በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የለውጡ አየር ከነፈሰባቸው ተቋማት መካከል ትምህርትና የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣንን የመሰሉት ይገኙበታል። የክልል ትምህርት ቢሮዎችና በሥራቸው የሚገኙትንም ለውጡ ዳሷቸዋል። ከእነዚህ የክልልና የከተማ አስተዳደር ትምህርት ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የከተማ አስተዳደሩ አስፈፃሚ አካላትና የመሳሰሉት ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣንና የከተማው ትምህርት ቢሮ በጋራ በመሆን በ2015 ዓ.ም የሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ዙሪያ ከግል ትምህርት ቤት ተቋማት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል። ዓቢይ የመወያያ አጀንዳቸውም አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በሚጠበቀው የጥራት ደረጃ መተግበር የሚገባው ስለ መሆኑ፤ የሥርዓተ ትምህርት ትግበራው ለዜጎች ሁለንተናዊ እድገት የሚያስፈልጉ የትምህርት ጥራትን መሠረት በማድረግ በተለያዩ የትምህርት አደረጃጀት የሚሠጥ መሆኑ እና ከ2015 በፊት በነበረው የትምህርት ዘመን በመርሐ ግብሩ ትግበራ የተገኙ መልካም ውጤቶች እንዳሉ ሁሉ በትግበራ ሂደት የነበሩ ክፍተቶች በቀጣይ መስተካከል ያለባቸው መሆናቸውና የመሳሰሉት ነበሩ።
በወቅቱ በትግበራ ሂደቱ በአንደኛው ምዕራፍ አንደኛ ደረጃ በመካከለኛ ደረጃ የሙከራ ትግበራ በ2014 ዓ.ም የተከናወነበት እና በ2015 ዓ.ም ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባበት ሲሆን፣ በቅድመ አንደኛ እና በአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ፤ እንዲሁም በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የሙከራ ትግበራ የሚደረግ እና በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ወደ ሙሉ ትግበራ የሚገባበት″ እንደሚሆን መገለፁም ይታወቃል። የአሁኑ ጠንከር ያለ አካሄድም ይህንኑ መነሻ ያደረገ ይመስላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን በደንብ ቁጥር 74/2014 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የእውቅና ፈቃድ ይሰጣል፤ ያድሳል፤ ያስፋፋል፤ ደረጃ ያሳድጋል። እንዲሁም ከደረጃ በታች የሆኑ ተቋማትን እውቅና ፈቃድ የማገድና የመሰረዝ ሥልጣን አለው። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን በመዲናዋ የሚገኙ 25 የግል ኮሌጆችና ካምፓሶች ከአንድ ተቋም በስተቀር ሌሎቹ እገዳው እንደተነሳላቸውና በ2016 ዓ.ም የአዲስ ሠልጣኞች ምዝገባ እንዳያካሒዱ ጊዜያዊ እግድ ስለመጣሉ በባለሥልጣኑ የቴሌግራም ገፅ ላይ ዜና ሆኖ ሰፍሯል።
ምንም እንኳን የተለቀቀው ዜና ድፍን ያለና ኮሌጆቹ ባለሥልጣኑ የሚጠይቀውን የምዘና ግብ ሳያሟሉና የምዝገባ ፍቃድ ሳያገኙ ለ2016 ዓ.ም ምንም አይነት አዲስ ሠልጣኝ መቀበል የማይችሉ መሆናቸውን፣ የትምህርት ተቋማቱ አስፈላጊውን የሠልጣኞች መረጃ እስከ ኅዳር 30/2016 ዓ.ም እንዲያቀርቡ መወሰኑን፣ ካላቀረቡ የእውቅና ፍቃዳቸው የሚሰረዝ መሆኑን ወዘተ የሚገልፅ ቢሆንም ጉዳዩን ለማጣራት አዲስ ዘመን አራት ኪሎ ወደሚገኘው ወደ ባለሥልጣኑ ቢሮ ያቀና ቢሆንም የሚመለከታቸውን አካል ለማነጋገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
በእገዳ ደብዳቤው ላይ እንደ ተገለፀው እገዳው ባለሥልጣኑ ባወጣው እውቅና ፍቃድ መመሪያ 02/2012 ዓ/ም፣ አንቀፅ 13፣ ንዑስ አንቀፅ 2፤ እንዲሁም አንቀፅ 15፣ ንዑስ አንቀፅ 2 (ዝቅ ብሎ “መመሪያ 01/2014” የሚልም ተጠቅሷል) መሠረት መሆኑ ተጠቅሷል።
በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ያለውን ተሞክሮ በመቀመር የኢንስፔክሽን ቼክሊስት በማዘጋጀት እና ግንዛቤ በመስጠት በ2014 ዓ.ም ወደ ምዘና መግባቱ የሚያስታውሰው ባለሥልጣኑ የኤንስፔክሽን ሥራው ከተከናወነ በኋላ የተቀመጠላቸው እስታንዳርድ እና ተቋማቱ ያሉበት አሁናዊ ሁኔታ መራራቁን መገንዘቡን በወቅቱ መግለፁ ይታወቃል።
በእነዚህ ማሠልጠኛ ተቋማት የሚያልፉ ሠልጣኞች ብቁ የሆነ፣ ጥራቱን የጠበቀ ሥልጠና እንዲያገኙ ለማድረግ ጥራቱን የማረጋገጥ ኃላፊነቱን የወሰደው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን ለምሳሌ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በዲኦፖል ሆቴል የተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች፣ አንደኛውም ሰሞኑን በዚሁ ተቋም የተወሰደው የማስተካከያ ርምጃ ነው።
የማሠልጠኛ ተቋማቱ ወደ እስታንዳርዱ በተቋሙ ቼክሊስትና እስታንዳርድ ኤንስፔክሽን መሠረት እንዲመጡ ለማስቻል ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ የሚለው ይህ ተቋም፣ ተቋማቱ በቂ ግንዛቤ በመውሰድ ጥራት ያለው ሥልጠና በመስጠት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ ከመግለፅም ባለፈ ተግባሩ የእለት ተእለት ሥራው እንደሆነም በኃላፊዎቹ አማካኝነት ሲነገር ቆይቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት፣ በባለሥልጣኑ የትምህርት ሥልጠና ጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ሙሉጌታ እንደሚሉት ባለሥልጣኑ በደንብ ቁጥር 74/2014 የተሰጠውን ሥልጣን መሠረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን የሚያመላክት ነው። በሀገራችን አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እየተደረገ ቢሆንም አንዳንድ ተቋማት ሥርዓተ ትምህርቱን በመጣስ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያከናውኑ መሆኑን በኢንስፔክሽን ግኝት በመታወቁ ይህንን አሠራር በማስተካከል ሁሉም ተቋም በሀገሪቱ ባለው ሥርዓተ ትምህርት በአግባቡ መተግበር ይኖርባቸዋል።
ተቋማት ላይ ጥራትን የማረጋገጥ ሥራ በየግዜው የሚሠራ ሲሆን፣ አጠቃላይ የሚሰጡት ትምህርት ተገቢነቱን፣ በተለይም ሥርዓተ ትምህርቱን ጠብቆ መሄዱን እንደ አዲስ አበባ ከተማ ስታንዳርድ ኢንስፔክሽን ብቻ ሳይሆን፤ በተጨማሪ፣ በድንገተኛ የኢንስፔክሽን ትግበራ በስፋት ይከናወናል።
ከዚህ አኳያ የትምህርት ቤትና በየደረጃው ያሉት አስፈፃሚ ተቋማት አመራሮች ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል። ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ክፍተቶችን የመለየት ሥራ ይሠራል። ተቋማቱ እንዲያሻሽሉ ይደረጋል፤ ይህ ካልሆነ ደግሞ ተቋማትን ተጠያቂ የማድረግ ሥራ ይከናወናል። በተጨማሩም ተቋማት ሥርዓተ ትምህርቱን ጠብቀው አጠቃላይ የማስፈጸም መመሪያዎችንና ፖሊሲዎችን መነሻ በማድርግ የተጣጣመ መሆኑ የሚረጋገጥበት አግባብ መኖሩን የገለጹ ሲሆን፣ የጥራት ቁጥጥርና ክትትል ሥራ ተጠናክሮ ይሠራል።
ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ከደረጃ በታች በሆኑ 12 ትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን፤ የተማሪዎችን ውጤት የሚገልጽ መረጃ ለተማሪዎችና እውቅና ፍቃድ ለሰጣቸው አካል እንዲያስረክቡ ማስታወቁን በወቅቱ ይፋ አድርጎ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ዘንድሮም በተመሳሳይ አካሄድ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ አሠራሮች ቢኖሩትም፣ የመታገድና አለመታገድ ምክንያትና መስፈርቶቹ ምን ምን እንደሆኑ የትምህርት ባለ ድርሻ አካል ለሆነው ኅብረተሰብ በአብዛኛው ግልፅ ባለመሆኑ ያለማሰለስ መረጃዎችን ተደራሽ ቢያደርግ የተሻለ ሥራን እንደሚሠራ በብዙዎች የሚሰጥ አስተያየት ነው።
ሰሞኑን በኢፌዴሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ካሰራጨው መረጃ መረዳት እንደ ተቻለው በአጠቃላይ የ382 ተቋማት ወቅታዊ የፈቃድ መረጃ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል 366 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (5 የግል ዩኒቨርሲቲዎች፣ 6 የግል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች፣ 6 ኢንስቲትዩቶች እና 349 የግል ኮሌጆች) ሲሆኑ፤ 16ቱ ደግሞ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (4 የርቀት ትምህርት ፈቃድ የወሰዱ፤ እንዲሁም፣ 12 የመደበኛ ትምህርት ፈቃድ የወሰዱ) ናቸው።
ባለሥልጣኑ የተቋማቱን የትምህርት መስኮች የፈቃድ ጊዜ ያለበትን ደረጃ ለማሳየት በየትምህርት መስኩ፣ በካምፓስ እና በፈቃድ ጊዜው ላይ በአረንጓዴ፣ በቢጫ፣ በቀይ እና በወይን ጠጅ ቀለማት ምልክት ያደረገ ሲሆን፤ አረንጓዴ የተደረገባቸው “የፈቃድ ጊዜያቸው ከ6 ወራት በላይ የሚቆይ እና አዲስ ተማሪ መመዝገብ የሚችሉ″፤ ቢጫ የተደረገባቸው “የፈቃድ ጊዜያቸው ከ1 እስከ 6 ወር በላይ የሚቆይና አዲስ ተማሪ መመዝገብ የሚችሉ” ናቸው።
ነገር ግን በቀሩት 6 ወራት ፈቃድ ሳያሳድሱ አዲስ ተማሪ መመዝገብ የማይችሉ፤ ቀይ ቀለም የተደረገባቸው “ፈቃድ ያላሳደሱና የፈቃድ ጊዜያቸው ያለፈ በመሆኑ ምክንያት አዲስ ተማሪ መመዝገብ የማይችሉ መሆናቸውን፤ እንዲሁም፣ ወይን ጠጅ ቀለም የተደረገባቸው” ያቋረጡ ስለሆነ አዲስ ተማሪ መመዝገብ የማይችሉ፤ የተመዘገቡ ተማሪዎችን ግን ማስጨረስ ያለባቸው መሆናቸውንም በዝርዝር አስፍሯል። ኅብረተሰቡ በየተቋማቱ ከመመዝገቡና ማስመዝገቡ በፊትም እነዚህን ባለ ቀለም ምልክቶች በአግባቡ ማጤን እንዳለበት ባለሥልጣኑ አሳስቧል።
የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን፣ ለአጠቃላይ መረጃ ሲባል፣ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ ያገኙበትን የትምህርት መስክ፣ ካምፓስ እና መርሐ ግብር አሟልቶ የያዘና በየጊዜው ወቅታዊ የሚደረግ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድን የማግኛ ድረ-ገጽ በመክፈት ሊንኩን (https://bit.ly/43Z1Rck) ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
የትምህርት ተቋማት ለደረጃው በተቀመጠው መስፈርት መሠረት አሟልተው ባለ መገኘታቸውና ከደረጃ በታች በመሆናቸው የተማሪዎች ውጤት፣ ብቃትና ክሂሎት እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ ለምሳሌ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ከበቂ በላይ ማረጋገጫ ነው። ይህ እየተነገረ ባለበት በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣንም ሆነ እንደ አገር በኢፌዴሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን እየወሰዱት ያለው ርምጃ ችግሩን ከመሠረቱ ይፈታዋል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ አለ።
ስለዚህ ተቋማቱ ይህንን የባለ ድርሻ አካላትን አደራና እምነት ከግምት በማስገባት የበለጠ እንደሚንቀሳቀሱ እምነት እንደሚኖር ይጠበቃል። ኅብረተሰቡም እንደ አንድ የትምህርት ባለድርሻ አካል በትምህርት ጉዳይ ላይ ችግሮችን ከተመለከተ በነፃ የስልክ መስመር 9302 ‹‹ሃሎ›› ብሎ ችግሩን ማሳወቅ ይችላል። ይህን ከሆነ “ባለ ድርሻ አካላት›› የሚለው ቃል ኅብረተሰቡን በትክክል የሚገልፅ ይሆናል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም