በሀገራዊ ለውጡ፣ የኢትዮጵያን አየር ክልል ንግሥና የተቀዳጀው – የኢትዮጵያ አየር ኃይል!

 የታላቋ ሀገር ታላቅ ተቋም፤ የሀገር ዳር ድንበር አለኝታዎቹ የሃገር መከላከያ ሠራዊት የሰማዩ ክፍል ፈርጥ፤ የሀገርም የወገንም ጋሻ፣ የኢትዮጵያን ሰማይ ቀዛፊም ጠባቂም የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል፤ እነሆ ዛሬ 88ኛውን የልደት በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል።

ለሀገር አለኝታ ሆኖ ሲሠራ፤ የኢትዮጵያን ዳርድንበር ለማስከበር ከመሬት ከፍ ብሎ በሰማዩ ሲናኝ 88 ዓመታትን የተጓዘው አየር ኃይሉ ታዲያ፤ የእነዚህ ዓመታት ጉዞው አልጋ በአልጋ ሆነውለት የዘለቀባቸው አይደሉም። ይልቁንም እንደየሥርዓቶቹ መለዋወጥ በከፍታም፣ በዝቅታም ውስጥ እየተፈተነ ያለፈ እንጂ።

የአየር ኃይሉ ምስረታ፣ ኢትዮጵያ በዘመናት ጉዞዋ ውስጥ የሚገጥሟትን ፈታኝ የሉዓላዊነት ስጋቶች ታሳቢ ያደረገ ነበር። በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የቴክኖሎጂ ጉዳይ፣ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ በምድር ጦር ስልታቸው ሽንፈትን ለማያውቁ ሀገራት ሌላ አማራጭ እንዲመለከቱ አስገድዷቸው ነበር።

በዚህ መልኩ ኢትዮጵያም ከውስጥም ከውጪም የሚቃጡበት የሉዓላዊነት አደጋዎችን በብቃት ለመመከት እንድትችል ከተለመደው መንገድ ወጣ ብላ የአየር ክልሏንም ማካለል እንዳለባት በመገንዘባቸው ነበር አፄ ኃይለሥላሴ በሥልጣን ዘመናቸው አየር ኃይል እንዲመሠረት ያደረጉት።

እናም አየር ኃይሉ በንጉሡ ዘመን ተደራጅቶ፤ በደርግ የሥልጣን ዘመንም የሀገር አለኝታነቱን በተግባር ተፈትኖ ማረጋገጥ ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ ለደርግ ሥርዓት ማብቃት በኋላ የአየር ኃይሉ ስምና ዝና ቀስ እያለ እንዲቀዘቅዝ ተደረገ። በዚህም በጀግንነታቸው አንቱታን ያተረፉ የአየር ኃይል አባላት ከተቋሙ እንዲገፉ ሆነ፤ የአየር ኃይሉ ወሳኝ ንብረቶችና የሎጀስቲክስ አቅሞች እንዲመናመኑ፤ በኋላም ከመኖር እሳቤ ውጪ እንዲሆኑ ተደረገ።

የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ በአንድ ወቅት ገናና የሆነውን፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር በኩል በሰማዩ መስመር አይተኬ ሚና የተወጣውን፤ ከሀገሩ አልፎ ለአፍሪካውያን አለኝታነቱን ያረጋገጠውን ተቋም የበለጠ ከዘመኑ ጋር እንዲራመድ ከማድረግ ይልቅ፣ ከመኖር ወደ አለመኖር ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ሆነ።

ይሁን እንጂ ለሁሉም ጊዜ አለው፣ እንዲሉ፤ ለአየር ኃይሉም የትንሳኤ ጊዜ መጣ። ይሄም የ2010 ሀገራዊ ለውጥ ነበር። እናም እንደ ሀገር በተደረጉ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎች ውስጥ የኢፌዴሪ መከላከያ ተቋም፣ በዋናነትን የአየር ኃይሉ በእጅጉ ካለመኖርነት ወደ ልዕልናው የተመለሰበት እድል ተፈጠረለት።

ለውጡ አየር ኃይሉን ለወጠው፤ ለውጡ አየር ኃይሉን ወደ ኃያልነት አሸጋገረው፤ ለውጡ አየር ኃይሉን ከዘመኑ ጋር እንዲራመድ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ እንዲታጠቅ፤ ለውጡ አየር ኃይሉን ከዘመኑ ጋር የሚራመድ አቅም ያላቸው አባላት ባለቤት እንዲሆን በጥቅሉ አየር ኃይሉ የኢትዮጵያ አየር ክልል ንጉሥ እንዲሆን አደረገው።

ምክንያቱም ከለውጡ ማግስት በአየር ኃይሉ ላይ የተሠሩ ሪፎርም ሥራዎች፤ አየር ኃይሉ ተቋማዊ አቅሙን መገንባት አስችሎታል። ተቋማዊ አቅሙ ደግሞ በሰው ኃይልም፤ በትጥቅ አቅምም፤ በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትም፤ በጥቅሉ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ፣ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች እንዲታጠቅ፤ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እንዲነግሥ ያስቻሉትን አቅም እንዲገነባ እድል ሰጥቶታል።

በዚህም ትናንትን አፍርሰነዋል ብለው ከተቋም ማፍረስ ወደ ሀገር ማፍረስ የተሸጋገሩ አካላት እንኳን አቅሙን መገመትም፣ መረዳትም እስኪያዳግታቸው ከፍታውን በተግባር ገልጦ እንዲመለከቱ አድርጓል። ዛሬም በየቦታው ከውስጥም ከውጪም እንደ ሀገር ኢትዮጵያ የሚሰነዘርባትን ጥቃት በሩቅ ማስቀረት የቻለባቸውን አጋጣሚዎች በተግባር ማስመልከት ችሏል።

ይሄ ተቋም ታዲያ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም የኢትዮጵያ አለኝታ ብቻ ሆኖ መቆየትን አልፈለገም። “ሰማዩም የእኛ ነው” በሚለው እሳቤው የሚታወቀው ተቋሙ፣ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ አለኝታነቱን ለማረጋገጥ እየተጋ ነው። ለዚህ ዐቢይ ማሳያው ደግሞ ከሰሞኑ የአፍሪካ የአየር ኃይል አዛዦች ፎረም መጀመሩ ሲሆን፤ የዚህ ፎረም ጅማሮ ደግሞ የአፍሪካ አየር ኃይሎች እንደ ኢትዮጵያ አየር ኃይል ራሳቸውን በማጠናከርና ተቀናጅቶ በመሥራት የአፍሪካን አየር በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ ነው።

ምክንያቱም ዛሬ ላይ የሉዓላዊነት ጉዳይ የአንድ ሀገር ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በጠንካራ የአየር ኃይሏ እየተጠበቀ ቢሆንም፤ አፍሪካውያን ጎረቤቶችም ሆነ አጠቃላይ አፍሪካውያን በዚህ መልኩ ራሳቸውን አጠናክረው ሉዓላዊነታቸውን መጠበቅ ካልቻሉ የአንዱ ቤት እሳት ወደሌላው መሰደዱ አይቀሬ ነው። ለዚህም ነው አየር ኃይሉ አፍሪካውያን አየር ኃይሎች ጠንክረውና ተባብረው አየር ክልላቸውን መጠበቅ፤ ሉዓላዊነታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ በ88ኛው ልደቱ ወቅት ፎረም መሥርተው በአንድ መሥራት የሚችሉበት እድል እንዲፈጠር መንገዱን እንዲጀምሩ ዕድል ያመቻቸው።

ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት ከፍ አድርጋ የያዘችው የአፍሪካውያንን የእርስ በእርስ መናበብና አብሮ መሥራት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መንገድ፤ እንደ አየር መንገዷ ሁሉ በአየር ኃይሏ ውስጥም በማስረጽ ይሄንኑ አብሮነት ወደ ላቀ አቅም የማሸጋገር ፍላጎትን የሰነቀ ነው። በለውጡ ማግስት ተለውጦ የነገሰው የኢትዮጵያ አየር ኃይልም፤ ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ሰማይ እያሳየ ያለው የጀግንነት ተግባር የሚደነቅም፣ የሚያስመሰግነውም ነው።

አሁንም “በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል” በሚለው መሪ ሃሳብ በዓሉን ሲያከብርም፤ ይሄንኑ ልዕልናውን ከሌሎች አቻ አህጉራዊ ተቋማት ጋር በማቀናጀት የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ከሀገር ወደ አህጉር ለማሸጋገር ትልቅ አቅም የሚሰጥ ነው!

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You