የከተማዋን ፈጣን እድገት ታሳቢ አድርጎ እየተዘጋጀ ያለው አዲስ መዋቅራዊ ፕላን

ከተማዋ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ በሚወስደው ዋና ጎዳና ላይ መገኘቷ፣ የአየር ፀባይዋ፣ የመሬት አቀማመጧና የመሳሰሉት ምቹ ሁኔታዎቿ ለኢንዱስትሪ፣ ለአገልግሎት ዘርፍና ለመሳሰሉት የኢንቨስትመንት ሥራዎች፣ ለመኖሪያነት ምቹ እንድትሆን እንዳደረጓት ይገለጻል።

በከተማዋ ለኢንቨስትመንት፣ ለመኖሪያ ቤትና ለመሳሰሉት የሚፈለገው የመሬት መጠን በየጊዜው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። የከተማዋን ደረጃና እድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ማካሄድ እድገቱ የግድ እያለ ነው። ይህ ከተማዋ በእጅጉ ተፈላጊ እየሆነች የመጣችበት ሁኔታ የከተማዋን አስተዳደር ስለከተማዋ ቀጣይ ሁኔታ ሰፋ አድርጎ እንዲመለከት አድርጎታል።

ይህች የአማራ ክልሏ የደብረ ብርሃን ከተማ በፍጥነት እያደገች መምጣቷን ነው ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት የሚገልጹት። በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት የሚመልስ መዋቅራዊ ፕላን እያዘጋጀች መሆኑንም ተናግረዋል። ይህን ሁኔታም አብነቶችን በመጥቀስ ሲያብራሩ፤ ባለፉት አምስት ዓመታትም ከ550 በላይ በማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሁም ከ220 በላይ በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ የገቡባት ከተማ መሆኗን ተናግረዋል። ይህም በከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ለውጥ እየታየ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችልም አመልክተዋል።

በ2007 ዓ.ም ተዘጋጅቶና በ2008 ዓ.ም ጽድቆ ሥራ ላይ የዋለው መዋቅራዊ ፕላን ለ10 ዓመት ያገለግላል ተብሎ የታቀደ እንደነበር አስታውሰዋል። በመዋቅራዊ ፕላኑ ለማከናወን የታቀደውን በሦስት ዓመት ገደማ መጠናቀቁን ገልጸው፤ ይህም በከተማዋ ያልተጠበቀ እድገት ለመታየቱ አመላካች ነውም ብለዋል።

ቀደም ሲል የቆዳ ስፋቷ አምስት ሺህ ሄክታር እንደነበር ተቀዳሚ ከንቲባው ያስታውሳሉ። ይህን የቆዳ ስፋት በአሁኑ ወቅት እየተዘጋጀ ባለው የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ወደ 124 ሺህ ሄክታር ለማሳደግ እየተሠራ ነው ሲሉ ይጠቁማሉ። መዋቅራዊ ፕላኑ ሁሉንም የከተማዋን ፍላጎት ያካተተ እንዲሆን ተደርጎ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።

ተቀዳሚ ከንቲባው እንዳሉት፤ መዋቅራዊ ፕላኑ እውን ሲሆን ለመኖሪያ ቤት የሚያስፈልግ ቦታ እጥረት ሊያጋጥም አይችልም፤ በፕላኑ ምላሽ ያገኛል። ለኢንዱስትሪ የሚሆን ቦታ ችግር እንዳያጋጥም ለማድረግም አዲሱ መዋቅራዊ ፕላን በበቂ ሁኔታ እየተዘጋጀ ነው።

ለወጣቶች በቂ መዝናኛ እንዲሁም የአረንጓዴ ስፍራ እንዲኖራት እንደሚደረግም ጠቅሰው፣ ለሌሎች እንደ ጤና፣ ትምህርትና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች የሚውል መሬት አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ማስተር ፕላኑ በበቂ ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑንም አመላክተዋል።

አቶ በድሉ በከተማዋ የስማርቲ ሲቲ ግንባታን ለመተግበር እንደሚሠራም ጠቁመዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ የስማርት ሲቲ ሲባል በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶች ፈጣን እንዲሆኑ እና በዲጂታል አሠራር የተደገፉ እንዲሆን የማድረግ ሥራ የሚሠራበት አሠራር ነው፤ ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው በሁሉም ደረጃ ተስማሚ ማድረግ ነው፤ መዋቅራዊ እቅዱም ይሄንን በሚያሟላ እና ማስተናገድ በሚችል መልኩ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል። መዋቅራዊ ፕላኑን ስማርት ሲቲን ባሟላ መልኩ ለመሥራት የመጀመሪያው ሥራ የፕላን ዝግጅት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህም የመዋቅራዊ ፕላን ዝግጅቱ እየተሠራ ነው ብለዋል።

እሳቸው እንዳመለከቱት፤ አሁን ባለው ደረጃ የደብረብርሃን ከተማን ለ20 እና ለ30 ዓመት ሊያገለግል የሚችል የመዋቅራዊ ፕላን መዘጋጀት አለበት። ከዚህ በፊት የተዘጋጁት ፕላኖች ከከተማዋ ዕድገት ጋር ሊመጣጠኑ ያልቻሉ በመሆናቸው የከተማዋን ፈጣን እድገት ሊያስቀጥሉ አልቻሉም፤ ይህንንም በመመልከት የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ኃላፊነቱን ወስዶ በጋራ የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን እየተዘጋጀ ይገኛል።

ከመዋቅራዊ ፕላኑ ፋይዳ አንዱ የኢንዱስትሪ ቦታዎች በበቂ ደረጃ እንዲኖሩ ያግዛል፤ በከተማዋ የሚስተዋለውን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረትም ለማገዝ ይጠቅማል።

በየዓመቱ 12 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ለቤት አቅርቦት የሚሆን ቦታ እየተሰጠ መሆኑንም ተቀዳሚ ከንቲባው ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም ደብረብርሃን ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለባት ከተማ እየሆነች መምጣቷንና የቤት ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። ለቤት ፍላጎቱ ምላሽ ሊሆን የሚችል በቂ የቦታ አቅርቦት መኖር እንዳለበት በመዋቅሩ ታይቶ እየተሠራ ነው ሲሉ አመልክተዋል። ሌሎች የወጣቶች መዝናኛዎችም እነዚህን ባካተተ መልኩ መዋቅራዊ ፕላን መዘጋጀት አለበት ተብሎ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱንም ተናግረዋል።

‹‹መዋቅራዊ ፕላኑን በተመለከተ አሁን ባለው ደረጃ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሥራዎች ተሠርተዋል። አስፈላጊው መረጃ ተሰበስቧል፤ የቀረው የመጀመሪያውን ፕላን ማዘጋጀት ወይም የመጀመሪያውን ፕሮፖዛል የእቅድ ዝግጅት ሥራ መሥራት ነው›› ብለዋል። እቅዱ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው በኅብረተሰቡ አማካይነት መሆኑን ጠቅሰው፣ የሕዝብ እንዲሆን ተደርጎ እንደሚዘጋጅ አመልክተዋል። ኅብረተሰቡ በእቅዱ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ በየጊዜው ሰፊ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕላን ዝግጅት ንድፈ ሀሳቡ እና በተግባርም ልምዱ ያላቸው ሙያተኞችን በማካተት እቅዱ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ የውጭ ልምዶችንም በመጠየቅ እየተሠራ ነው ብለዋል። በዚህ መልኩ ከተሠራ የተዋጣለት ፕላን ይሆናል የሚል እምነት አለ ብለዋል።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ለከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን ብቻ አይደለም የሚዘጋጅላት። ከተማዋ ስማርቲ ሲቲ እንድትሆንም በጽኑ ይፈለጋል። ከስማርት ሲቲ ግንባታ ጋር የሚጣጣም መዋቅራዊ ፕላን ሊኖራት ይገባል።

ሁሉም የከተማዋ አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ መደረግ ይኖርባቸዋል። ዘመኑ የዲጂታላይዜሸን ዘመን እስከሆነ ድረስ ለደብረ ብርሃን ከተማም እየተዘጋጀ የሚገኘው መዋቅራዊ ፕላን አንድ ፈጣን አገልግሎት ለሚሰጥ፣ ፅዳት እና ውበት እንደሚፈልግ ፅዱ እና ተመራጭ ከተማ፤ ኢንዱስትሪ ለሚፈልግ ተገልጋይ ለኢንዱስትሪ አልሚዎች የምትመች ከተማ መፍጠርን በማገናዘብ መዋቅራዊ ፕላኑ ስማርት ሲቲ ከተማን መሠረት ያደረገ እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ ውይይት እየተደረገበት ነው ሲሉ አብራርተዋል።

እስካሁን ባለው ሂደትም የደብረብርሃን ከተማን የሚመጥን የፕላን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ እድገቱም በዚያው ልክ እየፈጠነ መሆኑን አመላክተዋል። በተያዘው ዓመት በከተማዋ የሠላም ችግሮች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ተግዳሮት ቢኖርም ባለፉት ጥቂት ወራት በርካታ የመሠረተ ልማት ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

መዋቅራዊ ፕላኑ እስኪደርስ ድረስ በሚል የመሬት አቅርቦት ሥራው እንዳልቆመ ጠቅሰው፣ በፕላን ውስጥ እስኪካተት ድረስ በማስፋፊያነት ወደ ሁለት ሺህ ሃምሳ ሄከታር መሬት በዚህ ሩብ ዓመት ለባለሀብቶች እና ለአልሚዎች እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ከ29 ለሚበልጡ ፕሮጀክቶች መሬት ቀርቧል። ወደ 60 ለሚደርሱ ሌሎች ፕሮጀክቶች ደግሞ የመሬት አቅርቦት ሊሠራላቸው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል። አሁን ባለው ደረጃ ሁለት ሺህ ሄክታር ያህል መሬት እየተዘጋጀ ነው ይላሉ።

‹‹ይህም የሚያመለክተው የደብረብርሃን ከተማ እድገት እየተፋጠነ መሆኑን ነው›› ያሉት ተቀዳሚ ከንቲባው፣ ለዚያ የሚመጥን መሪ እና መዋቅራዊ ፕላን ያስፈልጋል በሚል በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማን ስማርት ሲቲ የማድረጉ ሥራና የመዋቅራዊ ፕላኑ ጥናት ከሁለት ዓመት በፊት መጀመሩን የገለጹት ተቀዳሚ ከንቲባው፣ የመጀመሪያው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃ መሰብሰቡን አስታውቀዋል። ለዚህም መሬት ላይ የሚዘጋጀው ፕላን ወይም ቤዝ ማፕ ሥራ መጠናቀቁን አመላክተዋል። የመሬት አጠቃቀሙ እየተሠራበት መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሠረተ ልማት ረገድም ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ በድሉ ‹‹በዋነኝነት በፕላን ሕግ ከ50 በመቶ በላይ ሊወስድ የሚችለው ቤዝማፕ ወይም መሬት ላይ የሚዘጋጀው የፕላን ሂደት ነው፤ የዚህና የካርታው ሥራም በከፊል እየተጠናቀቀ ይገኛል፤ በፕላን ደረጃ በ18 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅታዊ ሁኔታዎች ለመጓተት ቢዳረግም፣ በ2016 ተጠናቅቆ በ2017 ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገባ ይደረጋል›› ብለዋል።

ባለፉት ወራት በከተማዋ የሰላም እጦት እያለም ለአራት ሺ 500 ያህል ዜጎች ቦታ መዘጋጀቱን ጠቁመው፣ በሩብ ዓመቱ ማኅበራት ካሣ ወደሚከፍሉበት ደረጃ መደረሱንም ጠቁመዋል። የመሬት ዝግጅቱ ተጠናቆ በሚቀጥሉት ሳምንታት ቦታ ሊሰጥ እንደሚችልም ተናግረዋል።

ኢንቨስተሮች ወደ ከተማዋ እንዲመጡና መጉላላት እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ምቹ አገልግሎቶችን በማቅረብና በቀረቡ ፕሮጀክቶች ላይ የመወሰን ተግባር ይከናወናል። የሰላም ችግር ሲያጋጥም ኢንዱስትሪዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት አልታየም፤ ይህም የሆነው ሕዝቡ ባለቤት ሆኖ በመጠበቁ ነው። ይህ ሁሉ ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እያደረጋት እንደሚገኝም አመላከተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የመሬት አቅርቦቶችን በማመቻቸት ኢንዱስትሪዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር በጋራ ለመፍታት የሚያግዙ ፎረሞች እንደሚካሄዱ ተቀዳሚ ከንቲባው ጠቅሰዋል። ለአብነትም የመብራትና የውሃ እጥረት ሲያጋጥም፣ እንደ መንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶች ችግር ሲኖር ከተማ አስተዳደሩ ከክልሉ ጋር በመሆን ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

በ2015 ዓ.ም የክልሉ መንግሥት ከ72 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መድቦ የመንገድ መሠረተ ልማት ለማሟላት ጥረት ማድረጉን ተቀዳሚ ከንቲባው አስታውቀው፣ በተመሳሳይም ከብድር አቅርቦት ጋር በተያያዘ ባንክና እና የመሳሰሉት ተቋማት አካባቢ ያሉ ችግሮችን በመፍታት በኩልም ውጤታማ ተግባሮች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በየሩብ ዓመቱ ባሉት ፎረሞች ተቀራርቦ የመነጋገር እና ችግሮችን የመፍታት ሁኔታዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ይህም ለባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ተመራጭ ሆኖ መገኘቱን ጠቅሰዋል።

ተቀዳሚ ከንቲባው እንዳሉት፤ መሬት ከተረከቡ ባለሀብቶች ወደ ማምረት የገቡት 40 ያህል ሲሆኑ፤ 114 የሚሆኑት ግንባታቸውን አጠናቀው ማሽነሪ እየጠበቁ ይገኛሉ። 400 ያህል ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ በሙሉ አቅማቸው ወደማምረት ሲገቡ በአካባቢው ያለውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ ያስችላሉ።

ደብረብርሃን ከተማ የአጭር ጊዜ የኢንዱስትሪ ታሪክ እንዳላት ተናግረው፣ ኢንዱስትሪው ብዙ ሰዎች በልተው የሚያድሩበት የሥራ እድል እየፈጠረ ነው ብለዋል። ከግንባታ ጀምሮ በቀን ሠራተኛነት፣ በሙያተኛነት በመቀጠር እና በሌሎች የተለያዩ ተግባሮች በመሳተፍ ረገድ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያገኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ወደ ከተማዋ እየመጡ ያሉት ኢንዱስትሪዎች አንዱ እና ዋነኛው ሥራቸው ለነዋሪዎቿ የሥራ እድል መፍጠር መሆኑን የገለጹት ተቀዳሚ ከንቲባው፣ በ2015 በጀት አመት ወደማምረት የገቡት ኢንቨስትመንቶች ከ25 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል። በ2016 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ከአንድ ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You