የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም አፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ የሆኑ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑባት ነው፡፡ ከተማዋ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት የሚያበቋት የተለያዩ መሠረተ ልማቶችና የመዝናኛ ሥፍራዎች በስፋት እየተከናወኑባት ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባን ገጽታ የሚቀይሩና እና የቱሪስት ፍሰት የሚያሳድጉ ሥራዎችንም በመሥራት ከኢትዮጵያ አልፋ የአፍሪካ መዲና የሆነችው ከተማ በጎብኚዎች ተመራጭ ሀገር እንድትሆን የተሠራውም ሥራ የብዙዎችንም ቀልብ የገዛ ነው፡፡ በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የአንድነት፤ የወንድማማችነትና የእንጦጦ ፓርኮች ከአዲስ አበባ አልፈው የሀገር ኩራት ለመሆን በቅተዋል፡፡ በአዲስ አበባ የተሰሩት አመርቂ ሥራዎችም ኮይሻን፤ ጎርጎራንና ወንጪን ለመሳሰሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መነሻ ሆነዋል፡፡
ሆኖም እንደስሟ አዲስ እየሆነች የመጣችው አዲስ አበባ ከእድገቷ ጎን ለጎን በጸጥታ ችግርና በሕገ ወጥ ተግባራት መበራከት በመፈተን ላይ ትገኛለች፡፡ ሰዎችን አግቶ ገንዘብ መጠየቅ፤ የቡድን ዝርፊያ፤ በሞተር ሳይክል ንጥቂያ፣ ባጃጅና የራይድ ታክሲዎችን ተጠቅሞ ሰው መግደል፣ ሞባይል መንጠቅ፤ ሕገ- ወጥ የጦር መሣሪያና የተደራጀ ከባድ የዝርፊያ ወንጀል እና የመሳሰሉት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
የሺሻ ማስጨሻ፣ የጭፈራና የቁማር ቤቶች እንዲሁም ሕገ-ወጥ የንግድ ሱቆችም ለሕገ ወጥ ተግባራትና ወንጀል መስፋፋት የበኩላቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ከወረዳ ጀምሮ በየደረጃው የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሌላ የአዲስ አበባ ፈተናዎች ናቸው፡፡ ከመታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ በደንብ ማስከበር፤ በቤቶች አሰጣጥ፤ በግንባታ ፍቃድ፤ በመሬት አቅርቦትና በመሳሰሉት ዘርፎች የሚሰተዋሉ ችግሮች በግስጋሴ ላይ የምትገኘውን ከተማ ወደ ኋላ ሰቅዘው የሚይዟት ናቸው፡፡
በየስርቻው እንደ አሸን የፈሉትም ቁማር ቤቶች የወጣቱን የወደፊት ተስፋ እያጨለሙትና የነገ ሀገር ተረካቢ በሆነው ትውልድ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ነው፡፡ በስፖርት ውርርድ ስም ወጣቱ ጊዜውን በቁማር እንዲያሳልፍና የወደፊት ሕይወቱን በአግባቡ እንዳይመራ የሚያደርጉ ሕገ ወጥ ተግባራት በአዲስ አበባ በሁሉም አካባቢ ተንሰራፍቶ መመልከቱ ልብን የሚሰብር ነው፡፡
ከእነዚህ ችግሮች ባሻገር በተለይ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱን ከተገቢው በላይ የሚያጦዙና ከኅብረተሰቡ ችግር ማትረፍ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎችም የአዲስ አበባ ሕዝብ ሸክሞች ናቸው። በኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እየፈጠሩ የሚገኙ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች በሰዓታት ልዩነት የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረግ ኅብረተሰቡን ለምሬት ከመዳረጋቸውም በላይ በሕዝብና በመንግሥት መካከል አለመተማመን እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ፡፡
ሕገ ወጥነት እና የጸጥታ ችግር በተስፋፋበት ሁሉ ሰላም ይደፈርሳል፤ ሕግ ይዛባል፤ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት ይስተጓጎላል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ሕገ ወጦችና ሙሰኞች ምቹ መደላደል ይፈጠርላቸዋል። እንደልባቸው ሕዝብን እያማረሩ ሀብት ያጋብሳሉ፤ መደላድላቸውን ያጠናክራሉ፤ የሴራ ገመዳቸውን ያጠብቃሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህን ሕገ ወጦችንና ሕገ ወጥ ተግባራትን ሳይዘናጉ ማስተዋልና ችግሮች ተፈጥረው ሲገኙም ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ማሳወቅና አጥፊዎችም የእጃቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
ከዚህ በላይ ግን መንግሥት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እድገትን የማፋጠን ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህን ለማድረግ ሕገ ወጥ ተግባራትን እየተከታተሉ ማረምና የጸጥታ ችግሮችን ማስወገድ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ በአንድ ሀገር የተረጋጋ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲኖር፣ ዜጎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባሮቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ሲችሉ በመሆኑ የኅብረተሰቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ሂደት የሚያውኩትን እየተከታተሉ ርምጃ መውሰድ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
ከዚህ አንጻር ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የጸጥታ ችግርና ሕገ ወጥ ተግባራትን ፈር ለማስያዝ የጸጥታ አካላት በቅንጅት የወሰዱት ርምጃ የሚበረታታና ተጠናክሮም ሊቀጥል የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም