ያለማስያዣ ለመበደር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥረው ዲጂታል ፋይናንስ

በዓለም ታሪክ ውስጥ ከየትኛውም ጊዜ እና ዘርፍ በላይ በአሁኑ ጊዜ የግሉ ዘርፍ የሚፈጥረው የሥራ እድል ሰፊ ከመሆን በተጨማሪ፤ የብዙዎችን ሕይወት በማሻሻል ላይ ይገኛል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ የግሉ ዘርፍ ለማሳደግ በዓለም ላይ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከአምስት ያላነሱ አስርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ነፃ ገበያ ደግሞ ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥን አዳብሮታል፡፡ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልልቅ የኢኮኖሚ ትርፎችም ተገኝተውበታል፡፡ በዚህ ሂደት ብዙዎች ቢጠቀሙም አንዳንዶች ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች ወደኋላ ቀርተዋል። በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ከፍ ያሉት እና ተጠቃሚ የሆኑትን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ብዙም ያልተጠቀሙ ሀገሮች ደግሞ ተጠቃሚ መሆን እንዲጀምሩ በዓለም የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡

በዲጂታል መንገድ የሚቀርቡ የፋይናንስ አገልግሎቶች ግብ፤ ለድህነት ቅነሳ አስተዋፅኦ ማድረግ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የፋይናንስ ጥቅሞችን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህን መሠረት በማድረግ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ነፃነትን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የግል ኢንተርፕራይዝ ማዕከል (CIPE) የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡

በብዙ የዓለም ፈታኝ አካባቢዎች ተወዳዳሪ ገበያዎችን ለመገንባት የሚሰራ ይኸው ዓለም አቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያም የተለያዩ ጥናቶችን እያካሔደ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የግል ኢንተርፕራይዝ ማዕከል (CIPE) አማካሪ ሆነው ጥናት በማካሔድ ላይ የሚገኙት ካሊድ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት እና ለፈጠራ ሥራ በማነሳሳት ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት እና የቴክኒክ ድጋፎችን በተመለከተም ምን ያህል መሆን እንዳለበት አጥንተዋል፡፡ ካሊድ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡ ከእኚሁ አጥኚ እና በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የግል ኢንተርፕራይዝ ማዕከል አማካሪ ከሆኑት ካሊድ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የዲጂታል ፋይናንስን አስፈላጊነት እና በተለይ ለኢትዮጵያ ያለውን ጠቀሜታ በተመለከተ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- ዲጂታል ፋይናንስ ምንድን ነው ከሚለው እንጀምር?

ዶ/ር ካሊድ፡- ዲጂታል ፋይናንስ በተሳሳተ መልኩ እየተተረጎመ ይታያል፡፡ በቴክኖሎጂ ገንዘብ መላላክ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ብቻ ተደርጎ ይታሰባል። ነገር ግን የተለየ ነው፡፡ ለምሳሌ ቴሌ ብር የገንዘብ ልውውጥ ነው፤ ለዛ የአገልግሎት ክፍያ ይኖራል። ዲጂታል ፋይናንስ ግን አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ ዲጂታልን መሠረት ያደረጉ የብድር አገልግሎቶችን መስጠት ማለት ነው፡፡

ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከዲጂታል ፋይናንስ ይለያል። ቴክኖሎጂ የገባው ዲጂታል ፋይናንስን አስቻይ ለማድረግ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን መሠረት በማድረግ ብድር መስጠት ማለት ነው፡፡ የዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ የተፈጠረው ማስያዣ ሳይኖር መበደር እንዲቻል ዕድል ለማመቻቸት ነው። ማስያዣ የሌለው፤ ነገር ግን በዲጂታል ሊለካ የሚችል አቅም ያለው ብዙ ሰው አለ፡፡ ያንን በመለካት በዛ አቅም ወደፊት ይከፍላል ብሎ በመተንበይ ብድር መስጠት ላይ ያተኩራል፡፡

በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ያህል፤ አንድ ጉሊት ሽንኩርት ወይም ድንች የምትሸጥ ሴትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሥራዋን ለማስፋፋት ወይም ለሌላ ምክንያት ብድር ብትፈልግ የምታሲዘው ቤት ላይኖራት ይችላል። ሁለት ሺህ ብር ለመበደር ብትፈልግ፤ አበዳሪው ባለፈው ወር የነበራትን ሽያጭ፣ እዛ አካባቢ በቋሚነት መሥራቷን ወይም መኖሯን፣ ከአሁን በፊት ተበድራ ምን ያህል መልሳለች? ስንት ልጆች አላት? ልትጠፋ አትችልም? የሚሉትን እና ሌሎችም አመላካች ጉዳዮችን እና ቁጥሮችን ያያል፡፡ በሌሎችም በተለያዩ መመዘኛዎች ተለክታ በማበደሪያ ከአንድ እስከ አሥር ባሉ ደረጃዎች ላይ የት ትወድቃለች የሚለው ተቃኝቶ ስድስት ቁጥር ላይ ትወድቃለች ተብሎ እንደአቅሟ ብድር ሊሰጣት ይችላል፡፡

አበዳሪው ለአራት ቁጥር እስከ እዚህ ልናበድር እንችላለን፤ እስከ ስድስት ቁጥር ይህን ያህል ልናበድር እንችላለን፤ ለዘጠኝ ቁጥር እስከ እዚህ ልናበድረው እንችላለን ተብሎ ትንታኔ ተሠርቶ በዛ መሠረት ገንዘብ ብድር የሚገኝበት እና ኢኮኖሚውም የሚበረታታበት ሰፊ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ይህ የዲጂታል ፋይናንስ በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ ሲሆን፤ በትልልቅ ተቋማት ደረጃ ማበደርም የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ተበዳሪው ድርጅት ባለፈው አሥር ዓመት ምን ያህል ግብር ከፍሏል? አጠቃላይ የሠራተኛው ቁጥር ስንት ነው? ምን ያህል ትርፍ አለው? ከአሁን በፊት ምን ያህል ብድር መልሷል? የሚሉ እና በሌሎችም በተለያዩ መለኪያዎች ይመዘናል፡፡ በዛ በብድር ደረጃ መዘርዝር መሠረት ለዛ ተቋም አስርም፣ ሃያም የጠየቀው ብድር የሚሰጥበት መንገድ ይኖራል፡፡

አዲስ ዘመን፡- እስኪ ያጠኑትን ጥናት በተመለከተ በደንብ ይግለፁልን?

ዶ/ር ካሊድ፡- ጥናቱ ገንዘብ ማግኘት እና ዲጂታል ፋይናንስ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተለይም ንብረትን አስይዞ መበደር ብቻ ሳይሆን ችግሮችን ለመፍታት ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ገንዘብ ማግኘት ላይ ያተኩራል። በሌሎች ሀገሮች ላይ እንዳለው ንብረት ሳይያዝ ብድር ማግኘት ላይ ሲያተኩር፤ እዚህ ላይ በሌሎች ሀገሮች ያለመያዣ ብድር የተለመደ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም። ስለዚህ በኢትዮጵያም ይህንን ዕድል ለማስፋት የሚያስችሉ መንገዶች ምንድን ናቸው? በሚለው ላይ ከኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የግል ኢንተርፕራይዝ ማዕከል ከ(ሳይፕ) ጋር ጥናት አካሂደናል፡፡

ጥናቱ በአጠቃላይ የሀገሪቷ የፖሊሲ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የተካሔደ ቢሆንም፤ በዋናነት በዲጂታል ፋይናንስ ለሀገሪቷ ችግር መፍትሔ የሚሆኑ ብዙ ለውጦችን ማምጣት እንችላለን የሚል መነሻ በመያዝ የተካሄደ ነው፡፡ ጥናቱ ለአገልግሎትም ሆነ ለማንፋክቸሪንግ ዘርፉ ፋይናንስ የማግኘት ጉዳይ በጣም ቁልፍ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ይህንን ያመላከተው የእኛ ጥናት ብቻ ሳይሆን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ላይ የተካሄደው ጥናት እና ሌሎችም በኢኮኖሚ ዕድገት ዙሪያ የተካሔዱት ጥናቶች በሙሉ የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡

ለየትኛውም ሥራ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የፋይናንስ አቅርቦት (access to finance) በተለይ ለማንፋክቸሪንግም ሆነ ለአገልግሎት ዘርፉ ቁልፍ ነገር ነው፡፡ ይህ ተደጋግሞ የሚገለፅበት ምክንያት የገንዘብ አቅርቦት ጉዳይ በጣም ትልቅ ችግር ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ባለፉት 11 ዓመታት ከተመዘገቡት ኢንዱስትሪዎች ውስጥ በተለይ እሴት መጨመር ላይ የኢንዱስትሪው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንደስትሪዎች ሲኖሩ እና በእሴት ሠንሠለት ከትልልቅ ኢንደስትሪዎች ጋር ሲተሳሰሩ እንደሀገርም ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ታይቷል፡፡

በብዛት ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች በቀላሉ ገንዘብ የሚያገኙበትን ሁኔታ መፍጠር ለማንፋክቸሪንግም ሆነ ለአገልግሎት ኢንዱስትሪው እንደ ሀገርም ትልቅ ውጤት ያመጣል በሚል መንደርደሪያ ጥናት አካሂደናል፡፡ ከሰብሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት መካከል በኢትዮጵያ ገንዘብ የማግኘት ዕድል እጅግ የተመናመነ መሆኑን ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይ ኢንተርፕራይዞች የሚያገኙበት ሁኔታ አለመኖሩን ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከ10 እስከ 11 ነጥብ 7 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር በአማካኝ የፋይናንስ ክፍተት አለ፡፡ ይህ ችግር የመጣው በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ካላት ከ110 ሚሊየን ሕዝብ ውስጥ 330 ሺህ ሰው ብቻ ብድር የማግኘት ዕድል የነበረው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዓለም ላይ የዲጂታል ፋይናንስን በተመለከተ የዓለም ተሞክሮ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ካሊድ፡- በጣም ብዙ ተሞክሮዎች አሉ። የብድር ደረጃዎች (credit scoring) በየሀገሩ ይሠራል። በዚህ በተለይ ሕንድ ትልቅ ታዋቂነትን አትርፋለች፡፡ ቻይና አዕምሯዊ ንብረትን መሠረት በማድረግ በርካታ ተቋማት ብድር ይሠጣሉ፤ ተቋሞቹ ደረጃቸውን የጠበቁ እና መስፈርት የሚያሟሉ ናቸው። ለምሳሌ እዚህ ሀገር ልክ እንደ ኦዲት አድራጊ ተቋማት አበዳሪ ተቋማት ሥነ ምግባር ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ተቆጣጣሪ ተቋማት ያስፈልጓቸዋል። አሁንም አሉ፤ ግን እነዛን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለብድር ዋስትና መስጠት፤ ለሌላ ሰውም ዋስ መሆን፤ በብድር ደረጃቸው መሠረት ማበደር ይቻላል፡፡ በዚህ ላይ ትልቅ ጥናት አድርገናል፡፡

በብድር ደረጃ መሠረት የሚያበድሩ ተቋማት ለምሳሌ በሕንድ በጣም አራት ትልልቅ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ከሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭም ገንዘብ ማስጋባት የሚችሉ በጣም ትልልቅ ናቸው፡፡ የአዕምሯዊ ንብረትን መሠረት ያደረገ ትመናን መሠረት በማድረግ ቻይና በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች አሏት፡፡ ከአውሮፓ ባንኮች ሳይቀሩ ገንዘቦች በአዕምሯዊ ንብረት ይንቀሳቀሳሉ። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ በተመጠነ መንገድ ቢሞከር ጥሩ ነው፡፡ አሁን ላይ በተወሰነ መልኩ እየተሞከሩ ያሉ ጉዳዮች አሉ፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ባንኮችም ቅድሚያ ደመወዝ መስጠት ጀምረዋል፡፡ ብሩን የሚሠጡት በብድር ደረጃ ነው፡፡ የራሳቸውን መረጃ ሰብስበው አለኝታ እና ቴሌ እንዲሁም አዋሽ ባንክን የመሳሰሉ የተለያዩ ተቋማት እያበደሩ ነው፡፡ አሠራራቸው የተለያየ ቢሆንም፤ በየጊዜው ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ እና ብድር የሚከፍል ከሆነ መክፈል ይችላል ብለው ራሳቸው ኃላፊነት ወስደው እየሰጡ ነው፡፡ ይህ ለሁሉም ጠቃሚ ነው፡፡ ተበዳሪው ገንዘቡን በፈለገው ጊዜ ለፈለገው አገልግሎት ያውለዋል፡፡ አበዳሪው ደግሞ ወለድ ያገኛል፡፡

ለወደፊቱ ግን ትልልቅ መረጃዎች ተሰብስበው ከገቢ ሰብሳቢ፣ ከባንኮች እና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመገናኘት ስለአንድ ግለሰብ ከዲጂታል መታወቂያ ጀምሮ የደመወዙ መጠን፣ ያደረጋቸው የውጭ ጉዞዎች እና ሌሎችንም መረጃዎች ተጣርተው 100ሺም ሆነ 200ሺህ ብር የሚገኝበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። ልክ በሰፈር እቁብ እንደሚሰበሰበው በቅርብ ገንዘብ ማግኘት ይቻላል።

 ዶ/ር ካሊድ፡- የተጀማመሩ ነገሮች አሉ። ነገር ግን ተቋማዊ ሆነው ከባንኮች ጋር የተገናኙ አይደሉም። በራሳቸው በባንኮች ተነሳሽነት የሚሠጥ እንጂ በመንግሥት በኩል ገና መሠራት ያለባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ፡፡ በዋናነት ደግሞ የሕግ ክፍተቶች መስተካከል አለባቸው፡፡ ምቹ የሚሆኑት በግል ዘርፉ የሚሰጡት ብድሮች ናቸው፡፡ ጅምሮቹ ለማሳያነት በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ትልቅ ለውጥ ለማምጣት መሠራት አለበት፡፡

እነአለኝታ እና ቴሌ ብር ከአንድ ሚሊየን በላይ ወደሚደርሱ ተበዳሪዎች ብድር አቅርበዋል። 30 ባንኮች እስከ አሁን ያበደሩት ለ330ሺህ ሰው ብቻ ነው። ለዛውም 25 ቢሊየን ብር አካባቢ ነው። ያለመያዣ የሚያበድሩት ግን ትንንሽ ገንዘብ ቢያበድሩም ለብዙ ሰው ተደራሽ መሆን ችለዋል። ሕዝቡ ጋር ፍላጎቱ አለ፡፡ ተቋማዊ ሆኖ ከባንኮች ጋር ቢገናኝ፤ የሕግ ማዕቀፎች ቢቀመጡ፤ የብድር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቢሰፉ፤ መረጃዎች ቢጠሩ እና ሌሎች መረጃዎች ቢገኙ ብዙ ሰውን በቀላሉ ማገልገል እና ኢኮኖሚውን ማሳደግ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- በርግጥ በአዕምሯዊ ንብረት ለመበደርም ሆነ ለማበደር በኢትዮጵያ ምን ያህል ምቹ ሁኔታ አለ?

ዶ/ር ካሊድ፡- እኔ እንኳን ባለኝ ልምድ በጣም ብዙ ሰዎች ፋይናንስ ባለማግኘታቸው እንጂ አዕምሯቸው ውስጥ ሃሳብ ኖሮ ገንዘብ ማግኘት ከብዷቸው መሥራት ያልቻሉ ሰዎች አሉ። አንዳንዶች ገንዘብ የሚያገኙት ከሌሎች ሰዎች በመለመን ወይም ከቤተሰብ በመቀበል ነው፡፡ ትንንሽ ገንዘብ ምናልባትም በሶስት መቶ እና በአራት መቶ ሺህ ብር ትልልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ተቋማትን መገንባት የሚችሉ ይኖራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዘላቂ ኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ ፕሮጀክት ባካሔደው ጥናት ምቹ ሁኔታ እንዲመጣ ምን ዓይነት የፖሊሲ ግፊቶችን እናድርግ የሚል ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡

እስከ አሁን ያለው ገና ግፊት ለማድረግ ሲሆን፤ እስከ አሁን የአዕምሯዊ ንብረት ምዝገባ እንጂ የብድር አገልግሎት የለም፡፡ የብድር ደረጃ የለም፡፡ ስለዚህ ብድሩ እንዲኖር የተሠሩ በጣም ብዙ ጥሩ ሥራዎች አሉ፡፡ የሚቀረው ማገናኘት ነው፡፡ በሒደት ብዙ ለውጥ ማምጣት የሚቻል ይመስለኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የመንግሥት ድጋፍ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ካሊድ፡- በመንግሥት ብዙ ሰነዶች ላይ ብድር የማመቻቸት ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑ ተቀምጧል። ለኢንተርራይዞች ገንዘብ ማቅረብ ቀዳሚ ጉዳይ ነው። አማራጮች እንዲኖሩ ደግሞ እንዴት የሚለውን ማመላከት፤ የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ ማሳየት እና ድጋፍ ማቅረብ መንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት በተለይ ብሔራዊ ባንክ፣ ገቢ ሰብሳቢው ተቋም፣ የፋይናንስ ሚኒስቴር እነዚህ አንድ ላይ አምጥቶ ማገናኘት ቀጣይ ሥራ ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ ዲጂታል ፋይናንስ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ጠቃሚ ነው ይላሉ?

ዶ/ር ካሊድ፡– እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ሀገር ዲጂታል ፋይናንስ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ብዙ ሰዎች ሀብት ስለሌላቸው ተበድረው መሥራት ቢፈልጉም ማስያዣ የላቸውም፡፡ ዲጂታል ፋይናንስ ተግባራዊ ሲደረግ ያለ ማስያዣ የሚበደሩበትን ዕድል ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ብዙ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማስገባት አለባቸው። ከእዚህ አንፃር ዲጂታል ፋይናንስ አማራጭ የሌለው ትልቅ ጉዳይ ነው። ብድር የመመለስ አቅማቸውን በመተመን በተለየ ሁኔታ የተጀመሩ ሥራዎችን መሠረት አድርጎ ለብዙ ሰዎች መድረስ ይቻላል፡፡ በዲጂታል ፋይናንስ የገበያ ክፍተትን ለመዝጋት ያግዛል፡፡ ይህም ትልቅ መፍትሔ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚኖረው ጠቀሜታ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ካሊድ፡- በጥናት እንዳረጋገጥነው በርግጥ ለዚህ ዘርፍ ለብቻው ብለን የሠራነው ጥናት የለም። ነገር ግን በሀገር ደረጃ ቅድሚያ ከሚሠጣቸው ዘርፎች መካከል ግብርና አንዱ ነው፡፡ ማዕድንም ሆነ የማንፋክቸሪንግ ዘርፉ ሌሎችም ጤና ላይም ሆነ በእያንዳንዱ ዘርፍ ዲጂታል ፋይናንስ የራሱ በጎ አስተዋፅኦች እንዳሉት አረጋግጠናል፡፡

ግብርና ላይ ተንቀሳቃሽ ሀብትን እና የአዕምሮ ንብረትን አስይዞ መበደር የሚያስችል አዋጅ ማፅደቅ፤ ገበሬው አምርቶ የሚሸጥበትን አማራጭ እንደ አንድ የማበደሪያ ቴክኒክ መያዝ ይህ ሲባል በዓመቱ ሊያመርት የሚችለውን መሠረት በማድረግ አጠቃላይ ሊኖር የሚችለውንም ምርታማነት በመተመን ወደፊት ሊኖር የሚችለውን የገበያ ሁኔታ እና የዋጋ ሁኔታን በመተመን አርሶ አደሩም ቢሆን የተለያዩ ብድሮችን ማግኘት የሚችልበት ዕድል ለማመቻቸት መሞከር በዘርፉ ላይ ትልቅ ውጤት ያመጣል፡፡

ተንቀሳቃሽ የሆኑ ንብረቶችን ማሳ ላይ ያለውን ሰብል በመጠቀም መበደር የሚችልበት ሁኔታን ማመቻቸት ይቻላል፡፡ ከዛ ባለፈ የግብርና ሕብረት ሥራ ማህበራት ደግሞ ሰፊ ዕድል እንዲኖራቸው ማድረግ ይቻላል፡፡ ሕብረት ሥራ ማህበራት ሠፋፊ የመካናይዜሽንም ሆነ የሌሎች ሥራዎችን ማስፋፊያ ብድር የሚገኝበት ሁኔታ መፍጠር ይቻላል። ማህበራቱ በሚያወጧቸው የምርት መጠን እና ብዛት አጠቃላይ በደረጃቸው ላይ ተመሥርቶ ያንን መለኪያዎችን በመጠቀም ብድር ለማግኘት እንዲችሉ ማድረግ አይከብድም፡፡ በተጨማሪ አማራጭ ብድር የመመለስ አቅምን እየተጠቀሙ ዕድሉ እየሠፋ እንዲሔድ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ እንደየሀገሩ አካባቢ ሁኔታ ማደግ የሚችል ነው፡፡ ጥቅሙ ከግብርና አንፃርም ቢሆን እንዲህ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በዲጂታል ፋይናንስ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ መሆን ይቻላል?

ዶ/ር ካሊድ፡- አሁን ላይ ይህንን ለመግለፅ ያዳግታል። ነገር ግን መነሻ ጥናት ተካሒዷል፡፡ በርግጥም የባንኮች የገንዘብ አቅም በሂደት የሚፈታ ነው፡፡ በቴሌ ብር እና በሌሎችም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ሲቃኙ ረዥም ሂደት መሔድ እንደሚቻል አመላካች ሁኔታዎች ተገኝተዋል፡፡ 30 ባንኮች እስከ አሁን ያበደሩት 350 ሺህ ለማይደርሱ ሰዎች ብዙ ገንዘብ አበድረዋል፡፡ ባለፈው ሁለት ዓመት ብቻ እነዚህ ሁለቱ ያለ ማስያዣ ብድር የሚያቀርቡ ድርጅቶች ከአንድ ሚሊየን በላይ ተበዳሪዎችን ማዳረስ ችለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የተደራሽነት ችግር እንደማይኖር ነው።

የዲጂታል ፋይናንስ ብድር አቅራቢዎች ከተለመደው ከመደበኛው ባንክ የተሻለ ተደራሽ መሆን ይችላሉ። ሌሎችም እያስተዋወቁ ያሉ አሉ፡፡ የእነርሱንም ወደ መሬት ለማውረድ የሕግ ማዕቀፎች ያስፈልጋሉ። ተቋማትን ማደራጀት ያስፈልጋል። የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው፤ በሕግ ተስተካክሎ በተቋማት ተደግፎ ዲጂታል ፋይናንስ በሰፊው ቢተገበር በደንብ ማደግ ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዲጂታል ፋይናንስ በኢትዮጵያ መቼ እና እንዴት በስፋት ወደ መሬት ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል?

ዶ/ር ካሊድ፡– ይህንን ለመገመት ይከብዳል። ብዙ ተዋናዮችን የሚፈልግ ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም የተጀማመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ከዜሮ ስለማይጀመር በስፋት መቼ ተደራሽ ይሆናል የሚለውን ምላሽ መስጠት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ነገር ግን ጥናት ተጠንቷል፤ የሕግ ከፍተቶች እና ሌሎችም ሊሟሉ የሚገባቸው ጉዳዮችን በተመለከተ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል፡፡ በዛ ልክ ከተሄደበት ረጅም ጊዜ ይወስዳል ብዬ አልገምትም። በተለይ የሕግ ማዕቀፉ ላይ በትጋት ከተሠራበት እና ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ እየወሰዷቸው ያሉ ርምጃዎች በጣም ለዚህ የሚጠቅሙ በመሆናቸው በትኩረት የማስተዋወቅ ሥራ ከተሰራ ረዥም ጊዜ የሚወስድ አይሆንም፡፡ በአጭር ጊዜ ውጤት ማምጣት ይቻላል የሚል ግምት አለኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ?

ዶ/ር ካሊድ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You