ከጀምሮ መጨረስ ማሳያዎቹ ፕሮጀክቶችመማር ይገባል!

 የግንባታ መጓተት የሀገሪቱ ኮንስትራክሽን ዘርፍ መገለጫ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። በዚህ የተነሳም ሀገር እና ሕዝብ መጠናቀቃቸውን እየጠበቁ መጠናቀቅ የተሳናቸው በርካታ ፕሮጀክቶችን መታዘብ ተለምዶም ነበር። በተለይ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የእዚህ ሰለባ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል። ለእዚህም የዓባይ ግድብ፣ የስኳርና የመስኖ ፕሮጀክቶች በአብነት ይጠቀሳሉ።

በ2010 ዓ.ም ወደ ሥልጣን የመጣው የለውጥ መንግሥት ለተጓተቱ ፕሮጀክቶች ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ ሠርቷል። በምርጫ ሥልጣን የያዘው መንግሥትም እንዲሁ ይህን ስር የሰደደ የግንባታ መጓተት ለመፍታት ላለፉት ዓመታት በትኩረት ተንቀሳቅሷል። ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ችግሮች አንዱ የሆነውን ይህን የፕሮጀክት ማኔጀመንት አቅም ውስንነት ለመቀየር በፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩቱ በኩልም እየተሠራ ነው። በአስር ዓመቱ መሪ ዕቅድም የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅምን ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል።

በሀገሪቱ ከዓመታት በፊት ግንባታቸው ተጀምሮ መጠናቀቅ የተሳናቸው በርካታ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ በማመንም እነዚህ ፕሮጀክቶች እስከሚጠናቀቁ ድረስ አዳዲስ ፕሮጀክት ላለመጀመር በመወሰንም ነው ሲሠራ የቆየው። ግንባታቸው ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ በጀት በመመደብ ግንባታቸውን ለማጠናቀቅ በተደረገ ጥረትም የአንዳንዶቹ ግንባታ እንዲፋጠንና እንዲጠናቀቅም ማድረግ ተችሏል።

ለዚህም የዓባይ ግድብ ግንባታን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። የለውጡ መንግሥት ሲመጣ የግድቡ ግንባታ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደነበር ይታወሳል። የግድቡን ግንባታ አሁን ለደረሰበት ታላቅ ምዕራፍ ማድረስ የተቻለው ከለውጡ ማግስት አንስቶ የፕሮጀክቱን መሠረታዊ ችግሮች በመለየት ግንባታው እንዲፋጠንና ለታሰበው ዓላማ እንዲውል ለማድረግ በተከናወነው ጠንካራ ተግባር ነው።

እንደሚታወቀው ይህ ግድብ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉት የውሃ ሙሌቶች ተከናውነውለት የተወሰኑ ተርባይኖቹ ኃይል ወደ ማመንጨት ተሸጋግረዋል። ባለፈው ክረምትም እንዲሁ አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ተደርጓል፤ ዘንድሮ ሌሎች አምስት ተርባይኖቹ ወደ ሥራ እንደሚገቡም ይጠበቃል።

መንግሥት ምንም እንኳ በተጓተቱ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ቢያደርግም፣ እንደ ገበታ ለሸገር እና ገበታ ለሀገር የመሳሰሉ ታላላቅ አዳዲስ ፕሮጀክቶችንም ገንብቷል፤ በዚህም በተለይ ለቱሪዝሙ ዘርፍ መነቃቃት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማድረግ የጀመሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማንም የሀገሪቱንም ገጽታ የገነቡ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ተችሏል፤ ፕሮጀክቶቹን እውን ማድረግ ብቻ ሳይሆን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መገንባት ተችሏል። የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን የገርጂ ፕሮጀክት እዚህ ሊጠቀስ የሚገባው ሌላ ማሳያ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች የግንባታ ፕሮጀክትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ገንብቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳያ ሆነዋል። መንግሥት ይህን የፕሮጀክት ጀምሮ መጨረስ አቋሙን በገበታ ለትውልድ ቀጥሎበታል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተመሳሳይ ተግባሮች እየተፈጸሙ ናቸው። የመስቀል አደባባይ፣ የአብርኆት ቤተመጽሐፍት፣ የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላትና የመሳሰሉት ተጠናቀው ወደ አገልግሎት የተሸጋገሩበት ሁኔታ፣ ፕሮጀክቶቹ ግዙፍ መሆናቸው አንድ ነገር ሆኖ የተገነቡበት እና የተጠናቀቁበት ፍጥነትም ልዩ ያደርጋቸዋል።

ፕሮጀክቶቹ ፕሮጀክት ብቻ ተብለው የሚጠሩ አይደሉም፤ የፕሮጀክት መጓተት ትልቅ ችግር በሆነባት ሀገር በተያዘላቸው ጊዜ የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችም ናቸውና ጀምሮ መጨረስ እንደሚቻል ማሳየት የተቻለባቸው ናቸው።

ግንባታው በመሐል አዲስ አበባ ከከተማ አስተዳደሩ ጎን ሲካሄድ የቆየው የዓድዋ ዜሮ ዜሮ ሙዚየም ፕሮጀክት ግንባታም አሁን በማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ርብርብ ግንባታው ሲካሄድ የቆየው ይህ ታላቅ ፕሮጀክት፣ አሁን ግንባታው 95 በመቶ ላይ ደርሷል፤ በአሁኑ ወቅትም ዙሪያ ገባውን የማስዋብና የማሳመር ሥራዎች በጥድፊያ እየተካሄዱ ናቸው። የዘንድሮው የዓድዋ በዓልም በዚሁ ታላቅ ስፍራ እንደሚከበር ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ እጅግ ሰፊ ነው፤ በርካታ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ልዩ ልዩ ታላላቅ ሕንጻዎች፣ ቴክኖሎጂዎች የተካተቱበትና በዲዛይኑም ልዩ ነው። የዓድዋን ታሪክ ሊዘክሩ የሚችሉ ጥልቅ ምልከታን የሚጠይቁ ዲዛይኖች ተካተውበታል። የዚህ ፕሮጀክት መጠናቀቅም እንደ ሀገር ሌላው ትልቅ ስኬት ነው።

በአጠቃላይ እነዚህ ግንባታዎች ሰፋ ያለ ሀሳብ የሚታይባቸው፣ የቁጥቁጥ ያልሆኑ፣ በቅርቡ መመላለስ የማይደረግባቸው/ የተወጣላቸው/ ናቸው፤ ፕሮጀክቶቹ በከፍተኛ ባለሥልጣናት የቀን ተሌት ክትትል የተደረገባቸውና የሚደረግባቸው መሆናቸው ለመፋጠናቸው የራሱን አስተዋፅዖ ማድረጉም ይገለጻል። በርግጥም የፕሮጀክት ባለቤቶች ክትትልና ቁጥጥር ምን ያህል ፋይዳ እንዳለው በፕሮጀክቶቹ መመልከት ተችሏል። የግንባታ ተቋራጮችም ይህንኑ እየመሰከሩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በገበታ ለሸገርና በመሳሰሉት፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማ አስተዳደሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ላይ ያደረጓቸውና የሚያደርጓቸው የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች ለፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ሌሎች የፕሮጀክት ባለቤቶችም ይህን ማድረግ እንዳለባቸው ያመለከቱ የቁጥጥርና ክትትል ተግባሮች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል።

የሀገራችን ተቋራጮች፣ የፕሮጀክት ባለቤቶችና ሌሎች የኮንስትራክሸኑ ዘርፍ ተዋንያን ከአጠቃላይ የግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ የመጠናቀቅ ስኬቶች በመማር የሀገሪቱ የግንባታ ኢንዱስትሪ ከተጠናወተው የፕሮጀክት መጓተት በሽታ ለመፈወስ መሥራታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል። መንግሥት የዘርፉን የፕሮጀክት አስተዳደር ችግር ለመፍታት እየሠራ እንደመሆኑ፣ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት ይዞ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቁ እየሠራ እንደመሆኑ፣ ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን በተለይ ተቋራጮች ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሊጠናቀቁ ያስቻሉትን ጉዳዮች በጥናትም ይሁን በተለያዩ ዘዴዎች በመለየት ኢንዱስትሪውን ለመታደግ አጥብቀው ሊሠሩ ይገባል!

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You