ሀገራዊ ስጋት እየሆነ የመጣው የኮንትሮባንድ ንግድ

በአንድ ሀገር ውስጥ ጤናማ የሆነ የንግድ ሥርዓት መፍጠር ከተቻለ የዜጎችን የመልማት ጥያቄ በተገቢው መመለስ ይቻላል፡፡ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ማሻሻልና ማሳደግም ከባድ አይሆንም፡፡ በተመሳሳይ በአንድ ሀገር ጤናማ የንግድ ሥርዓት ባልሰፈነ ጊዜ እንዲሁ ሕገወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ፣ የንግድ ሥርዓትን በማዛባት የሀገር ኢኮኖሚን በእጅጉ ይጎዳል፡፡

ይህም በዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በመፍጠር እና የሀገር ደኅንነት አደጋ በመሆን ጭምር የነገ ተስፋን ያጨልማል፡፡ በሀገሪቱ ያለው ዕውነታም ይህው ነው።

ምክንያቱም በኢትዮጵያ ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ ይሄንን የሚከውኑ ሕገ ወጥ አካላትም እንዲበራከቱ፤ የኮንትሮባንድ ዓይነቱም ፈርጀ ብዙ እየሆነ መጥቷል። እነዚህ አካላትም ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ያለአግባብ ሀብት ማፍራት ሲችሉ መመልከት ተለምዷዊ ተግባር ሆኗል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አደጋ የደቀነ ስለመሆኑ በስፋት ይነሳል፡፡ ለዚህም በየጊዜው ከጉምሩክ ኮሚሽን የሚወጣው መረጃ ዕውነታውን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ሕገ ወጥና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ኪሳራ እንዲሁም የደቀነው አደጋ እጅግ አደገኛና ፈታኝ መሆኑን በየጊዜው ይገልጻል፡፡ ለምሳሌ፣ ኮሚሽኑ በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር እንደዋለ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በቅርቡ ባወጣው መረጃ ኮሚሽኑ ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እያደረገ ባለው ጥረት የመንግሥት ሹማምንት እንቅፋት እንደሆኑበት አቤቱታውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። ይሄንንም፣ ‹‹የማዕድናት እና የሌሎች ሸቀጦች ሕገ ወጥ ንግድ ከመንግሥትም ከፌዴራል ፖሊስም አቅም በላይ ሆኗል›› ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቤቱታቸውን ያቀረቡት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ናቸው።

የኮንትሮባንድ ንግድ በላዕላይ የመንግሥት ክፍል መፍትሔ የሚያሻ ጉዳይ እንደሆነም ኮሚሽነሩ መናገራቸውን ነው የመገናኛ ብዙኃን የዘገቡት። በተለይ በማዕድን ዘርፍ ያለውን ሕገ ወጥ ንግድ የሚከላከል ራሱን የቻለ የፀጥታ ኃይል እንደሚያስፈልግም ኮሚሽነሩ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል።

ወርቅ እና ሌሎችም ውድ ማዕድናት “ጥቁር መንገድ” ተብለው በሚጠሩ ጎዳናዎች ከሀገር እንደሚወጡ ነው የተገለጸው፡፡ እነዚህ ጎዳናዎች በፀጥታ ኃይሎች ከለላ የሚደረግላቸው እንደሆነና ከበርካታ የመንግሥት ተቋማትም ድጋፍ የሚያገኙ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ሲያዙ የመንግሥት ሹማምንት ሰዎቹንም አብሯቸው የተያዘውንም ሸቀጥ ልቀቁ በማለት ጫና የሚያሳድሩም ስለመኖራቸው ነው የተገለጸው፡፡ ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን በመያዛቸው ለእስር የተዳረጉ የጉምሩክ ሠራተኞች ስለመኖራቸውም ኮሚሽኑ ለፓርላማው ባቀረበው አቤቱታ ተጠቅሷል፡፡

ታዲያ ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ በተለያዩ ዘርፎች እንደ አሸን ፈልቶ የምናስተውለው ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ፤ ለሆዳቸው ባደሩ የመንግሥት ሹማምንቶች ድጋፍ ያለው ነው፡፡ ለዚህም ማሳያዎቹን አንድ ሁለት ብሎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለአብነትም ህልቆ መሳፍርት የሌለው አልባሳትና ሸቀጣሸቀጥ ህጋዊ የመግቢያና የመውጫ ሰነድ ሳይኖረው፤ ታክስ ሳይከፈልባቸው፤ ድንበር ጥሶ፤ ኬላ በጣጥሶ ከሀገር ሀገር ይዘዋወራል፡፡

ማንም ጠያቂ የሌለው በመሆኑም እንደልቡ ይገባል ይወጣል፡፡ ለዚህም በመቶ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙት የንግድ ሱቆች አፍ አውጥተው ይናገራሉ። በተለይም ሕጋዊ ከሆኑ የንግድ ሱቆች በላይ በየጥጋጥጉ ልባሽ ጨርቆችን፣ መጫሚያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችንም አሰማምረውና አበጃጅተው የያዙ ቦንዳ ቤቶችን ላስተዋለ የነጻነታቸውን ጥግ መረዳት አያዳግትም፡፡

እነዚህ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ታዲያ ሕጋዊና ግብር ከፋይ የሆነውን ነጋዴ በኪሳራ ከገበያ እንዲወጣ በማድረግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲፈጥሩ እየተስተዋለ ነው፡፡ የሥራ አጥ ቁጥር በየጊዜው እንዲጨምር በማድረግ ባለሀብቱ የፈጠረው የሥራ ዕድል በሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት ድርጅቶች ይዘጋሉ፤ ሠራተኛ የነበሩ ዜጎችም ሥራ አጥ ለመሆን ይገደዳሉ፡፡ ይህም በመንግሥት ላይ ጫና የሚፈጥርና ኢኮኖሚውን የማዳከም አቅሙ የላቀ ነው፡፡

ታዲያ ችግሩ በዚህ መልኩ የሚገለጸው ሕገ ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፤ በጊዜው መልክ ካልያዘና ካልተገታ መዘዙ ከዚህም በላይ የሀገር ስጋትነቱም ማደጉ አይቀሬ እንደመሆኑ ለችግሩ መቃለል መሥራት ለነገ የማይባል ተግባር ነው። ይሄን ማድረግ ግን የአንድና የሁለት ነጋዴዎችና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ በመሆኑ ሊሰመርበትና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑ የግድ ነው፡፡

ለዚህም መንግሥት ትልቁን ድርሻ በመውሰድ እንደ ሀገር የተጋረጠበትን አደጋ በጥሞና ሊከታተለውና ዛሬ እልባት ሊያበጅለት ካልቻለ ነገ እንደ ሀገር ሊያጠፋን የተዘጋጀ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ለዕድገትና ለልማት ጸር የሆነው ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡

ለአብነትም፣ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ በማድረግ ሕዝቡን ያማርራል፡፡ የበዛ ምሬት ደግሞ አደጋው የከፋ ይሆናልና እንደ ሀገር ሊያጠፋን እየተንደረደረ ያለውን ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መከላከል የግድ ይላል፡፡ ኮንትሮባንድ የማይገባበት ቦታና የማያጠቃልለው የሸቀጥ ዓይነት ባለመኖሩ በተለይም በሰዎች ጤና ላይ ለሚያስከትለው አደጋ ትልቅ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡

የኮንትሮባንድ ነጋዴ ዋነኛ ግቡ ለመንግሥት መክፈል ያለበትን ታክስ ሳይከፍል በነፃ ለማሳለፍ፣ የገበያ ተወዳዳሪነት መርህና የሀገሪቱን ሕግ በመጣስ ትርፍ ማጋበስ ነው፡፡ የፍተሻ ኬላዎችን ጥሶ በማለፍ ዕቃውና ሰነዱ እንዳይመሳከር በማድረግ ከተጠያቂነት ማምለጥ ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ኮንትሮባንድ ንግድ የደራበት ዋናው ምክንያት ምንድነው ብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

‹‹ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ›› እንዲሉ አበው፤ የሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ መነሻና መዳረሻውን በውስጡ የሚያልፉ አካላትን ጭምር በፍጹም በቁርጠኝነት፣ በብርቱ ጥረትና ርብርብ ለይቶ መድፈቅ የግድ ይላል፡፡

ባለፉት አራት ወራት ብቻ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ከሀገር ሊወጡ የነበሩ፤ እንዲሁም ሦስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ገደማ ግምት ያላቸው ወደ ሀገር ሊገቡ የነበሩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን የጉምሩክ ኮሚሽን መያዝ ችሏል፡፡ ይህ ቁጥር ታዲያ ከችግሩ ስፋትና ጥልቀት አንጻር ሲታይ ገና ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ነው፡፡ እናም እያንዳንዳችን የልማት፣ የብልጽግናና የሰላም ፀር የሆነውን ሕገ ወጥና ኮንትሮባንድ ንግድ ልንዋጋውና ልንጸየፈው ይገባል፡፡

 ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You