ዓለማችን ልጆቿን ካጣችባቸው ውስብስብና ጅምላ ጨራሽ ወረርሽኞች መካከል ዋነኛው ኤች አይቪ /ኤድስ ነው፡፡ ነው።መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ወረርሽኙ የሰው ልጅን ማጥቃት ከጀመረበት እ ኤ አ በ1978 አንስቶም ከ78 ሚሊየን በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፤ከ 39 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል፤16 ሚሊየን ህፃናት ወላጅ አልባ ሆነዋል።
በአሁኑ ወቅትም 36 ነጥብ 9 ሚሊየን ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ፣በየዓመቱም አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን ሰዎች አዲስ በኤች አይቪ ኤድስ እየተያዙ ይገኛሉ፤አንድ ሚሊየን የሚሆኑት ደግሞ ይህችን አለም ይሰናበታሉ።
ኢትዮጵያም ኤችአይቪ /ኤድስን አሁንም አልተሻገረችም።በእርግጥ ህዝብና መንግስት፣ ሲቪል ማህበራት፣ የኃይማኖት ተቋማትና ሌሎች አገር በቀልና የውጭ አጋር ድርጅቶች ወረርሽኙን ለመመከት ከፍተኛ ርብርብ በማድረጋቸው ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት ተችሏል።
በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት 610ሺ 335 የሚሆኑ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ሲሆን፣በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ዘርፈ ብዙ ምላሽ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የኤች አይ ቪ የስርጭት ምጣኔ 0 ነጥብ 9 በመቶ ላይ እንዲገኝ አርገውታል፤
በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት በአንድ ሀገር ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ ከአንድ በመቶ በላይ ከሆነ በሽታው ወረርሽኝ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው።በዚህ ምጣኔ መሰረትም ኢትዮጵያ ከወረርሽኙ ነፃ ብትሆንም፤ ስርጭቱ በገጠርና በከተማ ተከፋፍሎ ሲታይ በከተማ ያለው ስርጭት ወረርሽኝ ውስጥ መሆኗን መረጃዎች ያመላክታሉ።
በእርግጥም መድሃኒት የለሹ በሽታ ከአገር የጠፋና የተሸነፈ መሰለ እንጂ አሁንም ቢሆን አልጠፋም፤አልተሸነፈምም፤ የተዳፈነ እሳት እንዲሉ አድብቷል፡፡በተለይ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑም ይህንኑ የበሽታውን እየተቀጣጠለ መሆን ያመለክታል።
ይህም ከምንም በላይ ወረርሽኙን በመከላከልና መቆጣጠር በኩል የተገኘው ውጤት ያስከተለው መዘናጋት የፈጠረው ስለመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ አካላት ይገልጻሉ። በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ የሚሰጡት ትኩረት በእጅጉ ማነስ በሽታው በአሁኑ ወቅት ለደረሰበት አሳሳቢ ደረጃ እንዱ ምክንያት ነው ሲሉ የሚገልጹም በርካታ ናቸው።
የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ከከተማዋ ጤና ቢሮ ጋር በመተባባር ኤች አይቪ/ ኤድስ አሁንም ዋነኛው የአገሪቱ ዜጎች የጤና ተግዳሮት ሰለመሆኑ ግንዛቤ መፍጠርንና መገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ ትኩረት ይሰጡ ዘንድ ዓላማው ያደረገ የምክክር መድረክ ባለፈው ሳምንት በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የማህበረሰብ ንቅናቄና ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ቦጋለ፤ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ መገናኛ ብዙሃን ለኤች አይቪ ቫይረስ የሚሰጡትን ትኩረት ይበልጥ ማጎልባት አለባቸው የሚባለው በምክንያት ስለመሆኑ ነው ያስረዱት።
አቶ ተስፋዬ እንደሚገልፁት፤ኤች አይ ቪ በአገሪቱ ከተከሰተ አንስቶ የመገናኛ ብዙሃን ለጉዳዩ በሰጡት ልዩና ሰፊ ትኩረት በርካታ የማህበረሰቡ ክፍሎች ስለ በሽታው በቂ የሆነ መረጃና ግንዛቤ እንዲኖራቸው፤የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ፤ ራሳቸውን ለማወቅ እንዲመረመሩና ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ከተገኘም የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድሃኒቱን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ ውጤታማ ተግባሮችን ሰርተዋል።
በየዓመቱ በሚካሄዱ የዳሰሳ ጥናቶችም ወረርሽኙን በመከላከልና መቆጣጠር ስራው ለውጦች መታየታቸውን መረዳት ተችሏል። የስርጭት ምጣኔው፤ከኤድስ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሞትና እና አዲስ በቫይረሱ የመያዝ ሁኔታ እንዲሁም ከማግለልና መድሎ ጋር ተያይዞ የነበረው የማህበራዊና ስነልቦናዊ ችግርንም በእጅጉ መቀነስ ተችሏል።
«በአሁኑ ወቅት የኤች የአይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ መስፋፋት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ይባስ ብሎም ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ አጋላጭ ሁኔታዎች እየታዩ ነው»የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ችግሩ በዚህ ደረጃ እያለ እየተሰጠ የሚገኘው ትኩረት ግን በእጅጉ ደካማ ሆኖ እንደሚስተዋል ይገልፃሉ።
አቶ ተስፋዬ በአዲስ አበባ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የተካሄደ ጥናትን ጠቅሰው እንዳሉት፤ በመዲናዋ በአሁኑ ወቅት 107ሺ 917 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ይገኛል፤ በየዓመቱ 1ሺ 408 በቫይረሱ ይያዛሉ፤1ሺ879 የሚሆኑት ደግሞ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ ይህም ችግሩ አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ በቂ ምስክር መሆኑን ነው አቶ ተስፋዬ ያስገነዘቡት።
እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ፤ አሁንም ቢሆን ኤች አይቪ በደማቸው ውስጥ እያለ ተመርምረው ራሳቸውን ያላወቁ፣ የፀረ ኤች አይቪ ኤድስ ህክምና እየጀመሩ የሚያቋርጡ፣ጥንቃቄ የጎደለው ወሲብ በማድረግ የተጠመዱና በርካታ ናቸው ፡፡
የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማጎልበትና ከማንቃት፤ማህበራዊ ቀውሶቹን ከመከላከል አንፃር ራሱን የቻለ ተቋማዊ ሃላፊነት ያለባቸው መገናኛ ብዙሃነም ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጣር ህፀፅ የሆኑ ችግሮችን ለማስገድ በሚደረገው ጥረት ሲሰጡ የቆዩትን ዝቅተኛ ትኩረት ማሻሻል ይገባቸዋል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡
‹‹መገናኛ ብዙሃኑ ኤች አይቪ /ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠሩ ጥረት ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ሲባል እንደከዚህ ቀደሙ የእለት ተዕለት አጀንዳ ይሁን ማለትም አይደለም»የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤የኤች አይቪ ጉዳይ አሁንም ከተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አጀንዳዎች እንደ አንዱ መቃኘት እንደሚኖርበት ያመለክታሉ።
እንደ አቶ ተስፋዬ ማብራሪያ፤የመገናኛ ብዙሃኑም ሆነ የህብረተሰቡ የቸልተኝነት አመለካከት ሳይውል ሳያድር እስካልታረመና የቫይረሱ መስፋፋት በዚሁ ከቀጠለ ስርጭቱ ሊያገረሽ ፣ይህን ተከትሎም ለኤች አይቪ ኤድስ የሚያስፈልገው ወጪ አገሪቱን ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሊከታት ይችላል።
የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ መከላከልና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት የዘርፈ ብዙ ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፈለቀች አንዳርጌ፤አስከፊው የኤች አይቪ/ኤድስ ስርጭትን ተረባርቦ በመግታት ረገድ መገናኛ ብዙሃኑ የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው፣አገሪቱም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በላይ ትልቅ ምሳሌ ሆና እንደትጠራ ማስቻሉንም ያስታውሳሉ።
በባህሪያቸው የኤች አይቪን በመከላከና በመቆጣጠር ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት በአንድ ጀንበር ተጀምረው በአንድ ጅንበር የሚቋረጡ አለመሆናቸውን ጠቅሰው፣ ተከታታይ ስራዎችን እንደሚጠይቁ ይናገራሉ፡፡ መሰል ተግባራትን በመከወን ረገድ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ መዘናጋት እንደሚስተዋል ያስገነዝባሉ።
በተለይ መገናኛ ብዙሃኑ የኤች አይቪ /ኤድስ የህዝብ አጀንዳ መሆኑን በመዘንጋታቸው የሚሰጡት ትኩረት አለ ለማለት እንደማያስደፍር ጠቅሰው፣ በጣም ውስንና በዘመቻ ሰሞን የታጠረ እንደሆነም ነው የሚገልጹት፡፡ለጉዳዩ ትኩረት ከሰጡም እንዴት አድርገው ትፅእኖ መፍጠርና የተፈለገውን መልእክት ተደራሽ ማድረግ ላይ በቂ ዝግጅት የማድረግ ችግር እንደሚስተዋልባቸውም ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ዋነኛው ህዝብ ችግር የሆነው ቫይረስ የበለጠ እንዲዘነጋ ማድረጉን ያክሉበታል።
ወይዘሮ ፈለቀች ‹‹መገናኛ ብዙሃኑ ቫይረሱን የመቆጣጠርና የመከላከል ስራውን በእጅጉ ከመርሳታቸው በተጓዳኝ፣«ጥረቱን ከማገዝ ይልቅ ለቫይረሱ አጋላጭ የሆኑ ጭፈራዎችንና የመጠጥ ማስታወቂያዎችን በማስኮምኮም ላይ ተጠምደዋል ይላሉ፡፡ ይህም ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆነው ወጣቱ የማህበረተሰብ ክፍል ይበልጥ ችግር ውስጥ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ ሲፈጥር መስተዋሉን ይገልፃሉ።
እንደ ወይዘሮ ፈለቀች ገለጻ፤የተለያዩ ተቋማትና የልማት ድርጀቶችም ለህዝብ ጤና አጀንዳዎች በተለይም የማህበረሰብ ንቃተ ህሊናን በማዳበር ረገድ ለሚከናወኑ የመገናኛ ብዙሃን ፐሮግራሞች የሚሰጡት ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡አብዛኞቹ ተቋማትም ህልውናቸው ቀጣይ የሚሆነው ሰው በህይውት ሲኖር እንደሆነ እንኳን ዘንግተውታል።
‹‹የኤች አይ ቪ ኤድስ እሳት ተዳፈነ እንጂ አልጠፋምና በዚህ አይነት አካሄድ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት የማይቻል በመሆኑም መገናኛ ብዙሃኑም ሆነ ህብረተሰቡ ከመዘናጋት በፍጥነት ሊፋቱ እንደሚገባው ነው የተናገሩት።
የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሲስተር ብር ዛፍ ገብሩ በአሁኑ ወቅት በስርጭት ምጣኔ አገሪቱ ከኤች አይቪ ወረርሺኝ ነፃ መሆኗን ጠቅሰው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የስርጭቱ ምጣኔ ከአንድ በመቶ በላይ መሆኑን እሳቸውም ይገልጻሉ።
በተለይ ኤች አይ ቪ ኤስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይ ህብረተሰን ለማስገንዘብ ይሰጡ የነበሩ ድጋፎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእጀጉ መቀነሳቸውን ጠቅሰው፣ የመገናኛ ብዙሃንም ለጉዳዩ የሚሰጡት ትኩረት እየቀነሰና እየተቋረጠ መምጣቱን ይገልፃሉ።
የወረርሽኙን ስርጭት መግታት በመቻሉና አሁን ጉዳይ አብይ አጀንዳ ሆኖ ባለመታየቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ክፍተኛ መዘናጋት እንዲፈጠር ማድረገን አመልክተው፣አንዳንዶች በሽታው ጠፍቷል የሚል አስተሳሰብ ማራመድ መጀመራቸውንም ይናገራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ በቫይረሱ የመያዝ መጠን ማገርሸቱን አሳቸውም ጠቅሰው፣ መገናኛ ብዙሃኑ ካንቀላፉበት መነሳትና በሽታውም በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ደረጃ ላይ አይደለም ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ መላቀቅ፤ እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዩሃንስ ጫላ ፤«ኤች አይቪን በመከላካልና በመቆጣጣር ረገድ በተከናወኑ ተግባራት በተገኙ ስኬቶች መኮራራትና መዘናጋት በአሁኑ ወቅት የቫይረሱን የስርጭት መጠን በሚፈለገው ልክ መቆጣጠር እንዳይቻል አድርገውታል» ይላሉ፡፡
ለእዚህም አብነት የሚጠቅሱት በአዲስ አበባ የቫይረሱ የስርጭት መጠን ከነበረበት የመቀነስ አዝማሚያ በአሁኑ ወቅት ጨምሮ ሶስት ነጥብ አራት ምጣኔ ላይ መድረሱን ነው፡፡ ይህም በባይረሱ ስርጭት መዲናዋን ከጋምቤላ ከተማ ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጣት እና የቫይረሱ ስርጭት አሁንም በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በግልፅ የሚመሰክር ነው»ይላሉ።
በከተማዋ ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኙት መካከል ዘጠና በመቶው ወጣቶችና በአምራች እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ክባድ እንደሚያደርገው የሚያስገነዝቡት የቢሮ ሃላፊው፤ «የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትና የማህበረሰብ የጤና ችግር እንዳይሆን ለማድረግ በተለይም አዲስ በኤች አይቪ የመያዝ ምጣኔን ዜሮ የማድረስ እቅድ ለማሳካት የሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን ክግብ ለማድረስ፤የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት በሚካሄዱ ዘርፈ ብዙ ኤች አይቪን የመከላካልና የመቆጣጣር ተግባራት በባለቤትነት መንፈስ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ያስገነዝባሉ።
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤትም ባዘጋጀው የውይይት መድረክ፤በኤች አይ ቪ ኤድስ ርዕሰ ጉዳይ ህብረተሰቡን በማንቃት ረገድ የመገናኛ ብዙሃን ቸልተኝነት ሳይውል ሳያድር ሊታረም እንደሚገባው ነው የተጠቆመው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011
ታምራት ተስፋዬ