በማስተማር ዘዴዋ የብዙዎችን ቀልብ የሳበችው መምህርት ዙፋን

የተወለደችው አዲስ አበባ በተለምዶ አፍንጮ በር አካባቢ ነው፡፡ ተማሪ በነበረችበት ወቅት በቴአትር፣በውዝዋዜ እና በመሳሰሉት በክበባት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ተመርቃለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሀሌሉያ ቅድመ አንደኛ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የቅድመ አንደኛ(ኬጂ) ሁለት መምህርት ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ጨዋታ ተኮርና ልጆች ፊደላትን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችላቸውን አዲስ የማስተማር ስነ ዘዴ ይዛ ብቅ ብላለች፡፡ ይህንኑ የማስተማር ስነ ዘዴ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ ደግሞ በቲክቶክ አማካኝነት በማቅረብ በብዙኃን ይበልጥ ለመታወቅ ችላለች- መምህርት ዙፋን ተዓመር፡፡

መምህርት ዙፋን ማስተማር ከጀመረች ስድስት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ የመምህርነት ሙያዋን በፍላጎት፣ በፍቅር እና ደስተኛ ሆና ነው እየሰራችበት ያለችው። የዚህ ትውልድ አንዷ አካል እንደመሆኗ በክፍል ውስጥ ከምታስተምራቸው ተማሪዎች በተጨማሪ ሌሎች በየቤቱ ያሉ ልጆችን ለማስተማር ማህበራዊ ሚዲያን በተለይም ቲክቶክን ትጠቀማለች፡፡

መምህርት ዙፋን ወደ ቲክቶክ የመጣችው አብዛኛው ሰው እንደሚሠራቸው ትወናዎች የማስተማር ስራዎቿን ቀርፃ ነበር፡፡ በመቀጠል ግን ከልጆች ጋር ያላት ግንኙነት ምን እንደሚመስልና ውሎዋን ለተመልካቾቿ ማጋራት ጀመረች፡፡ ሃሳቧ አድጎ የሕፃናት መዝሙር መልቀቅ በቲክቶክ ለቀቀች፡፡ ተማሪዎችን በመዝሙር እና በተለያዩ መንገዶች እያስተማረች በቲክቶክ የምትለቃቸው ቪዲዮዎች ብዙዎቹ አስተማሪነቱን በማመን ወደዱላት፤ እርሷም ቀጠለችበት፡፡

ሕፃናትን ለማስተማር ድራማዊ እንቅስቃሴዎችን መጠቀምና ትምህርቱን ጨዋታ ተኮር ማድረግ እንደሚገባ በትምህርት ባለሙያዎች በኩል ይመከራል። ምንም እንኳን በኪነ ጥበቡ ብዙ ያልቀጠለች ቢሆንም መምህርት ዙፋን ትምህርት ቤት እያለች ክበባት ውስጥ መሳተፏና ልምምድ በማድረጓ ከልጆች ጋር በጋራ እየዘመረችና ሌሎች ኪናዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች እንድታስተምር አግዟታል ፡፡

የሕፃናት (ኬጂ) የመማር ማስተማር ሂደት ለሌሎች ክፍሎች ከሚሰጠው ትምህርት እንደሚለይ ይታወቃል፡፡ ከልጆች ጋር እንደ ልጅ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ቤተሰባዊነት እንዲኖርም ያስፈልጋል፡፡ መምህርት ዙፋንም ያደረገችው ይህንኑ ነው፡፡ ልጆች ወደ ትምህርት ቤት ሲመጡ በተቻለ መጠን ሊማሩ የመጡ እስከማይመስላቸው ድረስ ደስ ብሏቸው እየተዝናኑ፣እየተጫወቱ እና እየዘመሩ ትምህርት ቀስመው እንዲሄዱ እያደረገች ነው፡፡

የመምህራን የትምህርት አሰጣጥ ስነ ዘዴ ተማሪዎች ትምህርቱን እንዲወዱትም፤ እንዲጠሉትም የማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን በመረዳት እርሷ ፊደላትን በቀጥታ ከማስተማር ይልቅ ለተማሪዎች አሰልቺ እንዳይሆኑ ካሉት መዝሙሮች እና ተረቶች በተጨማሪ በራሷ በማዘጋጀት በጨዋታ መልክ ተማሪዎቿን እውቀት ታስገበያለች፡፡

በመማር ማስተማር ሂደቱ መምህራን ብቁ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የምትናገረው መምህርት ዙፋን፤ በተለይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ልጆች መሠረት የሚይዙበት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ትጠቁማለች፡፡ የአእምሮ ማበልጸጊያና ነገ ልጆች የተሻለ ሰው እንዲሆኑ ማፍሪያና ማዘጋጃ ቦታ ስለመሆኑም ትጠቅሳለች፡፡

የሕፃናት የአእምሮ እድገት የሚገነባበት ከውልደት እስከ ስምንት ዓመታቸው እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። ሰፊውን ጊዜ የሚይዘው ደግሞ የቅድመ አንደኛ (ኬጂ) ትምህርት ነው፡፡ ሕፃናት ነጭ ወረቀት እንደመሆናቸው መጠን የሚቀበሉበት የሚሰጣቸውን ነገር መሠረት አድርገው ነውና ሥራው ትልቅ ኃላፊነትን እንደሚሻም ነው መምህርት ዙፋን የምትናገረው፡፡ ‹‹እኛ መምህራን ትውልድ ላይ ብንሠራ ሀገራችንን በሚገባ መቀየር እንችላለንም›› ትላለች፡፡

አሁን አሁን ልጆች በስልክ፣ታብሌት እና ቤታቸው ውስጥ ባሉት የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች በመጠቀም ማኅበራዊ ሚዲያን ይመለከታሉ፡፡ ወላጆች ለዚህ ድርጊት ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ለልጆቻቸው ምን መስጠት እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው መለየት ይኖርባቸዋል፡፡ የሚሰጧቸው ነገሮች ሕፃናት ወደ ጥሩም ይሁን ወደ መጥፎ ነገር እንዲያመሩ ያግዛቸዋል፡፡

መምህርት ዙፋን በክፍሏ ውስጥ ከምታስተምረው በተጨማሪም ማህበራዊ ሚዲያውን በመጠቀም ልጆችን በሚስብ መልኩ በመሥራቷ ከምታስተምራቸው ተማሪዎች ውጪ ሌሎች ተማሪዎች መዝሙሮቹን ይዘምራሉ፤ እግረ መንገዳቸውን ትምህርትም ይቀስማሉ፡፡ ስለዚህ ማህበራዊ ሚዲያን ለበጎ ነገር መጠቀም እንደሚቻል ምስክር ሆናበታለች፡፡ መምህራን ለተማሪዎች አርአያዎች ናቸው፡፡

ተማሪዎች እነርሱ ያሏቸውን ይቀበላሉ፡፡ ከቤተሰባቸው ይልቅ እነርሱን ነው የሚሰሙት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የቤተሰብ እገዛ ካልተጨመረበት የመምህራን ሥራ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ እንደማይችልም ነው መምህርት ዙፋን የምትናገረው፡፡

መምህርት ዙፋን እየሠራች ባለው ሥራ ከጠበቀችው በላይ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝታበታለች። በተለይ በልጆች እና በወላጆች ዘንድ ተወዳጅ መሆን ችላለች፡፡ ‹‹በዚህ ሠዓት ምንድን ነው የምትወጂው?›› ብትይኝ ‹‹ልጅ ነው የምልሽ›› ብላ የመለሰችው መምህርቷ፤ ለልጆች ያላት ፍቅር ሥራዋን ወዳውና ፈልጋው በቁርጠኝነት ለመሥራት እንዳስቻላት ትገልፃለች፡፡ በዚህም ከብዙዎች ገንቢ እና ጥሩ የሚባሉ አስተያየቶችን ማግኘት በመቻሏ በሥራዋ ላይ ትልቅ መነሳሳት እንደፈጠረላት ታስረዳለች፡፡

መምህር ዙፋን በቀጣይ በልጆች ዙሪያ ብዙ የመሥራት እቅዶች አሏት፡፡ ልጆች እየተዝናኑ፣ እየተማሩ፣ ቁም ነገር እያገኙ በሥነ ምግባር ታንጸው ሀገራቸውን የሚወዱ፣ለራሳቸው ክብር የሚሠጡ ዓይነት ሕፃናት ሆነው እንዲያድጉ የተለያዩ ሥራዎችን ይዛ በስሟ በተከፈተው የዩቱብ ቻናል በስፋት ለመምጣትም ውጥን ይዛለች፡፡ ከዚህም ባለፈ በትምህርት ቤት ውስጥ ከቀለም ትምህርት፣ ከአእምሮ እድገት ባሻገር ሕፃናቱ ሀገራቸውን፣ ባህላቸውን እና እምነታቸውን እንዲወዱ ከወዲሁ መሠረት ለማስያዝ የመሥራት እቅድ አላት፡፡

በዚህ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ እንዲሁም የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ወደ ቲክቶኩ ዓለም ጎራ ሲባል ደግሞ አብዛኛው ጉዳዮች መዝናናት ላይ ያተኮሩ ናቸው። መምህርት ዙፋንም በቲክቶክ ብዙዎች ቁም ነገር እየሠሩበት እንዳልሆነ ታዝባለች፡፡ ከማህበራዊ ሚዲያው በሻገር ኪነ ጥበብን በመጠቀም ሕፃናት የሚማሩበትን መንገድ እና ሌሎች መልካም ነገሮችን በመሥራት ለመጪው ትውልድ መሥራት እንደሚገባ ትመክራለች። አዲሱ ሥርዓት ትምህርት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች እየተዝናኑ ማስገንዘብ እንደሚገባ የሚጠቁም በመሆኑና ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ብዙዎች ይህንን ብዙ መምህራን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ተግባራዊ እያደረጉት ባለመሆኑ ለመምህራንም ሆነ ወላጆች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል፡፡

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You