ግብጽ በዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የምታራምደው አቋም የግብጽን ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን ሊያደርግ አይችልም!

 በዓለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ ሕጎች መሠረት ያደረጉት ፍትሐዊ የውሃ አጠቃቀምን ነው። እነዚህ ሕጎች እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ በሀገራት መካከል ለተፈጠሩ አለመግባባቶች ዋነኛ መፍትሔ ሆነው አገልግለዋል። ዓለም ለፍትሐዊነት ካለው የላቀ አስተሳሰብ እና አስተምህሮ አንጻርም ወደፊትም መፍትሔ እንደሚሆኑ ይታመናል።

ከዚህ ዓለም አቀፋዊ እሳቤ ያፈነገጡ መንገዶች ሁሉ፤ ለግጭትና ለአለመተማመን ምንጭ ከመሆን ባለፈ፤ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አጠቃቀም ዙሪያ ለሚነሱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ሊያስገኙ አይችሉም፤ ያስገኛሉ ብሎ ማሰብና በዚሁ እሳቤ ለመንቀሳቀስ መሞከር፤ ዘመንን መዋጀት ከሚያስችል ዕውቀትና ጥበብ የመራቅ አንዱ መገለጫ ነው።

ይህ ደግሞ ዓለም ለጋራ ብልጽግና ወደ አንድ መንደር እየተለወጠችበት ባለበት አሁነኛ እውነታ፤ በምንም መስፈርት የሚያስኬድ አይደለም። በተለይም ይህንን አስተሳሰብ የማይሸከሙ ያረጁና ያፈጁ አስተሳሰቦችን ይዞ በዓለም አቀፍ መድረክ መገኘት ፤ እንደ መንግሥት የሚወክሉትን ሕዝብ ከማሳነስ ባለፈ ምንም ትርጉም ሊኖረው የሚችል አይሆንም።

ሀገራችን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍትሐዊ አስተሳሰቦች እንዲሰፍኑ ሰፊ ጥረት ስታደርግ የኖረች፤ ለዚህም በአደባባይ ለፍትሐዊነት ድምጿን ከፍ አድርጋ ስታሰማ የኖረች ናት። ለፍትሕና ለነጻነት የተደረጉ ትግሎችን በግንባር ቀድምትነት በመደገፍ ተጠቃሽና በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ እውቅና ያገኘች ሀገር ነች።

ከሊግ ኦፍ ኔሽን ምስረታ ጀምሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ወቅት፤ እንደ ሀገር ፍትሐዊ ዓለም ለመመስረት በተደረጉ ጥረቶች ተሳታፊ የነበረች ፣በተቋማቱ የምስረታ ታሪክ ውስጥ ሰፊ ስፍራ የነበራት ፣ ዛሬም ቢሆን ተቋማቱ ፍትሐዊ በሚሆኑበት መንገድ ላይ ሰፊ ጥረት ከሚያደርጉ ሀገራት ተርታ የምትጠቀስ ናት፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያውያን ያላቸው የረጅም ዘመን የሀገረ- መንግሥት ግንባታ ታሪክን ጨምሮ ለዘመናት የኖሩባቸው መንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ እሴቶች ትልቅ አቅም ፈጥረውላቸዋል፤ ዛሬም ያለው ትውልድ በእነዚህ እሴቶች የተገነባ፤ ለእነዚህ እሴቶች የተገዛ በመሆኑ ለፍትሐዊነት ያለው የአስተሳሰብ ቁርጠኝነት የተጠበቀና የማንንም ምስክርነት የሚፈልግ አይደለም ።

የቀደሙት አባቶቹ ለፍትሐዊነትና ለነጻነት ለነበራቸው ትልቅ ስፍራ ራሱን ያስገዛ በመሆኑም፤ በየወቅቱ ለሚያጋጥሙት ችግሮች /ድንበር ተሻጋሪ/ ችግሮች ፍትሐዊነትን ዋነኛ መፍትሔ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ላለፉት ሁለት አስርቶች የተነሱ አለመግባባቶችን በዚሁ አግባብ ለመፍታት በስፋት ተንቀሳቅሷል። ጉዳዩን ከፍትሐዊነት ባለፈም ጉዳዩ የወንድማማችነት የጋራ ልማት እንዲሆን በብርቱ ተንቀሳቅሷል።

የዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተከትሎ ሊስተናገድ የሚችል ስለመሆኑና ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ይህንኑ ተቀብላ ለማስተናገድ ያላትን ቁርጠኝነት በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለማሳወቅ ሞክሯል። በዚህም በሕግና በሥርዓት በሚታመነው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ እና ተቀባይነት ማግኘት የቻለችበት ተጨባጭ ሁኔዎች ተፈጥረዋል።

እውነታው ፍትሐ ዊነትን በሚያምኑ የግብፅ ፖለቲከኞች እና ምሁራን ሰፊ ተቀባይነት አግኝቷል። የረጅም ዘመን ታሪክ እና ከታሪክ የሚቀዳ እውቀትና ጥበብ ባለቤት በሆነው የግብጽ ሕዝብ ዘንድም መተማመን መፍጠር የሚያስችል ዕድል አስገኝቷል። በሀገሪቱ ሕዝቦች መካከል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመፍጠር ያስቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሮም ነበር።

የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ግን ምርጫ በመጣ ቁጥር ሆነ፤ በሀገሪቱ የውስጥ አለመረጋጋት በተከሰቱባቸው ወቅቶች ሁሉ የወንዙን የውሃ አጠቃቀም እንደ አዲስ አጀንዳ በማድረግ ፤የግብጽን ሕዝብ መንፈስና አእምሮ ለመያዝ ከሚያደርጉት ያልተገባ ጥረት የተነሳ ዛሬም የዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ጉዳይ በግብጽ ፖለቲከኞች አዲስ አጀንዳ ሆኖ ቀርቧል።

የሀገሪቱ ፖለቲከኞች ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለያዩ ወቅቶች በተደረጉ ድርድሮች ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ ሳይቀር በማፈንገጥ፤ ተመልሰው ወደ ቅኝ ገዥዎች የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ፊታቸውን አዙረዋል፤ የአፍሪካውያን ውክልና ለሌላቸው ስምምነቶች ሕይወት ለመዝራት ሲጥሩም ተስተውለዋል።

አፍሪካውያን ዛሬ ላይ ያሉበትን ነፃነትና ለነጻነት የከፈሉትን ዋጋ በማይመጥን መንገድ ላይ ቆመው በሁለቱ አፍሪካውያን ወንድማማች ሕዝቦች መካከል አለመተማመን እንዲሰፍን፤ ከዚህም ያልተገባ ፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እየተንቀሳቀሱ ይገኛል።

ይህ የግብጽ ፖለቲከኞች በዓባይ ወንዝ የውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚያራምዱት አቋም በየትኛውም መስፈርት የግብጽን ሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እውን ሊያደርግ አይችልም። በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ዘላቂነት ያለው መተማመን በመፍጠር የጋራ ተጠቃሚነትን የማስፈን አቅምም የለውም። ከዚህ ይልቅ በብዙ ታሪክና ከታሪክ የሚቀዳ ዕውቀትና ጥበብ ባለቤት የሆነውን የግብጽ ሕዝብ የሚያሳንስ ነው!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You