የኢትዮጵያ አየር መንገድና የአውሮፓ ህብረት ኢትዮ አውሮፓ የተሰኘ አለም አቀፍ የቢዝነስ ትምህርት ቤት ለመክፈት ተስማማሙ።
አለም አቀፍ የንግድ ትምህርት ቤቱን ለመክፈት አየር መንገዱና የአውሮፓ ህብረት የስምምነት ፊርማ በትናትናው ዕለት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምና በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆን ቦርግስታም ናቸው።
ስምምነቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአየር መንገዱ አቪዬሽን አካዳሚ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር የቢዝነስ አስተዳደር ትምህርት መስጠት ትጀምራለች።
በዚህ ወቅት ዋና ስራ አስፈጻሚው ባደረጉት ንግግር ፥ አለም አቀፍ የንግድ ትምህርት ቤት ለመክፈት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ደስተኛ አንደሆኑ ገልፀዋል።
አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የቢዝነስ አስተዳደር ትምህርት እንደሚሰጥ የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው በአቪዬሽን አካዳሚው እየተሰጠ ላለው የአመራር ትምህርት ተጨማሪ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጆን ቦርግስታም በበኩላቸው፥ በኢቪየሽን ኣካዳሚው የቢዝነስ አስተዳደር ትምህርት መጀመሩ ለወጣት ኢትዮጵያውያን ጥራት ያለው ትምህርት ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በስልጠናና ትምህርት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት የኢትዮጵያን የልማት እቅድ ውጤታማ ማድረግ እንደሚያስችል ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።
ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው አምባሳደሩ የወጣቶችን የስራ እጥነት ችግር ለመቅረፍና ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።