የቱሪዝም ምርት እና የሥራ እድል ፈጠራ – የወጣቶች ድርሻ

መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን ከአምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱ አድርጎ በመውሰድ በሀገሪቱ እድገት ላይ ተፅእኖው የጎላ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል። በተለይ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር፣ የቱሪዝም መሰረተ ልማት በማስፋፋት፣ የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲጨምር እና የገበያና ማስተዋወቅ ድርሻው እንዲያድግ ልዩ ልዩ ስልቶችን በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ ነው።

ቱሪዝም በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው በጎ ተፅእኖ እንዲያድግ በዘርፉ የሚገኙ ሀብቶችን ማቀናጀት እና በአግባቡ ለይቶ ማወቅ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይመክራሉ። ኢትዮጵያ በቱሪዝም እምቅ ሀብት አላቸው ተብሎ ከሚጠቀሱ ጥቂት ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች። በታሪክ፣ ተፈጥሮ፣ ቅርስ፣ ባህልና ልዩ ልዩ እሴቶች የተሞላች ነች። ከእነዚህ ሀብቶች ባሻገር በባህላዊ ውዝዋዜዎች፣ ምግቦችና አሰራራቸው፣ አልባሳት፣ ጌጣጌጦችና የጥበብ ውጤቶችም ትታወቃለች። ለዚህ ነው እነዚህን ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ አቅም መቀየር እንደሚያስፈልግ ታምኖበት ለዘርፉ ትኩረት የተሰጠው።

በቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያመጣሉ ተብሎ ከሚታሰብባቸው ንኡስ ዘርፎች ውስጥ አንዱ ባህላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦች፣ ቅርፃ ቅርፅ እና ሌሎቸም ምርቶች ለአገር ውስጥም ሆነ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በገበያ መልክ ማቅረብ ነው። ከ80 በላይ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም በርካታ ባህላዊ እሴቶች ያሉባት ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ የታደለችና የካበተ አቅም እንዳላት ይጠቀሳል። የቱሪዝም ምርትን እሴት ጨምሮና ኢትዮጵያዊ የሆኑ ማንነቶች ጎልተው እንዲታዩበት አድርጎ ወደ ገበያ ማውጣት ኢትዮጵያዊ ቀለምን ለቀሪው ዓለም ከማስተዋወቅ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አቅምን እንደሚያሳድግ ከዚህም ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር በእጅጉ ይታመንበታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች ታሪክ፣ ማንነት፣ ባህል እና የኑሮ ዘይቤ የሚያሳዩ የቱሪዝም ምርቶችን ገበያ ላይ ማቅረብ እየተለመደ መጥቷል። ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችም እነዚህን ምርቶች የመግዛት ፍላጎታቸው እያደገ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንድ ጎብኚ ወደ ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች ተጉዞ ባህላዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ ቅርሶችን ጎብኝቶና ተዝናንቶ ከመምጣቱ ባሻገር የአካባቢው መገለጫ የሆኑ ጌጣጌጦች፣ አልባሳቶች እና ልዩ ልዩ ቁሶችን ለማስታወሻነት ሸምቶ የመምጣት አጋጣሚው ሰፊ ነው። ይህ ደግሞ ምርቶቹን በማቅረብ ላይ የተሰማሩ ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ነው።

ወጣት አቤል ደሳለኝ ይባላል። የኢኖ አርቲስቲክ ብሮንዝ መስራች ነው። ከሌሎች ወጣት ባልደረቦቹ ጋር ኢትዮጵያዊ ቀለምን የሚያሳዩ ቅርፃ ቅርፆችን በመስራት ለሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ያቀርባል። ከቱሪስቶች ባሻገርም ኢትዮጵያዊ መልክ ያላቸው፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም ልዩ ልዩ ቅርፃ ቅርፆችን ለሚገዙ ግለሰቦችና ድርጅቶች በትእዛዝ እየሰሩ እንደሚያቀርቡ ይገልፃል። ወጣቶቹ የሚሰሩትን የፈጠራ ስራ ለማስተዋወቅም የተለያዩ አውደርእይ እንዲሁም የግንኙነት መድረኮችን ተጠቅመው እንደሚያስተዋውቁ ይገልፃል። ለአብነት ያህልም መስከረም ወር ላይ ተካሂዶ በነበረው የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት አውደ ርእይ ላይም እንደተሳተፉ ይናገራል።

ከነሀስ ምርት ተጠቅመው ኢትዮጵያዊ ባህል፣ እሴት፣ ታሪክና ልዩ ልዩ መገለጫዎችን በቅርፃ ቅርፅ መልክ እንደሚያቀርቡ የሚናገረው ወጣት አቤል፤ ስራዎቻቸው ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳላቸው ይገልጻል። ከውጪ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡና ኢትዮጵያውያን ምርቶቹን በፍላጎት እንደሚገዙ ይናገራል። ድርጅቶችም በሆቴል፣ በሥራ ቦታ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች ጭምር እንደሚወስዱና ተፈላጊነቱ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራል። ምርቶቻቸውን በአውደ ርዕይና በንግድ ትርኢቶች ላይ ከማስተዋወቅ ባሻገር በዲጂታል አማራጭ በኦላይን እንደሚያቀርቡ ያስረዳል። በዚህ ምክንያት የውጪ ሀገር ዜጎችና ድርጅቶች ምርቶቹን እንደሚፈልጉና እንደሚገዟቸው ይገልፃል።

ወጣት አቤል የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት እና አጠቃላይ ገፅታ የሚገነባና በበጎ መልኩ የሚያስተዋውቅ ምርት ወደ ገበያው ለማቅረብ ከወጣት ባልደረቦቹ ጋር እየሰሩ መሆኑን ይናገራል። በቅርቡ እራሳቸውን በማደራጀት የቱሪስት መዳረሻ በሆኑት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ተደራሽ ለመሆን እየሰሩ እንደሆነም ገልፆልናል።

ወጣት መራያድ ደጀኔ የቱሪዝም ምርት በማቅረብ በሚታወቀው ቦኩ ክራፍትስ ውስጥ በመስራችነትና በባለሙያነት ይሰራል። በሙያው የሌዘር ኢንጂነሪንግ ምሩቅ ነው። ድርጅታቸው የኢሮሚያን፣ ባህል፣ ታሪክ እሴቶች የሚያሳዩ የተለያዩ አልባሳት፣ ቅርፃ ቅርፆች፣ የቆዳ ላይ ምርቶችን ዲዛይን በማድረግና በማምረት ለገበያ እንደሚያቀርብ ይናገራል። ቦኮ የሚለውን ስያሜ ያገኘውም ከወይራ እንጨት ከሚሰራውና በኦሮሞ ባህል የስልጣን መገለጫና የሰላም ለማስፈን የሚጠቀሙበት ነው። ቦኩ የሚባለውን የሚይዘው ሰውም አባ ቦኩ እንዲሁም ቤተሰቦቹ ደግሞ ወረ ቦኩ እንደሚባሉ ይናገራል። ከዚህ መነሻ እነርሱም ስያቤውን በመውሰድ ባህላዊ እሴቱን ለመጠበቅ እንደሞከሩ ይናገራል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የቆዳ ሀብት ያላት እንደሆነች የሚናገረው ወጣት መራያድ እርሱን በመጠቀም የኦሮሚያን ባህል፣ እሴት እና መገለጫዎች ለማቅረብ እንደተነሱ ይናገራል። ከቆዳ ባሻገር በእንጨትና ተመልሶ ጥቅም ላይ በሚውል ወረቀትም ባህላዊ እሴቶቹን በማንፀባረቅ እንደሚያቀርቡ ይናገራል። በዚህም ቱሪስቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ምርቶቹን የኦሮሚያን እሴቶች እንዲይዙ በማድረግ ለማቅረብ መነሳታቸውንም ይገልፃል። ባህሉን ሳይለቅ ዘመናዊ መልከ እንዲኖረው በማድረግ ምርቶቻቸውን እንደሚያቀርቡ የሚናገረው ወጣቱ፣ ተቀባይነት እያገኙ እንደሆነ ይገልፃል። ዋናው ግባቸውም የኢትዮጵያንና የኦሮሚያን ቱሪዝም ማነቃቃትና ለዚያም ምርቶቹን እንደአጋጣሚ መጠቀም እንደሆነ ይናገራል።

በቆዳ ምርቱ የላፕቶፕ መያዣ፣ የሴቶች ቦርሳ እና ሌሎች መሰል ምርቶችን ከኦሮሞ ባህላዊ አልባሳትና ጨርቆችና ጥለቶች ጋር በማዋሃድ እንደሚያቀርቡ የሚናገረው ወጣት መራያድ፣ አዲስ የፈጠራ ይዘትና የኢትዮጵያን ቱሪዝም የማስተዋወቅ መንገድ መሆኑን ይናገራል። ከኦሮሚያ ባህላዊ እሴቶች ባሻገርም የሌሎች የኢትዮጵያዊ እሴቶችን ጨምረው እንደሚሰሩም ይገልፃል። ከዲዛይን ስራው ጀምሮ እስከመጨረሻው የምርት ውጤት ድረስ ተነሳሽነታቸው ከፍ ያለ ወጣቶች እንደሚሳተፉበት ይናገራል። በዚህም የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ባህሉን፣ ታሪኩን፣ ማንነቱንና እሴቶቹን ጠንቅቆ የሚረዳ ወጣት እየተፈጠረ መምጣቱን ይናገራል።

ኦሮሚያ በተፈጥሮና በባህል የታደለች ነች የሚለው ወጣት መራያድ የወለጋ፣ የባሌ፣ የጉጂ ባህላዊ እሴቶችን በእንጨት፣ በቆዳና በወረቀት ላይ በማዋሃድ እንደሚያስተዋውቁ ይገልፃል። በአፋር፣ በሶማሌ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ እሴቶችንም ጭምር በስራዎቻቸው ላይ እንደሚያንፀባርቁ ይናገራል።

ቦኩ ክራፍትስ በወጣቶች ተነሳሽነት የተፈጠረ የቱሪዝም ምርት አቅራቢ ድርጅት ነው። ዋና ትኩረቱንም የኢትዮጵያን እሴቶች በማስተዋወቅ ላይ ያደረገ ነው። እንደ ወጣት መራያድ ገለፃ ምርቶቻቸው በጎብኚዎች ተቀባይነት ያለው ነው። ኢትዮጵያ መጥተው ማስታወሻ ይዘው መሄድ የሚፈልጉ ምርቶቹን ምርጫቸው እንደሚያደርጉ በመናገርም ይህ ለዓላማቸው እንዳቀረባቸውና ይበልጥ ለመስራት እያነሳሳቸው እንደሆነ ይገልፃል።

ከውጪ ሀገር ቱሪስቶች ባሻገር የቦኩ ክራፍትስ የቱሪዝም ምርቶች በሀገር ውስጥ ዜጎች ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ወጣት መራያድ ይናገራል። በምሳሌነት የሚጠቅሰውም የበዓላት ወቅትን ነው። በእነዚህ ጊዜያት ባህላዊ ምርቶችና አልባሳት ተፈላጊነታቸው እንደሚጨምር ይናገራል። በተለይ በመስቀል፣ በጥምቀትና በኢሬቻ በዓላት ወቅት በርካታ የሀገር ውስጥ ዜጎች ለምርቶቹ ፍላጎት እንደሚያሳዩ ነው የሚገልጸው። የበዓሉ ተሳታፊዎች ከሚለብሱት ባህላዊ አልባሳት ጋር የሚዋሃድ የቆዳ ምርቶችን ሲፈልጉ በቀጥታ ወደ እነርሱ እንደሚመጡም ይናገራል።

የቱሪዝም ምርቶቹ የሚዘጋጁት በኤክስፖርት ደረጃ መሆኑን የሚናገረው ወጣት መራያድ፣ ግብዓቶቹን ከተለያዩ አቅራቢዎች እንደሚያገኟቸው ይገልፃል። ይህም የሥራ እድል ፈጠራውን እንደሚያሰፋውና ለገበያ ትስስር መፈጠር የራሱ ሚና እንዳለው ይናገራል። ከግብዓት አቅራቢዎቹ ባሻገር ድርጅታቸውም ወጣቶችን በሙያው በማሰልጠን እየቀጠረ እንደሆነ በመናገር ለሥራ እድል ፈጠራ ያለውን የጎላ ሚናም ያሳያል።

ወጣት መራያድ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ ፌስቲቫሎችን፣ አውደ ርዕይ እና የንግድ ትርኢቶች ላይ እንደሚጠቀሙ ይናገራል። በተለይ ቱሪዝምን መሰረት ያደረጉ አውደ ርዕይ ሲዘጋጅ በዚያ ላይ በመሳተፍ ያላቸውም አቅም እንደሚያሳዩ ይገልፃል። ይህም በቀጥታ የኢትዮጵያን ባህል የሚወዱ የውጪ ዜጎችና የሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ እድሉን እንደከፈተላቸው ይናገራል። በተለይ በአውደ ርዕዮች ላይ መሳተፋቸው ከውጪም ሆነ ከሀገር ውስጥ አብረው ለመስራትና ፅንሰ ሀሳቡን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ፍላጎት ያላቸው አካላት ጋር እንዲገናኙ አማራጭ እንደሚከፍትላቸው ይገልፃል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሥራ አጥ ቁጥር መኖሩን የሚናገረው ወጣት መራያድ፤ ለዚህ መፍትሄው የሥራ ፈጠራ መሆኑን ይናገራል። የቱሪዝም ዘርፍ ለዚህ ምቹ መሆኑን በመግለፅም ወጣቶች ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ ይመክራል። በኦሮሚያ ብቻ የቱሪዝም እድገት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን የሚያነሳው ወጣቱ፣ ይህንን ወደ እድል መቀየር እንደሚያስፈልግ ያምናል። ቦኮ ክራፍት መንግሥት ለቱሪዝሙ የሰጠውን ትኩረት እንደ በጎ አጋጣሚ በማየት የተፈጠረ ድርጅት መሆኑንም ይናገራል። አንድ ጎብኚ በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች ሲንቀሳቀስ ማስታወሻ የሚሆን ምርት እንደሚፈልግ በማመን ለዚያ ፍላጎት የሚሆን አቅርቦት ላይ መሳተፋቸውን ይናገራል። ሌላውም ወጣት ገና ያልተነካና እያደገ ያለው ዘርፍ ላይ ቢሰማራና አዳዲስ ሃሳቦችን በማምጣት ቢሳተፍ ውጤታማ እንደሚሆን ይናገራል።

የቱሪዝም ምርት ለውጪ ጎብኚዎች ማቅረብ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚገልፀው ወጣት መራያድ፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ መልካም ገፅታ መገንባት እንደሆነ ይናገራል። አንድ ጎብኚ ኢትዮጵያ ደርሶና ጎብኝቶ ምርቶቹን ገዝቶ ወደ ሀገሩ ሲሄድ ለሌሎች ሰዎች የማስተዋወቅ እድሉ ሰፊ መሆኑን ይናገራል። ይህም ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ እና ገፅታዋን በመገንባት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አስተዋጽፆ እንደሚኖረው ይገልፃል።

መራያድ እንደሚለው፣ የቱሪዝም ምርት ጎብኚዎች ስፍራው ድረስ ሲመጡ ብቻ የሚሸምቱት አይደለም። ከርቀት የሚፈልጉትን ሀገር ባህልና ማንነት የሚወክል ምርት በዲጂታል አማራጭ ይገበያሉ። ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶችን ጨምረው ወደ ገበያ የሚያቀርቡ አምራቾች ምቹ መሆን ይኖርባቸዋል። ቦኩ ክራፍት ይህንን አጋጣሚ እንደሚጠቀምና በተለያዩ ማህበራዊ አማራጮች ምርቶቹን ገበያ ላይ ከማቅረብ ባሻገር የኢ-ኮሜርስ ገበያውን ለመቀላቀል ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You