ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለጀመረችው ልማት ስኬት በግብርናው ዘርፍ ያላትን ትልቅ አቅም አሟጣ ለመጠቀም ከፍ ባለ መነቃቃት መንቀሳቀስ ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም በዘርፉ ውጤታማ መሆን ችላለች። በዘርፉ እያስመዘገበች ያለችው ይህ ውጤታማነት ዓለም አቀፍ እውቅና እያገኘ ከመጣም ውሎ አድሯል።
በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለስንዴ ልማት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ተከትሎ ሀገሪቱ በዘርፉ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት የብዙ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ሆኗል፤ እንደ አንድ ዓለም አቀፍ ተሞክሮም ተወስዶ እውቅና ሲቸረውም ተደጋግሞ ተደምጧል።
ከዚህም ባለፈ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክ የመሳሰሉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት፤ ይህን ሀገራዊ ስኬት በዓለም አቀፍ መድረክ ደጋግመው ሲያነሱ ፤ ስለዚህ ውጤታማ ተሞክሮና ሀገሪቱ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የጀመረችው የራሷ መንገድ ተስፋ ሰጪ ስለመሆኑ በልበ ሙሉነት ሲመሰክሩ ተሰምተዋል።
ለዚህም የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንውሚ አዴሲና / ዶ/ር/ ከዓመት በፊት የሀገሪቱን የስንዴ ልማት አድንቀው ሲናገሩ መደመጣቸውን በቅርቡ በተካሄደ የዓለም የምግብ ሽልማት መድረክ ላይም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ብቻ ሳይሆን የስኬታማነት ማሳያዎችን በመጥቀስ አድናቆታቸውን ሲገልጡ ተደምጠዋል ፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ከትናንት በስቲያ የሚኒስቴሩን የ2016 በጀት ዓመት የአምስት ወራት ሥራ አፈጻጸም አስመልክተው የሰጡት መግለጫ፤ እውነታው ከዚህም ከፍ ያለ ስለመሆኑ አመላክቷል፡ ፡ ሀገሪቱ አጠቃላይ በሆነው የግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለችው ስኬት፤ አህጉራዊው የአፍሪካ ግብርና እድገት ፕሮግራም ያስቀመጠውን ግብም ያሳካ ነው፡፡
እንደ ሚኒስትሩ መግለጫ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት አማካይ የግብርና ምርት ውጤቶች የምርት እድገት ምጣኔ ስድስት በመቶ ደርሷል፤ ይህም ፕሮግራሙ በአፍሪካ ደረጃ የግብርና ምርት እድገት ያስቀመጠውን የስድስት በመቶ የእድገት ምጣኔ የሚያሟላ ነው፡፡
ሀገሪቱ በግብርናው ዘርፍ አዋጭ ፖሊሲዎችንና የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን አስቀምጣ በትኩረት መስራቷ፤ ስኬቶችን ከማጣጣሟ ባለፈ በአህጉራዊ ተቋማት ደረጃ የተቀመጠ ግብን ማሳካት መቻሏ የአፍሪካ ኅብረትን ግቦች እያሳካች ስለመሆኗም ተጨባጭ ማሳያ ነው፡፡
በተለይ እንደ ሀገር በስንዴ ልማት የምትከተለው ብሔራዊ የስንዴ ልማት ስትራቴጂ ያስገኘው ስኬት ከሀገራዊ ፍጆታ ባለፈ፤በዓለም አቀፍ ደረጃ በስንዴ ገበያ ውስጥ ብቁ ተወዳዳሪ ሊያደርጋት የሚችለውን ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ አስችሏል፡፡
ሀገሪቱ ካላት ለስንዴ ልማት የሚውል ሰፊ መሬት ፣ ምቹ የአየር ንብረት ፣ ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ አንጻር፤ እነዚህን አቅሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና እውቀት አቀናጅቶ በትኩረት መስራት ከተቻለ በዘርፉ እንደ ሀገር አዲስ ታሪክ መጻፍ አስቻጋሪ ሊሆን የሚችል አይደለም።
ለዚህም በመንግሥት በኩል የተጀመረውና በብዙ መልኩ ተስፋ ሰጪ የሆነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንደ አንድ ማሳያ ይጠቀሳል፡፡ ልማቱ በተጀመረበት ዓመት ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ማምረት ተችሏል፤ ይህ አሀዝ ባለፈው ዓመት 47 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ አሀዙን በተያዘው ዓመት ወደ 117 ሚሊዮን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡
የሀገሪቱ የግብርና ምርት እድገት በተለይ በስንዴ ልማቱ እየታየ ያለው ትልቅ እምርታ ሀገሪቱ በምግብ እህል ራስን ለመቻል የጀመረችውን ጥረት የሚደግፍ ፤ ከዛም ባለፈ ሀገሪቱ ስንዴ ወደ ውጪ በመላክ ተጨማሪ የውጪ ምንዛሪ የምታገኝበትን እድል የሚያሰፋም ነው።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ሀገሪቱ ቀደም ባለው ጊዜ ስንዴ ከውጭ ለማስገባት በየዓመቱ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታደርግ ነበር፡፡ የስንዴ ልማቱ ይህን ታሪክ የቀለበሰ አልፎም ተርፎ ስንዴ ለጎረቤት ሀገር በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ያስቻለም ሆኗል፡፡
በስንዴ ልማቱ የተገኘው ስኬት ዓለም በስንዴ አምራችነታቸው የሚታወቁት ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በገቡበት ባለፈው ዓመት በርካታ ሀገሮች ስንዴ ለመግዛት የተቸገሩበት ሁኔታ በኢትዮጵያ እንዳይከሰት ማድረግ አስችሏል፡፡ በዚያ መልኩ ስንዴ በሀገሪቱ ተመርቶ ባይሆን ሀገሪቱ ማዳበሪያ ለመግዛት የገጠማት ፈተና በስንዴ ግዥ ሊገጥማት ይችል እንደነበርም መገመት አይከብድም፡፡
ይህ እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የተያዙ እቅዶች ስኬትን ያመላከተ፣ከዚህም አልፎ የአፍሪካ ግብርና ልማት ግብን ማሳካት የቻለ፣ ለዓለምም ጭምር ታላቅ መልዕክት ያስተላለፈ የግብርና ልማት ስኬት እውቅና ሊሰጠው፣ በሚገባው ደረጃ አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም