መቂ ባቱ – የአርሶ አደሩን ተስፋ ያለመለመው ኅብረት ሥራ ዩኒየን

አብዛኛው የኢትዮጵያ አርሶ አደር ምርቱን ወደገበያ አውጥቶ ፍትሀዊ በሆነ ዋጋ ለመሸጥና ከዚያም ተጠቃሚ ለመሆን ሲቸገር ይስተዋላል፡፡ በብዙ ልፋትና ድካም ያመረተው የደላላ ሲሳይ እየሆነ ይገኛል፡፡ የምርቱ የበለጠ ተጠቃሚዎች ህገወጥ ደላሎችና ደላሎች ብቻ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በመካከል የተፈጠረው ረጅም የደላላ ሰንሰለት አርሶ አደሩንና ተጠቃሚውን ከተጠቃሚነት እንዳወጣቸውም ሁሌም የሚገለጽ ሀቅ ነው።

ለዚህም ነው አምራቹ የድካሙን ፍሬ ማግኘት እንዲችልና ተጠቃሚ እንዲሆን ጤናማ የገበያ እድል መፍጠር ዋናው መፍትሔ እንደሆነም የሚታመነው። ይህንን ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ስትራቴጂዎች መካከል የህብረት ሥራ ዩኒየኖችን ማደራጀት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይገለፃል፡፡

ዩኒየኖቹ አርሶ አደሩ ያለበትን የገበያ ችግር በመቅረፍ ምርቱን ወደ ገበያ በማቅረብ፣ ግብአቶችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ፣ በአርሶ አደሩ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ገበያ በማቅረብ ሰፊ ሥራ እንደሚሰሩ ይታመናል፡፡ በዚህም ዩኒየኖቹ አርሶ አደሩ የልፋቱን ውጤት እንዲያገኝና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ፣ ሸማቹም ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ገበያን በማረጋጋት እንዲጨምር በማስቻል የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተቋቋሙ ይህን መሰል አደረጃጀቶች ለአርሶ አደሩና ለሸማቹ ተጠቃሚነቱ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ በመሰረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራት የተመሰረቱ ዩኒየኖች በተለይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ሰፋፊ ተግባሮች እያከናወኑ ናቸው፡፡ ዩኒዮኖቹ ለአርሶ አደሮች ግብአት በማቅረብም ለምርትና ምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ በማበርከት ይታወቃሉ፡፡ አንዳንድ ዩኒየኖች የአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎችን በመገንባት የአርሶ አደሩ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ በማድረግ አርሶ አደሮች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ ናቸው፡፡

በሀገሪቱ ከሚገኙ ዩኒየኖች መካከልም መቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾ ህብረት ሥራ ዩኒየን አንዱ ነው፡፡ የዛሬ የስኬት አምዳችን ርእሰ ጉዳይ የሆነው ዩኒየኑ፣ የአርሶ አደሩን የገበያ ችግር በመቅረፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል። መቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን ጥራት ያላቸው ምርቶቹን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ (ለስካይ ላይት ሆቴል፣ ለጉዞ መስተንግዶ) እና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረጉም ይታወቃል፡፡

አቶ አሸናፊ ሮባ የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ህብረት ስራ ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ዩኒየኑ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶቹ ይታወቃል፡፡ 12 ማህበራትን እንዲሁም 527 አባላትን ይዞ የተመሰረተው ሲሆን፣ 21 ዓመታትን እንዳስቆጠረም ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት 153 አባል ማህበራት አሉት፤ አጠቃላይ የአባላቱ ብዛትም ስምንት ሺ 410 ደርሷል፡፡ መነሻውን ግማሽ ሚሊዮን ብር ያደረገው ዩኒየኑ በአሁኑ ወቅት 91 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ካፒታል መፍጠር ችሏል፡፡

አቶ አሸናፊ እንደሚናገሩት፤ አባላቱ ምርቱን በቀጥታ ለዩኒየኑ ያቀርባሉ፤ ይህም የገበያ ትስስር በቀላሉ እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል፡፡ ዩኒየኑም ምርቶቹን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ሸማቾችና ድርጅቶች እያቀረበ ይገኛል፡፡

ዩኒየኑ በተለይም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በፈጠረው የገበያ ትስስር ካለፉት አስር ዓመታት ጀምሮ የሚያመርታቸውን የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከአየር መንገድ በተጨማሪም ምርቶቹን ለሆቴሎች፣ ለዩኒቨርሲቲዎች እና በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሱቆቹ አማካኝነትም ለሸማቹ ማህበረሰብ ያደርሳል፡፡

አቶ አሸናፊ መቂ እና አዲስ አበባ ከተማ ቃሊቲ አካባቢ የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ መሸጫ ሱቆች እንዳሉት ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ ሱቆች በተጨማሪም በየሳምንቱ በእሁድ ገበያና በተለያዩ ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ላይ ይሳተፋል፡፡

ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚቀርበው ምርት በተወሰነ መልኩ እሴት ተጨምሮ እንደሆነ ነው የሚያስረዱት ምክትል ሥራ አስከያጁ፤ የዩኒየኑ አባላት በቀዳሚነት የሚያመርቱት ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ቃሪያ፣ ፓፓያ፣ ዝኩኒ፣ ኩከምበር፣ ወተርሚሎን (ሀባብ) መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እሴት ሲጨመር ሽንኩርቱ ተልጦና ታጥቦ የሚቀርብ ሲሆን፤ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ፓፓያና ሌሎቹ አትክልትና ፍራፍሬዎች ደግሞ ታጥበውና ታሽገው ይቀርባሉ፡፡ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶቹ የአየር መንገዱ ንብረት ለሆነው ስካይ ላይት ሆቴል ሲቀርብ ለሌሎች ድርጅቶች ደግሞ አትክልትና ፍራፍሬዎቹ በጥሬው ይደርሳሉ፡፡

ዩኒየኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ከፈጠረው የገበያ ትስስር በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋርም እንዲሁ የገበያ ትስስር በመፍጠር ለተማሪዎች ካፌ አገልግሎት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በቋሚነት ያቀርባል፡፡ ከዩኒቨርሲቲዎቹ መካከልም አርሲ ዩኒቨርሲቲ፣ አዳማ ዩኒቨርሲቲና አምቦ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል፡፡

እንደ አቶ አሸናፊ ገለፃ፤ ዩኒየኑ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ ሸማቾችም ምርቶቹን በስፋት ለመድረስ እሁድ ገበያን ተመራጭ ማድረጉን ይገልፃሉ፡፡ በተጨማሪም ሳርቤት አደባባይ፣ ካርል አደባባይ፣ ገርጂ ክፍለ ከተማ እንዲሁም በኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ግቢ ውስጥ ምርቶቹን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ እንደሚገልፁት፤ በዩኒየኑ አባላት በሆኑ አርሶ አደሮች የማይመረቱ አምስት አይነት ምርቶችን በራሱ ማሳ ወስዶ እያመረተ ይገኛል፡፡ ለአብነትም የቻይና ጎመን፣ ብሮኮሊ፣ ፓውሮሊፍና ሌሎች አትክልቶችን አምርቶ ያቀርባል፡፡ በዚህም የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ዩኒየኑ ከሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ ምርቶቹን ወደ ውጭ ገበያ የመላክ ጅማሮ አድርጓል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ በአትክልት ዘርፍ ወደ ሳውዲአረቢያ መድረስ መቻሉን ይናገራሉ፡፡ ዩኒየኑ ምርቱን የሚልከው በቀጥታ ሳይሆን ግሪን ዌይ ከተባለ ኩባንያ ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ምርቶቹን ከዩኒየኑ ተቀብሎ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ በማቀዝቀዣ አቆይቶ የሚልከው ግሪን ዌይ ከዩኒየኑ ጋር በጋራ የሚሰራ በመሆኑ ቢተርጋርድና ኦክራ የተባሉ የአትክልት ዘሮችን ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡

ዩኒየኑ ከግሪን ዌይ ኩባንያ ጋር ትስስር በመፍጠር በኮንትራት ፋርሚንግ ስምምነት አድርጎ ያመርታል፡፡ በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው የአትክልት ዘሩን ያመጣል፤ በቅድሚያ ዋጋውን በመነጋገር ዩኒየኑ አትክልቱን አምርቶ ያቀርባል፡፡ ኩባንያውም ምርቱን ተረክቦ ለውጭ ገበያ እንደሚልክ ያስረዱት አቶ አሸናፊ፤ ከዚህ ቀደምም ትስስር በመፍጠር የፎሶሊያ ምርትን ወደ እንግሊዝ ሀገር ሲልክ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ዩኒየኑ በራሱ አቅም ምርቶቹን በቀጥታ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሸናፊ፤ ለዚህም አዳዲስ የገበያ መዳረሻ ሀገራትን እያፈላለገ እንደሆነ ይገልፃሉ። በተለይም ጎረቤት ሀገር በሆነችው ጅቡቲ ትልቅ ሱፐርማርኬት ካለው ካምፓኒ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመሥራት ዩኒየኑ ምርቶቹን በቀጥታ እንደሚልክ አመልክተው፣ ከሌሎች ጉረቤት ሀገራት ጋርም ግንኙነት በመፍጠር ገበያውን ሰብሮ ለመግባትና የውጭ ምንዛሪ ግኝት በማሳደግ አባላቱም የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

መቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ህብረት ሥራ ዩኒየን የሽንኩርት ዘር በማባዛትም እንደሚታወቅ የገለጹት አቶ አሸናፊ፤ ከመልካሳ የጥናት ማዕከል ጋር በመተባበር ቦምቤ እና ናፊስ የተባሉ የሽንኩርት ዘሮችን እያባዛ ይገኛል ይላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ስምንት ኩንታል የሚደርስ ዘር በማባዛት ለአባላቱ እያከፋፈለ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ ለተፈጠረው የሽንኩርት ምርት እጥረት መፍትሔ መሆን እንዲቻል ከአርሶ አደሮች ጋራ ትስስር በመፍጠር በኮንትራት ፋርሚንግ እያመረተ ይገኛል፡፡

የዩኒየኑ አትክልትና ፍራፍሬ እያለማ የሚገኘው የአርሶ አደሩ ንብረት በሆነ አጠቃላይ ስድስት ሺ ሄክታር መሬት ላይ መሆኑን ገልጸው፤ በተጨማሪም ዩኒየኑ ከመንግሥት ያገኘው አምስት ሄክታር መሬት ስለመኖሩ አቶ አሸናፊ ይናገራሉ። በዚህ ቦታ ላይ የግብርና ሥራዎችን ሠርቶ ለአርሶ አደሮቹ ያሳያል፡፡

አርሶ አደሩ የሚያመርታቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ በአይነት፣ በጥራት እያደጉ ቢመጡም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ዩኒየኑ የሚያመርተው የምርት መጠን በተለያዩ ምክንያቶች እየቀነሰ መሆኑን አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል፤ ዩኒየኑ ከዚህ ቀደም በዓመት አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል ያመርት እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅትም ሰባት መቶ አስራ ስምንት ሺ ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ በዩኒየኑ አባላት ለማምረት አቅዶ እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ዩኒየኑ ይህንኑ ምርት ለገበያ በማቅረብ ረገድ የሚሠራ ሲሆን፤ በአባላቱ የሚመረተውን 30 በመቶ ያህሉን ምርት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለሱቆች እንዲሁም ባዛርና ኤግዚቢሽኖች ላይ አከፋፍሎ ያቀርባል፡፡

የዩኒየኑ ዋና ሥራ አትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያተኮረ ቢሆንም በተጓዳኝ የበቆሎ፣ የስንዴና የቦሎቄ ዘር አባዝቶ ያቀርባል፡፡ እነዚህን ዘሮችም ለመላው ኦሮሚያ ያቀርባል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ አርሶ አደሩ ሁልጊዜ አትክልትና ፍራፍሬ ብቻ እያመረተ መቆየት እንደሌለበትና መቀያየር እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም አርሶ አደሩ አልፎ አልፎ በቆሎ፣ ስንዴና ሌሎች ምርቶችን እንዲያመርት ምክር በመስጠት እንዲሁም ዘር አባዝቶ በማቅረብ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የሥራ ዕድልን መፍጠርን አስመልክቶ አቶ አሸናፊ እንደሚገልፁት፤ ዩኒየኑ በኮንትራት ለ18 ዜጎች የስራ ዕድል አመቻችቷል። 91 ለሚደርሱ ዜጎች ደግሞ ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በማሳ ላይ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች እንደመኖራቸው በጊዜያዊነትም እንዲሁ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በጊዜያዊነት ምርት በሚሰበሰብበት ወቅት በአንድ ጊዜ ብቻ 500 የሚደርስ የሰው ኃይል የሚፈለግበት የግብርና ሥራ አለ፡፡

ሌላው እሴት ጨምሮ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ስለመኖራቸው ያነሱት አቶ አሸናፊ፤ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚቀርበው አትክልትና ፍራፍሬ የሚዘጋጅበት የሥራ ክፍል ውስጥ ሽንኩርት ተልጦና ታጥቦ ይዘጋጃል፡፡ ጎመን መጠኑን በማስተካከልና በማጠብ ሌሎች ምርቶችንም እንዲሁ በማጠብና በማሸግ ሥራ ላይ ለተሰማሩ 90 ሴቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ እነዚህ እናቶች ያዘጋጁትን አትክልትና ፍራፍሬም ወደ አየር መንገድ ለሚጭኑና ለሚያወርዱ 10 ወጣቶችም እንዲሁ የሥራ ዕድል ተፈጥሮ በድምሩ ከ600 በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻለ ተናግረዋል፡፡

ዩኒየኑ የአባላቶቹን ምርት መሰብሰብ እና ማምረት ብቻ በቂ እንዳልሆነ በማመን ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ መቀየር መግባት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነም አቶ አሸናፊ ጠቅሰዋል፡፡ በቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ ባገኘው ቦታ ላይ የቲማቲም ድልህ (ካቻፕ) ለማምረት በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፤ ለዚህም አስፈላጊውን ማሽን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በሂደት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

እንደ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ ማሽኑ በቅርቡ ተተክሎ ወደ ምርት የሚገባ ሲሆን በሰዓት 50 ኩንታል ቲማቲም የመጭመቅ አቅም ይኖረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ፋብሪካው 70 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፡፡ የቲማቲም ድልሁም ለሀገር ውስጥ ገበያ ተደራሽ በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለሚገኙ ሱፐርማርኬቶች፣ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለተለያዩ ተቋማት ይቀርባል፡፡

ለዚህ ሥራ ተግባራዊነትም የቲማቲም ምርት በከፍተኛ መጠንና በጥራት መመረት ይኖርበታል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ ለዚህም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት 12 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ግሪን ሀውስ እያስገነባ እንደሆነና ግንባታውም 80 በመቶ አፈፃፀም ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ዩኒየኑ ለማህበረሰቡ ድጋፍ ያደርጋል ያሉት አቶ አሸናፊ፤ በሚሰራባቸው ስድስት ወረዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ትምህርት ቤት በመገንባት፤ መንገድ በመስራት፤ አቅመ ደካማ ለሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ለአብነትም በሁለት ወረዳዎች አራት መኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከቡን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ አሸናፊ ገልፀዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You