አትሌቲክሱን ከጥፋት የሚታደግ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል!

 ኢትዮጵያ የዕንቁ አትሌቶች ምድር መሆኗ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አትሌቶቻቸውን “ዕንቁ” ብለው የሚጠራቸውም በምክንያት እንጂ በከንቱ ሙገሳ አይደለም። ከጀግናውና ታሪካዊው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ የኦሊምፒክ ማራቶን የባዶ እግር ገድል አንስቶ እስካሁኖቹ ኮከቦች ድረስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከሌሎች የሚለዩባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ።

በአስቸጋሪና ፈታኝ የሕይወት ውጣ ውረዶች አልፈው ሁሌም ለሀገራቸው ክብር በጀግንነት መዋደቅና ሰንደቃቸውን በዓለም አደባባይ ከፍ ለማድረግ እልህ አስጨራሽ ትግል ማድረጋቸው አንዱ መገለጫቸው ነው። በዚህም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ዓለም አክብሯቸዋል።

እልፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባልሸነፍ ባይነት ባሕላቸው ለማመን የሚከብዱ ዘመን ተሻጋሪ ስኬቶቻቸውን ያስመዘገቡት የስፖርቱ ዓለም የሚፈቅዳቸውን ሕግጋት አክብረው በንፁሕ የፉክክር መድረክ ነው። ይህም ልዩ መገለጫቸው ሆኖ ቆይቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህን ሁሉ አኩሪ ታሪክ፣ ገድልና ስኬትን የሚንድ አንድ አደጋ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ መንደር እየተስተዋለ ይገኛል።

ባለፉት ጥቂት የማይባሉ ዓመታት የበርካታ ሀገራት አትሌቶች የስፖርቱ ነቀርሳ እየሆነ በሚገኘው የአበረታች ንጥረነገሮች (ዶፒንግ) ተጠቃሚነት ሲታመስ ቆይቷል። በዚህም ኦሊምፒክን በመሳሰሉ ታላላቅ መድረኮች እስከመታገድ የደረሱ ሀገራት አሉ። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ከዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች መድኃኒት ተቆጣጣሪ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባት ምክረሃሳብ ከመቀበል የዘለለ ስጋት ያለባት ሀገር አልነበረችም። አሁን ግን በፍጥነት ነገሮች እየተቀያየሩ መጥተዋል። ችግሩ አፍጥጦ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን “ከቁጥጥሬ ውጪ ነው” እስከማለት ደርሷል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት አልፎ አልፎ ቅጣት የተጣለባቸው አትሌቶች ቢኖሩም ትልቅ ስም ያላቸው አይደሉም። ሰሞኑን በዚህ ቅሌት ውስጥ አሉ ከተባሉ አስር አትሌቶች መካከል ግን ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች የወከሉ ጭምር ይገኙበታል። ይህም ችግሩ ምን ያህል ስር እንደሰደደ ያመላከተ ሲሆን ኢትዮጵያም ጉዳዩን በሚቆጣጠረው ዓለም አቀፍ ተቋም ቀይ መብራት ከበራባቸው ሀገራት አንዷ አድርጓታል።

ለዚህ ችግር መባባስ ብዙ ምክንያቶች ቢመዘዙም የአትሌት ወኪሎች (ኤጀንቶች) ሚና ትልቅ መሆኑ ይነገራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው የአትሌት ወኪሎች 23 ብቻ ናቸው። ሕገወጦቹ ግን ከ300 በላይ ደርሰዋል ሲባል ይሰማል። እነዚህ ግለሰቦች ያለመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ እንደልባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ሲሆን በየጫካው እየዞሩ አትሌቶቻችንን እየበረዙ ነው ሲባልም ይደመጣል። እነዚህ ግለሰቦች በአውሮፕላን ጉዞ ያለውን ቁጥጥር ፍራቻ ከጎረቤት ሀገራት በብዛት በመኪና የሚገቡ መሆቸው መባሉ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።

በተጨማሪም ሙያው ከሚፈቅደው ሕግ ውጭ አንዳንድ የመድኃኒት መደብሮችና የጤና ባለሙያዎች መድኃኒቱን እንደፈለጉ እያቀረቡ ይገኛሉ። አትሌቶች ልምምድ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ለዚሁ ዓላማ የሚከፈቱ በመሆኑም የችግሩ ስፋት የከፋ አድርጎታል።

በኤሽያና በተለያዩ ሀገራት የሚወዳደሩ አትሌቶች በጉዳዩ እየተጠረጠሩ በመሆኑ ኢትዮጵያን ጥርስ አስነክሶባታል። ይህን ችግር በብዛት ጎትተው እያመጡ የሚገኙት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በማይቆጣጠረው መንገድ በቱሪስት ቪዛና በንግድ ቪዛ ከአገር እየወጡ ውድድሮችን የሚያደርጉ አትሌቶች ናቸው የሚል መረጃ ይነገራል።

እነዚህ አትሌቶች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ወይም በጥቅም ተደልለው በዚህ ቅሌት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ላይ እያደረሱ የሚገኙትን ውድመት ቆም ብለው ሊያስቡና ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። አትሌቲክስ የኢትዮጵያ አንድ ዓይን ነው። አንድ ዓይን ያለው ደግሞ በአፈር አይጫወትም። በዚህ ጉዳይ ላይ ቀልድ የለም።

ለግል ጥቅም ሲባል የሚጠፋ ነገር መኖር የለበትም። ይህ የእነ አበበ ቢቂላ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ሌሎችም እልፍ የተከበሩ ጀግኖች አትሌቶች ሀገር ነው።

አትሌቶችም ይሁኑ ወኪሎች ለግል ጥቅም የሚጓዙበት አቋራጭ መንገድ አያሌ ጀግኖች በከፍተኛ መስዋዕትነት በዘመናት የትውልድ ቅብብል የገነቡትን ታሪክ፣ ዝናና የሀገር ክብር እንደሚንድ ሊገነዘቡ ይገባል።

ይህን አሳሳቢ ችግር ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ እስከ እስር የሚያደርስ ሕግ ብታወጣም አፈፃፀሙ ግን አመርቂ አይደለም። በዚህ ቅሌት ውስጥ የተገኙ አካላት ሕግ ፊት ቀርበው የሚቀጡበት አጋጣሚ እየታየ አለመሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። እዚህ ላይ ሕግ አስፈፃሚው አካል ቆም ብሎ ነገሮችን መፈተሽ ይኖርበታል።

የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ለአትሌቶች ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ የአበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት እስከማድረግ ጥረት አድርጓል። ችግሩ ግን ከግንዛቤና ካለማወቅም የተሻገረ በመሆኑ መንግሥት ጭምር ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ግድ ይላል።

ከስፖርት አበረታች ቅመሞች ነፃ የሆኑ ጤናማ ስፖርተኞች እንዲፈጠሩና ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ተወዳድሮ ማሸነፍን ባሕል ለማድረግ በየደረጃው ችግሩን ለመቆጣጠር ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጠንክሮ መሥራት አለበት። ከፖሊስ በተጨማሪ የደህንነት ተቋማትም ችግሩን እያቀጣጠሉ አትሌቲክሱን ስጋት ላይ የጣሉ አካላት ላይ ክትትል በማድረግ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ይገባቸዋል!

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You