የትምህርት አባት ዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ የቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት

እድሜያቸውን ሙሉ ለትምህርትና በትምህርት የኖሩ ሰው ናቸው። የዛሬ 70 ዓመት አብዛኛው ዜጋ ስለ ትምህርት ባልገባውና ባልተረዳበት ወቅት ትምህርትን ወደውና አስቀድመው ጠንክረው በመማር በሀገራችን የመጀመሪያዎቹ 13 ኢትዮጵያዊያን በዲግሪ ሲመረቁ አንዱ ለመሆን ችለዋል። በትምህርት ዓለም ከተማሪነት እስከ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት የሄዱበት ጉዞ ወርቃማ እንደነበር ይናገራሉ።

ሁሉንም ዲግሪዎቻቸውን በትምህርት መስክ ያገኙ ሲሆን፤ በአለም ባንክ ውስጥ በሚወዱት የትምህርት ሙያ በማገልገላቸው ተመስግነዋል። የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት፣ የመጀመሪያው የባህል ሚኒስቴር፣ የመጀመሪያው አፍሪካዊና ኢትዮጵያዊ የዓለም ባንክ የትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ በዩኒሴፍ የመጀመሪያው የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ከማገልገላቸውም በላይ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ በሚል 600 ገፅ ያለው መጽሐፍ ያሳተሙ ናቸው፡፡ መጽሐፉ የኢትዮጵያን የትምህርት ታሪክ ተንትኖ የሚያስረዳ ነው።

የዛሬው የህይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን ዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ ይህንንና ሌሎች ሊነገሩ የሚገቧቸውን ታሪካቸውን በዚህ መልክ አሰናድተነዋል፡፡

አክሊሉ (ዶ/ር) ሀብቴ የተወለዱት በ1921ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ “ኦርማ ጋራዥ” በሚባለው ሰፈር ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆዩ የጣሊያን ወረራ በመከሰቱ ምክንያት እርሳቸውና ቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባን ለቀው ለመውጣት ተገደዱ፡፡

“……የተወለድኩት አዲስ አበባ የአሁኑ ሊሴገብረማርያም ትምህርት ቤት አካባቢ ኦርማ ጋራዥ እየተባለ የሚጠራው ሰፈር ነበር፡፡ ነገር ግን ጣሊያን ሲገባ እኛም ከአዲስ አበባ ሎሜ ወደሚባለው የአባቴ አባት ሀገር ለመሄድ ተገደድን ” ይላሉ፡፡

በወቅቱ ዶ/ር አክሊሉ ገና ትንሽ ልጅ ቢሆኑም ጣሊያን ሀገሪቱን መቆጣጠሩን፤ ቤተሰቦቻቸውም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ በሚያወራውና በሚያደርገው ድርጊት ለመረዳት አልተቸገሩም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹ጣሊያን እየዞረ ቤት ያቃጥላል›› በመባሉ ምክንያት ዶ/ር አክሊሉ ፤ ቤተሰቦቻቸው አርፈውበት የነበረውን ቤት ለቀው በአቅራቢያው ወዳለ ዋሻ ገብተው በመሸሸግ የጣሊያኖችን ሥራ ያስተውሉም እንደነበር ይናገራሉ፡፡

እንደአጋጣሚ ግን አባታቸው ለማረፊያ ሰርተውት የነበረው ቤት የቆርቆሮ ስለነበርና ለመቃጠልም አስቻይ ሁኔታ ስላልነበረ ሳይቃጠል መቅረቱንም ነው ዶክተር አክሊሉ የሚያስረዱት። አካባቢው ላይ ትንሽ ከቆዩ በኋላም እርሳቸው በውል በማያውቁት ምክንያት ዳግም ወደሞጆ መሄዳቸውንም ያስታውሳሉ፡፡

“……ሞጆ ኮልባ ጊዮርጊስ የሄድነው የአባታችን እናት ሀገር ስለሆነ ነው፡፡ እኔም ነብስ እያወኩ የነበርኩበት ጊዜ ስለነበር የሚደረጉትን ነገሮች ሁሉ አውቃለሁ፡፡ ጣሊያን ሀገራችንን ለቆ እስከሚወጣ ድረስም የቆየነው እዛው ነው፡፡”ይላሉ፡፡

በእንዲህ ያለው ሁኔታ ውስጥ ሆነው ልጅነታቸውን ሲያስታውሱ፤ “…. እንደ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ልጅ ከብት እንጠብቃለን ቤተሰቦቻችንን ማገዝ ባለብን ነገሮች ሁሉ እናግዛለን እንላላካለን በዚህም ልዩ ትዝታ ያለኝ ነኝ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ እንዲህ እንዲህ እያሉ እድሜያቸው ለትምህርት በመድረሱ ምክንያት ፊደል ይቆጥሩ ዘንድ አባታቸው ከሩቅ ቦታ አስተማሪ አፈላልገው በማምጣት ፊደል እንዲቆጥሩ አደረጉ፡፡ ዶ/ር አክሊሉ ግን ከፊደል ቆጠራ አልፈው በመምህራቸው ዳዊት እስከመድገም መድረሳቸውን እና ከመምህራቸው ጋር አብረው መቆየታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

ዶ/ር አክሊሉ ሲናገሩ፤ በፈጣሪ እርዳታና በአርበኞች ቆራጥ ተጋድሎ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፤ አባታቸው የመንግሥት ሥራ በማግኘታቸው ከሞጆ ወደ ቢሾፍቱ ቤተሰባቸውን ጠቅለው መጡ፡፡ በወቅቱ ዶ/ር አክሊሉና ታናሽ ወንድማቸው ዘመናዊ ትምህርትን ለመማር በእጅጉ ፈልገው ነበር፡፡ ነገር ግን አባታቸው ‹‹የፈረንጁን ትምህርት ትደርሱበታላችሁ መጀመሪያ የሀገራችሁን ትምህርት አድቅቁት፡፡›› በማለታቸው ምክንያት አጎታቸው ግቢ ውስጥ መምህር ተፈልጎ ለአንድ አመት ያህል አማርኛና የግዕዝ ትምህርት እንዲማሩ በመደረጉ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የመተርጎም ሂደቱን ሙሉ በሙሉ መለየት ቻሉ፡፡

የአንድ አመት ግዴታቸውን ከተወጡ በኋላም፤ አሁን ወደ ፈረንጅ ትምህርት ቤት መግባት ትችላላችሁ መባላቸውን የሚያስታውሱት ዶ/ር አክሊሉ የተመኙትን ለመማርም ወደመረጡት ትምህርት ቤት ገቡ፡፡

“…….ትምህርት ስንጀምር አሁን ሊሴ ገብረማርያም የሆነው ትምህርት ቤት የአሁኑን ይዘቱን ከመያዙ በፊት የአርበኛ ልጆች ትምህርት ቤት ይባል ነበር። በወቅቱ ወላጆቻቸውን ያጡ የአርበኛ ልጆችም እያደሩ እንዲማሩበት ይደረግ ነበር፤ እኛ ደግሞ ቤታችንም አቅራቢያው ላይ ስለነበር በተመላላሽነት እንማር ነበር፡፡ ” ይላሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ የአሁኑ ሊሴገብረማርያም የቀድሞው የአርበኞች ልጆች ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙ መቆየትን አልፈለጉም፤ ይልቁንም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ሄደው የሚወዱትን ዘመናዊ ትምህርት በተሻለ ሁኔታ ለመቅሰም አሰቡ፤ ይህንን ሲያስቡ ደግሞ ለአባታቸውም ሆነ ለተቀሩት ቤተሰቦቻቸው ምንም ያሉት ነገር አልነበረም፡፡

ይህንን ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ከአንድ የሰፈር ጓደኛቸው ጋር በመሆን በቀጥታ ያመሩት ትምህርት ሚኒስቴር ነበር፡፡ እዛም ደርሰው ሚኒስትሩ ቢሮ በመግባት በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን መቀጠል እንደሚፈልጉ ይናገራሉ፡፡ ሚኒስትሩም አጠገባቸው የነበረውን መጽሐፍ እስኪ አንብብ ብለው በመስጠት ከፈተኗቸው በኋላ፤ በሚፈለገው ልክ ስለነበሩ በቀጥታ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ የሚያስችላቸው ደብዳቤ እንደተጻፈላቸው ያብራራሉ፡፡

“…..በወቅቱ ተፈሪ መኮንን ትልቅ ትምህርት ቤት ከመሆኑም በላይ ለሁለት የተከፈለ ነበር። አንደኛው በጣም ህጻናት (ልጆች) የሆኑ የሚማሩበት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እድሜያቸው ከፍ ከፍ ያሉ ከፖሊስነት ጀምሮ ለተለያዩ ሙያዎች እንዲሁም ለውጭ ሀገር የትምህርት እድል ሲፈለጉ የሚመለመሉበት ነበር፡፡ እኛም ሁለተኛ አልያም ሶስተኛ ክፍል እንድንገባ ተብሎ ነበር፡፡” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናቸውን እስከሚወስዱ ድረስም እዛው ተፈሪ መኮንን የተማሩ ሲሆን፤ በእዚህም በተለይም የ12ተኛ ክፍል ትምህርትን ተምረው ሲፈተኑ ካሉት ተማሪዎች ሁሉ የላቀ ውጤት አመጡ፡፡ ትምህርታቸውን በአንደኝነት አጠናቀቁ፡፡

“…..በወቅቱ ንጉሱ እራት ሰዓት ወይም ደግሞ በትምህርት ላይ ባለንበት ወቅት እየመጡ ይጎበኙን ልዩ ልዩ ጥያቄዎችንም ይጠይቁ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንድንበላ ያመጡልን ነበር፡፡ በሌላ በኩልም ሀገር በሚጎበኙበት ወቅት ጎበዝ ተማሪ ሲያገኙ ስጡኝ ብለው ይዘው ይመጡና ተፈሪ መኮንን ያስገቡም ነበር፡፡” በማለት በትምህርት ቤቱ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

የንጉሱ የእጅ ሰዓት ሽልማት

“……የ 12ተኛ ክፍል ትምህርቴን በሚገባ አጠናቅቄ ከክፍል ጓደኞቼ በላቀ ውጤት 1ኛ በመውጣቴ ጃንሆይ ሰዓት ሸለሙኝ፡፡ ሰዓቷ ወርቅ ቅብ የሆነች በጣም ቆንጆ ሆና የተሰራች ከመሆናም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ አይነት ገጽታም ያላት ነበረች፡፡ እርሳቸውም ሽልማቱን ሲሰጡኝ የጠየቁኝ ጥያቄ ‹መጽሐፍ ቅዱስ ታነባለህ?› የሚል ነበር። እኔም በአዎንታ መለስኩ እርሳቸውም ‹በል በንባብህ ቀጥል› ብለው ሰዓቷን ሰጡኝ፤ በመቀጠልም ሰዓት የሰጠንህ ልክ እንደ ሰዓት ሁሉ በተማርከውና ባወቅከው ልክ ሀገርሀን በእራስህ አውቀህ እንድታገለግል ነው ሲሉም መከሩኝ፡፡” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከጎበዝ ተማሪዎች ብዙ የሚጠብቁ ነበሩና ስታድጉ ምን መሆን ትፈልጋላችሁ? እያሉ ተማሪዎችን የመጠየቅ ልምድ እንደነበራቸው የሚናገሩት ዶ/ር አክሊሉ ይህ ጥያቄ ደግሞ እርሳቸውም ጋር ደርሶ መጠየቃቸው አልቀረም፤ መልሳቸው የነበረው ግን ከሆነልኝ የህግ ወይም የጤና ባለሙያ ብሆን እፈልግለሁ የሚል ነበር፡፡ ንጉሱ ግን ‹‹ለምን መምህር አትሆንም፤ መምህርነት ትልቅ ሙያ ነው እናንተን ያስተማሯችሁ መምህራንም ተተኪ ይፈልጋሉ።›› በማለት የሰጧቸውን ምክር ልባዊ በሆነ ደስታ መቀበላቸውንም ነው የሚናገሩት፡፡

ከ 1950 እስከ 1954 ዓ.ም የመጀመሪያው የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ

ዶ/ር አክሊሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እጅግ አመርቂ በሚባል ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ፤ በቀጥታ ኮሌጅ የመግባት እድልን አገኙ፡፡ በወቅቱ የአርትና ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች (ፋኩሊቲ) ብቻ ነበር የነበሩት የሚሉት ዶ/ር አክሊሉ ሁሉም ደግሞ አራት ኪሎ ግቢ ውስጥ የነበሩ ስለመሆናቸውም ያስታውሳሉ፡፡

“…..አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ እንማርበታለን፣ እንመገብበታለን ማታ ደግሞ ረጅም በሆነው የማደሪያ ክፍል ውስጥ 18 ያህል ወጣቶች አልጋ ተዘርግቶልን እንተኛም ነበር፡፡ ብቻ በጠቅላላው ግን እንደ ሀገራችን አቅም ሁሉ ነገር ተሟልቶልን ነው ተምረን ያጠናቀቅነው” ሲሉም ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

የውጭ ሀገር የትምህርት እድል

በወቅቱ መንግሥት ጎበዝ ሆኖ የተማረውን ሰው ሁሉ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ የተሻለ ትምህርትን ቀስሞ መጥቶ ሀገሩን ያገለግል ዘንድ ይሠራ ነበር። እነ ዶ/ር አክሊሉም የኮሌጅ ትምህርትቸውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቁ በመሆናቸው መንግሥት በትምህርት አታሼዎቹ አማካይነት የተለያዩ ሀገራት ላይ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን አወዳድሮ አንዱ ጋር ሄደው እንዲማሩ እድሉን ፈጠረላቸው፡፡

“……በወቅቱ የትምህርት እድሉን ለማግኘት የሚያስፈልገው ጎበዝ ተማሪ መሆን እንጂ ከዚህ ክፍለ ሀገር መጣህ አንተ እንዲህ ነህ እንደዛ የሚባል ነገር በፍጹም አልነበረም፡፡ ብቻ ጎበዝ ነወይ? የሚፈልገው ምን መማር ነው? በሚፈልገው የትምህርት አይነትስ ትምህርት ያለው የት ነው? የሚለውን ተመርጦ ሲጠናቀቅ መንግሥት ሙሉ ወጪን ችሎ ያስተምር ነበር፡፡” በማለት እርሳቸውና መሰሎቻቸው የውጭ የትምህርት እድልን እንዴት ያገኙ እንደነበር ያብራራሉ።

እርሳቸውም የጀመሩትን የመምህርነት የትምህርት ዘርፍ ይበልጥ ይሰለጥኑበት ዘንድ መንግሥት ወደ ካናዳ እንደላካቸው የሚናገሩት ዶ/ር አክሊሉ፤ በካናዳም ዩኒፔግ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ትምህርታቸውን በብቃት ተምረው፤ በመምህርነት የባችለር ዲግሪያቸውን ስለማግኘታቸው ይናገራሉ።

ይህንን ዲግሪያቸውን ካገኙ በኋላም በቀጥታ ወደ አሜሪካን ኦሀዩ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ መምህራኖቻቸው ተነጋግረው መጨረሳቸውን ሰሙ፡፡ ወደዛ ሄደውም እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ትምህርታቸውን ተምረውና አጠናቀው ወደሀገራቸው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡

ከመምህርነት እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነት

ዶ/ር አክሊሉ በ1959 ዓ.ም የውጭ ሀገር ትምህርታቸውን አጠናቀው እንደተመለሱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ ከዛ በፊት ግን ይላሉ ዶ/ር አክሊሉ፤ “…..በወቅቱ ንጉሱ በሀገር ደረጃ ዩኒቨርሲቲ እንዲኖረን ምኞትና ፍላጎት ነበራቸው። ይህንን ህልማቸው ለማሳካት ደግሞ አንዳንድ አሜሪካኖች ዩኒቨርሲቲ ለመክፈት ምን ያስፈልጋል? የሚለውን እንዲያጠኑላቸው የማድረግ ሁኔታዎች በሰፊው ነበሩ። በኋላም ስራው ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ የሚሰጠውን ትምህርት ፈር የሚያስይዝ ሆኖ በመገኘቱም ዩኒቨርሲቲው እንዲቋቋምና የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ተብሎም እንዲጠራ ሆነ።” በማለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን አመሰራረት ይናገራሉ፡፡

ከዛም ዶ/ር አክሊሉ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መምህር ኋላም በማስተማር (በኤጁኬሽን) ትምህርት ክፍል ኃላፊ ከዛም ዲን በመሆን በኃላፊነት መስራታቸውን ቀጠሉ፡፡ የአርት ትምህርት ክፍልም ዲን ሆነው ከሰሩ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት የመሆን እድል ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡

የዩኒቪርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነውም በአንድ ወቅት ለንጉሱ የዩኒቨርሲቲውን የሥራ እንቅስቃሴ የተማሪዎቹን ሁኔታ አስተዳደራዊ ስራዎችን ብሎም መሟላት የሚገቡ ነገሮችን አስመልክተው ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ በእዚህን ጊዜ ደግሞ ንጉሱ ዓይን ውስጥ መግባታቸው አልቀረም፡፡ ንጉሱ ዓይን ውስጥ ከመግባታቸውም በላይ ለከፍተኛ ኃላፊነት የታጩ ሰው ሆኑ፡፡

“…….በወቅቱ እኔ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት እንደመሆኔ አመታዊ የሥራ እንቅስቃሴውን በሪፖርት መልክ የማቅረብ ኃላፊነቱ የእኔ ነው፡፡ ኃላፊነቴንም ያዘጋጀሁትን ሪፖርት በአግባቡ በማቅረብ ተወጣሁ፤ ንጉሱና በዙሪያቸው ያሉ እንዲሁም ሌሎች የካቢኔ አባላት መመለስ አለበት ያሉትን ጥያቄ ሁሉ ሰነዘሩ፤ እኔም እስከቻልኩ ድረስ መለስኩ፡፡ ኋላም ከንጉሱ ሌላ የሥራ ትዕዛዝ ተሰጥቶኝ በፍጥነት አጠናቅቄ ቤተመንግሥት እንድመጣ ታዘዝኩ ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ ትዕዛዝ መቀበላቸውን እንጂ በዚህን ያህል ደረጃ ንጉሱ ስራውን ይከታተላሉ ብለው ባለማሰባቸው ትንሽ ዘንጋ ብለው ነበር። ነገር ግን ከቀናት በኋላ ከቤተ መንግሥት ስልክ ተደውሎ ስራውን ምን አደረስከው? የሚል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ እርሳቸውም እየሰሩ እንዳሉና በቀናት ውስጥ እንደሚያጠናቅቁ ተናግረው ስልኩ ይዘጋል፡፡

“……እውነት ለመናገር ንጉሱ አዘዙኝ እንጂ እንዲህ ተከታትለው ውጤቱን ይጠይቁኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ተደውሎ ስጠየቅም ተደናግጫለሁ፡፡ ነገር ግን ስራው እጄ ላይ የነበረ በመሆኑ በሁለት ቀን ሌት ተቀን ሰርቼ ይዤ ቀረብኩ። እርሳቸውም በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር ቁጭ ብለው በል ያመጣኸውን አንብበው አሉኝ። እኔም አነበብኩ፡፡ በጣም ተደስተውም ‹‹ከአሁን በኋላ ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዚዳንትነት የምትመራው አንተ ነህ፤ ደብዳቤ ይደርስሃል፡፡›› ብለው አሰናበቱኝ” በማለት የተሾሙበትን አካሄድ ይናገራሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ ሹመታቸውን ተቀብለው የዩኒቨርሲቲው ሁለተኛ ፕሬዚዳንት በመሆን የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች እንዲከፈቱ በማድረግ፤ ከዛም በላይ በዝቅተኛው የትምህርት እርከን ላይ ብዙ በመስራትና ዘመናዊ ትምህርት በሀገሪቱ እንዲስፋፋ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚናቸውን እየተወጡ ባሉበት ወቅት ንጉሳዊ አስተዳደሩ ወርዶ ወታደራዊው ሥርዓት ሀገሪቱን በመቆጣጠሩ እርሳቸውም ብዙ ከሰሩበትና ሊሰሩበት ካቀዱበት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለቀቁ፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነታቸው ይነሱ እንጂ ወታደራዊው ሥርዓትም እንደርሳቸው ያሉ የተማሩ ለሀገር ብዙ የሚሰሩ ሰዎች ያስፈልጉት ነበርና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ሀገር ለተቋቋመው ባህል ሚኒስቴር ሚኒስትር ይሆኑ ዘንድ ተሾሙ፡፡

የመጀመሪያው የባህል ሚኒስቴር ሚኒስትር

የመጀመሪያ የሚለው ነገር በብዙ መልኩ አስፈሪ እንዲሁም ኃላፊነቱም ከባድ ቢሆንም ዶ/ር አክሊሉ ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ለማቋቋም ብዙም የተቸገሩ አልነበሩም፡፡ የተሰጣቸውን የሚኒስትርነት ኃላፊነት ተቀብለውም ሥራውን “ሀ” ብለው ጀመሩ፡፡

“…ባህል ሚኒስቴር አዲስ መሥሪያ ቤት እንደመሆኑ ለማቋቋምም ብዙ የሚያስፈልጉ ነገሮች ነበሩ፡፡ እኔም እውቀቴን ተጠቅሜ የመንግሥትም ድጋፍ ስለነበር የተለያዩ የትምህርትና የሥራ ተቋማትን በአንድ አቀናጅቼ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእግሩ እንዲቆም አደረኩት፡፡ ነገር ግን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ መስራት አልቻልኩም፡፡” በማለት ሁኔታውን ይናገራሉ፡፡

ዶ/ር አክሊሉ ባህል ሚኒስቴር እያሉ ዓለም አቀፍ የሥራ ጥሪ ከዓለም ባንክ ቀረበላቸው፤ እርሳቸውም እድሉ እንዲያመልጣቸው ስላልፈለጉ የልቀቁኝ ጥያቄያቸውን ለመንግሥት አቀረቡ፡፡ ነገር ግን እርሳቸውን መልቀቅ ቀላል ስላልነበር ሚኒስትሮችና ሌሎችም ሁለት ተከፍለው መከራከር ጀመሩ፤ ግማሾቹ ዓለም አቀፍ ተቋም ላይ መስራቱ ለሀገራችንም ጠቃሚ ነው፤ ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ አይ በቂ የተማረ ሰው ኃይል በሌላት ሀገር ላይ ያስተማርናቸውን ሰዎች መልቀቅ ተገቢ አይደለም የሚሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ‹‹ቢሄድም ለሀገራችን ይጠቅማል፡፡›› የሚለው ሃሳብ ስላሸነፈ ዶ/ር አክሊሉ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ብሎም ኢትዮጵያዊ የዓለም ባንክ የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሆኑ፡፡

እዛም እየሰሩ ዓለም ባንክና ዩኒሴፍ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ለማስፋፋት ስምምነት ሲያደርጉ ዶ/ር አክሊሉ በዩኒሴፍ የመጀመሪያው የትምህርትና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ ሆነው ለመሾም በቁ፡፡ በዚህ ተቋም ላይም ለ20 ዓመታት አገልግለው በጡረታ ተሸኙ፡፡

የቤተሰብ ሁኔታ

ዶ/ር አክሊሉ በሥራና ትምህርት በቆዩበት አሁንም እየኖሩ ባሉበት ሀገረ አሜሪካን ባለቤታቸውን ወይዘሮ ሰላማዊትን ተዋወቁ፡፡ ትውውቃቸውም ወደ ፍቅር አድጎ ከዛም በትዳር ሊተሳሰሩ ሲያስቡ፤ ሁለቱም በአንድ ዓመት ልዩነት ማለትም ዶ/ር አክሊሉ ቀደም ብለው ወይዘሮ ሰላማዊት ደግሞ በአመቱ ሀገራቸው በመግባት በሀገር ባህል ወግ ሽማግሌ ልከው ተፈቅዶላቸው በትዳር አንድ ሆኑ፡፡ ከትዳራቸውም አራት ወንድ ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ ሁለቱ የህክምና ዶክተሮች መሆናቸውን በአንደበታቸው ይናገራሉ። ዛሬ ላይ ዶ/ር አክሊሉ 10 የልጅ ልጆችን ለማየት ችለዋል፡፡

እውቅናና ሽልማት

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2014 ዓ.ም ክብርት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ እንዲሁም የወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በተገኙበት ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ እውቅና ተሰቷቸዋል፡፡

ዘንድሮም በ2016 ዓ.ም ለባዊ ኢንተርናሽናል አካዳሚ ከተወዳጅ ሚዲያ ጋር በመሆን የህይወት ዘመን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You