ፓን አፍሪካኒዝም፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ከፍ ያለ እሳቤን በውስጡ ያቀፈ ሲሆን፤ ለዚህ እሳቤ እውን መሆን አፍሪካውያን እውቀትና ሀብታቸውን ጨምሮ ያላቸውን አቅም ሁሉ አሰባስበውና አቀናጅተው በአንድ የመሥራት እና ታላቅ የመሆን ትልም ውስጥ የተቃኘ ተግባር ነው::
እሳቤው የጀመረው ቀደምት የአፍሪካ መሪዎች በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውን ክፉ ግብር ገጹን ለመቀየር ያስችል ዘንድ፤ አፍሪካውያንን በአንድ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጥላ ስር አሰባስቦ ጠንካራ ኅብረት ያላት አንድ ጠንካራ አፍሪካን እውን ከማድረግ ነበር::
ይሄ አንድነት ደግሞ የጠነከረ ኢኮኖሚን፤ የጠነከረ የፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነትን፤ የጠነከረ የውስጥ አንድነትንና ወንድማማችነትን፤ የጠነከረ የሰው ሃይል ግንባታና ሥልጠና አውድን፤ በጥቅሉ በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም፣ በቴክኖሎጂውም፣… ዘርፎች የሚገለጽ ከፍ ያለ የመበልጸግ ዕድልን እንደሚፈጥር ታምኖበት የተጀመረ ነው::
ታስቦም አልቀረ፣ ይሄ በአንድ ተሰልፎ የመሥራት ጅማሮም አፍሪካውያን የቅኝ ተገዢነትን ቀንበር ከላያቸው ላይ አሽቀንጥረው እንዲጥሉ አቅም ፈጥሮላቸዋል:: አፍሪካ እንደ አህጉር የራሷን ጠንካራ ሕብረት ፈጥራ የምትሠራበት የፖለቲካም፣ የኢኮኖሚም፣ የዲፕሎማሲም፣ የሠላምና ደህንነትም፣… አቅሟን አሰባስባ የምትተገብርበት አንድ ወጥ ተቋምን እውን እንድታደርግም አስችሏታል::
ይሄን መሰል ተግባርና ውጤት ለመገኘቱ ግንባር ቀደም ሥራ ከሠሩ ሀገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር ናት:: በወቅቱ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩት አፄ ኃይለሥላሴ “የአፍሪካ አባት” እስከመባል የደረሱትም በዚሁ ለአፍሪካውያን አንድነትና ከፍታ እውን መሆን ባበረከቱት አዎንታዊ አስተዋጽዖ ነው::
ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ይሄን መሰል አበርክቶዋ በአንድ ወቅት ተቀንብቦ የሚገለጽ ብቻ አይደለም:: ይልቁንም በትናንቱ እርሾ እየተቦካ አዳዲስ እሳቤን በማመንጨት ለአፍሪካውያን ኅብረትና ከፍታ የሚሠራበት እንጂ:: የኢትዮጵያን ስም አንግበው የኢትዮጵያም የአፍሪካም ከፍታ ማሳያ መሆን የቻሉ ተቋማትና ግብራቸውም የዚህ አንድ ማሳያ ናቸው::
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጠቃሽ ሲሆን፤ አየር መንገዱ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊነትን በዓለም ደረጃ ከፍ አድርጎ መግለጥና ማስረዳት የቻለ የአፍሪካውያን የመቻልና የማድረግ አቅም አብነትም ነው::
ከዚህ ጎን ለጎን የሚታየው ደግሞ የአፍሪካውያንን ብሎም የዓለምን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ባበረከተውና እያበረከተ ባለው ከፍ ያለ ተግባር ቀድሞ የሚገለጸው የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው:: ይሄ ሠራዊት ከትናንት እስከ ዛሬ፣ ከኮሪያ ልሳነ ምድር እስከ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት ከፍ ያለ የሰላም ማስከበር ተግባርን በማከናወን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንም ኩራት መሆን የቻለ ነው::
የዚህ ሠራዊት ብርቱ ክንድ የሆነው እና በአየር ክልል ላይ በመዋል ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ዋጋ እየከፈለ የዘለቀው ሌላው የኢትዮጵያም የአፍሪካም የመቻል አቅም ደግሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነው::
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ትናንት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ባለቤት የሆኑ መሪዎች መሠረቱን ጥሎ በበዛ ውጣ ውረድ ውስጥ ግዳጁን እየፈጸመ ያለ ተቋም ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ በተለይ ከ2010 ሀገራዊ ለውጥ በኋላ ኢትዮጵያ የምትፈራና የምትከበር ሀገር አድርጓል:: አፍሪካውያንንም በዚሁ ገጽ ለመሳል ደፋ ቀና በማለት ላይ ይገኛል::
አየር ኃይሉ፣ የኢትዮጵያን አየር ክልል መጠበቅ የሚያስችለውን ሙሉ ቁመና የገነባ ከመሆኑ በሻገር፤ በፓን አፍሪካኒዝም ቅኝት ውስጥ ገብቶ አፍሪካውያን የአየር ክልላቸውን በአስተማማኝ መልኩ መጠበቅ የሚያስችላቸውን ቁመና እንዲጎናጸፉ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ የበኩሉን እያበረከተ የሚገኝ ነው::
የ88 ዓመት አንጋፋ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ ከለውጡ ማግስት በሠራቸው ሥራዎች የሰው ኃይሉን አቅም በመገንባት፤ ዘመኑን የመጠነ የውጊያ ቴክኖሎጂን መታጠቅ፤ የትጥቅ አቅሙን ማንቀሳቀስም መጠገንም የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎችን በራሱ አቅምና ተቋም ማሠልጠን ችሏል::
ይሄ ተግባር ደግሞ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ መቅረት ያለበት ባለመሁኑና እሳቤውም ከራስ አልፎ ለአፍሪካውያን ልዕልና መሥራት እንደመሆኑ፤ አፍሪካውያን አየር ኃይሎች በዚህ ልክ ራሳቸውን እንዲያበቁ የሰው ኃይላቸውን ከማሠልጠን ጀምሮ በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል::
ከዚህ በተጓዳኝ ተቋማቱ በጋራ ተናብበውና ተጋግዘው መሥራት የሚችሉበትን አካሄድ ቀይሶ የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች ፎረም እንዲመሠረት እና የመጀመሪያው ሁነትም በዚሁ እንዲካሄድ በማድረግ የትብብር ጉዞው ፈር እንዲይዝ አድርጓል:: ይሄ ደግሞ አፍሪካ ከፍ ወዳለ መዳረሻዋ ለምታደርገው ጉዞ አህጉራዊ ሰላምና ደህንነቷ የተጠበቀ እንዲሆን ከማስቻል አንጻር ያለው አበርክቶ እጅጉን የላቀ ነው::
በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ እንደ ተቋም በዚህ መልኩ ራሱን አብቅቶና አተልቆ፣ ወንድም አፍሪካውያን በዚሁ ልክ ከፍ ብለው ለሀገራቸውም፣ ለአህጉራቸውም የሚሆን አቅም እንዲፈጥሩ እያደረገ ላለው አርዓያነት ያለው ተግባር ሊወደስም፣ ሊታወስም ይገባዋል::
በተመሳሳይ እንደ ትናንቶቹ የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ መስራቾቹ ሁሉ፤ ዛሬም የእነዚያ ልጆች የሆኑት መሪዎች ይሄ ተቋም የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ሌላ ማዕከል ሆኖ እንዲገለጥ እያደረጉ ላለው ጉልህ የመሪነት ሥራም እንዲሁ ሊወደሱም፤ ሊታወሱም የተገባ ነው!
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም