
አዲስ አበባ፡- ጅግጅጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታወቀ፡፡ አልሸባብ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ ስምሪት የሰጠው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ፊቅ፣ ዋርዴር እና ቢኬ አካባቢዎች እንደነበርም ነው የተገለጸው፡፡
የጋራ ግብረኃይሉ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 14 የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡
በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በብቃት በመወጣት ላይ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተደጋጋሚ ሽንፈትና ኪሳራ የደረሰበት የአልሸባብ የሽብር ቡድን አባላትን በህቡዕ በመመልመልና በማደራጀት በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ እና በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት በመፈፀም ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶችን ለማድረስ ዕቅድ አውጥቶ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም ሴራው ሙሉ በሙሉ መክሸፉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መግለጫ አስታውቋል።
አልሸባብ በህቡዕ አደራጅቶና ተልዕኮ ሰጥቶ የላካቸው 14 የቡድኑ አባላት ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጇቸው ተቀጣጣይ ቁሶችና የተለያዩ ሰነዶች ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉት በኢትዮጵያና በሶማሊያ ድንበር ሾልከው ወደ ሶማሌ ክልል ዘልቀው በመግባት በጅግጅጋና በሌሎችም የክልሉ ከተሞችና አካባቢዎች ዒላማዎችን በመለየት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ዕቅድ አውጥተው ሲንቀሳቀሱ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።
በሕግ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ከተደረጉት ከእነዚህ ተጠርጣሪዎች መካከል አሊ አብዲ በቅፅል ስሙ መዓሊን አሊ በመባል የሚታወቀው የሽብር ቡድኑ መሪና አስተባባሪ መቀመጫውን ሶማሊያ ካደረገው የአልሸባብ ክንፍ ጋር ግንኙነት በመፍጠር በሶማሌ ክልል ውስጥ ሆኖ የሽብር ቡድን አባላትን በማደራጀት፣ በመገናኘት፣ በመመልመል፣ የሽብር እቅድ በማውጣትና ዒላማዎችን በመለየት ጥቃቶች እንዲፈፅሙ የሥልጠናና የሎጀስቲክስ ድጋፎችን ሲያደርግ ከሌሎች 13 ግብረ አበሮቹ ጋር በተካሄደው የተቀናጀ ክትትል በሞያሌ ከተማ የመግቢያ ኬላ በኩል ሾልኮ ለመውጣት ሲሞክር በቁጥጥር ሥር መዋሉን የጋራ ግብረ- ኃይሉ መግለጫ አመልክቷል፡፡
አልሸባብ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ ስምሪት የሰጠው በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ፣ ፊቅ፣ ዋርዴር እና ቢኬ አካባቢዎች እንደነበር ያመለከተው መግለጫው÷ የህቡዕ አደረጃጀት በመፍጠር የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም የተንቀሳቀሱት ተጠርጣሪዎች ለሽብር ጥቃቶች ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጇቸው በርካታ ክላሽንኮቭ መሣሪያዎች፣ ጥይቶች፣ ሽጉጦች፣ ቦንቦች፣ ተቀጣጣይ ቁሶችና የተለያዩ ሰነዶች ጋር መያዛቸውን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይሉ በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን ምኤሶ ወረዳ፣ ፋፋን ዞን ጅግጅጋ ከተማና ዙሪያው፣ ዶሎ ዞን ዋርደር ከተማና ዙሪያው፣ ቆራሄ ዞን ህግሎሌ ወረዳ እና ኤረር ዞን ፊቅ ከተማ ባካሄደው ተከታታይ ኦፕሬሽኖችና የአሰሳ ሥራዎች የሽብር ቡድኑ ለጥቃት ሊያውሏቸው የነበሩ 84 ክላሽንኮቭ መሣሪያዎች፣ 10 የቡድን መሣሪያዎችና 12 ሽጉጦች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን መግለጫው አክሎ ገልጿል።
በተለይም አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ዒላማ ያደረገውን የሽብር እኩይ ሴራና ጥቃት ለማሳካት የፈንጅ መቀመሚያ ንጥረ ነገሮች በህቡዕ ባደራጃቸው ህዋሶች አማካኝነት በሕገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ ድንበር ወደ ደቡብ ሶማሊያ በሟጓጓዝ ላይ እያለ በኤረር ዞን ጋሻሞ ወረዳ በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ባወጣው መግለጫ አያይዞ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ከሶማሊያና ሌሎች አጎራባች ክልሎች ጋር ሰፊ ድንበር የሚጋራ በመሆኑ የአልሻባብ የሽብር ቡድን ሐሰተኛ መታወቂያዎችና ፓስፖርቶችን እንዲሁም ሌሎች ሰነዶችን በመጠቀም አባላቶቹን ወደ ኢትዮጵያ አስርጎ በማስገባት በመሠረተ ልማቶችና የነዳጅ ማጠራቀሚያዎች ላይ የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል ያለው መግለጫው፤ ከውጭ አቻ የመረጃ ተቋማት ጋር በሚደረግ የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም እየተካሄዱ ባሉ ጥብቅ ክትትሎችና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት የሽብር ሴራዎችንና ተልዕኮዎችን ማክሸፍ መቻሉን የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጠቁሟል።
በዚህ አጋጣሚ የሽብር ቡድኑ ሴራዎች እንዲከሽፉ፤ የሶማሌ ክልል መንግሥት የፀጥታ መዋቅር እና የክልሉ ሕዝብ ላደረገው ከፍተኛ አስተዋፅዖ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
በመጨረሻም በመላ ሀገሪቱ የፀጥታና ደኅንነት ስጋቶችን በማስወገድና በሽብር ቡድኖች እንዲሁም በፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚታቀዱ የጥፋት ሴራዎችን በማክሸፍ እና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በኩል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመቀናጀት እየወሰዱት ያለው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም