ያልጠገነው ስብራት …

ያልተመቸ ልጅነት …

ዛሬ ላይ ሆና ልጅነቷን ስታስብ በዓይኗ ውሀ ይሞላል። ለእሷ ልጅነት ማለት መልከ ብዙ ነው። መከራን ቀምሳበታለች ፣ ችግርን አይታበታለች ። ዓለም ተሰማ ከእናቷ እቅፍ እንደወጣች ህይወት የተቀበለቻት በከፋ ድህነት ነበር። በጊዜው ወላጆቿ ለእሷ ፍላጎት የሚሞላ አቅም የላቸውም። ከእጅ ወደ አፍ በሆነው ኑሮ ቤተሰቡ የተገኘውን ተቃምሶ ሊያድር ግድ ሲለው ቆይቷል ።

ዓለም ለቤቱ አራተኛ ልጅ ነች። በሽመና ሙያ የሚያድሩት አባቷ እሷን ጨምሮ እህት ወንድሞቿን ለማሳደግ ብዙ አይተዋል ። ለእናቷ በዕለት የሚገኘውን ጥቂት ገቢ አብቃቅቶ ለጎጆ ማዋል ቀላል አልነበረም። ድህነትና ችግር በሚመላለስበት ቤት ህይወት ከባድና ፈታኝ ሆኖ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ትንሽዋ ዓለም ዕድሜዋ ከፍ ሲል እንደ እኩዮቿ ትምህርት ቤት ገባች። ጥቂት ቀናት መመላለስ ስትጀምር ግን እሷን ከሌሎች ማነጻጸሯ አልቀረም። ባልንጀሮቿ በጥሩ ጫማና ልብስ ይታያሉ። ደብተራቸው በቦርሳ ተሰንዶ ጸጉራቸው አምሮ ተሰርቷል። መለስ ብላ ራሷን አየች ። ጎስቋላው ልብሷ ከእነሱ የሚያቆማት አይደለም። ያለጫማ የሚራመዱ እግሮ ቿ መሰ ነጣጠቅ ጀም ረዋል ።

ዙሪያዋን ደጋግማ ቃኘችው ። ሁሉም በኑሯቸው ከእሷ በእጥፍ የሚበልጡ ናቸው። ጓደኛ መርጦ ለመያዝ ተሸማቀቀች። ውስጧ አዘነ። በዓይኖቿ ትኩስ ዕንባ ተመላለሰ። ዓለም ከባልንጀሮቿ በታች መሆኗን አውቃለች። እንዲያም ሆኖ ትምህርቷን አልተወችም። በጥንካሬ ፣በብርታት መማሯን ቀጠለች ። ዓመቱ መጋመስ ሲይዝ መቸገሯ አልቀረም። እስክሪብቶ ፣ እርሳስ ፣ ደብተሯ ማለቅ ጀመረ ።

እሷ እንደ ሌሎቹ ወላጆቿን ‹‹ይህን ግዙልኝ፣አሟሉልኝ›› ማለትን አትደፍርም ። ልሞክርው ብትል እንኳን ሰሚ ጆሮ የለም። ዓመቱን እንደምንም ጨርሳ ለቀጣዩ ጊዜ ተዘጋጀች። አሁንም ችግሮቿ እግር በእግር ተከተሏት። የደብተሯ ገጾች ፣ የእግሯ ላይ ጫማዎች አለቁ ።

ለተማሪዋ ዓለም ዓመታት በችግር ተሞሽረው አለፉ። አራተኛ ክፍልን አልፋ አምስተኛ ላይ ስትደርሰ የቤተሰቡ ችግር ከትናንቱ ባሰ ። ለጀመረችው ትምህርት ትኩረት የሚሰጠት ጠፋ ። ወላጆቿ ህይወት ቢከብዳቸው ሁሉን ትታ ከቤት እንድትቀር አስገደዷት። ምርጫ አልነበራትም። ትምህርቷን አቋርጣ ለፍላጎታቸው እጇን ሰጠች።

አፍላነትን በምርጫ …

አሁን ዓለም ቤት መዋል ከያዘች ሰነባብታለች። ጀምራ ያቆመችው ትምህርት ቢቆጫትም ስለራሷ እያሰበች ፣ እያቀደች ነው። ዛሬም ከድህነት ያልወጡት ወላጆቿ ልጆች ያሳድጋሉ ። አሁንም የቤታቸው ችግር እንዳለ ነው። የጓዳው ጎዶሎ የልጆች ፍላጎት አልሞላም። ይህን ስታይ ተስፋ ትቆርጥና ቆም ብላ ታስባለች። ውስጠቷ አርቆ ያልማል ።

የአፍላነት ዕድሜዋ ከወላጆቿ ሀሳብ ካራቃት ቆይቷል። ከዚህ በኋላ ስለራስዋ የምትወስነው ራሷ ብቻ ናት። ይህን እውነት ካመነች ወዲህ ልቧ አልተቀመጠም። ከአዲስ አበባ ርቃ አዳማ ገብታለች ። ዓለም የአዳማ ህይወቷ የተጀመረው በሆቴል ቤት መስተንግዶ ነበር። ለአካባቢው አዲስ ብትሆንም ስራው አልከበዳትም። የታዘዘችውን እየፈጸመች ‹‹አቤት ወዴት›› ማለቱን ለመደች።

ውሎ ድሮ ግን የአዳማ ኑሮ ከበዳት። ገቢዋ ከወጪዋ አልታረቅ አለ። እየተከዘች ቀናትን ገፋች። ለውጥ አላገኘችም። ዓለም ቢሻለኝ ብላ አልጋ አንጣፊነቱን፣ ወጥ ቤትነቱን ሞከረችው። በሰራችው ልክ አለማግኘቷ ከእጇ አሳጣት። ርቃ መጥታ ኑሮን ተሽሎ አለማግኘቷ ያበሳጫት ያዘ። እየቆየች ስትሄድ አማራጭ ፍለጋ አይኖቿ ቃበዙ ። ጆሮዋ ለሰዎች ምክር ቦታ ሰጠ።

አንድ ቀን አንድ ደላላ ለኑሮዋ ይበጃል ያለውን እየዘረዘረ አዋዝቶ ነገራት። ያለችበትን ትታ እሱ የሚለውን ብትሰራ ህይወቷ እንደሚለወጥ ነገራት ። ዓለም በሰውዬው ንግግር ተመሰጠች። ሥራው ገንዘብ የሚገኝበት መሆኑን ስታውቅ ፈጥና ልትጀምረው ጓጓች። የአዲስ አበባዋ ወጣት በደላላው ተማርካ የገባችበት ህይወት እንዳሰበችው አልሆነም። ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በብዙ ፈተናዎች ተመላለሰች። በየጊዜው በክፉና ጨካኝ ወንዶች መዳፍ ብትወድቅም ሥራውን ጨክና መተው አልሆነላትም። ባይመቻትም የምታገኘው ገንዘብ እያጓጓት ኑሮን ቀጠለች።

ዓለም አዳማ ከመጣች ወዲህ የቀድሞ ማንነቷ ተለውጧል። ጫት ትቅማለች፣ መጠጥ ትጎነጫለች፣ ያሻትን ለመሆን ከልካይ ይሉት ታዛቢ ጎኗ የለም። በየቀኑ እሷን የመሰሉ እኩዮቿ ነጻነት ሲማርካት ይውላል። እነሱን ለመሆን አብራቸው ውላ ትደሰታለች። ይህ እንዲሆን የአዳማ ኑሮ ሜዳውና ፈረሱን ለግሷታል ።

ዓለም እንደቀልድ የጀመረችው የቡና ቤት ህይወት መተዳደሪያዋ ሆኗል ። ቀኑን በሱስ ውላ አምሽታ

 የምታድርበት ሥራዋን ‹‹እንጀራዬ›› ብላዋለች ። አንዳንዴ ከልጅነቷ የሆነባትን እያሰበች ትተክዛለች። ዛሬም ከፈተና ያልወጣ ማንነቷ ከአስጊ ችግር ላይ ነው። በየቀኑ ከእጇ የሚደርሰው ገንዘብ ዋጋ ያስከፍላታል። ደስታና እፎይታ ርቋታል።

አንድ ምሽት ..

ዓለምና የቡና ቤት ህይወቷ ቀጥሏል። እንጀራዋ የባንኮኒ ስራ ከሆነ ቆይቷል። በሚሆነው ሁሉ ባትደስትም በይሁንታ የመረጠችውን ህይወት እየኖረችበት ነው። አንዳንዴ መልካም ሰዎች ሲያገኟት በሰላም ውላ ታድራለች። ብዙ ግዜ ግን ገንዘባቸውን ብቻ የሚያስቡ ወንዶች ይገጥሟታል ።

ከነዚህ መሀል አብዛኞቹ ተሳዳቢዎች፣ ጨካኞች፣ ተደባዳቢዎች ናቸው። ዓለም እነዚህን ሁሉ እንደየባህሪያቸው ችላ ታልፋለች ። ከቀናት በአንዱ ያጋጠማት ግን ከሁሉም ጊዜ የከፋ ሆነ። ምሽት ላይ በገንዘብ ተስማምታ አብራው የሄደችው ሰው ከሆቴሉ ክፍል ሲደርስ ባህሪው ተቀየረ።

ሰውየው ሴተኛ አዳሪ መሆኗን እያወቀ ያለኮንዶም ካልተጠቀምኩ ሲል አስፈራራት። ዓለም ሀሳቡን ተቃውማ ሞገተችው። በፍርሀት እየተንቀጠቀጠችም ልትለምነው ሞከረች፣ ሰውየው ፈጽሞ ሊሰማት አልፈቀደም። እያለቀሰች ደጋግማ ተማጸነች። ጆሮ አልሰጣትም። በመጨረሻ ጉልበቱን ተጥቀሞ ያሻውን ፈጸመ።

ዓለም የተሰበረ ልቧን ደግፋ በዕንባ ስትታጠብ ከረመች። ሰውየው ከማስገደድ ባለፈ የማይገቡ ድርጊቶችን ፈጽሟል። ይህ ችግር ውሎ አድሮ ለጤናዋ ችግር ሆነ ። ዓለም ክፉኛ ታመመች። ከሀኪም ያመላለሳት ችግር በቀላሉ አልተፈታም። በአስቸኳይ ለከፍተኛ ህክምና ወደ አዲስ አበባ ተላከች። አዲስ አበባ ያደረሳት ህመም አልጋ አስይዞ ወራትን አስቆጠረ።

በየጊዜው የሚደረግላት ህክምና እንደታሰበው ፈጥኖ አላዳናትም። ተደራራቢው የጤና ችግር አቅሟን አዳክሞ ካልጋ አከረማት። አንድ ቀን ከሀኪሟ ፊት ቀረበች። ሀኪሙ በእጁ የገባውን ውጤት እያገላበጠ በደሟ የኤችአይቪ ቫይረስ መገኘቱን አሳወቃት። ከዚህ ክፉ ዜና ማግስት ዓለም ህይወቷ መዛባት ጀመረ። የሰማችውን ውጤት ተከትሎ ሌላው የጤና ችግር ፈተናት።

ችግሩ በአንድ ብቻ አልቆመም። የማህጸን ኢንፌክሽን፣ የአእምሮ ጭንቀትና ድብርት አስጨነቃት። ኢንፌክሽኑን እየታከመች በአንድ ሆስፒታል የስነልቦና ምክር መታገዝ ያዘች። የሚደረግላት ክትትል መልካም ሆኖ ጤናዋ ተመለሰ። ዓለም ውሎ ሲያድር ራሷን እያረጋጋች ውስጧን አሳመነች። እንዲህ መሆኑ ከሰው አግባብቶ ከትዳር አጋሯ አገናኛት።

ጎጆ ቀልሳ ኑሮ እንደጀመረች የመጀመሪያ ልጇን አረገዘች። ይህን ባወቀች ጊዜ ሆስፒታል የእርግዝናዋን ክትትል ጀመረች። ወሯ እየገፋ ሲሄድ በህክምናው አልቀጠለችም። ሁሉን ትታ ራቅ ካለ ፀበል አቀናች ። ጊዜያት የቆጠረው ቆይታ ዳግም ከሀኪም አላደረሳትም። በድንገቴ ምጥ ሴት ልጅ ወልዳ ታቀፈች።

አሁን ዓለም የልጅ እናት ሆናለች። ከብዙ ችግር በኋላ ዓይኗን በዓይኗ ማየቷ ተስፋ ሆኗታል። በልጇ ነገን አሻግራ ታያለች። በልጇ ሁሉን ችግር ትረሳለች። በየቀኑ ይህ አይነቱ እውነት ከውስጧ ውሎ ያድራል። አንዳዴ ግን ልቧን የሚረብሻትን ሀቅ ታግላ መሸሸ ይሳናታል።

ሥጋትና ፀፀት…

ዓለም ልጇን የወለደቻት በደሟ ቫይረሱ እንዳለ ካወቀች ወዲህ ነው። በእርግዝና ጊዜ እሷና ህፃኗ ተገቢውን ክትትል አላደረጉም። አሁን ደግሞ ትንሸዋ ልጅ ጤና እያጣች መታመም ይዛለች። ዓለም ክፉኛ ተጨንቃለች። ልጇን ባየች ቁጥር ውስጧ በስጋት ይናወጣል።

አሁን ልጇ የሶስተኛ ዓመት ሻማዋን ለኩሳለች። እንደልጅ ግን ደስተኛ አይደለችም። ዘወትር ያማታል። የህጻኗ ህመም መባባስ ሲቀጥል ሆስፒታል ልትሄድ ግድ ሆነ። ሙሉ ምርመራ ባገኘች ማግስት ውጤቷ ደረሰ። የተሰማው እውነት ለእናቷ ልብ ሰባሪ ነበር። በደሟ የኤችአይቪ ቫይረስ ተገኝቷል።

ዓለም በጸጸትና ድንጋጤ ተሰብራ ከረመች። ለልጇ ጤና መጉደል ተጠያቂዋ እሷ ናትና ስሜቱን መቋቋም አልቻለችም። በየቀኑ ራሷን አብዝታ ወቀሰች ፣ ቀና ብላ የልጇን ዓይን ለማየት እስኪሳናት አፈረች። ምንም ማድረግ አልቻለችም። በግራ መጋባት ስትወዛገብ ቆየች።

ከባዱ የፈተና ቀን ካለፈ በኋላ ህይወት እንደቀድሞው ቀጠለ ። ዓለም አሁንም ራሷን አሳምና እውነቱን ተቀበለች። ልጇን ከእሷ ሳትለይ የአቅሟን ማድረግ ያዘች። የባለቤቷና የእሷ ህይወት ተመሳሳይ ቢሆንም በትዳሯ ደስታ አላገኘችም። በጥበቃ ስራ የሚኖረው ባለቤቷ ገቢው በቂ አይደለም። ይህን ተከትሎም ጓዳቸውን ችግር ይፈትነዋል።

የኪራይ ቤት ህይወት ኑሯቸውን ከእጅ ወደአፍ ያደረገው ጥንዶች ህይወታቸው በጎ አልሆነም። በዚህ ችግር መሀል የወለዷቸው ሌሎች ሁለት ልጆች የቤተሰቡን ቁጥር አበራከተው አምስት አድርሰውታል። አሁን በነ ዓለም ቤት ችግር ዓይኑን አፍጥጦ እየፈተናቸው ነው። እሷ እንደባለቤቷ ሰርታ አትገባም።በየጊዜው የሚመላለስባት ህመም እጇን ለምጽዋት እያዘረጋት ነው ።

ጥቂት ዓመታት ያስቆጠረው የዓለም ትዳር እንዳሰበችው አልዘለቀም። በድንገት ባለቤቷን በሞት አጣች። ይህኔ በአንድ እጅ የቆመው ጎጆ ይበልጥ ጎደለ። ወይዘሮዋ ሶስት ልጆችን ያለ አባት ማሳደጉ ከበዳት ። ከዓመታት በፊት የራቀቻቸው ቤተሰቦቿ ዛሬ ከእሷ አይደሉም። ማንንም አትጠይቅም፣ ማንም አያያትም ። ለዚች ሴት ህይወትና ኑሮ ቀላል አልሆነም።

ያልጠገነው ህመም…

ዓለም ከህመሟ ታግላ መኖር ጀምራለች። ታማሚ ልጇ ከዓይኗ አትርቃትም። እናትና ልጅ መድሀኒቱን ሲጠቀሙ በቂ ምግብ ይፈልጋሉ። ይህ እውነት ቢታወቅም ከሌሎች ልጆቿ የተለየ ምቾትን ሞክራው አታውቅም። ተማሪ ልጇ ትምህርት ቤት ውላ ስትገባ እናት ተስፋዋ ያብባል። ስለእሷ ስታስብ ጸጸቷ ቢበዛም ጥንካሬዋን አይታ ትበረታለች።

ዓለም ብዙ ጊዜዋን ያሳለፈችው ከሆስፒታል አልጋ ተኝታ ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ ጎጆዋ ይጎድላል፣ ልጆቿ ይጎዳሉ። ለቀለብ፣ ለቤት ኪራይ፣ ለዕለት ወጪ እጇ ይነጣል። በምትታከምበት ሆስፒታል ችግሯን የሚያውቁ ሀኪሞች አይጨክኑባትም። ለእሷና ለልጆቿ ጉሮሮ የአቅማቸውን ያደርጋሉ።

ዓለም ከዛሬ ሀያ ዓመታት በፊት በደሟ ኤችአይቪ በተገኘ ጊዜ ሚስጥሯን ያወቁ አንዳንዶች ፊት ነስተው አግልለዋታል። ዛሬም ቢሆን ስለእሷ ምቾት የማይሰማቸው ብዙ ናቸው።፡ ይህ እውነት ዓለምን ከስብራቷ አላዳናትም።ሁሉን ለማስረዳትና ችግሯን ለማሳወቅ ፊት ባጣች ጊዜ መከፋቷ ይበረታል።

ዛሬም ድረስ በማህጸን ኢንፌክሽን የምትሰቃየው ዓለም ከሆስፒታል ደጃፍ ርቃ አታውቅም። በየጊዜው አልጋ መያዝ፣ መድሀኒት መውሰድ ልምዷ ሆኗል። ይህ ችግሯ በሙሉ አቅሟ ሰርታ እንዳታድር ሰበብ ሆኗል።

በብዙ ውጣውረዶች እየታገለች ሶስት ልጆች የምታሳድገው ዓለም እነሱ በእሷ መንገድ እንዳያልፉ ትመክራለች። እንደሌሎች ባይመቻቸውም ከትምህርት እንዲውሉ ትጥራለች። ዛሬም ያልተፈታው ችግሯ ፍላጎታቸውን የሚሞላ ሀሳባቸውን የሚያሳካ አይደለም።

ዓለም ልጆቿ እንደእኩዮቻቸው ጥሩ ለብሰው፣ አምሮባቸው ብታይ ትወዳለች። እንደ እናት ያማራቸውን ብታጎርሳቸው ፣ የጠየቋትን ብትሞላላቸው ደስ ይላታል። ያልጠገነ ኑሮዋ ግን ይህን ሊፈቅድ አልቻለም።

ዛሬን …

ዛሬ እሷና ልጆቿ በቂ መኝታና የሚደርቡት የብርድልብስ እንኳን የላቸውም። ሲገኝ ተቃምሶ ሲታጣ ፆም በሚታደርበት ቤት የህይወት ፈተናው ቀጥሏል። የዓለም ምኞትና ተስፋ ይህ ታሪክ እንዲቀየር ነው። እንዳሻት ሰርታ የማትገባው ሴት ዛሬ በትኩረት የሚያይዋትን ዓይኖች ትሻለች። ትናንት የበረከቱ ችግሮችን የተሸከመ ትከሻዋ ዛሬ ሌላውን የህይወት ፈተና ሊቀበል ተስኖታል።

‹‹እርዱኝ አግዙኝ›› የምትለው እናት ጤናዋ መለስ ሲል ሰርታ የምታድርበት ለልጆቿ ተስፋ የምትሆንበት መተዳደሪያ ቢኖራት ትወዳለች። የትናንት ክፉ ህይወት ለዛሬ ማንነቷ ጋሬጣ ሆኗልና መልካም ዓይኖች እንዲያይዋት የበረቱ ክንዶች እንዲያነሷት ፍላጎቷ ነው ።

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You