ቤተክርስቲያኗ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመቀራረብ ለሀገር ሰላምና አንድነት በትብብር ትሠራለች

አዲስ አበባ፡- ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመቀራረብ ለሀገር ሰላምና አንድነት በትብብር የመሥራት ፍላጎት እንዳላት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ገለጸች፡፡ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የቀጣይ 10 ዓመት እቅዷን በትናንትናው እለት ይፋ አድርጋለች፡፡

ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ እንደገለጹት የዓለም አቀፍ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ የስብከተ ወንጌል ተልእኮ እንድትፈጽም ባለፉት ሁለት ዓመታት ምክክር ሲደረግ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ይህንን ጥሪ ተቀብላ ውጤታማ ስብከተ ወንጌል ልትሰጥባቸው የምትችልባቸው ዘዴዎች ላይ በሁሉም ሀገረ ስብከቶች ውይይት አድርጋ በቀጣይ 10 ዓመታት ትኩረት የምትሰጥባቸው ተግባራት ለይታ መርሀግብር ነድፋለች ብለዋል።

ይህ እቅድም የቤተክርስቲያን ቀኖናዊ መዋቅሮች ለማጠናከር፣ ደቀመዛሙርትን ለማፍራት ፣ አብሮነትን ለማዳበር ፣ ሰላምን ለማስፈን፣ ማህበራዊ አገልግሎቶች ከስብከተ ወንጌል ጋር ለማስተሳሰር እንዲሁም ቤተክርስቲያኒቷን ንብረት ለማስተዳደር የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ በዚህ እቅድም ቤተክርስቲያን የዘመኑን ፣ የሀገሪቱንና የሕዝቡን ችግር ብቻዋን መፍትሄ መስጠት እንደማትችል ተገንዝባ ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመቀራረብና በመወያየት ለዜጎች ሁለንተናዊ አድገት ፣ ለሀገር ሰላምና አንድነት ፣ ለዜጎች ሞራላዊ ሕይወት መታነጽ በቅንነት በትብብር መንፈስ ለመሥራት ፈልጋለች ብለዋል፡፡

ክፉውን የመጥላትና የጽድቅ መንገድ የማሳየት ተልእኮዋን የምትወጣ ቤተክርስቲያን እርቅና ሰላም እንዲሰፍን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅታ የምትሠራ መሆኗን አክለዋል፡፡

የጳጳሳት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ አባ ተሾመ ፍቅሬ በበኩላቸው የ 10 ዓመቱ መሪ እቅድ የቤተክርስቲያን አባላት ሁሉ የተሳተፉበት የውይይት ፍሬ ነው ብለዋል፡፡

በ 10 ዓመት መሪ እቅድ የቤተክርስቲያን ቀኖናዊ መዋቅር፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ፣ የልግስና አገልግሎት ፣ የሰብዓዊ ርዳታ ፣የሰላም ግንባታና ማህበራዊ ትስስር ላይ ማሻሻያዎች መደረጉን ገልጸዋል፡፡

አባ ተሾመ የቤተክርስቲያኗ አንዱ ተልዕኮ የተጎዱትን በማገዝና ተፈጥሮን በመንከባከብ የፍቅር አገልግሎት መስጠት ነው ያሉ ሲሆን በዚህም ዘላቂ ልማት ከሚያስቀጥሉና ሀገሪቷን ከድህነት ለማውጣት ከሚሠሩ አካላት ጋር ቤተክርስቲያኒቷ በጋራ ትሠራለች ብለዋል፡፡

የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ከ 400 በላይ ትምህርት ቤቶችና ከ90 በላይ የጤና ተቋማት ያሏት ሲሆን በነዚህም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጥራት ያለው የጤናና የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ አበርክቶ እያደረጉ ይገኛል ብለዋል፡፡

መስከረም ሰይፉ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You