ሰብዓዊ እጆች ከሁሉም ወደ ሁሉም!

በአንድ ወቅት አግኝቶ ኑሮው የተደላደለለት፣ በሌላ ወቅት የወገኖቹን እጅ የሚመለከትበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በአንጻሩም በሆነ ወቅት የሚበላው እንኳን አጥቶ በመንገድ ላይ የወደቀ ሰው፣ ከጊዜ በኋላ ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ባለፀጋ ሰው የሚሆንበት ዕድልም የሰው ልጆች የኑሮ ገጽ ነው።

ይሄ የማግኘትና የማጣት የሕይወት ውጣ ውረድ ታዲያ፣ የሰው ልጆችን የሰውነት ከፍታ ማንጸሪያ፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች የማሰብና የመድረስን ልዕልና መመልከቻም፤ መግለጫም ሆኖ የተሳለ የሰው ልጅ ደግነት አልያም ንፍገት መመዘኛ የፈጣሪ ሚዛን ተደርጎም በሰዎች ዘንድ ይወሰዳል።

ምክንያቱም መልካም ማድረግ በፈጣሪም ሆነ በሰው ዘንድ ምስጋናና ክብርን የሚያጎናጽፍ ሲሆን፤ በአንጻሩ ንፉግነት በፈጣሪ መንገድ የአለመጓዝ መገለጫ፣ በሰው ዘንድም መጠላትና መገፋትን የሚያስከትል ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በአንድ በኩል ከፈጣሪ ጋር ያለን ቁርኝት፤ በሌላ በኩል ጠንከራ የሚባለው ማኅበራዊ እሴትና መሰረታችን ከክፋት ይልቅ ደግነትን፤ ከጭካኔ ይልቅ ርህራሄን፤ ቆሞ ከመመልከት ይልቅ ደርሶ ማገዝና መደገፍን እንድንመርጥ ያደርገናል። በዚህ መልኩም እየተገለጥን ዘመናትን ተጉዘናል።

ዛሬም ይሄንኑ ከፍ ያለ የሰውነት መገለጫ ግብራችንን የምናሳይባቸው በርካታ ጉዳዩች በሀገራችንም፤ በወገናችንም ላይ ተከስቷል። ትናንት ለወገኖቹ ካመረተው ያለ ስስት ሲሰጥ የነበረው ወገን፤ ዛሬ ከማሳው የሚያነሳው፣ ከበረቱም የሚጠምደው፣ ከጎተራውም የሚዘግነው አጥቶ እጆቹን ለመጽዋት ዘርግቷል።

ኢትዮጵያም አንድም ድርቅን በመሳሰሉ የተፈጥሮ ችግሮች፤ ሁለተኛም፣ በእኛው በሰዎች ምክንያት በተፈጠሩ የሰላም መደፍረሶችና ጦርነቶች በቀዬውም ሆነ ከሞቀ ቀዬው ተፈናቅሎ ኑሮውን በችግር እየገፋ ላለው ዜጋዋ መከራ ተጨንቃለች።

ልጆቿን ለመመገብም ያላትን ብትጥርም፤ እርሷም ገና ከጦርነት ሸክሟ አላገገመችምና በሙላት ልትደርስላቸው አልቻለችም። የውጪ ረጂ ተቋማትም ቢሆኑ በክብርና ሉዓላዊነቷ አስታክከው በሚፈጥሩት ጫና ምክንያት ለልጆቿ በሰብዓዊነት ተልዕኳቸው ልክ የመድረስ ፍላጎታቸውን ገታ አድርገዋል።

ይሄ ደግሞ ለዜጎች ሊደርስላቸው የሚገባው ሰብዓዊ ድጋፍ እንዳይደርስ በማድረግ ከዕለት ዕለት ወደ ከፋ ችግር እንዲገቡ እያደረጋቸው ይገኛል። ዛሬ ላይ በትግራይ፣ በአማራ፣ እና ሌሎችም አከባቢዎች የሚስተዋለው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትም ከዚሁ የመነጨ ነው።

መረጃዎች እንሚያመለክቱት፣ በአማራ ክልል ከ600 ሺህ በላይ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፤ በትግራይ ክልል ደግሞ 32 ወረዳዎች ድርቅ እና የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል። በሌሎችም አከባቢዎች በድርቅና በግጭት ምክንያት በቀያቸውም፣ ከቀያቸው ተፈናቅለውም ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች አሉ። እነዚህ ውስጥ ደግሞ እናቶች፣ ሕጻናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያንን የመሳሰሉ ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የኅብረተብ ክፍሎች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።

ለእነዚህ ዜጎች የዕለት ደራሽ ምግብም ሆነ ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎችን ከማድረግ አኳያ መንግስት አቅም በፈቀደ ልክ በከፍተኛ ድጋፍ እየሰራ ይገኛል። ይሁን እንጂ በመንግስት ብቻ የሚደረገው ድጋፍ ካለው ተጨባጭ የድጋፍ ፍላጎት አኳያ በቂ አይደለም። በመሆኑም ተግባሩ ከመንግስት ባሻገር ያለውን የወገን ለወገን ደራሽነት ተግባር አብዝቶ የሚሻ ነው።

እንደሚታወቀው ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት በተለያየ ምክንያት በኢትዮጵያ እያደረጉ ያሉት ድጋፍ ላይ እጅ አጠር ሆነዋል። ይሄን ለመሙላትም ጭምር ነው መንግስት አሁን እየሰራ ያለው። በዚህም ተቋማቱ ድጋፋቸውን ካቋረጡ ጀምሮ መንግስት ባደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መድረስ ችሏል።

ይሁን እንጂ የተረጂዎች ቁጥር በድርቅም ሆነ በግጭት ምክንያት እየጨመረ ከመሄዱ አኳያ፣ በተለይ የዕለት ደራሽ ምግብ ፈላጊ ወገኖች በጊዜው ሊደርስላቸው ካልቻለ ለከፋ አደጋ መጋለጣቸው የማይቀር ነው። ለዚህ ደግሞ ከመንግስት ባሻገር ያሉ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅባቸውን ወገናዊ ኃላፊነት ሊወጡ ያስፈልጋል።

በዚህ ረገድ ሰሞኑን በላይነህ ክንዴ ፋውንዴሽን እና ወረታ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የዕለት ደራሽ ምግብ ለሚፈልጉ ወገኖች እንዲውል ያደረጉት ድጋፍ ዓርአያነት ያለው ተግባር ነው።

ተግባሩ፣ በሕዝብ ውስጥ ሆነው ያፈሩት ሃብት መልሶ ለሕዝብ ጥቅም መዋል እንዳለበትም ያሳየ፤ ሌሎች መሰል ባለሃብቶች እና ተቋማትም በሕዝብ ውስጥ ሆነው ያገኙትና የበለጸጉበትን እውነት ተረድተው ሕዝብ በተቸገረ ጊዜ የመድረስ ማኅበራዊም፣ ሞራላዊም ግዴታ እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ነው።

በዚህ መልኩ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያየ መልኩ የሚገለጹ የሰብዓዊ ድጋፍ ትብብሮች ነበሩ። ዛሬ ላይ እነዚህን መሰል የድጋፍ ትብብሮች ተቀዛቅዘዋል።

በመሆኑም ሥራው ከመንግስትም በላይ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደመሆኑ ሰው በመሆን ልኬት ብቻ ለሰዎች መድረስ የተገባ ነው። ይሄ በሰውነት ልኬት የሚደረግ የሰብዓዊነት ተግባር ደግሞ የሰብዓዊነት እጆች ከሁሉም አቅጣጫ ወደ ሁሉም ድጋፍ ፈላጊ ዜጎች የሚደርስ መሆን ይገባዋል!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You