ትችትና ነቀፌታ መማሪያ ወይስ መማረሪያ?

 ስለትችትና ነቀፌታ ብዙ ተብሏል፤ ብዙ ተጽፏል። በትችትና ነቀፌታ ዙሪያ ሁሉንም ሊያግባባ የሚችለው መሠረታዊ ሀሳብ ግን መተቸትና መንቀፍ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባሕሪ መሆኑ ነው። ማንም ሰው ከመሬት ተነስቶ ስለፈለገው ነገር ትችትና ነቀፌታ ማቅረብ ይችላል። ማንም ሰው ነገሮች እስካልጣሙትና እርሱ በሚፈልገው መልኩ እንዲሄዱለት እስከፈለገ ድረስ ትችት ሊያቀርብና ነቀፌታ ሊሰነዝር ይችላል። ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ መብቱም ጭምር ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን መተቸትና መንቀፍ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕሪ ቢሆንም ከምክንያታዊ ትችትና ነቀፌታ ባለፈ መልኩ የሚሳደብና የሚዘረጥጥ አለ። እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ ውሀ ቀጠነብኝ ሰማይ ተደፋብኝ የሚል ሞልቷል። በሆነው ባልሆነው ተነስቶ የሚያማርረው ብዙ ነው። ችግሮች ሁሉ ከሌላው አካል እንጂ ከእርሱም ጭምር የመነጩ እንደሆነ የማይረዳም ጥቂት አይደለም።

በተለይ በዚህ ፖለቲካው እለት በእለት በሚለዋወጥበት፣ የሰላም ሁኔታው አስተማማኝ ደረጃ ባልደረሰበትና የኑሮ ውድነቱ ሰማይ በነካበት ግዜ ተቺውና ነቃፊው በዝቷል። ይህ በሌላው ዓለምም የሚታይ በመሆኑ የሚገርም አይደለም ።

ሰው በጋራ ተሰባሰቦ ቡና እየጠጣ፣ ምግብ እየበላ፣ ቢራ እየተጎነጨ፣ የእግር ጉዞ እያደረገ ሰፈሩን፣ ጎረቤቱን፣ አካባቢውን፣ መንደሩን፣ መንግሥትን፣ ሀገሩን፣ መሪውን….. ወዘተ ይተቻል፣ ይነቅፋል።

የአንዳንዱ ሰው ትችትና ነቀፌታ ምክንያታዊ ቢሆንም የአብዛኛው ግን ደፈናዊና በነሲብ የሚደረግ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ማኅበረሰቡ የሚያቀርባቸው ትችቶችና ነቀፌታዎች አይረቤ ናቸው ብሎ መናቅ አይቻልም። ምክንያቱም ኅብረተሰቡ በምክንያትም ሆነ ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ የሚያቀርባቸው ትችቶችና ነቀፌታዎች በበጎ መልኩ እስከተወሰዱ ድረስ ለመማሪያና መለወጫ ጥቅም የሚሰጡበት እድል በመኖሩ ነው። ግን ደግሞ በነሲብና ያለበቂ ምክንያት የሚቀርቡ ትችቶችና ነቀፌታዎች ትክክለኛ መልካቸውን ይዘው ቢቀርቡ ይበልጥ ሊያስገኙ የሚችሉትን ጥቅም ማጤን ያስፈልጋል። ስለዚህ እዚጋ ደፈናዊ ትችትና ነቀፌታን ከተራ ስድብ፣ ማማረርና አጉል ወቀሳ ለይቶ ማየት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሁሌም ቢሆን ትችትና ነቀፌታ በምክንያት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው።

በአንድ ወቅት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም “ሁሉ ተቺ፣ ሁሉ ተናጋሪ፣ ሁሉ አዋቂ ነኝ ባይ፣ እኔ ለሀገሬ ምን አደረኩላት ከማለት ይልቅ ሀገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ የሚል፣ ወርቅ ቢነጠፍለት ፋንድያ ነው የሚል” ብለዋል። ልክ ናቸው። በግዜው ከነችግራቸውም ሆነው ለሕዝባቸው የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። ግን ደግሞ የሠሩትን ያህል በጥቂቱ እንኳን ምስጋና ባለማግኘታቸው ይህን ለማለት ተገደዋል። ንግግራቸው እውነት ያለው የመሆኑን ያህል የቀረበባቸውን ትችትና ነቀፌታ በበጎ ተቀብለው ለመሥራት አለመፈለጋቸውን በጥቂቱም ቢሆን ያሳያል።

በርግጥ የሀገር መሪ ሆኖ ጥሩም ፤መጥፎ ተሠራ ከትችት የሚድን ማንም የለም። ዴሞክራሲን በሀገራቸው በደምብ ያስፋፉና መሠረታዊ የሕዝብ ፍላጎቶችን በሚገባ የመለሱ መሪዎች እንኳን ከትችትና ከነቀፌታ አልዳኑም ። እዚህ ጋር ዋናው መስመር ያለበት ነጥብ ግን ትችቱና ነቀፌታው እንደው ከቶውኑ ይቅር ማለት አይደለም። ምክንያቱም ትችት አስተማሪና ወደትክክለኛ አቅጣጫ እስካመጣ ድረስ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ ስለሚበልጥ ነው።

ትችትን በበጎ ተቀብለው እንደመማሪያ የወሰዱ ግለሰቦችም ሆኑ የሀገር መሪዎች ተጠቀሙበት እንጂ አልተጎዱም። ነቀፌታን ከቁብ ሳይቆጥሩ አንገታቸውን ደፍተው የሠሩ ሀገራት ዛሬ ዓለምን ያስደመመ ደረጃ ላይ ደርሰዋል ። ትችትና ነቀፌታ ያልሆነ አቅጣጫና መልክ የሚኖረው ተቺውና ነቃፊው አካል ትችቱንና ነቀፌታውን በጎ ባልሆነ መልኩ ሲሰነዝር ነው። በተመሳሳይ ትችቱንና ነቀፌታውን የሚቀበለው አካል ለትችቱና ለነቀፌታው በመልካም መልኩ ምላሽ ሳይሰጥ ሲቀር ነው በጎ ውጤት ሳይገኝ የሚቀረው።

አሁን ባለው ሁኔታ ግን በእኛም ሀገር ሆነ በሌላው ዓለም የሚታየው የዚህ ተቃራኒ ነው። በበጎ መልኩና በአመክንዮ ከመተቸትና ከመንቀፍ ይልቅ ትችቱና ነቀፌታው በደፈናው ነው የሚካሄደው። ትችትና ነቀፌታ የሚቀበለው አካልም ትችቱንና ነቀፌታውን በመጥፎ ነው የሚመለከተው። ትችትና ነቀፌታ ሁሌም ቢሆን መሠረትና ምክንያት አለው ። ያለአመክንዮ ትችት የሚባል ነገር የለም። አንድ ሰው ለመተቸትና ለመንቀፍ ሲነሳ በቂ ምክንያትና ማስረጃ ሊኖረው ይገባል። እንዲህ ካልሆነ ትችቶችና ነቀፌታዎች ሁሉ ትርጉም አልባ ይሆናሉ።

ሰዎች ግለሰቦችን፣ ኅብረተሰቡን፣ ማኅበረሰቡን፣ ሀገራቸውንና መሪዎቻቸውን በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ይተቻሉ፤ ይነቅፋሉ። ግን ደግሞ ትችታቸውና ነቀፌታቸው መሠረት ያለው፣ ምክንያታዊ፣ ገንቢና አነሰም በዛ ነገ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆን ይኖርበታል። መሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ትችት የሚሰነዘርባቸው አካላት ትችቱንና ነቀፌታውን በመጥፎ ከማየት ይልቅ በበጎ ወስደው ለመማሪያ፣ ማስተካከያና ራሳቸውን መለወጫ ሊጠቀሙበት ይገባል። ይህ ሲሆን አንዱ ከሌላው ብዙ ይማራል። ድክመቶችን በቶሎ በማረም ራስን ማሻሻልና መለወጥ ይቻላል። ያኔ በግለሰብ፣ በኅብረተሰብ፣ በማኅበረሰብና በሀገር ደረጃ በሁለንተናዊ መልኩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You