‹‹መስረቅ ክልክል ነው›› ይባላል?

መቼም በመሠልጠን ጉዳይ ላይ የጻፍኩት ትዝብት ቢቆጠር ሌሎች ትዝብቶች ሁሉ ተደምረው አይደርሱበትም፡፡ በእርግጥ የአንዲት አገር ዕድገትም የማኅበረሰብ ዕድገት ነው፤ የማኅበረሰብ ዕድገት ደግሞ የአስተሳሰብ ልዕልና ሲኖር ነው፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ባየሁ ቁጥር ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ስለሀገሬ ሁኔታ አስባለሁ፡፡ ለምንድነው በዚህ ልክ ወደኋላ የቀረነው? የሚለው ነገር አሁንም ጥያቄ ሊሆንብን ይገባል፡፡

ከትናንት ወዲያ ጠዋት (ሰኞ) በአንድ ትልቅ የፌዴራል መሥሪያ ቤት መፀዳጃ ቤት ውስጥ የእጅ መታጠቢያው መስታወት ሥር ‹‹እባክዎ የእጅ ሳሙና ቀንሰው አይውሰዱ!›› የሚል ማሳሰቢያ አየሁ፡፡ የተማረሩ የጽዳት ሠራተኞች ይመስሉኛል የለጠፉት። የተቋሙ አመራሮችም ሆኑ ፅዳቶች ይህን ከማለት ውጭ ምንም አማራጭ የላቸውም፤ ወደው አይደለም ለማለት ነው፤ ሁኔታው አስገድዷቸው ነው። የሚሰርቅ ሰው ስላለ ነው፡፡

እንግዲህ አስቡት የኋላቀርነታችንን ደረጃ! ‹‹አትስረቁ›› ተብሎ መነገር ነበረበት? መስረቅ ክልክል መሆኑ በማሳሰቢያ መጻፍ ነበረበት? ይህን ለማወቅ የትኛውም የትምህርት ደረጃ ይቅርና ዝም ብሎ ሰው መሆን ብቻውን አይበቃም ነበር?

እንዲህ አይነት ሰው በማሳሰቢያም አይመለስም። መቼም የሚሰርቀው ረስቶት አይሆንም፤ አስቦበት ነው፡፡ እንዲህ አይነት የተበላሸ ሥነ ምግባር ያለው ሰው ደግሞ ማሳሰቢያም አይመልሰውም፤ ምክንያቱም ማሰቢያ የለውም፡፡ ማሳሰቢያ የሚደረገው ማሰብ ለሚችል ሰው ነው፡፡ ማሳሰቢያ የሚደረገው የሚፈቀዱና የሚከለከሉ ነገሮችን ለመለየት ነው እንጂ ጤነኛ ሰው በመሆን ብቻ ሊታወቁ ለሚገባቸው ነገሮች አልነበረም፡፡

ለምሳሌ ‹‹የሴቶች መጸዳጃ ቤት፣ የወንዶች መጸዳጃ ቤት›› ተብሎ የሚጻፈው ወይም ምልክት የሚደረገው የውጭ ሰው (እንግዳ) ማወቅ ስለማይችል ነው፡፡ ወደ አንድ ተቋም ወይም ሆቴል ወይም ሌላ የአገልግሎት ቦታ ስንሄድ ጽሑፍ ወይም የሴትና የወንድ መሆኑን የሚለይ ምስል ከሌለው የሴትና የወንድ መፀዳጃ ቤት ለይተን ልናውቅ አንችልም፡፡ ከመፀዳጃ ቤቱ ውስጥ የእጅ ሳሙና መውሰድ እንደሌለበት ግን ሊነገረው አይገባም፡፡ ውሃ መድፋት እንዳለበት፣ የእጅ መታጠቢያውን ሳይዘጋ መሄድ እንደሌለበት ግን ሊነገረው አይገባም ነበር፡፡ ዳሩ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነና እነዚህን ነገሮች ሁሉ መናገር ግዴታ ሆነ ማለት ነው፤ ብክነት!

በአውሮፓዊቷ አገር ኖርዌይ ለትምህርት የቆየ አንድ ጓደኛዬ የነገረኝ ገጠመኝ ነበር፡፡ የሆነ የኳስ መጫወቻ ሜዳ አለ፡፡ ከአፍሪካ የሄዱ ጥቁሮችም አብረው ይጫወታሉ፡፡ ነጮች በልማዳቸው ኳስ ተጫውተው እንደጨረሱ ኳሱን ይዘው አይሄዱም፤ እዚያው ነው የሚቀመጠው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የአንዲት አፍሪካዊት አገር ሰው ወደ ሀገሩ መመለሻ ጊዜው ሲደርስ ኳሷን ይዞ ሄደ፤ ‹‹ለምን?›› ሲባል ‹‹ለልጆቼ መጫወቻ›› ብሎ መለሰ፡፡

አስቡት እንግዲህ ኳስን ያህል ተራ ነገር ከአውሮፓ ሰርቆ ወደ አፍሪካ ሲያመጣ፡፡ ‹‹ለካ ከእኛም አገር የባሰ አለ!›› ብለን ተገረምን አለ ያ ጓደኛዬ፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊ ውጭ አገር በጣም ኩሩ ነው፡፡ ቢያንስ የአገሩን ገመና አያሳይም! ግን ጥቁር ነውና ‹‹ከኑግ ጋር ያለሽ መጭ አብረሽ ተወቀጭ›› እንደሚባለው›› አብሮ መታማቱ አይቀርም፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ነጮች ቢንቁን፣ እንደ እንስሳት ቢቆጥሩን፣ ‹‹ያልሠለጠኑ ኋላቀሮች›› እያሉ ቢሰድቡን ይፈረድባቸዋል? ጥቁር ሲሰደብ ያንጨረጭረናል፣ ደማችን ይፈላል፡፡ ያ ወኔ እና እልህ ግን የምንሰደብበት ምክንያት ላይም ጠንካራ ሊሆን ይገባል፡፡ እንዲህ አይነት የተበላሸ ሥነ ምግባር ሲያጋጥመን ልክ ነጭ እንደሰደበን ሁሉ ለዚህም ልንቆጣ ይገባል፤ ምክንያቱም ያ ነጭ የሰደበን በዚህ ምክንያት ነው፡፡

‹‹የሥልጣኔ ባለቤት ነን፣ ቅኝ ያልተገዛን ኩሩ ሕዝቦች ነን›› እያሉ መፎከር ብቻውን ለዛሬ ኩራት አይሆንም፡፡ አዎ! የሥልጣኔ ባለቤቶች ነን፤ ዳሩ ግን በዚያው ልክ ደግሞ የብዙ ብልሹ ሥነ ምግባሮች ባለቤትም ሆነናል፡፡ ‹‹ውሃ ይድፉ›› ተብሎ ማሳሰቢያ የሚጻፍበት ተቋም ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ዲግሪ እና ማስተርስ የትምህርት ደረጃ የደራረቡ ናቸው። የዓለምን የሥልጣኔ ደረጃ ለማወቅ ቅርብ ናቸው። ዳሩ ግን እንደ ሕጻን ስለግል እና አካባቢ ንፅሕና እየተነገራቸው ነው፡፡

ስለራሳችን ገመና ላውራ ብዬ እንጂ ሌሎች ከዚህ የባሱ ሀገራት እንዳሉ የብዙ ሰዎችን ገጠመኞች ሰምቻለሁ፣ አንብቤያለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ኩራት የሆነው አየር መንገዳችን አየር ማረፊያ በሄድኩ ቁጥር፤ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስለአንዲት ሀገር ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የጻፉት ትዝ ይለኛል። በዚያች ሀገር አየር ማረፊያ ውስጥ ያለው መፀዳጃ ቤት በእጅ እንኳን ለመንካት በሚቀፍ ቆርቆሮ መሳይ ነገር መጥፎ ሽታ የፈጠረ ውሃ ነው፡፡ ይህን እንግዲህ እዚያ ቦታ የደረሰ የዓለም ዜጋ ሁሉ ያየዋል፡፡

ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ስትገቡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መሆናችሁ ሁሉ ይረሳችኋል፤ ለዚያውም እኔ ያየሁት የሀገር ውስጥ በረራውን ነው፡፡ በሌሊትም በቀንም አይቸዋለሁ፡፡ 24 ሰዓት የሚሠሩ (ለዚያውም ከትህትና ጋር) የጽዳት ሠራተኞች ናቸው ያሉት፡፡ ወደ አፍንጫ የሚመጣው ሽታ ‹‹ሽንት ቤት ነው ሳሎን ነው ያለሁት!›› ያሰኛል። መጸዳጃ ቤት መሆኑን የምታውቁት ሲንኩን በማየት ብቻ ነው፡፡ እንደዚህም ማድረግ ይቻላል ለማለት ነው።

መቼም ሁሉም ተቋም የ24 ሰዓት የጽዳት ሠራተኛ ሊቀጥር አይችልም፡፡ ለተጠቃሚም ምቾት አይሰጥም፡፡ ዋናው ነገር ዜጋው ሲሠለጥን እና የኔነት ስሜት ሲሰማው ነው፡፡ ያ ካልሆነ የ24 ሰዓት የጽዳት ሠራተኛ ቢቀጠርም መበላሸቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም የሚያበላሸው አንድ ሰው ነው፡፡ ይህን ሁሉ ብልሹ ነገር የምናየውም በጥቂት ምግባረ ብልሹ ሰዎች ነው፡፡

ጽዳት ላይ ያተኮርኩት የጤና ነገር ስለሆነ ነው እንጂ በብዙ የአገልግሎት ማግኛ ቦታዎች ላይ ብዙ አይነት ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ፤ ብዙ ጊዜ ከሚገርሙኝ ነገሮች አንዱ የአሽከርካሪዎች በክላክስ መጫወት ነው፡፡ ከፊቱ ያለ ተሽከርካሪ በትራፊክ መብራት ቆሞ ከኋላ ያለው ያለማቋረጥ ክላክስ ያንባርቃል፡፡ መንገድ ዳር ቆመው ከአስፋልት ማዶ ካለ ካፌ አስተናጋጅ የሚጠሩት በክላክስ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሰው እየረበሹ ነው፡፡

በአጠቃላይ፤ ሞራላዊ እና ጤነኛ ሰው በመሆን ብቻ ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮችን ‹‹አታድርጉ›› የሚል ማሳሰቢያ እየተሰጠን ነው፡፡ ማሳሰቢያ የሚደረገው የተፈቀዱና የተከለከሉ ነገሮችን ለመለየት ነበር፡፡ የሥልጣኔ ደረጃችን ግን ‹‹መስረቅ ክልክል ነው›› የሚል ማሳሰቢያም እንዲኖረን እያደረገ ነውና የሥልጣኔ ባለቤትነታችንን በተግባር እናሳይ!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You