ጀመረ።
ያለምንም ማቋረጥ እያነበነበ ቢሆንም ከቃሉ አንዳች ሃሳብ አይስትም፡፡ በሽምደዳ ያጠናው የሚመስለውን ጉዳይ ከመነሻ እስከ መድረሻ ያንበለብለዋል፡፡ በየመሀሉ ቆም ይልና የሚናገረው በትክክል እየተደመጠለት መሆኑን ማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡ በልፍለፋው ልቤ ውልቅ ቢልም እየተገረምኩ በትእግስት ሰማሁት፡፡
‹‹ወዳጆቼ!›› እናንተንም እንደኔው ካስገረማችሁ ሰውዬው ያለኝን ላካፍላችሁ፡፡ የዚህ ሰው ዓላማ አንድ ታዋቂ ሪል ስቴትን ለነዋሪዎች ለመሸጥ በየመንገዱ ሰዎችን ማግባባትና ገበያን መሳብ ነው። እሱ እንዳለኝ ከሆነ ሪል ስቴቱ በከተማዋ ካሉት ሁሉ በዋጋ፣ በጥራትና በታማኝነት የላቀ የሚባል ነው፡፡ ይህን የመኖሪያ ቤት ፈጥኖና መርጦ የሚገዛ ቢኖር በእጅጉ ያተርፋል፤ በኑሮው ረክቶ በህይወቱ ይደሰታል፡፡
በጣም ያስገረመኝ ቢኖር ወደር የለሹን የመኖሪያ መንደር ለማስተዋወቅ ሰውየው በእግራቸው የሚራመዱ ሰዎችን እያደነ መምረጡ ነው፡፡ እንተዛዘብ ከተባለ እኮ ከእነዚህ ሰዎች አብዛኞቹ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ እንኳንስ ዘመናዊ ቤቶችን ተሻምተው ለመግዛት፣ ለአንገት ማስገቢያ ጎጇቸው የኪራይ እጅ ያጠራቸው፣ ችግር አብዝቶ የፈተናቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እኔና መሰሎቼም ብንሆን ሪል ስቴት ይሉትን ጉዳይ በታሪክ ካልሆነ በአካል አናውቀውም፡፡ እስከዛሬም በተግባር ልንሞክረው አላሰብንም፡፡ ለምን ከተባለ ማንም የሚኖረው በአቅምና በልኩ ስለሆነ፡፡ ይህ ሰው ግን ምን አሳይቶት፣ በእግሩ የሚኳትነውን መንገደኛ ምርጫው እንዳደረገ አይታወቅም፡፡
እንዴትና በምን አግባብ ይሆን ሌት ተቀን ኑሮ የሚያናውዘው በእግር ኳታኝ መንገደኛ ሪል ስቴቱ የሚያሳስብ የሚያስጨንቀው? ሰውየው ግን የምርጫ አቅጣጫውን በኑሮ ከበለጸጉት መንደር ማድረግን ያሰበ አይመስልም፡፡
በዘመንኛ መኪኖች የሚፈሱትን፣ በቅንጡ ኑሮ የሚቀማጠሉትን ተፈላጊዎች ተራምዶ ኑሮ አንገታቸውን ባስደፋቸው ሰዎች መሀል ልብ ሲያወልቅ፣ ይውላል፡፡ በእኔ እሳቤ ግን ይህ አይነቱ አታካች ‹‹ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ይሉት አይነት ነው፡፡ አንድም ቀልድ፣ሌላም ኪሳራ ስለሆነ፡፡
መቼም በእግርዎ መራመድ ከጀመሩ የሚገጥምዎት ብዙ ነው፡፡ አንድ አፍታ አልፈውት በሚሄዱት መንገድ ልብ የሚያወልቅና አብዝቶ የሚያሰለች አይጠፋም። አንዳንዳዴ ከምታዘባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አስተውሎት የጎደላቸው እውነታዎች ያጋጥሙኛል፡፡ ይህኔ ሰው ምን ነክቶታል ከማለት ባለፈ ውስጤ አብዝቶ ይሸማቀቃል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሚባል ሁኔታ በየመንገዱ የግል ሃይማኖታቸውን የሚሰብኩ ሰዎች በዝተዋል፡፡ በእኔ እይታ እስካሁን ይህን በማድረጋቸው መብታቸው ሲጣስ ሃሳባቸው ሲታፈን አላጋጠመኝም፡፡ ችግሩ እንዲህ መሆኑ ላይ አይደለም፡፡ ከእነዚህ መሀል አንዳንዶቹ አብዝተው የሚይዟቸውን በራሪ ወረቀቶች ላገኙት ሁሉ ያድላሉ። ማደል ሲባል ደግሞ በሰዎች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ አይምሰላችሁ፡፡
ወረቀት አዳዮቹ የእጃቸውን አሳልፈው ከመስጠት ባለፈ መንገደኞችን አስቁመው መወትወት ልማዳቸው ነው። አልገባቸው ይሆናል እንጂ ከሚያናግሯቸው አብዛኞቹ የእነሱን ዕምነት የማይከተሉ ሊሆኑ ይችላል። ይህ አይነቱ ያልተገባ አጋጣሚ ባስ ባለ ጊዜ ዱላ የሚያማዝዝ ጠብን ሊያጭር ይችላል፡፡
እንዲያም ሆኖ አሁንም ድረስ ልብ ያልተባለው ስህተት ሳይታረም መቀጠሉን ልብ ይሏል፡፡ በመንገድ ላይ ከዚህም የባሰ ሃይማኖታዊ ስህተቶች ሲፈጸሙ ይስተዋላል።
አንዳንዶች የቅዱሳንን ስነ ስዕል አሳትመው በየጎዳናው ጥግ ይቆማሉ፡፡ እንዲህ ማድረጋቸው አላፊ አግዳሚውን በመወትወት በሚሰጡት ስዕል ያሰቡትን ገንዘብ ለመቀበል ነው፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ እንዲህ አይነቶቹ ይሉኝታና ትዕግስትን አያውቁትም፡፡
ድንገት ባገኟችሁ ጊዜ ከኋላ ከፊት እየተከተሉ ያደርቋችኋል፡፡ ጉዳዩን እንዳልሰማ ለማለፍ ከሞከራችሁ ደግሞ በዋዛ አትለቀቁም፡፡ ትከሻችሁን እየነካኩ፣ ልብሳችሁን እየጎተቱ፣ ሰላም ይነሷችኋል። ለመሸጥ የሚጠቀሙት ቃላትና ማግባባት ደግሞ ለየት ይላል፡፡
አሁንም አስገራሚው ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም። እነሱ በውትወታ ‹‹ካልገዛችሁን›› የሚሉትን ምስል ለማን እንደሚያደርሱት አያስተውሉም፡፡ ጉዳዩ ገንዘብ እስካመጣላቸው ድረስ መንገደኛው ሁሉ ቢገዛቸው፣ ቢወስድላቸው ይወዳሉ፡፡ እኔ ግን ይህ አይነቱ ልማድ ከስህተት አልፎ የሌሎችን መብት እንደመጋፋት ይቆጠራል ባይ ነኝ ፡፡
አንዳንዴ እነዚህን መሰል እንከኖች ሲያጋጥሙኝ ከሌሎች ጋር አለመግባባቶች እንዳይፈጠሩ እሰጋለሁ። ሁሉም ሰው በተፈጥሮው ታጋሽ ነው ማለት አይደለም። በተለይ ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ማስተዋል ያለመኖሩ ስሜታዊነትን ሊያስከትል ይችላል ፡፡ ይህ አይነቱ እውነት እየተስተዋለ ካልተከወነ ጉዳቱ ከአንድ አልፎ ለብዙኃን ይተርፋል፡፡
የመንገድ ላይ ልብ አውልቆች ብዙ ናቸው፡፡ በየዕለት እንቅስቃሴችን ለምደናቸው ካልሆነ በቀር አሰልቺነታቸው፣ መብትና ፍላጎትን ጭምር መጋፋታቸው አይቀሬ ነው። አንዳንዴ እንደዋዛ ቆጥረን የምንለምዳቸው አጋጣሚዎች ውሎ አድሮ ጉዳታቸው ሊከፋ ይችላል፡፡
ጥቂቶች በሚፈጽሙት የስህተት መነሻም ብዙኃን የሚወቀሱበትና በርካቶች የሚጎዱበት አጋጣሚ ይኖራል። የመንገድ ላይ ልብ አውልቆች፣ መነሻና መድረሻቸው የግላቸውን ገቢ በማጋበስ የሌሎችን ኪስ ማራቆት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ እነዚህ ግብር የማይከፍሉ፣ ይሉኝታና ክብር የሌላቸው ወገኖች ግን መስመር ሊበጅላቸውና አደብ ሊገዙ ይገባል፡፡ የግል አስተያየቴ ነው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም