በኢትዮጵያ ታሪክ እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን፤ስማቸው ከፍ ብሎ የሚነሳ ብዙ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች ተፈጥረዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ጀግኖች መፍጠር የቻሉ ተቋማትም ስማቸው አብሮ ይነሳል። ከእነዚህ ተቋማት መካከል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ የ88ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያየ ዝግጅት ያከበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል አንዱ ሲሆን፤ ጀግኖችን በማፍራት በጉልህ ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከልም ቀዳሚ ሆኖ ስሙ ይነሳል።
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስም ከዚህ ተቋም የወጣ የሀገር ባለውለታ ጀግና ነው፡፡ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በጀግንነት ከተፋለሙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መካከል አንዱ ነው።
ጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ከአባቱ ከአቶ ጴጥሮስ ሎዳሞ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ሸዋዬ አብርሃም በአሁኑ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ምስራቅ ባዳዋቾ ወረዳ አንደኛ አምቡርሴ ቀበሌ ሐምሌ 13 ቀን 1943 ዓ.ም ነው የተወለደው፡፡(ፎጊ) በሚል የበረራ ኮድ ስሙ የሚታወቅ የሰማዩ ጀግና ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ለወላጆቹ ሶስተኛ ልጅ ነው።
ከልጅነቱ ጀምሮ በአመለሸጋነቱ ይታወቃል፡፡ደፋር፣ቁጡ ግን ደግሞ ይቅር ባይና ተግባቢ ባህሪይ መገለጫው ነው፡፡ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ትምህርትቤት ገብቶ የተከታተለ ሲሆን፤ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በሆሳዕና ከተማ በቀድሞ ራስ አባተ ቦያለው በአሁኑ የካቲት 25/67 ትምህርት ቤት ትምህርቱን ለመከታል በቅቷል፡፡ በትምህርት አቀባበሉም ቢሆን ፣ንቁና ጎበዝ ነበር፡፡ ወታደር የመሆን ዝንባሌም ነበረው፡፡
ኮሎኔል በዛብህ 12ኛ ክፍል ሆኖ ነበር በወቅቱ የኢትጵያ አየር ኃይል ባወጣው ማስታወቂያ የተወዳደረው፡፡ የተሰጠውን ምዘና በብቃት በመወጣት ጥር 26 ቀን 1961 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ተቀላቀለ፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ከተቀላቀለ በኋላ በተቋሙ የሚሰጡ ሥልጠናዎችን በብቃት ተከታትሏል።ከተከታተላቸው የሥልጠና ዘርፎች ውስጥ፦ የስድስት ወር መሠረታዊ የውትድርና ትምህርት(ኮርስ)፣የሰባት ወር መሠረታዊ የበረራ ኮርስ፣የስድስት ወር የመጀመሪያ ደረጃ የበረራ ሥልጠና ኮርስ፣የአውሮፕላን አብራሪነት ዲፕሎማ እንዲሁም ከፍተኛ የተዋጊ አውሮፕላን ሥልጠና ኮርስ በሀገር ውስጥ ሰልጥኗል።
ከሀገር ውጭ በሀገረ አሜሪካ እና በቀድሞ ሶቭየት ህብረት የሚሰጠውን የበረራ ትምህርት ስልጠና ተከታትሎ በብቃት አጠናቋል፡፡በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በወሰዳቸው የሥልጠና ኮርሶች ባገኘው ዕውቀት እና ክህሎት እንዲሁም ባዳበረው ልምድ በአየር ኃይል ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ለረዥም ጊዜ ተዛዋውሮ አገልግሏል፡፡
ኮሎኔል በዛብህ አገልግሎት ከሰጠባቸው የተለያዩ ቦታዎች ውስጥ በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነት፣ በበረራ አስተማሪነት፣ በስኳድሮን ምክትል አዛዥነት፣በተዋጊ ስኳድሮን የበረራ አስተማሪነት፣ በበረራ ትምህርት ቤት የትምህርት መኮንን በመሆን (በተደራቢነት)፣በበረራ ትምህርት ቤት አዛዥነት በተደራቢ፣በሰሜን አየር ምድብ ጥገና አዛዥነት፣በኤል-39 አውሮፕላን በረራ አስተማሪነት፣ በበረራ ትምህርት ቤት ምክትል አዛዥነት፣በበረራ ማሰልጠኛ ትምህርትቤት የሥርዓተ ትምህርት ደረጃ እና ምዘና ኃላፊነት፣በበረራ ትምህርትቤት የዕቅድና ሥርዓተ ትምህርት ኃላፊነት፣በኤል-39 አውሮፕላን ስኳድሮን አዛዥነት እንዲሁም በምሥራቅ አየር ምድብ አዛዥ ተደራቢ በመሆን የሰራባቸው ቦታዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
በአየር መቃወሚያ ተመትቶ አበቃለት ሲባል ከጅጅጋ እስከ ደብረዘይት በሰላም በመብረር ያሳረፈ ፓይለት እንዲሁም ጠላትን እግር በእግር ተከታትሎ የጠላት ተዋጊ ጄት በማጋየት ታሪክ የሰራ፣ የምንግዜም የኢትዮጵያ ጀግና ነው። ከሀገር ሉዓላዊነት የሚቀድም ምንም ነገር የለም የሚል ፅኑ አቋም እንደነበረው የሚነገርለት ኮሎኔል በዛብህ ይህንን አቋሙን በተግባር ኖሮ ማሳየት ችሏል።
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ታላቅ ገድል ከፈፀመባቸው የውጊያ ውሎዎቹ መሃል የሐምሌ 27 ቀን 1969 ዓ.ም በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በዚያ ወቅት ትምክህተኛው የዚያድባሬ መንግሥት በምሥራቅ ኢትዮጵያ ግዙፍ ወታደራዊ ወረራ ፈፅሞ ነበር፡፡ ይህንን ወረራ ለመመከት ከተሰማሩት የአየር ኃይል (አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ 5 ኢ) ተዋጊ ጀቶች መሃል አንዱን የያዘው እሱ ነበር፡፡
በወቅቱ በኦጋዴን ሐረዋ፣ አይሻ፣ በእነኖሜጢ እና በሌሎችም ቦታዎች የሮኬት ናዳ በማውረድ ወራሪውን የሶማሊያ ጦር ባለበት እንዲገታ ከማድረግ ባሻገር፣ 8 የጠላት ታንኮችን ከእነ ምድብተኛው ረምርሟል። ይህንን ታላቅ ጀግንነት ባስመዘገበ በ10 ሰዓት ልዩነት እንደገና ወደምሥራቅ ጦር ግንባር በመብረር የኢትዮጵያን አየር ኃይል ብቃት ያስመሰከረም ነው።
ጥቅምት 7 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሠራዊት በጅጅጋ ካራማራ ላይ ከፍተኛ ትንቅንቅ ላይ ነበር። ያኔ እሱ ከላይ ከሰማይ በሚያወርደው ቦንብ የሶማሊያን ወራሪ ጦር ብትንትኑን ማውጣት ተያያዘ። በዚህ ጊዜ ከጠላት ወገን በተተኮሰ አየር መቃወሚያ የሚቀዝፈው ኤፍ 5 ኢ ተዋጊ ጀት ተመታ፡፡ ይኼኔ እሱ በዥንጥላ ወርዶ ህይወቱን ማትረፍ ነበረበት፡፡
ነገር ግን የሚያበረውንም ጀት ጭምር እንጂ የራሱን ህይወት ብቻ ማትረፍ አልፈቀደም፡፡ እናም የሚያበረውን ጀት በቆራጥነት እየቀዘፈ ወደ ደብረዘይት አየር ማረፊያ ገስግሶ በሰላም አረፈ። የተመታውም ጀት ተጠግኖ እንደገና ለግዳጅ መሰማራት ችሏል።
የጀግናው ኮሎኔል ገድል ይቀጥላል፡፡ በነገሌ ቦረና ግንባር የተሰማራውን የሶማሊያ ጦር የቦንብ ናዳ በማውረድ ጠላትን ብትንትኑን ማውጣቱን ቀጠለ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁለት የሶማሊያ ጦር ጀቶችን በአየር ላይ አጋይቶ መጣል ችሏል። የሚገርመው አንዱን የሶማሊያ ጦር ጀት ያጋየው ሶማሊያ ግዛት ውስጥ ዘልቆ ገብቶ ስለመሆኑ ታሪክ ያስረዳል።
ጥቅምት ወር 1970 ዓ.ም የሶማሊያ ጦር ጀቶች ድሬዳዋ ከተማ ላይ ጥቃት ፈፀሙ፡፡ ይኼኔ ለጥቃቱ የአፀፋ መልስ እንዲሰጡ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ተዋጊዎች ታዘዙ፡፡ ከታዘዙት ተዋጊዎች መሃል አንዱ የነበረው ኮሎኔል በዛብህ ነበር እናም ጀቱን እየቀዘፈ የአየር ላይ ትርዒት ጭምር በማሳየት ጀግናው ተልቅ ገድል ፈፀመ፡፡ እናም የሶማሊያን ሚግ 21 ተዋጊ ጀት ከነአብራሪው በአየር ላይ አጋይቶ በሰላም ወደ ደብረዘይት ተመለሰ፡፡
ታህሳስ 13 ቀን 1970 ዓ.ም በዛብህ፤ ዩጎ ውጫሌ በሚባል ቦታ ላይ የሚገኝን የሶማሊያ ጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት እና መካናይዝድ ክፍለጦር መምሪያ በቦንብ እያጋየ ሳለ ከጠላት ወገን በተተኮሰበት አየር መቃወሚያ ጥይት የሚያበረው አውሮፕላን ሞተር ክፍል ተመታበት፡፡ በዛብህ ጴጥሮስ አውሮፕላኑ ክፉኛ ቢመታም አልተደናገጠም፡፡ የተመታውን አውሮፕላን መልሶ ደብረዘይት ለማሳረፍ ታላቅ ጥረት አደረገ። ሆኖም ጥረቱ አልተሳካም፡ የአውሮፕላኑ ነዳጅ አለቀበት፡፡ በዚህ የተነሳ ደብረዘይትና ሞጆ መሃል በሚገኝ ገላጣ ሜዳ ላይ አውሮፕላኑን አሳርፎ ድርብ ጀግንነቱን አስመሰከረ፡፡
ጀግናው በዛብህ ጴጥሮስ፤ በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር ተፈሪ በር በተባለ የጦር መንደር ላይ የሚገኘውን (በጥር ወር 1970) የከባድ መሳሪያ ግምጃ ቤት እና የጠላት ጦርም ድባቅ መታ፡፡ በዚህ ወቅት 5 የጠላት ታንኮችን ከነምድብተኛቸው ደመሰሰ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ከጠላት በተተኮሰ ፀረ አውሮፕላን ጥይት ተመቶ የሚያበረው አውሮፕላን በእሳት ተያያዘ። ጀግናው ይህም ጥቃት አላሸበረውም፡፡ እሳቱን በመከላከያ በማጥፋት ወደመጣበት ተመለሰ፡፡ አሁን ግን ደብረዘይት መድረስ አልቻለም፡፡ አውሮፕላኑን ድሬዳዋ አየር ማረፊያ አሳረፈው፡፡ አውሮፕላኑም ተጠግኖ እንደገና ለግዳጅ በቃ፡፡
ይህ ጀግና፤ ከሚያዝያ ወር 1970 ጀምሮ ኤርትራ ወደሚገኘው 2ኛው አየር ምድብ እንዲዛወር ተደረገ። በዛብህ ጴጥሮስ የሶማሊያን ወረራ ለመቀልበስ ከሐምሌ ወር 1969 እስከ የካቲት ወር 1970 በተደረገ የመከላከልም ሆነ የማጥቃት ውጊያ 191 ጊዜ ወደጠላት ወረዳ በርሯል። የጠላትን እግረኛ እና የሜካናይዝድ ጦር፤ ተዋጊ አውሮፕላንና የራዳር ጣቢያዎችን ደምስሷል፡፡ በዚህ የላቀ እና ታላቅ ሀገራዊ ተጋድሎ ላበረከተው አስተዋፅኦ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት መስከረም 3 ቀን 1972 ዓ.ም “የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳይ” ሸልሞታል፡፡
በዛብህ ጴጥሮስ ህዳር 21 ቀን 1972 ዓ.ም ለንባብ በበቃው “ታጠቅ” ለተሰኘ የሠራዊቱ ጋዜጣ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ የሚከተለውን ተናግሮ ነበር “… እኛ ብንሞት ሌላ ሰው ይተካናል፤ መተኪያ የሌላት ኢትዮጵያ ከሞተች ግን ተተኪው ትውልድ ስለሚሞት ዋጋ አይኖረውም፡፡ የሀገርን ሉአላዊነት በአስተማማኝነት መጠበቅ ቆራጥነት እና ልበ ሙሉነት ይጠይቃል፡፡ እኛ በሕይወት ቆመን እያየን ጠላት አንዲት ስንዝር መሬት ቆርሶ መሄድ ቀርቶ በአንድ እግሩ እንኳ ሊቆምባት አይችልም፡፡ ከሀገር ወዲያ ሌላ መኖሪያ ዋሻ ስለሌለ በሃገር እና በነፃነት ጉዳይ ምንም ቀልድ ሊኖር አይችልም፡፡…”ነበር ያለው።
ከሶማሊያ ወረራ በኋላ ወደ ኤርትራ ዘምቶ እስከ 1977 ድረስ ግዳጁን በአግባቡ የተወጣው ኮሎኔል በዛብህ፤ በ1977 ዓ.ም (ከሻዕቢያ)ኤርትሪያ ጋር እየተዋጋ ሳለ አውሮፕላኑ ተመታ፡፡ በዚህን ጊዜ ወደተነሳበት ቦታ አውሮፕላኑን መመለስ ያልቻለው በዛብህ በሻዕቢያ(ኤርትራ)እጅ ወደቀ፡፡ በዚህ ምክንያት እስረኛ ሆኖ በ1983 ዓ.ም ከእስር ተለቆ ከቤተሰቡ ጋ መቀላቀልም ችሎ ነበር፡፡
ከ7 ዓመት በኋላ በ1990ዓ.ም በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል በተነሳ ጦርነት ዳግም ለመሳተፍ በቃ፡፡ግንቦት 5 ቀን 1990 ዓ.ም ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ወደ ኤርትራ ምድር ዘልቀው ከገቡ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ተዋጊዎች አንዱ ነበር፡፡ የሚያበረውን አውሮፕላን እጅግ ዝቅ አድርጎ ሲበር እንደገና በኤርትራ ኃይሎች እጅ ወደቀ ተማርኮም እስረኛ ሆነ፡፡ ኮሎኔል በዛብህ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ ተሳትፏቸው የሚታወቁት የፕሮፈሰር በየነ ጴጥሮስ ወንድም ነው። ኮሎኔል በዛብህ በውጊያ ወቅት በኤርትራ ኃይሎች ከተያዘ በኋላ በህይወት አለ ወይስ የለም የሚል ድምዳሜ ላይ እስካሁን አለመደረሱን ቤተሰቦቻቸው ይገልፃሉ።
በጉዳዩ ላይ በተደጋጋሚ አስተያየት የሚሠጡት አንጋፋው ፖለቲከኛ በየነ ጴጥሮስ ወንድማቸው “በዛብህ በህይወት ላለመኖሩ በቂ ማስረጃ” አለመገኘቱን ይገልፃሉ። በህይወት አለ የሚሉ መኖራቸውን የሚያነሱት ፕሮፌሰር በየነ፤ አሁን ይህንን ማረጋገጥ ያለበት የኤርትራ መንግሥት መሆኑን ያነሳሉ።
አሁን ላይ ሞቷል እያሉ የሚጽፉት ነገር የዐይን እማኞች ከሚሉት ጋር እንደሚጋጭም ነው የሚያረጋግጡት። የኮሎኔል በዛብህን ጉዳይ በተመለከተ ማረጋገጥ ያለበት የኤርትራ መንግሥት ነው ቢሉም በየደረጃው ያሉ የኤርትራ ባለሥልጣናት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ነበር።
ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠራዊት አባል ሆኖ በተሰማራባቸው አውደ ውጊያ ግንባሮች ከፍተኛ ጀብድ እየፈፀመ የኖረ የሀገር ኩራት የሆነ ጀግና ነው። ጀግናው ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ከወይዘሮ ወይንሸት ኃይሌ ጋር ትዳር መሥርተው ሶስት ወንድና ሁለት ሴት በድምሩ አምስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም