ሰዎች ከራሳቸው ስህተት የሚማሩ ከሆነ ልምድ ይባላል። ሰዎች ከሰዎች ስህተታቸውን የሚማሩ ከሆነ ደግሞ ጥበብ ነው። ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ስህተት መማር የሚችሉት ደግሞ በእድሜ፣ በልምድና በእውቀት ከሚበልጧቸው ሌሎች ሰዎችና ከመፃህፍት ነው። በርግጥ ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ አቋራጭ ነገር እንወዳለን።
አስር ዓመት የሚፈጅብንን ነገር በሁለትና በሶስት ዓመት ብናሳካው ደስ ይለናል። በዚህ ዓለም ላይ በጣም ፈጣንና አቋራጭ መንገድ የሚገኘው ግን በመፃሕፍት ውስጥ ነው። መተግበር ከተቻለ የእውቀት ሀገሩ መፃሕፍት ውስጥ ነው ያለው። እስቲ ተፅእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉና በሕይወታችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ ስለሚችሉ ሰባት መፃሕፍት እናውራ።
1ኛ.«ሊሚትለስ›› በጂም ኪዊክ
ይህ መጽሐፍ ‹‹የአእምሯችን አቅም ገደብ የለሽ ነው። ነገር ግን ይህን ኃይል እንዳንጠቀምበት ያደረጉንና ወደኋላ የጎተቱን የተለያዩ አመለካከቶች፣ እምነቶች፣ ፀባዮችና ልማዶች ናቸው›› ይለናል። እነዚህን መቀየር ስንችል ሕይወታችን በበዙ መልኩ ይቀየራል። ስለዚህ መጀመሪያ አመካከታችንን መቀየር አለብን። አመለካከቱን ያልቀየረ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ነገር ይጎድሉታል።
አመለካከትህን ቀይረህ ዓላማ ቢስ ከሆንክ ቆመህ ትቀራለህ። የሰዎች ለውጥ ያስቀናሃል። ብዙ ርቀት የተጓዙ ሰዎችን ታይና ‹‹እኔ ምንድን ነው የጎደለኝ?›› ትላለህ። ነገር ግን የሚያነቃና የሚያባንን ዓላማ፣ ምክንያትና ህልም ከሌለህ ቆመህ ትቀራለህ። ወይም መነቃቃት ያስፈልግሃል። አመከካከት ለውጥ ካለህና አእምሮህ ቢዘጋጅ፣ ዓላማውና መነሳሳቱና መነቃቃቱ ቢኖርህ እንዴት እንደምታሳካው፣ በሕይወት ጎዳናህ ላይ ሮጠህ የምትፈልገው ጋር እንደምትደርስ ካላወክ ግን በቃ ከንቱና ተንሳፋፊ ነው የምትሆነው። ያ ማለት ዘዴውን ማወቅ አለብህ። በአጭሩ መፅሐፉ ምን እደሚቀይርህ፣ ለምን እንደምትቀየርና እንዴት እንደምትቀየር የምታውቅበት መፅሐፍ ነው።
2ኛ.«ዘ ሚሊየነር ፋስትሌን»በዲማርኮ
ይህ መፅሐፍ ርእሱ የሆነ የሚያጓጓና ማርኬቲንግ የበዛበት ይመስላል። የእውነትም መፅሐፉ የሚሊየርነትን ፈጣን መንገድ የሚያሳይ ነው። በተለይ ተግባራዊ ከተደረገ ሕይወትን እስከመጨረሻው ይቀይራል። ለመሆኑ በምትሠሩት ሥራ ደስተኛ ናችሁ?፣ በምታገኙት ገቢስ ደስተኛ ናችሁ? ከሁለት አንዱ ጥያቄዎች መልሳችሁ አዎ! ከሆነ በጣም ተገቢ ነገር ነው።
ለምሳሌ በምተሠሩት ሥራ ደስተኛ ሆናችሁ ገቢያችሁ ትንሽ ቢሆን ብዙ ችግር የለውም። ምክንያቱም ነገ ምትሠሩትን ሥራ ይበልጥ እያወቃችሁት ስትሄዱ፣ እድሎችን መጠቀም ስትጀምሩና ራሳችሁን ስታሳድጉ ገቢ መምጣቱ አይቀርም። ወይም ደግሞ የምትሠሩትን ሥራ ላትወዱት ትችላላችሁ ነገር ግን ገቢያችሁ ደስተኛ ካደረጋችሁ ነገ የገንዘብ ነፃነት ላይ ደርሳችሁ የምትፈልጉትንና ምትወዱትን ሥራ ልትሰሩ ትችላላችሁ።
ከሁለት አንዱ መልሳችሁ አዎ! ከሆነ ጥሩ መንገድ ላይ ናችሁ። ነገር ግን መልሳችሁ ከሁለት አንዱ አዎ! ካልሆነ ማለትም በገቢያችሁም በሥራችሁም ደስተኛ ካልሆናችሁ በጣም ከባድ መንገድ ላይ ናችሁ። አንዱን መቀየር አለባችሁ። ይህም መፅሐፍ ይህንን ነው የሚያማክረው።
እንደውም ደራሲው ሶስት የሀብት መንገዶች እንዳሉ ይጠቅሳል። እነዚህም አንደኛው የእግረኛ መንገድ ሲሆን በዚህ መንገድ የሚጓዙ ሰዎች ከወር ወር ገንዘብ አይበቃቸውም። እንደውም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው። ይሠራሉ፣ ይጥራሉ፣ ይደክማሉ ተቀማጭ ገንዘብ ግን የላቸውም። የሆነ ሰአት ከባድ ችግር ቢገጥማቸው፣ ቢታመሙና አደጋ ቢደርስባቸው ኑሯቸውን መግፋት የሚያስችል አቅም አልገነቡም።
ሁለተኛዎቹ የዝግታ መንገድ ላይ የሚጓዙ ናቸው። በዚህ መንገድ ላይ ብዙ ሰዎች ናቸው እየተጋፉ የሚጓዙት። እነዚህ ሰዎች እድሜ ልካቸውን ይጥራሉ፤ ይለፋሉ። ለፍተው ጥረው ግን የሆነ የሀብት ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። እድሜያቸው ስልሳ አምስትና ሰባ ሲደርስ ሀብታም ይሆናሉ። ነገር ግን ወጣትነታቸውንና ትልቁን ወርቃማ ጊዜያቸውን በሥራ ሸጠውታል። ደክመዋል። ሲደክሙ ደግሞ በስተርጅና መዝናናት አይችሉም። የሠሩትን መብላት አይችሉም።
ሶስተኛዎቹ በፈጣን መንገድ የሚጓዙ ናቸው። በዚህ መንገድ በጣም ጥቂት ሰዎች ናቸው የሚጓዙት። ግፊያ የሌለበትና ፀጥ ረጭ ያለ መንገድ ነው። አዋጩም መንገድ ነው። ይህን መንገድ የሚከተሉ ሰዎች የገንዘብ ነፃነት ለማግኘት የሚሠሩት ከሰባት አስከ አስር ዓመት ነው። ይህም በሃያ አምስት ዓመት ሥራ የጀመረ ወጣት በሰላሳ አምስት ዓመቱ የገንዘብና የጊዜ ነፃነት አለው ማለት ነው። ይህን ፈጣን የሕይወት መንገድ ለመከተል ግን ምን ማድረግ እንደሚገባ መፅሐፉ ዘርዝሮ ያስቀምጣል። የዛኑ ያህል ደግሞ በየትኛው መንገድ ላይ እንዳለን ራሳችንን እንድናይ ያስችለናል።
3ኛ. «ዘ ፎር አግሪመንት» በዶን ሚጉዌል
ከራሳችን ጋር የምናደርገው አዲስ ስምምነት ያስፈልገናል ይላል ይህ መፅሐፍ። እነዚህ ስምምነቶች በሕይወታችን ውስጥ ያለንን ደስታ ይቀይሩታል። አይታችሁ ከሆነ ሰዎች እኛን የሚያስተናግዱን ወይም ለእኛ ያላቸው ቦታ እኛ ለራሳችን ከምንሰጠው ቦታ ተነስተው ነው። ራሱን የሚንቅ ሰው ሌሎች ይንቁታል። ራሱን የሚያከብር ሰው ደግሞ ሌሎች ያከብሩታል።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት፣ በሥራችን፣ ከሰዎች ጋር ባለን ቅርርብ ውስጥ ደስተኛ ያልሆንባቸው ግንኙነቶች ይኖራሉ። እንደማንችል፣ አርፈን መቀመጥ እንዳለብን፣ መለወጥ እንደማንችል፣ በብዙ ነገር አእምሯችንን የሚጎዱ ሰዎች ይኖራሉ። ነገር ግን እንዴት ነው ከነዚህ ሰዎች ጋር መኖር የምንችለው? ልንቀይራቸውስ የምንችለው እንዴት ነው? የመፅሐፉም ትኩረት መጀመሪያ ራስህን እንድትቀይር ነው። በመቀጠል አንተ ስትቀየር ሰዎች ላንተ ያላቸው አመለካከት መቀየር ስለሚጀምር እነርሱም ይለወጣሉ ነው የመፅሐፉ ጭብጥ።
4ኛ.«ኢሴንሺያሊዝም» በግሬግ ሚኪየን
አንዳንዶቻችን መቀየርና ማስተካከል የምንፈልገው የሕይወት ክፍል ይኖራል። ሥራችን ላይ፣ ከቤተሰባችን ጋር ያለን ግንኙነት፣ ገንዘብ ወይም ገቢያችን ላይ፣ አካላዊ ቁመናችን፣ አእምሯችን ላይ፣ መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ…..ወዘተ መሥራት እንፈልግ ይሆናል። አንዱ ላይ በደምብ ሠርተን ረጅም ርቀት ተጉዘናል። አንዱ ላይ ደግሞ ምን አልባት ቆመን ቀርተናል። አንዱ ላይ በደምብ ነቃ ብለን እየሠራን ሊሆን ይችላል። ሌላው ላይ ደግሞ ፈዘን ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ገቢያችን ጥሩ ሆኖ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ደስተኛ አያደርገንም። ወይ ደግሞ በትዳርና በመንፈሳዊ ሕይወታችን ደስተኛ ላንሆን እንችላለን። ከዚህ አንፃር ይህ መፅሐፍ ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሄ ይሰጣል። ለሕይወታችን ጠቃሚ ነገሮችን ይጠቁማል፤ ያስተምራል። እንደውም ብዙ ነገር ላይ የሚሮጥ ሰው ከንቱ ነው የሚሆነው፤ የሚጠቅመውን የሚያውቅ ሰው ግን በጣም ሃይለኛ ሰው ነው ይላል መፅሐፉ።
5ኛ.«ዘ አቶሚክ ሃቢት» በጀምስ ክሊር
ህልምህን ወይም በአእምሮህ ያሰብከውን ነገር እውን የምታደርገው በተግባር ነው። አሁን ያለህበት ደረጃ ላይ ያደረሱህ ደጋግመህ ያደረካቸው ድርጊቶች ወይም ልማዶችህ ናቸው። ወደፊትም በምትፈልገው መንገድ እንድትቀየር የሚያደርጉህ ልማዶችህ ናቸው። ግን ጥሩ ልማዶችን እንዴት ትገነባለህ ነው ጥያቄው። ብዙዎቻችን መጀመር የምንፈልጋቸው ጥሩ ልማዶች ይኖራሉ። መፅሐፍ ማንበብ፣ ገንዘብ መቆጠብ፣ በጠዋት መነሳት፣ ስፖርት መሥራት፣ መንፈሳዊ መፅሐፍትን ማንበብ ወይም ልንቀይረው የምንፈልገው የሕይወታችን ክፍል አለ።
ከዚህ በፊት በሞቅታ ወይም ራሳችን ተነቃቅተን ስፖርት ጀምረን እናውቃለን። በጠዋት መነሳት ጀምረን እናውቃለን። መፅሐፍ ማንበብ ጀምረን እናውቃለን። ለምንድን ነው ይህን የማድረግ ልምዳችንን ምናቆመው? ይህንን ነው መፅሐፉ የሚመልሰው። እንደውም የመፅሐፉ ዋናው ትኩረት ትናንሽ የሚባሉ ልማዶችን በመጀመር ሕይወትን መቀየር እንደሚቻል ነው። ይህ ማለት በቀን አንድ ከመቶ ራስህን የምታሳድግ ከሆነ በዓመቱ መጨረሻ ላይ በ37 እጥፍ ትለወጣለህ ይላል መፅሐፉ።
ይህ ማለት በገቢ፣ ከሰዎች ጋር ባለህ ግንኙነት፣ በስፖርት፣ በአካላዊ ነገር፣ በመንፈሳዊ ሕይወትና በሌሎችም ሊሆን ይችላል። በተለይ እነዚህን ቀላል ልማዶች እንዴት ከሕይወታችን ጋር ማገናኘት እንደምንችል ሳይንሱን ይጠቁማል። ወደመሬት የምናወርድባቸውን ትናንሽ መንገዶች ያሳየናል።
6ኛ.«ዘ ኮድ ኦፍ ኤክስትራኦርዲነሪ ማይንድ» በቪሼን ላካሃኒ
ብዙዎቻችን ከሰዎች ወደኋላ ያስቀረን ምንድን ነው ብለን እንጠይቃለን። አንዳንዴ ‹‹አብረን ነው የተማርነው፣ አብሮኝ ነው ያደገው፣ አብረን ነው የሠራነው፣ ከኔ የተለየ ብዙ ችሎታ የለውም፣ እንደውም እኔ በእውቀት፣ በልምድና በተለያየ ነገር እበልጠዋለው። ግን በኑሮ ሁኔታ የተሻለ ነገር እንዴት እሱ ሊያገኝ ቻለ፤ እንዴት በለጠኝ?›› የምንላቸው ሰዎች አሉ።
ሌላውን ተዉት በብዙ ነገር በልጠናቸው ግን በሕይወታቸው ላይ በጣም ደስተኛ የሆኑ፤ እንደውም ከራሳቸው አልፈው እኛን ሊረዱ የቻሉ ሰዎች እናይና ‹‹እኔ በምንድን ነው ከእነሱ ያነስኩት›› እንላለን። ብዙ ጊዜ እኛን ያሳነሰን አቅም፣ ብቃት፣ ችሎታ ላይሆን ይችላል። ምን አልባት የጎደለን አመለካከት ሊሆን ይችላል። ወደኋላ የጎተተን እምነት ሊኖር ይችላል። ከልጅነታችን ጀምሮ ሲነገሩን የነበሩ ጎታች አስተሳሰቦች ይሆናሉ ሕይወታችን ላይ መሰናክል የሆኑ።
በሕወታችን አሁን መበጠስ የምንችላቸው ግን ስላመንን ብቻ መቀየር ያልቻልናቸው የሕይወት ዘርፎች ይኖራሉ። እኔ እኮ ሰው አይወደኝም፣ እኔ እኮ ገቢዬ ሊሻሻል አይችልም፣ እኔ እኮ … ብለን ራሳችንን የምንገልፅባቸው አመለካከቶች አሉ። እናም ይህ መፅሐፍ ከዜሮ ራስን መቀየር እንደሚቻልና በተለይ እንዴት ራሳችንን መሆን እንደምንችል ያስተምራል። ሁሉም ሰው ግር ብሎ ከሚሄድበት መንገድ ይልቅ በራሳችን መንገድ ስንሄድ የምንከፍለውን ዋጋ እንዴት አድርገን በአጭሩ እንደምናቀለው ያሳያል።
7ኛ. «ካል ፖይንት» በብሪያን ሬሲ
ብዙዎቻችን ምንድን ነው እንደፈለግን እንዳንለወጥ ያደረገን ነገር እያልን ራሳችንን እንጠይቃለን። እንጥራለን፣ እንሠራለን፣ እንፈልጋለን፣ ከእኛ የሚጠበቀውን ሁሉ እንደርጋለን ነገር ግን ለምንድን ነው ገቢያችን ያልተቀየረው እንላለን። የምንፈልገውን ለውጥ ያላመጣነው ለምንድን ነው እንላለን። ችግሩ ከችሎታችን፣ ሙያችን፣ ከራስ መተማመናችን ላይሆን ይችላል። ትኩረት ማድረግ ዋናው ችግር ሊሆን ይችላል።
ከመፅሐፉ ታሪክ ውስጥ አንደኛው እኛ 80 ከመቶ የምንለፋው ልፋት የሚያመጣው 20 ከመቶ ገቢ ነው ይላል። ነገር ግን 20 ከመቶ ወይም በትንሹ የምንለፋው ልፋት ግን 80 ከመቶ ገቢውን ወይም ትልቁን ገቢ ያመጣል። ስለዚህ ብልጥ ሰው ትልቁ ገቢ የሚመጣለት ላይ ብዙ ሰአት ያጠፋል፤ ብዙ ይለፋል። ሌሎቹን ትናንሽ ገቢ የሚያመጡለትን ግን ወይ ይተዋቸዋል አልያም ወደ ሌሎች ሰዎች ያስተላልፋቸዋል ነው የሚለው መፅሐፉ።
በጣም ብዙ ጥረት እያደረጋችሁ፣ እየለፋችሁ ነገር ግን በሕወታችሁ ለውጥ ከራቀ ምንአልባት ችግራችሁ ጠንክሮ የመሥራት ላይሆን ይችላል። የዲስፕሊን ችግር ላይኖርባችሁ ይችላል። ነገር ግን የትኛው ሥራ ላይ ትኩረት ብታደርጉ ለውጥ እንደምታመጡ አለማወቃችሁ ይሆናል። ምክንያቱም ሁለትና ሶስት ሥራ የሚሠሩ ሰዎች ታውቃላችሁ። ግን ገቢያቸው እንደተለመደው ነው። የተለየ አይደለም። አንድ ሥራ ሰርቶ ግን ያውም ቀለል አድርጎ ብዙ ሰአት ሳያጠፋ ሕይወቱን የሚቀይር ሰው አለ። ታዲያ ለምንድን ነው ይህ ሰው የተለየ ውጤት ያመጣው? ቅድሚያ የሚሰጠውን ጉዳይ ስለሚያውቅ ነው። ትኩረት ማለት እሱ ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም