‹‹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ምርት ጎረቤት ሀገራትን ጭምር እየመገበ ነው ››

– መለስ መኮንን (ዶ/ር) የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ

ኢትዮጵያ ግብርና የሕልውና መሠረቴ ነው በማለት በሰፊው እየሠራች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት እየታመሰ የሚገኘውን የዓለም ገበያ በተለይም ደግሞ በምግብ ፍጆታ ራስን ማሸነፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን በማመን ሀገሪቱ ለግብርና ዘርፍ ትኩረት መሰጠቷ የሚበረታታ ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በኢትዮጵያ ሰፊ የሚታረስ መሬት ቢኖርም አሁንም ድረስ የምግብ ዋስትናን በቅጡ ማረጋገጥ አልተቻለም። በመሆኑም መንግሥት ላለፉት አራት ዓመታት በሰፊው ፊቱን ወደ ግብርና ያዞረ ሲሆን ስንዴን ከውጭ ማስገባት ማቆሙንና የሀገር ውስጥ ፍጆታ መሸፈኑን ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅትም ግብርናን በማዘመንና በቀጣይ የሀገሪቱን አቅም ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸው ይነገራል። በተለይም የግብርና ሚኒስቴር የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ በመከተል በርካታ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እየታተረ መሆኑ ሲገልጽ ይሰማል። በስንዴ፣ ሩዝ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎችና ሌሎች ዘርፎችም ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረጉን ሚኒስቴሩ ይናገራል።

በዛሬው ዕትማችን የግብርና ሚኒስቴር አሁናዊ እንቅስቃሴዎችና ቀጣይ ትኩረቶችን አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፤ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ።

አዲስ ዘመን፡- የግብርና ሚኒስቴር በሁሉም ዘርፍ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የገበያ ፍላጎትን ለማሟላት ምን እየሠራ ነው?

መለስ (ዶ/ር)፡- ግብርና ለሀገራችን በጣም ወሳኝ ነው። የግብርና ሚኒስቴርም ዘርፉ ለአገር ያለውን ፋይዳ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአስር ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቷል። ይህ እንዲሁ የተዘጋጀ ሳይሆን በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ምክክሮች፣ ወርክሾፖችና አሁናዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብም የተዘጋጀ ነው። የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ሲዘጋጅም የምርምር ተቋማት፣ የሀገራችንን ግብርና የሚደግፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችና ደጋፊ አካላት፣ የመንግሥት ተቋማት እና የሚመለከታቸው አካላትም በሙሉ ተሳትፈውበታል።

እነዚህን አካላት በማሳተፍ የተሻለ ስትራቴጂክ እቅድ ማዘጋጀት ተችሏል። ነገር ግን ሀገሪቱ ካላት አቅም አኳያ ብሎም ለግብርና ምቹ ከመሆኑ አንፃር መታረስ የሚችል ሰፊ ምርታማ መሬት አላት። ለዚህም ምቹ የሆኑ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች፣ ተስማሚ የአየር ንብረት ብሎም ለመስኖም ሰፊ ውሃ ያላት ሀገር ናት።

ካለው ተስማሚ የአየር ንብረት የተነሳ በኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የግብርና ምርት ማምረት ይቻላል። በእንስሳት ግብርና ላይም በስፋት ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። የሕዝብ ቁጥር ትልቅ ሃብት ነው። አንዳንድ ጊዜ የሕዝብ ሃብት እንደ ችግር ይታያል። ነገር ግን እንደ እኛ ሀገር ያለው ሕዝብ በአግባቡ ከተያዘ፤ አምራች እንዲሆን ከተሠራ እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው።

65 ከመቶ የሕዝባችን ቁጥር አምራች ወይንም መሥራት የሚችል ነው። ይህ ካስተባበርነው ተዓምር የሚሠራ ኃይል ነው። እኛ ያለን ይህ ሃብት በርካታ ሀገራት የሌላቸው ሃብት ነው። በእርግጥ ይህ ሁሉ ሃብት እያለን ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ መጠቀም የሚገባትን እየተጠቀመች አልነበረም፤ አሁንም እየተጠቀመች አይደለም። በመሆኑም በ10 ዓመቱ እቅድ ውስጥ የመጣንበት የዘመናት አካሄድ አዋጭ ስላልሆነ ለየት ያለ አካሄድ መንደፍ ግድ ብሎናል። አሁን ባለን እቅድ ጊዜ የለንም በሚል መንፈስ እየሠራን ነው። በተለይም በአስር ዓመቱ እቅድ በጣም ልንረባረብ ይገባል ብለን 10 ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገናል።

ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የስንዴ ምርታማነትን ማሳደግ ሲሆን ይህን በበጋ እና በመስኖ እርሻ በሰፊው መሠራት አለበት ብለን በትኩረት እየሠራንበት ነው። ሀገራችን ለስንዴ ምርት በጣም ምቹ ናት። በሦስት ዙር ማለትም በመኸር፣ መስኖ እና በልግ ስንዴ ማምረት የሚቻልባት ሀገር ናት። ነገር ግን በመስኖ እና በልግ አናመርትም ነበር። ምርታማናትንም ይጨምራል ብለን አናስብም ነበር። አሁን ሦስቱም ላይ ትኩረት አድርገን ውጤታማ እያደረግን ነው።

በየዓመቱ ሀገራችን ስንዴ ለመግዛት እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች። ይህም ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ይህን ሁሉ የማምረት አቅም እያላት ስንዴ እየተሰፈረላት ወይንም ስንዴ የምትመፀወት ሀገር መሆን ስለሌለባት ይህን ለማስቀረት ደግሞ ጠንከር ብሎ መሥራት ይገባል በሚል እሳቤ የተጀመረ ነው።

የሀገር ውስጥ ስንዴ ፍላጎት ማሟላት በሚለው ዓላማ ላለፉት አራት ዓመታት ስንሠራ በመቆየታችን በየዓመቱ ካሰብነው እና ካቀድነው በላይ እቅዳችንን እያሳካን ነው። በመንግሥት ተቋማት፣ የምርምር ማዕከላት እና ባለሙያዎች በመተባበር እና ከላይ እስከ ታች ያሉ አመራሮች በመናበብ ትልቅ ለውጥ ተመዝግቧል። ስንዴ አምራች ያልነበሩ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት ትልቅ ምርት የሚገኝበት አካባቢም ሆነዋል። ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል በስንዴ የሚታወቁት ባሌ እና አርሲ ነበሩ። ጅማ እና መካከለኛ ሸዋ ላይ ብንመጣ ብዙም ስንዴ ምርት አይታወቅም ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን በስንዴ ምርት ወደፊት መጥተዋል። በደቡብ፣ አፋር እና ሶማሌ፣ አማራ ክልልም በሰፊው እየተሠራ ነው።

አሁን ደግሞ ትግራይን ክልል ጨምረን ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በዚህ ዓመትም በመኸር መሥራት ያለብንን ሥራ እየሠራን ነው። በበጋው ደግሞ በመስኖ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ በመሸፈን ወደ 117 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው። እስካሁን ድረስ ቀድመው ምርት በሰበሰቡና ቀድሞ ዘር መዝራት ባለበት አካባቢ እየተረባረብን ስንዴ እየዘራን ነው። በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ በዘር ተሸፍኗል። ሌሎች አካባቢዎችም ምርት እያነሱ የሚሄዱ በመሆኑ በእርግጠኝነት ይህን ሦስት ሚሊዮን ሄክታር በስንዴ እንሸፍናለን።

ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት እና ውጤታማ ለመሆን መሥራት አለብን በሚል የጀመርነው በጣም የተሳካ ነው ብለን እናስባለን። ይሁንና ይህ ሁሉ ምርት እየተመረተ ተጠቃሚው ጋር እንዴት እየደረሰ ነው የሚለውን ማየት ይገባል። ስንዴ ብቻ ሳይሆን አኩሪ አተር እና ሩዝ ላይ በልዩ ትኩረት ላይ እየሠራን ነው። ይህ ብቻ አይደለም በመኸርም በሠራነው ሥራ እና የቆዩ ዓመታትን ዳታ ብንመለከትም የምርት መጠን እየጨመረ ነው። ነገር ግን ገበያ ላይ ስንሄድ ዋጋው ይጨምራል ወይንም ደግሞ የምርት እጥረት ይኖራል። ይህን ለምን ሆነ የሚለውን በደንብ ማየት ይገባል። የተመረተው ምርት የት እየገባ ነው ብሎ መረዳት ይፈልጋል። ምርት እየተመረተ አይደለም እንዳይባል በከፍተኛ ሁኔታ ምርታማናት እየጨመረ ነው። በዘመናዊ ማሽኖች ጭምር እየተመረተ ነው። ስለዚህ ምርቱ የት እየገባ ነው? የሚለው ማጤን ይገባል።

ለዚህ አንደኛው ችግራችን የገበያ ሰንሠለቱ ደካማ መሆን ነው። በዚህ ላይ በደንብ መሥራት አለብን። ይህን በተመለከተ ሌሎች ሚኒስትሮች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እየሠራን ነው፤ መፍትሔም ይኖረዋል።

ሌላው በመኸር፣ መስኖ እና በልግ የምናመር ታቸው ምርቶች የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ እየቀለበ ነው ብዬ አላምንም፤ ይህ የእኔ እምነት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የጎረቤት ሀገራትን ሕዝብ ጭምር እየመገበ ነው ማለት ስህተት አይሆንም። ጅቡቲ እና ሶማሊያ በርካታ ግብርና ምርቶችን ከኢትዮጵያ ይሄድላቸዋል። ሰሜን ኬኒያ እና ሶማሌ ላንድም ከኢትዮጵያ በርከት ያሉ ምርት ይሄድላቸዋል። በተመሳሳይም ሱዳን እና ኤርትራም ከኢትዮጵያ ምርቶችን ይወስዳሉ። 360 ዲግሪ ዙሪያውን ብንመለከት ከኢትዮጵያ ምርት ይወስዳሉ። ጎረቤት ሀገራት ከኢትዮጵያ ምርት መውሰዳቸው ክፋት የለውም፤ ኢትዮጵያም ከእነዚህ ሀገራት የተለያዩ ምርቶችን ልትወስድ ትችላለች። ትልቁ ቁም ነገር እነዚህ ከሀገር ውጭ የሚሄዱ ምርቶች በደንብ ‹‹ሬጉሌት›› ተደርገው ለሀገር ጥቅም በሚያስገኝ እና የውጭ ምንዛሪ በሚያመጣ መልኩ ቢሆን በጣም ጥሩ ነው። ይሁንና አብዛኛው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ነው የሚወጣው። ስለዚህ በግብርና ላይ ያለን አመራሮች እና ባለሙያዎችም ጊዜ የለንም በሚል መንፈስ ምርታማናትን ለመጨመር መሥራት አለብን።

ሌላው በግብይት እና ቁጥጥር ሴክተር ላይ በጋራ መሥራት አለብን። በንግዱ ማኅበረሰብ ላይ ያሉትም ሀገርን በሚጠቅም መንገድ መሥራትና የዋጋ ንረትን በሚቀንስ መንገድ በኃላፊነት መሥራት ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የግብርና ምርት መጨመር እንደተጠበቀ ሆኖ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ምርታማነት አለመመጣጠን ችግር ፈጥሯል የሚል የሰላ ትችትም አለ። እርስዎ ምን ይላሉ?

መለስ (ዶ/ር)፡- የሕዝብ ቁጥር ሲጨምር ፍጆታ ይጨምራል፤ ይህ ለጥያቄ እና ለድርድር የሚቀርብ አይደለም። ነገር ግን የሕዝብ ቁጥር በጣም እየጨመረ ቢሆንም ምርትና ምርታማነትም በዚያው ልክ እየጨመረ ነው። ከሕዝብ ቁጥራችን መጨመር ይልቅ በሕገ ወጥ መንገድ የሚወጣው ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳን ነው። ለምሳሌ ስንዴ ከውጭ ማስገባት አቁመናል። አሁን ገበያ ላይ የስንዴ እጥረት የለም። ዳቦ ቤቶችም የስንዴ ዱቄት አለ። ግን ምርት በመያዝ ዋጋ የመጨመር አዝማሚያ አለ። በእርግጥ በቂ ሥራ ሠርተናል ብለን ማሰብ የለብንም፤ ገና ብዙ ሥራ መሥራት አለብን።

አዲስ ዘመን፡- በአስር ዓመቱ እቅድ ውስጥ አንዱና ትልቁ የቅባት እህሎች ላይ ያለውን ምርታማነት እና አቅም ማሳደግ ነው። ሚኒስቴሩ በዚህ ላይ ራሱን እንዴት ይገመግማል?

መለስ (ዶ/ር)፡- ከስንዴ ቀጥሎ ሁለተኛው ፕሮግራማችን የቅባት እህሎች ላይ ሲሆን፤ ዘይትን በሀገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት

 መተካት ነው። በዚህ ላይ የሚሠሩ በርካታ ተቋማት አሉ። ንግድ ሚኒስቴርና እና ሌሎች ሚኒስትሮችም አሉ። በርካታ ፋብሪካዎችም እየተተከሉ ነው። ለእነዚህ ፋብሪካዎች ደግሞ ግብዓት ማቅረብ ተገቢ ነው። ለውዝ እና ሌሎች ቅባት እህሎችን እያመረትን ነው። በልዩ ትኩረት አኩሪ አተር ላይ እየሠራን ነው፤ በሰፊው ተመርቷል። ነገር ግን ላመረትነው አኩሪ አተር ምርት ገበያ እያጣን ነው። አርሶ አደሩ ያመረተውን አኩሪ አተር የሚገዛው የማጣት እና ዋጋ መቀነስ ይታያል። ይህ ደግሞ በኤክስቴንሽን ሥርዓታችን አኩሪ አተር ምርትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ላይ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በዚህ ላይ ከንግድ ሚኒስቴር እና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ብሎም ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የገበያ ችግሩን ለማቃለል፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የምንሠራው ይሆናል።

ከሩዝ ጋርም በተያያዘ በሰፊው እየተሠራ ነው። ለተወሰኑ ዓመታት በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ሩዝ ይመረት ነበር። አማራ ክልል ፎገራ አካባቢ ሰፋ ባለ መልኩ ይመረት ነበር። ብዙውን ጊዜም ሩዝ ለምግብነት የምናውልበት ልምድ አናሳ ስለሆነና የአንድ አካባቢ ምርት አድርጎ ማሰብም ስለነበር ከአማራ ክልል ውጭ ብዙም የተስፋፋ አልነበረም። ላለፉት ሦስት ዓመታት በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በኦሮሚያ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማስፋፋት ሥራ ሠርተናል፤ አልፍ ሲልም በሱማሌ ክልል የማስፋፋት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። በየዓመቱ እስከ 300ሺ ሄክታር ሩዝ ነበር የሚሸፈነው። በዚህ ዓመት ግን አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሩዝ ተሸፍኗል።

ከአማራ ክልል በመቀጠል በኦሮሚያ ክልል በሩዝ ሰፊ ክላስተር ተሸፍኗል። በስንዴ እና አኩሪ አተር ልክ ሩዝ ላይም እየሠራን ነው። ሩዝ ስናመርት በየዓመቱ ከውጭ የሚመጣው ምርት ለመተካት ነው። በአሁኑ ወቅት የሩዝ ምርት ፍጆታም እየጨመረ ነው። በተለይም አፋር እና ሶማሌ ክልል ከፍተኛ ፍጆታ አለ። ስለዚህ ትልቁ ዓላማችን ከውጭ የሚገባው ሩዝ በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ነው።

በአትክልትና ፍራፍሬ ላይም ትኩረት አድርገን እየሠራን ነው። በተለይም ሽንኩርት እና ቲማቲም ላይ አፅንዖት ሰጥተናል። ፍራፍሬ በተመለከተም አቮካዶ፣ ሙዝ እና ማንጎ ላይ በሰፊው እየሠራን ነው። አቮካዶ በደቡብ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልል እየተሠራ ነው። በተለይም የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመምረጥ በየዓመቱ ተከላ እያደረግን እና ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት በመጨመር እየላክን ነው። በሀገር ውስጥም ምርትን በማቀነባበር የአቮካዶ ዘይት በማምረት ለውጭ ገበያ የሚውል ምርት እየተመረተ ነው። ማንጎ ላይም ትልቅ አቅም አለ። ነገር ግን ችግር እየገጠመን ነው።

አዲስ ዘመን፡- ምንድን ነው የገጠማችሁ ችግር ?

መለስ (ዶ/ር)፡- ከማንጎ ጋር ተያይዞ ያለው ማንጎ በተለይ በሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ አቅም አለ። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ አቅሙ ትልቅ ነው። ድሬዳዋ እና ሐረር አካባቢም ትልቅ ምርት ይመረታል። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቸገርን ያለነው በማንጎ በሽታ ነው። ምርትን ከጥቅም ውጭ እያደረገ ሲሆን፤ አርሶ አደሮችንም እንደመፍትሔ እየወሰዱ ያሉት ቀደም ብለው የተከሉትን ትልልቅ ማንጎ ዛፍ በመንቀል አዳዲስ የተሻሻሉ ተክሎችን ወይንም ማንጎ ችግኞችን መትከል ነው።

ይህ ማለት ግን ከባድ ነው። ማንጎ ምርት ለመስጠት ረጅም ዓመታት የሚወስድ ሲሆን፤ ምርት እየሰጠ የሚቆየውም ረጅም ዓመታትን ነው። ስለዚህ አርሶ አደሮቻችን በዚህ ጉዳይ መፈተን የለባቸውም። በመሆኑም ችግሩን ለማቃለል በርካታ ምርምሮች እየተደረጉ ነው። የምሑራንን ምክረ ሃሳቦችን ይዘን ሥራ እየሠራን ነው። በተለይም ደግሞ ሥነ ሕይወታዊ የመከላከያ ዘዴ መጠቀም አንዱ ሲሆን፤ ይህ ወደ ተግባር ሲገባም አዋጭም ነው። በርካታ መፍትሔዎችን አንድ ላይ አካተን የምንሠራበት አሠራር መኖር አለበት። አይሲፔኤ (icipe- International Centre of Insect Physi­ology and Ecology) የሚባለው ድርጅትም በዚህ ላይ እየሠራ ነው። በዚህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ታንዛኒያን ጨምሮ በአራቱ ሀገራት ላይ የሚሠራ ፕሮጀክት ነው። በዚህ ፕሮጀክት ላይ የሚገኝ ውጤትን በሌሎች ፕሮጀክቶች እና የኢትዮጵያ ክፍሎች የማስፋፋት ሥራም ይከናወናል።

አዲስ ዘመን፡- ከማንጎ በሽታ መበራከት አንዱ ያልተመረጡ ዘሮችን በዘፈቀደ መጠቀም እንደሆነ ይነገራል። በዚህ ላይ ሚኒስቴሩ በቂ ትኩረት ሰጥቷል?

መለስ (ዶ/ር)፡- ይህን ለመቋቋም እንደ ሀገር እየሠራን ያለውና በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ሥራ ‹‹በኳንታይን›› ሥርዓታችን ማዘመን ነው። የማንጎ ዘር ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል እናጓጉዛለን። በማንጎ የዘር ምንጭነቱ በትክክል ከታወቀ አካባቢ ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል። ይህ ሲደረግ የማንጎ በሽታ ከአንዱ ቦታ ሌላ ቦታ እንዳይሄድ ወይንም እንዳይዛመት ያደርጋል።

አጠቃላይ ግን በማንጎም ሆነ በስንዴ ወይንም በግብርና ምርት ላይ ስናወራ እና ምርትና ምርታማነትን እንጨምራለን ስንል በርካታ ፈተናዎች እንዳሉም እንገነዘባለን። ከመነሻው ቴክኖሎጂ ከማግኘት ጀምሮ፣ ዘመናዊ አሠራር፣ ዘመናዊ የግብርና ማኔጅመንት ሥርዓት እና እንክብካቤ በአግባቡ መሥራት፣ ግብዓት አጠቃቀምን እና ሌሎችንም አካቶ በዚህ ላይ መሥራት አለበት። በእርግጥ ከእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ የሚከፋው በተለያዩ ወቅቶች የሚከሰተው በሽታ ነው። በስንዴ ላይ በተለይ ዋግ እና ‹‹ፉዛሪየም›› በጣም አስቸጋሪ ሲሆን፤ ትልቅ ክትትል የሚጠይቅ ነው።

‹‹ፉዛሪየም››ን ለመከላከል ወቅቱ አጭር ከመሆኑ የተነሳ ይህ ትንሽ ካለፈ ማሳው በሙሉ ከመበከል አያድነውም። ይህን ተከታትሎ ከመከላከል አኳያ ደግሞ ባለሙያዎችን አቅም ማሳደግ እና ሥልጠናዎችን መስጠት ተገቢ ነው። ባለሙያዎችን ማቀናጀትም ትልቅ ሥራ ነው። ዋግ እና ፉዛሪየም ለመከላከል የሚያስችሉ ኬሚካሎች በየጊዜው አቅርቦት አለ። በመሆኑም የመከላከሉን ሥራ ጎን ለጎን እየሠራን ነው። በአጠቃላይ በሽታ እና ተባይ ላይ ያሉ ሥራዎች ጎን ለጎን በፍጥነት ካልተሠሩ በስተቀር ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል።

ሌላው ትኩረት የምንሰጠው ቅድመ ማምረት ያለው ሂደት ነው። በተለይ ደግሞ ልዩ ትኩረት መስጠት ያለበት ለአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ የምንሰጠው ትኩረትና አያያዝ አናሳ መሆን ነው። የሚፈለገውን የምርት መጠንና ጥራት ለማግኘት በዚህ ላይ በሚገባ መሠራት አለበት። ድህረ ምርት ለአዝርዕት ምርት የከፋ ችግር ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን አትክልትና ፍራፍሬ ላይ በጣም ወሳኝ ነው። በዚህ ላይ ያለውን አሠራር ባለሙያው ማሠልጠን፤ ለአርሶ አደር ማሳየትና ቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢ ነው። እስከ ዛሬ የድህረ ምርት ስብሰባ ስትራቴጂ አልነበረንም፤ አሁን ግን ይህንኑ ለማስፈፀምም መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል።

ይህ ሂደት ላይ ነው። በድህረ ምርት ከከረጢት ጀምሮ ምን ዓይነት ጎተራዎችን እንጠቀም የሚል መመሪያም አለ። አትክልትና ፍራፍሬ ላይም ስንሄድ ሳይበላሹ ለረጅም ጊዜ የሚቆይበትና ወደ ገበያ የሚቀርብበት አሠራርና ብልሃት ምንድን ነው? የሚለው ወደ ሥራ እየተገባበት ነው። ይህን ለማዘጋጀት በዘርፉ ላይ ልምድ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል። ይህ ሥራ በአዝዕርት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ ሃብት ላይም የሚሠሩ ሥራዎች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- ግብርናን ለማዘመን የኤክስቴንሽን፣ መስኖና መካናይዜሽን ሂደታችን ለማጠናከር ሚኒስቴሩ ምን እየሠራ ነው?

መለስ (ዶ/ር)፡- የአስር ዓመቱ ስትራቴጂክ እቅዳችን ቴያዥና ተመጋጋቢ ጉዳዮችን የያዘ ነው። በዚህም ኤክስቴንሽን፣ መስኖና መካናይዜሽን በሰፊው የምንሠራበት ጉዳያችን ነው። ቀደም ሲል ዲዛይን የተደረገው የኤክስቴንሽን ሥርዓችን እስካሁን ድረስ ያለው የኤክስቴንሽን ሲስተማችን በጣም የተጠና ነው፤ ይህን ላደረጉትም እውቅና መስጠት ተገቢ ነው። አደረጃጀቱ ለእኛ ሀገር በጣም አስፈላጊ ነው። የእኛ በጣም ሰፊ የሆነ ሥርዓትና የሰው ኃይል የተሠማራበት ነው።

ችግሩ ይህን በአግባቡ መከታተል እና በሙሉ አቅም ማስፈፀም ላይ ክፍተት አለ። ይህን ባለብዙ ተዋናይ አድርገን አዘጋጅተናል። በቀጣይ ይህን ወደ ትግበራ ይገባል ብለን እናስባለን። በዚህ ሴክተር ውስጥ በርካታ ተዋንያን ያስፈልጋሉ። መንግሥት በበላይነት እየመራው የግሉ ሴክተር፣ ዩኒየኖች እና ባለድርሻ አካላትም የሚሳተፉበት ሥርዓት መኖር አለበት። በአጠቃላይ ኤክስቴንሽን፣ መስኖና መካናይዜሽን ላይ በሰፊው እየተሠራበት ነው። ግብርና ሕልውናችን በመሆኑ የአንድ ወቅት ሥራ ሳይሆን በየጊዜው እየሠራን፤ የጎደለንን እያጠናከርን እንሄዳለን።

አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበርዎት ቆይታ እና ለሰጡትን ማብራሪያ አመሰግናለሁ።

መለስ (ዶ/ር)፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You